ኢትዮጵያ እና ጀርመን ዘመናትን የተሻገረ የረዥም ዓመታት ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ታሪክ የሚያወሳው ነው። በአጼ-ምኒልክ የሥልጣን ዘመን የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። የሀገራቱ አሁናዊ ወይንም ዲፒሎማሲያዊ ግንኙነት ምን ይመስላል? ጀርመን በኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አውር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ አድርገዋል። ቃለ ምልልሱም እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።
አዲስ ዘመን፡- የጀርመን ቻንስለር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው። የዚህ ጉብኝት ዓላማ ምን ነበር?
አምባሳደር ስቴፈን፡– የጀርመን ቻንስለር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ይህ ጉብኝት ጀርመን ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ጠቃሚ አጋር የምትሰጠውን ቦታ የሚያሳይና በመላው አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ምስክርነት የሚሰጠው ነው። በዚህ ጉብኝት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የሰላም ሂደት ለመጠየቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ተፋላሚ ወገኖችን በሰላም መንገድ እንዲቀጥሉ ለማበረታታትና ጀርመን የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ለማየት ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የብሄራዊ ምክክር ኮምሽንን ለማቋቋም፣ የሽግግር ፍትህ አሰራርን ለመመስረት እና የሰብዓዊ አቅርቦትን ለማሻሻል እያደረገች ባለችው ጥረት ጀርመን ከጎኗ እንደምትቆም ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
ስለዚህም ጀርመን ካለፉት ሁለት የግጭት ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ግንኙነት ለመመለስ ቁርጠኛ ናት። በእርግጥ እኛ እራሳችን በአውሮፓ ከሩሲያ የዩክሬን ወረራ ጋር በተያያዘ እያጋጠሙን ያለን ፈተናዎች ቢኖሩም። አፍሪካ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፣ በተለይም ኢትዮጵያ በአጀንዳችን ላይ ትልቅ ቦታ አላት።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያሉትን የጀርመን የልማት ፕሮጀክቶች እንዴት ይገመግማሉ?
አምባሳደር ስቴፈን፡- በተለይ በልማት ትብብር ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ አንድ ወይም ትልቋ የልማት መዳረሻ መሆኗን እናውቃለን። በዚህ አካባቢ የሚሰሩ በርካታ ኤጀንሲዎች አሉን፣ KfW Development Bank (የመልሶ ግንባታ ክሬዲት ኢንስቲትዩት) ጂአይዜድ፣ (የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኮርፖሬሽን) እና ሌሎችም። ጂአይዜድን ብቻ ከወሰድኩ፣ በስሩ የሚሰሩ 1 ሺህ ሰራተኞች አሉት፣ ይህም የሚያሳየው በሥራ እድል ፈጠራው በስፋት እንደተሰማራን መሆኑን ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ወደ ተለያዩ የትብብር ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመልካም አስተዳደር ማስፈን፣ እንዲሁም በአሳታፊና ሰላማዊ ማህበረሰብ ላይም በስፋት እየተሰማራን ነው። ምክንያቱም በሦስቱም የዘላቂ ልማት ዘርፎች፣ በኢኮኖሚ፣ በሥነ-ምህዳር እና በማኅበረሰብ ልማት ውስጥ ሁሉም እድገቶች ሊኖሩ ይገባል ብለን ስለምናስብ። ይህ ይብዛም ይነስም በኢትዮጵያ ውስጥ ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን እያከናወንን ያለነው ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ስለ ጂአይዜድ አንስተው ነበር፣ ጂአይዜድ የተሰማራበትን የፕሮጀክቶች አይነቶች ሊነግሩን ይችላሉ?
