በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሥራ አጥነትን ችግር መፍታት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ሥራ ፈጠራን ማበረታታትንና መደገፍን ይጠይቃል፡፡ በተለይ በአፍሪካ ለዓመታት የተከማቸውን ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ልማት ማካሄድ በብዙ መልኩ ተመራጭ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በውሃ ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ልማት በብዙ መልኩ አዋጪ ነው፡፡ በከተሞች ያሉ የውሃ አካላትን በማልማት ለወጣቶች ሰፊ ሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ይገለጻል።
ለምሳሌ፤ በከተሞች ባሉ የውሃ አካላት ላይ የእርሻ ሥራና የዓሣ ርባታ ማካሄድ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ የትራንስፖርት ወጪ አይጠይቅም፤ በትንንሽ ቦታዎች አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት በቀላሉ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ አፍሪካዊያን ያለባቸውን የወጣቶች የሥራ ችግር ለመፍታት በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ሥራ መፍጠር እንደሚገባቸው የተለያዩ ምሁራን ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ። በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ አህጉራዊ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ሚስተር ላሚን ማናህ እንደገለጹት፤ አፍሪካ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ቢኖራትም የሚፈለገውን ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበችና ለወጣቶቿም የሥራ ዕድል እየፈጠረች አይደለችም፡፡
ችግሩን ለመፍታትም በውሃ አካላት ላይ ማዕከል ያደረገ የሥራ ዕድል መፍጠርና ቴክኖሎጂ መጠቀም አለባት፡፡ በከተሞች በሚገኙ ወንዞች፤ ባህሮችና ሀይቆች ላይ ያተኮር የሥራ ዕድል ፈጠራ ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ይጠቅማል። ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ ኢኮኖሚም ለመገንባት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ባይ ናቸው ዳሬክተሩ፡፡ ቻይና፤ አሜሪካ፤ ጃፓንና መሰል አገራት በከተሞች በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ቴክኖሎጂና የሥራ ዕድል ፈጠራ በማስፋፋታቸው ለዚህ ዕድገት መብቃታቸውን በአብነት አንስተዋል፡፡
እነዚህ አገራት በእርሻ፤ በእንስሳት፤ በዓሣ፤ በቱሪዝም፤ በማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና በቴክኖሎጂ መስኮች ለዜጎቻቸው ብዛት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ፉሚዮ ሺሙዝ በበኩላቸው የአፍሪካ አገሮች ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት በመስጠት የሥራ አጥነትና የፈጠራ ውስንነትን ችግር መፍታት አለባቸው። በተለይ የሥራ ፈጠራቸው በውሃ አካላት ላይ ቢያተኩር የተፈጥሮ ችግሮችን በመቋቋም ዘላቂ ሰማያዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላቸዋል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ ለዚህም ተቀዳሚ ተግባራቸው የትምህርት መስክን ማስፋፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርት የፈጠራና የዕድገት መሰረት ነው።
ለአንድ አገር ዕድገት መሰረቱ የሰው ኃይል ልማት ነው። በእውቀት፤ በስነ ምግባርና በክህሎት የታነጸ ማህበረሰብ ሥራ ዕድልና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ቅርብ ነው፤ ይላሉ፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ አገራት በሰው ኃይል ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ጃፓን ከአውዳሚው የ2ኛው የዓለም ጦርነት ወጥታ ባለፉት 70 ዓመታት በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ቁንጮ ላይ የተቀመጠችው በሰው ኃይል ልማትና በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ልማት በማካሄዷ እንደሆነ አውስተዋል፡፡
በስነ ምግባር የታነጸ፤ ለፈጠራ ትጉህ የሆነ፤ ለሥራ የታተረ፤ ጤነኛ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል። በተጨማሪም፤ አገራቱ የሚያስመዘግቡት የኢኮኖሚ ዕድገትም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያረካና የሚያስደስት መሆን እንዳለበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በስፋት የሰው ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት እንደጀመረች አውስተው፤ ዛሬም ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ የጃፓን ህልውና ፈተናዎች ቢሆኑም፤ እነዚህን የተፈጥሮ አደጋዎች በመቋቋም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ማስቀጠል የቻለችው በሰው ኃይል ልማት፤ በውሃ አካላትና በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ልማት በማካሄዷ መሆኑን ተናገረዋል።
