የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና በመሳሰሉት ላይ የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲታከል ለማድረግ፣ አባላቱ በግብር ክፍያና በታክስ ዙሪያ የሚገጥማቸውን ችግር እንዲሁም የሚያቀርቡትን ቅሬታ ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮቹ እንዲፈቱ ይሰራል፡፡ መንግስት በሚያወጣቸው የተለያዩ አሰራሮች ላይ ለንግዱ ማብራሪያዎች እንዲሰጡ በሚደረግበት ሁኔታም ላይ እንዲሁ ይሰራል። ምክር ቤቱ ይህን ከሚያከናውንባቸው መንገዶች አንዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ነው። በዚህም የዘርፉ ችግሮች እንዲፈቱና የንግድና የኢንቨስትመንት ምህዳሩ እንዲሻሻል አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ምክር ቤቱ በቅርቡም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ በሆነው የቤት ግብር ማሻሻያ ላይ በከተማዋ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ከተሰማሩና በተለያየ ደረጃ ግብር ከፋይ የሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
የተሻሻለውን የቤት ግብር የትመና ምንነትና አስፈላጊነት አስመልክቶ በመድረኩ ተገኝተው ለንግዱ ማህበረሰብ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ እንዳሉት፤ የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968ን አስታውሰው፣ አዋጁን ለማስፈጸምም ደንብ ቁጥር 36/1968 ወጥቶ በከተማዋ የቤት ግብር ሲሰበሰብ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው ይህ የግብር አሰባሰብ ውስንነት ያለው ስለመሆኑ በጥናት መለየቱን አስታውቀዋል። ከተማዋ እየሰፋችና እያደገች ከመሆኗ ጋር ተያይዞም የቤት ብዛት በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከቤቶች ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣት ጋር ተያይዞ ወደ ግብር ቋቱ የሚገባው ገቢ ግን እንዳልጨመረ ነው ያመለከቱት። በግብር ቋት ውስጥ ያልተካተቱ በርካታ ቤቶች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ አንደኛው የቤት ግብር ማሻሻያ ያስፈለገበት ምክንያትም ይሄው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በግብር ቋቱ ውስጥ ሳይካተቱ የቆዩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በግል አልሚዎች የሚገነቡ ቤቶች /ሪልስቴቶች/ና ሌሎችም አሁን እንዲካተቱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ሁለተኛው ክፍተት በወቅቱ ትክክል የነበረ፣ አሁን ላይ ተገቢነት የሌለውና አስገራሚ የሆነ የግብር መጠን እየተሰበሰበ መሆኑን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ አምስት ብር፣ አስር ብርና ትልቁ የቤት ግብር እስከ አምስት መቶ ብር እንደሚከፈል ጠቁመዋል፤ ከአንድ ብር በታች እስከ 14 ሳንቲም ዓመታዊ የቤት ግብር እየተሰበሰበ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ይህ የግብር መጠን እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባለፈ የግብር መሰብሰቢያ ወጪውን እንኳን መሸፈን እንደማይችል ተናግረው፣ ይህን ማየትና ማሻሻል ማስፈለጉን አስረድተዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፤ የግብር ክፍያ መጠኑ መሰረት የሚያደርገው የቤቱን የኪራይ ዋጋ ግምት እንደሆነ አዋጁ ላይ በግልጽ ሰፍሯል፤ ይህን ዓመታዊ የኪራይ ግምት ወቅታዊ ማድረግ ሶስተኛው ለግብር አሰባሰቡ ማሻሻል አስፈላጊነት የተቀመጠ ምክንያት ነው፡፡ ያኔ የግብር ግምቱ አነስተኛ የሆነው በወቅቱ የነበረው የኪራይ ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የተደረገው ማሻሻያ የአዋጁን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ በወቅታዊ የኪራይ ዋጋን መነሻነት ነው፡፡
የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የከተማው ነዋሪ የሚፈልገው አገልግሎትም እንዲሁ ከኑሮ መሻሻል ጋር እየጨመረ እንደሚሄድ የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህን የግብር ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገውም ከተማዋ የምትፈልገውን አገልግሎት ለማቅረብ ነው ይላሉ፡፡
