• እናት ለልጇ የቅርብ እሩቅ አትሁን
ሴት ልጅ ዘጠኝ ወራት በሆዷ ተሸክማ የወለደችውን ልጅ ጡት አጥብታ ለማሳደግ ትልቅ መስዋዕትነት የምትከፍልበትና ሰፊ ጊዜ የሚጠይቃት ወቅት ነው። ታዲያ፤ በዚህ ወቅት ሥራ ያላት ሴት ከሆነች የወሊድ ፈቃዷን፤ የዓመት ዕረፍቷንና አንዳንዴም ከደሞዝ ውጪ ተጨማሪ ፈቃድ ልትወስድ ትገደዳለች። ይህን ሁሉ አጠናቅቃ ወደ ሥራዋ ስትመለስ ልጇን ለሞግዚት አልያም ለቤተሰብ ለመተው ትገደዳለች።
ይሁን እንጂ፤ ዛሬ ሞግዚት ለመቅጠር በትንሹ ከ1000 እስከ 1500 ብር በሚጠየቅበት በዚህ ጊዜ የስንቶች አቅም ይፈቅድ ይሆን?… ከአቅሙም ባሻገር ምን ያህል ተማምነን ሕፃናት ልጆቻችንን ለሠራተኛ ጥለን እንወጣ ይሆን?… ወጥተንስ ምን ያህል ውጤታማ ሥራ ሠርተን እንውል ይሆን?… “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንዲሉ አበው፤ ምን ያህሎቻችንስ መክፈል ባለመቻላችን ሥራችንን ለቅቀን ይሆን?… ሁሉንም ቤት ይቁጠረው። መንግሥት ታድያ ይህን ማህበራዊ ችግር በመረዳት በቅርቡ ሦስት ወር የነበረውን የወሊድ ፈቃድ ወደ አራት ወር ከፍ በማድረጉ ብዙ እናቶችን አስደስቷል።
ይሁን እንጂ፤ አራት ወራትም በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ እነሆ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ ተገንብቶ እናቶች ልጆቻቸውን ወደ ተቋማቸው ይዘው በመምጣት በቅርበት መጎብኘት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል። ይህ ደግሞ በሀገር ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ የጎላ ነው። አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2011 አንቀፅ 48 ሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሠራተኞች ሕፃናት ልጆቻቸውን በሥራ ቦታቸው ማቆየት እንዲችሉ የሕፃናት ማቆያ ማዕከል እንዲገነባ ይደነግጋል።
በዚህም መሰረት ጥቂት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተነሳሽነቱን በመውሰድ ወደ ሥራ ገብተዋል። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግም በዝግጅት ላይ ያሉ መስሪያ ቤቶችም አሉ። ዛሬ በዚህ አምዳችን ልናነሳ የወደድነው በቅርቡ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሕፃናት ማቆያ ማዕከል አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የገባውን የከተማ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን ተሞክሮ ልናካፍላችሁ ወደናልና እነሆ!
ወይዘሮ ፍቅርተ አበበ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የማህደርና ሪከርድ ክፍል ሠራተኛ ናት። ፍቅርተ የወሊድ ፈቃዷን፤ የዓመት ዕረፍትና ያለ ደሞዝም ተጨማሪ ፈቃድ ወስዳ ልጇን ተንከባክባለች። ይሁን እንጂ፤ ሕፃን ልጇ አሁንም ተንከባካቢ ይፈልጋል። ፍቅርተ ደግሞ ለልጇ ሞግዚት የመቅጠር አቅምም ሆነ የሚጠብቅላት ሰው የላትምና ሥራዋን ልታጣ ሆነ። ይሄኔ ተቋሙ የሕፃናት ማቆያ ማዕከል ሊከፍት እንደሆነና እስከዚያው ልጇን ይዛ እየመጣች ሥራዋን መሥራት እንደምትችል ተነግሯት የዘጠኝ ወር ልጇን ይዛ እየተመላለሰች መሥራት ጀመረች። አቅም ለሌለው ሰው ልጅ ይዞ ሥራ መሥራት በጣም አስቸጋሪና ከማህበራዊ ህይወት እንድንገለል ያስገድዳል የምትለው ፍቅርተ፤ በመስሪያ ቤት ውስጥ በስብሰባም ሆነ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተሳትፋ እንደማታውቅና የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞችም አውቀው እንደተረዷት ትናገራለች።