አምባሳደር ስቴፈን፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ፕሮጀክቶች አሉን፣ ይህ ደግሞ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በልማት ትብብር ረገድ ሁለተኛዋ ትልቅ ለጋሽ ሀገር መሆኗን በድጋሚ ያሳያል። አብዛኛዎቹ በግብርና ዘርፍ ውስጥ ናቸው፤ በሌላም በኩል በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናና እንዲሁም በሌሎች በሙያ ሥልጠና መስኮች ላይ በስፋት ተሰማርተናል። ትብብሩ የግሉ ሴክተርንም ያካተተ ነው። ምክንያቱም እንደማንኛውም ሀገር እንደምታውቁት የግሉ ሴክተር ለዚህች ሀገር የሚያስፈልገውን የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተሻለ ነው ብለን ስለምናስብ ነው። አገሪቱ የምትፈልገውን የሥራ ዕድል መፍጠር እንድትችል የግሉን ሴክተር አፈጻጸም ማሻሻል ያስፈልጋል፣ ለዚህም ነው ጂአይዜድ በዚያ አካባቢ በስፋት የተሰማራው።
ሆኖም የግሉ ዘርፍን እና የሥራ እድል ፈጠራን ለማበረታታት ብቃት ያላቸው ሰራተኞች ሊኖሩ ይገባል። ለዚህም ነው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በጣም አስፈላጊ የሆነው። ከዚህም በተጨማሪ አሁን እያጋጠመን ባለው ተግዳሮት ምክንያት የማዳበሪያ፣ የነዳጅ እና የእህል ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት እና ምርትን ለማሳደግ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት እንፈልጋለን።
በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጌ ነበር፣ ገበሬዎቹ ለሥራ ያላቸው ቁርጠኝነት አስደንቆኛል። በመሬታቸው ላይ እንዲሰሩ መንገዱን እና እድሎችን ከሰጡዋቸው አስደናቂ ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ ይህን እንዲያደርጉ ማበረታታት ያለብን ለዚህ ነው። ለዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ፣ የፋይናንስ ማዕቀፉ እና የተለያዩ ደንቦች የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የግሉን ዘርፍ ማጎልበትና ማበረታታት በጣም አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን።
እንደሚታወቀው በጀርመን የጂ 20 ፕሬዚዳንትነት ስብሰባ ወቅት ጀርመኖች እ.ኤ.አ. በ2017 ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል። የዚህ ዓላማ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን፣ የግል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና እነዚህን አወንታዊ ማዕቀፎች ለመፍጠር ነው። እናም ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት አጋርነት ከተፈጠረባቸው 12 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት። ስለዚህ በሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን በባለብዙ ወገን ግንኙነትም ብዙ ነገር እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ውህደት ያላትን ሚና እንዴት ያዩታል? እና ከዚህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ጀርመን ይህን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በተመለከተ የምትከተለው ፖሊሲ ምንድን ነው?
አምባሳደር ስቴፈን፡-እኔ እንደማስበው የኢትዮጵያ ሚና ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ነው። እንዲሁም በአፍርካ ጠቃሚ የፖለቲካ ተጫዋችና የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ አሁን ካላት ሚና ባሻገር እናም ይህ የፕሪቶሪያው የሰላም ሂደት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በሚያስችል ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ምክንያቱም ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትኖርና የምንፈልገው የመልህቁን ሚና እንደገና እንድትጫወት ነው። ይህንንም በጣም እየደገፍን ነው።
ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው፣ በሰላም ማስከበር ተግባርና የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሰላም ድጋፍ ዘመቻ በመላክ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ህብረትን እዚህ በማስተናገድና የአፍሪካን ውህደት በማስተዋወቅም ጭምር ሚናዋ ከፍተኛ ነው።
በአጎራባች አገሮች ያሉ ሌሎች የጀርመን አምባሳደሮችም፣ በአገራት ሰላምና መረጋጋትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ የኢኮኖሚ ልማትን ለማስፋፋት እየሞከሩ ነው ማለት ይችላል። እኛ ግን ይህንን በሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን ኢጋድን እና የአፍሪካ ህብረትንም እየደገፍን ነው። የአፍሪካን የውህደት ሂደት፣ የፖለቲካዊም ሆነ የኢኮኖሚያዊ የውህደት ሂደትን በጣም እየደገፍን ነው። ስለዚህ ይህ የእኛ ፖሊሲ እና ትኩረት የምንሰጥበትም ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ጀርመን በውህደት ሂደት እጅግ በጣም ጥሩ ልምድ ስላላት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እና ጀርመን ለረጅም ጊዜ የቆየ የባህል ትስስር አላቸው። ሁለቱ ሀገራት የባህል ግንኙነታቸውን እንዴት ሊያሳድጉ ይችላሉ ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ስቴፈን፡- ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረ ጥሩ የባህል ትስስር አላቸው። ያ በጣም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ንቁ የሆኑ የባህል ዘርፍ ተዋናዮች አሉን። ለምሳሌ ጎኤዝ-ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት፣ የጀርመን አካዳሚ ልውውጥ አገልግሎት እና እንዲሁም የጀርመን አርኪኦሎጂ ኢንስቲትዩት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በቁፋሮ ላይ ተሰማርቷል።
ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ባህላዊ ትስስራችንን የበለጠ ለማስተዋወቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ተዋናዮች ናቸው ብዬ አስባለሁ። የጀርመን ኤምባሲም ከዚህ የባህል ትስስር ጋር በመሆን በባህል መስክ ትብብራችንን እንዴትና በየትኛዎቹ አካባቢዎች ማሳደግ እንደምንችል የተሻለ ግንዛቤን ለመፍጠር እንዲቻል እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎና አስተዋፅኦ ምን ይመስላል? እስካሁን ምን አይነት ውጤት እያስመዘገቡ ነው?