የቢሮ ኃላፊው እንዳብራሩት፤ የከተማዋ ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፤ ይህን ፍላጎት ጥራት ባለው አገልግሎት ለመመለስ የገቢ አቅምን ማሳደግ የግድ ይሆናል፣ የቤት ግብር ማሻሻያው አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም መደረጉም ለእዚህ ነው፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ የቤት ግብር ማሻሻያ አዋጁን አዲስ የወጣ አዋጅ አድርጎ የመረዳት ሁኔታ ስለመኖሩም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፤ ሕዝቡ እንዲከፍል የተደረገው የግብር አይነት በተለምዶ ብዙ ሰው የሚረዳው የጣሪያና ግድግዳ ግብር ተብሎ የሚሰበሰብና የተለየ ነገር የሌለው መሆኑንም ጠቅሰው፣ የተለየው ነገር አሁን ባለው የኪራይ ገቢ ትመና መደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ትመናውም ግምቱ ላይ ጥናት ተደርጎ የኪራይ መጠንን በማወቅ የተደረገ መሆኑን ተናግረው፣ የኪራይ ግምት ዋጋው ተሰልቶ የቀረበው አዋጁ ባስቀምጠው መሰረት እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
አዋጁ 45 ዓመታትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ማሻሻያ ሳይደረግበት ተመኑን ብቻ ማሻሻል ከሕግ አንጻር ተገቢነት የሌለው ስለመሆኑ የሚያነሱ አካላት ስለመኖራቸው የቢሮ ኃላፊው ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አዋጁ የሕግ ጥሰት እንደሌለበት ነው ያስታወቁት፡፡ በኪራይ ዋጋ ግምት መሰረት የግብር መጠኑ የሚሰላ ስለመሆኑ በአዋጁ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም አዋጅ እስካልተሻረ ድረስ እንደሚያገለግል ጠቅሰው፣ አዋጁን መሰረት በማድረግ ማሻሻያው መደረጉ የሕግ ክፍተት የሌለበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቤት ግብር ማሻሻያው አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ ሊያባብሰው የሚችልና ሸማቹንም ሆነ አጠቃላይ የንግዱን ማህበረሰብ የሚረብሽ ነው የሚሉ አካላት ስለመኖራቸውም በማንሳት ጉዳዩ በተለይም አቅመ ደካማና ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው ለአብነትም ጡረተኞችን ስጋት ውስጥ የጣለ ስለመሆኑ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ሰዎች ጉዳዩን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ስለመሆኑ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ሰዎች ስለጉዳዩ ካላቸው እውቀትና መረዳት ተነስተው ሊተቹ እንደሚችሉ ገልጸው፤ ገቢ ያለውና መክፈል የሚችል ሰው ብቻ ግብር እንዲከፍል እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ ግብሩ መክፈል የማይችሉ ጡረተኞችንና ምንም አይነት ገቢ የሌላቸውን መክፈል የማይችሉ ሰዎችን አይመለከትም። ከተማ አስተዳደሩ ገቢ የሌላቸው ሰዎች መክፈል ሲያቅታቸው አውጥቶ አይጥላቸውም፡፡ እንዲያውም በተለያየ መንገድ ያግዛቸዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ አቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት ሰርቶ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችና ድጎማዎችን በማድረግ ያግዛል። ይህን ተግባርም ትናንት ሲያደርገው የነበረ ሲሆን፤ ዛሬም ነገም የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡
የከተማዋ የተለያዩ ህንጻዎችና የንግድ ተቋማት ጭምር ቆጠራ እየተደረገባቸው ስለመሆኑ የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሕንጻዎችን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጠናቀቁ ህንጻዎችና ባዶ መሬቶችን ከተማ አስተዳደሩ እየቆጠረ እንደሆነም አብራርተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከፖሊሲ አንጻር የግል አልሚዎችን ማበረታታትና መደገፍ ላይ እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት፡፡ በየደረጃው ከሚገኙ የግል አልሚዎች የሚደገፉትን በመደገፍ የሚቀጡትንም በመቅጣት ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ሥራውን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ያሉ የግል አልሚዎችን ችግር ለመፍታት ቆጠራ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስከ አሁን ድረስ በግብር ሥርዓት ውስጥ እንደሌሉ የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፣ በከተማ ውስጥ ያለው የግብር አከፋፈል ሥርዓት ወጥነት የሌለውና ገሚሱ ግብር ከፋይ ገሚሱ ደግሞ የማይከፍል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሌላው ችግር መሆኑን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ የፍትሐዊነት ክፍተት እንዳለም አመላክተዋል፡፡ በከተማዋ ከአንድ ብር በታች ዓመታዊ ግብር የሚከፈልበት ሁኔታ ስለመኖሩም