በተለይም በማህደርና ሪከርድ ክፍል ሕፃን ልጅ ይዞ መሥራት ከባድ ቢሆንም አማራጭ አልነበራትምና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆና ልጇን ይዛ እየተመላለሰች ሥራዋን ስትሠራ ቆይታለች። ፍቅርተ፤ አሁን በመስሪያ ቤቴ ውስጥ የሕፃናት ማቆያ ማዕከል በመቋቋሙ አጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ እኔም ልጄም እናርፋለን። ሥራዬን በሙሉ ልቤ ያለሃሳብ እሠራለሁ። በቅርበትም እጎበኘዋለሁ። ይሄ ደግሞ ለልጄም ሆነ ለኔ ትልቅ ጥቅም ነው። አሁን ችግር የሆነውን የትራንስፖርት ጉዳይ ደግሞ መንግሥት መፍትሔ ቢሰጠው መልካም ነው። የሠራተኞች ማመላለሻ ሰርቪስ ሕፃናት ይዘን ለምንንቀሳቀስ እናቶች አልተጀመረም ይህ ቢሟላ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል በማለት ሃሳቧን ትቋጫለች።
የከተማ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሴቶችንና ሕፃናትን ማገዝ ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት መሆኑን በማመን፤ እንዲሁም አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2011 አንቀፅ 48ን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ገብረ እግዚአብሔር የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ዳይሬክቶሬቱ በቅድሚያ የፍላጎት ጥናት በማድረግ 40 የመስሪያ ቤቱ ሴት ሠራተኞችን በመመዝገብ ስለ አስፈላጊነቱ አጠቃላይ ስብሰባ በማድረግ ያወያየ ሲሆን፤ የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ ሁሉንም የሚጠቅምና ዕረፍት የሚሰጥ መሆኑን በመተማመን ወደ ሥራ መገባቱን ዳይሬክተሯ ይናገራሉ።
በዚህም ወንዶችን ጨምሮ አጠቃላይ ሠራተኛው በጣም ደስተኛ መሆኑን ገልጿል። ዳይሬክቶሬቱም ይህን የሠራተኛውን የጋለ ስሜትና ያሳየውን ፍላጎት በመረዳት ጉዳዩን ለአመራሩ በማቅረብ በጋር በመሥራት የፋይናንስና የተለያዩ የቁሳቁስ ወጪዎችን በፍጥነት አሟልቶ ምቹ የሕፃናት ማቆያ ክፍሎች አዘጋጅቷል። የተዘጋጀው የሕፃናት ማቆያ ማዕከል በተቋሙ ውስጥ ባሉ ክፍት ቢሮዎች ሲሆን፤ ቢሮዎቹ ቀድሞ ለሕፃናቱ ምቹ እንዲሆኑ በማሰብ እድሳት ተደርጎላቸዋል። የተዘጋጁት የሕፃናት ማቆያ ክፍሎች እድሜያቸው ከሦስት ወር እስከ ሦስት ዓመት የሚደርሱ 20 ሕፃናትን ማስተናገድ የሚችል ነው።
ለጊዜው በተዘጋጁት አራት ክፍሎች ውስጥ መጫወቻዎች፤ የመኝታ ፍራሾችና ሌሎች ለሕፃናቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ተሟልተው ወደ ማቆያው የሚመጡትን ሕፃናት ለመቀበል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። “ሴት ሠራተኞች ሕፃናት ልጆቻቸውን እቤት ውስጥ ትተው ወደ ሥራቸው ሲመለሱ የሚያድርባቸው ስጋትና ጭንቀት ከሚገመተው በላይ ነው። በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው የሚያስቡት እቤት ጥለውት ለመጡት ሕፃን በመሆኑ ሥራቸውን በሙሉ ልብ መሥራት አይችሉም። ይህ ደግሞ በሥራቸው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለምና ብዙ ጊዜ ሴት ሠራተኞች ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም፤” የሚሉት ወይዘሮ አበራሽ፤ ይሁን እንጂ የሕፃናት ማቆያ በየተቋማቱ ቢገነባና ሴት ሠራተኞች ሕፃናት ልጆቻቸውን በቅርበት ማግኘት ቢችሉ ሴቶችም ከወንዶች እኩል በሥራቸው ውጤታማ መሆን ይችላሉም ብለዋል።
በየተቋማቱ የሕፃናት ማቆያ ቢኖር ለእናት፤ ለአባትና ለሕፃናቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ በሀገር ኢኮኖሚ ላይም የሚያሳድረው በጎ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በየተቋማቱ ያሉ አብዛኛው ሴት ሠራተኞች ብዙ ጊዜ ፈቃድ በመጠየቅ በሥራ ገበታቸው ላይም ሳይገኙ ይስተዋላሉ። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ከመስሪያ ቤታቸው በተጨማሪ በቤት ውስጥ ካለባቸው ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት የተነሳ ነው። ታዲያ እነዚህ ድርብርብ የቤት ውስጥ ጫና በተወሰነ መጠን ቢቀንስላቸው በሥራ ቦታቸው ተረጋግተው መሥራት ይችላሉ። ተረጋግተው በመሥራታቸው ውጤታማ በመሆን ምርታማነታቸው ይጨምራል። ከዚህም በላይ እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን በቅርበት ማግኘትና ማጥባት ሲችሉ ሕፃናቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