አምባሳደር ስቴፈን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የጀርመን ኩባንያዎችንና ኢንቨስትመንቶችን እያበረታታን ነው። የጀርመን ኢኮኖሚ ብዙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባካተተ መንገድ የተዋቀረ ነው። እነኚህም የጀርመን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው። በጀርመን የሥራ እድል ፈጠራውን ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን ይዛሉ። ለዚህም ነው ወደ ኢትዮጵያ እንዲሳቡ፣ እዚህ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው።
አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኢንቬስትመንት ካጡ ለኪሳራ ሊጋለጡ ይችላሉ። ስለዚህም በአንድ ሀገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ከፈለጉ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፤ እኛ የምንፈልገው ኢንቨስት የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ነው። እያደረግን ያለነውም ይህንን ነው። አንዳንዶቹ ወደዚህ አካባቢ ሲመጡ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል በሕግ፣ በግብር፣ በቪዛና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ችግሮች አሉ። በውጭ ኢንቨስትመንት መስክ (forex)፣ ብዙ የጀርመን ኩባንያዎችን ለመሳብ ያሉትን ችግሮች ማጥናትና ለችግሮችም መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል።
ሁሌም ለኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ እና አጋሮቼ እነግራቸዋለሁ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት ጋር ፉክክር ውስጥ ትገኛለች። የጀርመን፣ የአውሮፓ ወይም የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ከተፈለገ ከዚህ የተሻለ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሆነው ከመጡ አንድ ዓመት አለፈ። የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እስካሁን ያከናወኗቸውን ስኬቶች በምን ይለካሉ?
አምባሳደር ስቴፈን፡- እኔ ወደዚህ የመጣሁት በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ነው። የኮቪድ ወረርሽኝ በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭትና ከዛም በአውሮፓ ከሩሲያ የዩክሬን ወረራ ጋር በተያያዘ ችግሮች ነበሩ። ስለዚህ ለኔ በሁለትዮሽ ግንኙነታችን ላይ ማተኮር እና ግንኙነቶቻችንን ማጠናከር በጣም አስፈላጊ ነበር። ሆኖም ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም፣
ለኢትዮጵያ የምናደርገውን ሰብዓዊ ዕርዳታ በእጥፍ በመጨመር ወደ 82 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍ አድርገናል። የልማት ትብብራችንንም ሳይቋረጥ ጠብቀን አቆይተናል። የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ወደ ቀድሞው ደረጃ ለማደስ እና ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ እየሠራሁ ነው። ከዚህ ቀደም በጣም ጥሩ ግንኙነት ነበረን እና ወደዚያ እንደምንመለስ እርግጠኛ ነኝ። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እና ቻንስለሩ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ለዚህ ጥሩ ምልክቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ጀርመን የምስራቅ አፍሪካን የሰላም እና የልማት ትብብር እንዴት ነው የምትመለከተው? የሱዳንን የውስጥ ግጭት በተመለከተ የእርስዎ ሀገር አቋም ምን ይመስላል?
