መገናኛ ብዙኃን ለአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የሕዝቦቻቸውን የማደግ መሻት ተጨባጭ ለማድረግ ሁለንተናዊ አበርክቷቸው መተኪያ የሌለው እንደሆነ ይታመናል።
በአንድ በኩል መረጃዎችን በብዛት፣ በጥራትና በጊዜ በማድረስ ማኅበረሰባዊ ዕድገቶችን ለማፋጠን፤ ከዚህም ጎን ለጎን የማኅበረሰቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን ለተቀረው ዓለም በማድረስ ሀገራዊ ዕውቅናን ለማትረፍ ወሳኝ አቅም ናቸው።
በሀገራችንም በነገሥታቱ ዘመን የተጀመረው መረጃዎችን የመሰብሰብ እና ወጥ በሆነ መንገድ አደራጅቶ ለትውልዶች የማስተላለፍ አሠራር / ዜና መዋእል / በ18ኛው ክፍለ ዘመን የጋዜጣ ቅርጽ ይዞ ለአደባባይ መብቃቱ ይታወሳል።
ይህ ጅማሮ ከነፃነት ማግስት /ከ1932/ በኋላ የዘመናዊውን ጋዜጣ ቅርጽ ይዞ ከመቀጠሉም ባለፈ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጪ ቋንቋዎች መታተም ጀምሯል። ከእነዚህ ጋዜጦችም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ”ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ” ጋዜጣ አንዱ ነው።
ጋዜጣው የወቅቱን አሁናዊ ብስራት እና የመጪዎቹን ዘመናት ተስፋ አብሳሪ በመሆን ህትመቱን አንድ ብሎ ከጀመረ እነሆ ዛሬ 80 ዓመቱን አስቆጥሯል። በዚህ ረጅም የህትመት ዘመኑም ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል።
ለህትመት ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የሀገሪቱን የዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች/ እውነታዎች በስፋት በማስተዋወቅ ፣ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ስለ ኢትዮጵያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው፤ በዚህም ሀገሪቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተገቢውን እውቅና እና ስፍራ እንድታገኝ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ አሁንም እያበረከተ ይገኛል።
በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ / ሃይማኖታዊ እሴቶች በማስተዋወቅ፤ ዓለም ለሕዝቦቿዋ ከበሬታ እንዲኖረው ያስቻሉ ሥራዎችን ሠርቷል፤ አሁንም እየሠራ ነው ።
በእነዚህ የሕዝቦቿ ማህበራዊ እሴቶች ለሀገሩ ቀናኢ ትውልድ በማፍራት፤ በብዙ መስዋእትነት በነፃነት መኖር የቻለች ሀገር መፍጠር መቻሉን፤ ይህም የብሔራዊ ክብሩ መሠረት እንደሆነ ዓለምአቀፍ ግንዛቤ ፈጥሯል።
ሀገሪቱ ያላትን ለኑሮ የተመቸ የተፈጥሮ አካባቢን ለዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ከማስተዋወቅ ባለፈ ፤ የቀደሙ ስልጣኔዎች ባለቤት መሆኑን በማሳወቅ ፤ በዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ሀገራዊ ትናንቶቻችን በቂ እውቅና እና ከበሬታ እንዲያገኙ በስፋት ሠርቷል።
በተመሠረተበት ማግስት ጀምሮ የአፍሪካውያን የነፃነት እንቅስቃሴ ከመደገፍ አንስቶ ለነፃነት ትግሉ ዋነኛ ድምጽ ሆኖ አገልግሏል፤ የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በማስፋትና በአፍሪካውያን ልብ ውስጥ ሰፊ ስፍራ እንዲያገኝ ያበረከተው አስተዋጽኦም በታሪኩ ውስጥ የሚዘከር ትልቁ ገድሉ ነው።
የአፍሪካውያን የነፃነት አባቶች የነፃነት አስተሳሰቦችን፤ ለአስተሳሰቡ የተገዙ ታላላቅ ጉባኤዎችን በስፋት ከመዘገብ አንስቶ፤ በጉዳዮቹ ላይ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎችን በመሥራት፤ የአፍሪካውያን ትግል ድምቀት ከመሆን ባለፈ ፤ ለመላው ዓለም የመረጃ ምንጭ በመሆን አገልግሏል፤ እያገለገለም ነው ።
ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን፤ ስለ አፍሪካና አፍሪካዊ ህልሞች፤ ስለ አፍሪካና የአፍሪካውያን የተጋድሎ ታሪኮች በመዘገብ፤ በየወቅቱ የነበሩ አፍሪካዊ መነቃቃቶች ለአፍሪካውያን ትግል ትርጉም ያላቸው የአቅም ምንጮች እንዲሆኑ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።
ዛሬም ቢሆን አፍሪካዊ አጀንዳዎችን ከፍ አድርጎ በማስደመጥ፤ የአህጉሪቱ ሕዝቦችን የትናንት የመሆን መሻታቸውን እና እያጋጠሟቸው ያሉ ፈተናዎች /ተግዳሮቶች በግልጽና በድፍረት በመዘገብ እና በመተንተን የአፍሪካውያን ድምጽ ሆኖ በማገልገል እንደ አንድ አህጉራዊ ጋዜጣ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል ።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም፤ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል እንኳን ለ80ኛ አመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ ሲል፤ ጋዜጣው እንደ አንድ ሀገራዊ ጋዜጣ የተጣለበትን ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ለመወጣት ለሄደበት ርቀት እና ላስመዘገበው ትርጉም ያለው ውጤት እውቅና በመስጠት ነው።
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በቀጣይ እንደሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ በበለጠ ቁርጠኝነት በመወጣት፤ የትናንት ስኬቱን ከፍ ባለ ደማቅ ታሪክ በማጀብ ለሀገርና ለሕዝብ ኩራት ምንጭ እንደሚሆን ያለንን እርግጠኝነት ከወዲሁ በማሳወቅ እንኳን ለ80 ዓመት አደረሳችሁ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015