እንደሚታወቀው ሕፃናት እስከ ሁለት ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ማለትም ከእናት ጡት ጀምሮ የቤተሰብ ምግብ እስኪቀላቀሉ ድረስ ያላቸው የአስተዳደግ ሁኔታ በቀጣይ ለሚኖራቸው አካላዊ፣ አዕምሯዊና ስነልቦናዊ ዕድገት ወሳኝ ነው። በመሆኑም ለእናቶችና ለሕፃናት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ጠቀሜታው የጎላና ለሀገር የሚተርፍ መሆኑን ዳይሬክተሯ አብራርተዋል። በቀጣይም ይህን በጎ ጅምር አጠናክሮ መቀጠልና በሥራ ሂደት የጎደሉትን በማሟላት ሴት ሠራተኞች ያለ ሃሳብ በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ልጆቻቸውን ማጥባትና መንከባከብ እንዲችሉ የማድረግ ሥራ ይሠራል። ይህም በሴቶች ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል።
በተለይም ከአንድ የመንግሥት ሠራተኛ አቅም በላይ የሆነውንና በአሁን ወቅት በትንሹ ከ1000 እስከ 1500 ብር የሚጠየቅበትን የቤት ሠራተኛ ዋጋ ለመክፈል እጅግ ፈታኝ በመሆኑ ይህ በጎ ተግባር በሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው ብለዋል። አቶ ላቀው አበጀ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ በተቋሙ ውስጥ የመሬትና መሬት ነክ ምዝገባ ኤጀንሲን ጨምሮ አጠቃላይ ከ600 በላይ ሠራተኞች መኖራቸውን ገልጸው፤ ለተቋሙ የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ ያለውን ክፍት ቦታ በማመቻቸት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ይህም እናቶች ልጆቻቸውን በቅርበት እየተከታተሉ ውለው ማታ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ይዘው መግባት መቻላቸው ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸውና እጅግ ደስተኞች እንደሆኑም ገልጸዋል። ለሕፃናቱ የተለያዩ ክፍሎች የተዘጋጀ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ ማዕከልን ጨምሮ የመኝታ፣ የመጫወቻ፣ የመመገቢያ፣ እናቶች ጡት የሚያጠቡበት ቦታ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያና የመፀዳጃ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ተዘጋጅተዋል። ማዕከሉ በአሁን ወቅት በቁሳቁስም ሆነ በሰው ኃይል ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል። በሰው ኃይል በኩል ሕፃናቱን የሚንከባከቡ ሦሰት ሠራተኞች ቅጥር የፈፀሙ ሲሆን፤ የአንድ ዓመት ክፍያቸውም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ይህን በጎ ጅምር ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ በማድረግ ሠራተኛው የሚደርስበትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መቀነስ ይገባል። ከዚህም ባሻገር ወደ ሥራ የገቡ ተቋማት የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ በሥራ ላይ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ለሕፃናቱ፤ ጤንነት፣ አካላዊና ስነለቦናዊ ዕድገት፤ ለወላጆችም ዕረፍት የሆነው ይህ መልካም ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በፍሬህይወት አወቀ