ጠቅሰው፣ የመጠኑ ጉዳይ ሊያከራክርና ሊያወያይ ይችል ይሆናል እንጂ፤ አንድ ብርና ከአንድ ብር በታች ግብር ለመክፈል መሥሪያ ቤት መሄድም ሆነ ግብር ሰብሳቢው ይህን ለመቀበል የሚደርገው እንቅስቃሴ ትርጉም እንደሌለውም ይገልጸሉ፡፡ የቤት ግብር መሻሻሉ የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ሌላው አካል ሊረዳው የሚገባውና ተገቢ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ የመንግሥት ህንጻዎችን በተመለከተ በመንግሥት በጀት የተሰሩና ለመንግሥታዊ አገልግሎት የሚውሉትን አዋጁ ነጻ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ግብር አይከፍሉም። ቤተ ዕምነቶችም ግብር አይከፍሉም፡፡ ለልማት የተቋቋሙ መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ ለትርፍ የተቋቋሙና ሌሎች የግል ድርጅቶች በሙሉ ግን በግብር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር መሰብሰብ አቅም መኖሩ በጥናት የተረጋገጠ ስለመሆኑ የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህን ገቢ መሰብሰብ የሚቻለው ከአንድ ብር በታች የሆነ የቤት ግብር በመሰብሰብ አለመሆኑን አስታውቀዋል። ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራትና እየሰፋ የመጣውን የከተማዋን አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የቤትና ቦታ ግብርን ማሻሻል እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ይህ የግብር አይነት ከአቅም ጋር ሊስማማ የሚችልና ተገቢነት ያለው እንዲሁም ምንም አይነት የህግ ጥሰት የሌለበት መሆኑን በመረዳት የንግዱ ማህበረሰብ ለተግባራዊነቱ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች ለንግዱ ማህበረሰብ ማስተዋወቅና ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ በእዚህ መድረክም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተደረገውን የግብር ማሻሻያ አስመልክቶ የንግዱ ማህበረሰብ ማብራሪያ እንዲያገኝ ተደርጓል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ግብር ከፋይ አባላቱ በግብር ክፍያና በታክስ ዙሪያ የሚገጥማቸውን ችግርና የሚያቀርቡትን ቅሬታ ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮቹ እንዲፈቱ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡
ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ያለው የግሉ ዘርፍ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር እንዲችል ጤናማ በሆነ መንገድ ግብር መክፈል ወሳኝነት እንዳለው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ግብር ለአንድ አገር የህልውና ምሰሶ መሰረት ነው። አገራት እንደ አገር መቀጠል የሚችሉት ግብር መሰብሰብ ሲችሉና የተሰበሰበውን ግብርም በአግባቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ማዋል ሲቻል ነው።
ሕዝቡ ግብር መክፈል የሚችለውና መንግሥትም ግብር መሰብሰብ የሚችለው አስቻይ የፍትህ ሥርዓት ሲኖር ነው የሚሉት ወይዘሮ መሰንበት፤ መንግሥት ሰላምና ጸጥታን ማስፈን እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል፡፡ የግብር አዋጆች ከመውጣታቸው አስቀድሞ እንዲሁም ከወጡ በኋላ ህብረተሰቡ በሚረዳው ልክ ማሳተፍና ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ክፍተት እንዳይኖር በማድረግ አፈጻጸሙን የተሟላ በማድረግ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተናግረው፣ ለዚህም ለንግድ ምክር ቤቱ ለአባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የጠቀሱት ወይዘሮ መሰንበት፣ በተለይም ችግሮች ካሉ ችግሮችን በመፍታት መንግሥት መሰብሰብ ያለበትን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ያስችለዋል። ገቢ ሰብሳቢው አካል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት ከቻለ ግልጽነትና መግባባት እንደሚፈጠርም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተሻሻለው የቤት ግብር በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያለው አንድምታ ምን እንደሚመስል እና የንግዱ ማህበረሰብም ወቅታዊ አቅምን ያገናዘበ ነው ወይ የሚሉትን ፈትሾ በውይይቱ ማጥራት እንደተቻለም ነው ያመለከቱት፤ በቀጣይም የንግድ ምክር ቤቱ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ችግሮችና እንቅፋቶች መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015