አምባሳደር ስቴፈን፡- አሳዛኝ ጉዳይ ነው። የሱዳን ሕዝብ እየተሰቃየና እየሞተ ነው። በጣም አስከፊ ነው። ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም እንፈራለን። ቀጣናዊ አንድምታ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን በመጀመሪያ ከሱዳን የሚመጡትን ስደተኞች ለመቀበል ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት በጣም የሚመሰገን ነው። ኢትዮጵያ እነዚህን ስደተኞች ለመቀበል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትገኝም የሰራቸው ሥራ ትልቅ የሰብአዊነት ምልክት ነው።
ይህ በእውነቱ የማደንቀው ነገር ነው። ይህን ካልኩ፤ ወደ ሱዳን ጉዳይ ሲመጣ፣ አገሪቱ ያላትን ችግሮችና ፍላጎቶች ሁሉ ለማስቻል፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ለማስፋት አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ያስፈልጋል። ነገር ግን የተኩስ አቁም ብቻ ሳይሆን ወደ ፖለቲካዊ ሂደት ለማምራት፣ የሽግግር ሂደቱን ወደነበረበት ለመመለስ የሲቪል መንግሥት እንዲኖር ያስፈልጋል። ይህም ለዚያች ሀገር ተጨማሪ እድገት ወሳኝ ይመስለኛል።
በዚህ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት የሚጫወተውን የመሪነትና የማስተባበር ሚና በጣም እንደግፋለን። በሱዳን ቀውስ ውስጥ እንዲያስታርቁ የተጠየቁት አራቱ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነም እናምናለን። ይብዛም ይነስም በሱዳን ላይ ያለን አቋም ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ በስደት ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች። እባክዎን ጉዳዩን የበለጠ ማብራራት ይችላሉ?
አምባሳደር ስቴፈን፡- አዎ፣ ያንን በማድረጋችን ደስተኞች ነን። በእርግጥ ስደተኞችን መቀበል እና ድጋፍ ማድረግ ትልቅ ሸክም እንደሆነ እንገነዘባለን። ቀደም ብዬ እንዳልኩት ኢትዮጵያ ስደተኞችን የምትቀበልበትን መንገድ እናደንቃለን። እናም በዚህ የአቀባበል ሥራ ኢትዮጵያን መርዳት እንፈልጋለን። ይህንን የምናደርገው በሰብዓዊ ርዳታ ነው።
እንዳልኩት በ2022 ያደረግነውን የሰብዓዊ እርዳታ በእጥፍ ወደ 82 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አሳድገናል። እናም እያደረግን ያለነው ይህንን እርዳታ በተባበሩት መንግሥታት በኩል ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎችም በሰብዓዊነት ላይ ንቁ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ተቋማትም ጭምር በኩል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ በመደገፍ በተለይም የወጣቶችን የቴክኒክና የሙያ ክህሎት በማሳደግ ረገድ ሀገራችሁ የምትጫወተው ሚና ምንድን ነው?
አምባሳደር ስቴፈን፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ከኢትዮጵያ ጋር በምናደርገው የልማት ትብብር አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ነው። ከዛሬ ከ25 ዓመታት ጀምሮ ከኢትዮጵያውያን ጓደኞቻችን ጋር በሙያ ሥልጠና ላይ አብረን ስንሠራ ቆይተናል። ይህም በተለያዩ ዘርፎች እየተሰራ ነው። እኛ የፋይናንስና የቴክኒክ እገዛዎች በማድረግ ለትምህርት ቤቶቹ መሠረተ ልማት ዝርጋታና የሙያ ሥልጠና በመስጠት ጥራታቸውን በማሻሻል የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ቆይተናል።
የሥራ ገበያን ፍላጎት ለማሟላት የሙያ ሥልጠና ወሳኝ ነው ብለን እናስባለን። በሥራ ገበያ የማይቀጠሩ ሰዎችን ብቁ ማድረግና ማሠልጠን ትርጉም የለውም። ስለዚህ ህዝቡን በሥራ ገበያው ፍላጎት መሠረት ብቁ ማድረግ አለብን። በዚህ ረገድ ጥራት ያለው የሙያ ሥልጠና በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። ስለዚህ እኛ እያደረግን ያለነው ይህንን በትክክል የሚሰሩ ፕሮግራሞችን እንዴት ማዘጋጀት እንደምንችል ለማየት እየሞከርን ነው። ይህንን ሀገር አቀፍ የሙያ ሥልጠና እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ በሚያደርግ እና አቅምን በሚያግለብት መልኩ የተለያዩ ድጋፎችን እያደርግን ነው።
ሌላ በጣም የሚገርመኝን ፕሮግራም ልጥቀስልህ። ቀጣይነት ያለው የሥልጠና እና የትምህርት መርሃ ግብር (Sustainable Training and Educational Program, STEP) ይሰኛል። ይህ ፕሮግራም ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች ምቹ የመማር ማስተማር አቅም እንዲኖራቸው የምንደግፍበት ነው።