ለምሳሌም፤ እኤአ በ2012 የጃፓን ዓመታዊ በጀት 490 ትሪሊዮን የን ነበር። ይህ በጀትም እኤአ በ2018 ወደ 550 ትሪሊዮን የን ማደግ መቻሉን ነው የጠቀሱት። እናም አሉ አምባሳደሩ፤ የአፍሪካ መንግሥታት በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ የሥራ ዕድል ፈጠራን ቢያካሂዱ አህጉሪቱ በተደጋጋሚ የሚያ ጋጥማትን የድርቅ አደጋ መቋቋም ያስችላታል። ለዕድገቷ ቀጣይነትም ዋስትና ይሆናል። ስለዚህ የሥራ ፈጠራን ለማበረታታትም መንግሥታት የታክስ ማበረታቻ ማድረግ፤ ለንግድና ለፈጠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ የብድር አገልግሎትን ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋት ድህነትን ለመቀነስ አንዱ መንገድ ነው ሲሉም ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ አፍሪካውያን ለአገራቸው ምርት ዋጋ አለመስጠት፤ ለፈጠራ የሚረዱ ተግባራዊ ትምህርት አለመኖርና የፋይናነስ አቅርቦት አለመኖርና የተንዛዛ መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ፈጠራን ለማስፋፋት ተግዳሮቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ በፈጠራና በቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ አተኩራ እየሠራች መሆኑን የገለጹት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመት ግዛው፤ በዚህ መስክም ይበልጥ ወጣቶችን ተሳተፊ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
ሥራ ፈጠራን ለማበረታታ ወጣቶችን በሂሳብ አያያዝ፤ በአስተዳደር፤ በንግድ ክህሎት፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ክህሎትና ዕውቀት ማስጨበጥ ለሥራቸው ስኬታማነት ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን ጠቁመዋል። በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ልማትና ሥራ ፈጠራም የምግብ ዋስትና የማረጋገጥን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፤ ድህነትን ለማጥፋትና ለቱሪዝም ትልቅ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማቋቋም የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች መሥራት አለባቸው፡፡
ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ማምረት ቢቻል ለብዙ ሥራ አጥ ዜጎች ሥራ መፍጠር ይቻላል። የአፍሪካ አገራት በአብዛኛው ኢኮኖሚያቸው የሌሎችን አገሮች የኢንዱስትሪ ምርቶች በመግዛት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እነዚህን ምርቶች በአህጉራቸው ማምረት ቢችሉ ጥሬ ዕቃ ከማቅረብ ጀምሮ ምርቶቹን እስከ መሸጥ ድረስ ባሉ ሂደቶች ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል ተብሏል፡፡
እናም መንግሥት አማራጭ የሥራ መስኮችን በባለሙያዎች እያስጠና ለተደራጁ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ እንዲሰማሩ እያደረገ ነው ብለዋል ዶክተሩ፤ በተለይ የአነስተኛ እና የጥቃቅን ኢንዱስትሪ ማህበራትን በማስፋፋት፤ ለወጣቶቹ ስልጠና በመስጠት፤ መስሪያና መሸጫ ቦታ በማዘጋጀት፤ ብድርና የገበያ ትስስር በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መስክም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመላመድ ሥራ እንዲሚሥራ ይፋ አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ካደረጉት የኢኮኖሚ ሴክተሮች ውስጥም ቱሪዝም አንዱ ነው።
በተለይ፤ ዘርፉ በሥራ ዕድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድ የማይናቅ አስተዋፅኦ አለው። በቱሪዝም ዘርፍ ጠቀም ያለ ገቢ እያገኙ ካሉ ሀገራት መካከልም ደቡብ አፍሪካ፤ ኬንያና ኢትዮጵያ ይገኙበታል። ስለዚህ በከተሞች የሚካሄደው በውሃ አካላት ላይ ያተኮረ ልማት ለወጣቶች ሥራ ከመፍጠር በሻገር የቱሪስትን ፍሰት ከመጨመርና ከተሞችን ማራኪ ከማድረግ አንጻርም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ሌላው በከተሞቹ የሚሠራው ሥራ ከውጭ አገር የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱም ያበረታታል፡፡
ብዙ ዜጎችን በከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ የውሃ አካላት ዙሪያ መስኖ ልማት በስፋት በማካሄድ ለብዙ ዜጎች ሥራ መፍጠር ይቻላል፡፡ አፍሪካውያን መንግሥታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣት የሥራ አጥ ችግር ለመፍታት በተለይ ወንዞችን፤ ሐይቆችንና ባህሮችን ማዕከል ያደረገ የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ማካሄድ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ጉባኤ ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምና በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በጌትነት ምህረቴ