የጀርመን የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ይብዛም ይነስም ለዚህ አርአያ ናቸው። ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር አጋርነት ያላቸው ሲሆን፤ በቀጣይም የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሥርዓተ ትምህርት እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችሉ ለማየት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ምሁራን ከአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ከወጡ በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ በሥልጠናቸው፣ በክህሎታቸው ለኢትዮጵያ ኩባንያዎች ተወዳዳሪነት የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየሞከርን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ምን ይመስላል? በንግድ ልውውጡ ውስጥ ምን ዓይነት ምርቶች ይገኙበታል? ባለፈው ጊዜ ጀርመን በኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው። የዚያ ኤግዚቢሽን ምላሽ ምን ነበር?
አምባሳደር ስቴፈን፡- በእርግጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነቱ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን በቂ አይደለም። ኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍ ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። እንዲሁም ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛዋ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ናት። ስለዚህ የንግድ ግንኙነታችንን ማስፋፋት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራንበት ነው።
ጀርመን የኢትዮጵያን ቡና በብዛት ከሚገዙ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት። እኛ የኢትዮጵያ ቡና በጣም እንወዳለን፤ የጨርቃ ጨርቅና የአበባ ምርቶችንም እንዲሁ ምርጫዎቻችን ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ ብዙ ማሽነሪዎችን፣ የመድሃኒት ምርቶችን፣ ሞተሮችን፣ አውሮፕላኖችን እና ተሽከርካሪዎችን ከጀርመን ታስገባለች።
ከዚህ ባሻገር የጠቀስከው የንግድ ትርዒት በጣም የተሳካ ነበር፣ በመጋቢት 2024 ቀጣዩ የንግድ ትርኢት ይኖረናል። በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ሰርኩላር ኢኮኖሚና ለአግሮ- ምግብ ሲባል ሌሎች የንግድ ኤግዚቢሽኖችን እያደረግን ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊትም እዚህም ኤግዚቢሽን ከፍተናል። ስለዚህ የንግድ ግንኙነታችንን ማስተዋወቅ የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን። የሁለቱን ሀገራት የንግድ ለውውጥም ለማሳደግ እየተጠቀምንባቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመደገፍ ረገድ ጀርመን ምን አይነት ሚና እየተጫወተች ነው?
አምባሳደር ስቴፈን፡- ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት መከበር መሠረታዊ ነገር ነው። ዘላቂነት ያለው የረዥም ጊዜ ብልጽግናን ለማምጣት ይህንን ሂደት የሚደግፉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና እና ህዝብ ያስፈልጋል። አሁን ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሂደቱን ለመደገፍ መነሳሳትን ፈጥሮልናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲ የቆሙ ሁለት ተቋማትን በጣም ስንደግፍ ቆይተናል። አንደኛው በኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ብዙ ስኬቶችን አስመዝግበዋል፤ በቀጣይም እነዚህን ተቋማት መደገፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። ይህ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው፤ ለዚህም የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማድረጋችን ደስተኞች ነን።
በመጨረሻም መናገር የሚፈልገው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ኢትዮጵያ አሁን ወደ ሰላምና መረጋጋት እየመጣች ነው። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተወሰደ ያለው ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ነው። ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ጉዞ በጣም እናበረታታለን፤ ምክንያቱም በአፍሪካ ውስጥ እንደገና የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሃይል ባለቤት ለመሆን ትልቅ አቅም ስላላት ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የመረጋጋት መልህቅ እንድትሆን እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለ ጊዜዎት ከልብ እናመሰግናለን።
አምባሳደር ስቴፈን፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም