ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴር ሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱንና የተፈጠሩ ክፍተቶችን እያጠና አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። ከነዚህ ውስት አንዱ ዛሬ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጀምረው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው።
ንቅናቄውን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መረጃ ይፋ ያደረጓቸው አሃዞች አስደንጋጭ እንደነበሩ መገመት የሚከብድ አይደለም። የአንዲት ሀገር መሰረት የሆነው ትምህርት በዚህ ደረጃ በተግዳሮት ውስጥ መገኘቱ ማንንም እንቅልፍ የሚያስተኛ አይደለም።
እንደሚኒስትሩ መግለጫ ከሆነ፤ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአንደኛ ደረጃ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው። ሙሉ በሙሉ ከደረጃ በታች ሊሆኑ ምንም የቀራቸው አይደሉም። ከ71 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ከደረጃ በታች ናቸው። ሁለተኛ ደረጃ ማለት እንግዲህ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም (ለምርምር ማለት ነው) የሚዘጋጁበት መሰናዶ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መሆኑ ነው።
ትምህርት ቤቶቹ በዓለም አቀፍ የጥራትና ደረጃ መለኪያ ተለክተዋል። ዝቅተኞቹ ደረጃ አንድ ከፍተኞቹ ደረጃ አራት ሆነው ማለት ነው። በዚህ ልኬት ደረጃ አራት ላይ የደረሱ ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዜሮ ነጥብ ዜሮ ዜሮ አንድ በመቶ ብቻ ናቸው። በቁጥር ሲታይ ደግሞ ደረጃውን ያሟሉት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 6 ብቻ ናቸው። 10 በመቶ የሚሆኑት 3ኛ ደረጃ ላይ ናቸው። ከ89 በመቶ በላይ ያሉት ግን ገና አንደኛውና ሁለተኛው ደረጃ ላይ ናቸው፤ ለትምህርት በፍጹም ብቁ ያልሆኑ ማለት ነው።
በዚሁ መግለጫ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ይህን ችግር በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት ከ30 እስከ 40 ዓመታት ይፈጃል፤ እንዲህ ከሆነ ሁለት ትውልድ የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት አያገኝም ማለት ነው። ሁለት ትውልድ ዘመኑ የሚጠይቀውን ትምህርት አያገኝም ማለት አገሪቱ ምን እንደሚያጋጥማት መገመት ቀላል ነው።
ከዚህ ሀገራዊ አስደንጋጭ ችግር ለመውጣት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበትና የአቅሙን የሚያበረክትበት ሁኔታ ማመቻቻት አስፈልጓል ፤ ጥራት ያለው ትምህርት ለመጪው ትውልድ ብሩህ ነገዎች ከሚኖረው መተኪያ የሌለው አስተዋጽኦ አንጻር ችግሩን በቁርጠኝነት መጋፈጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት፤ ግዴታ ጭምር ነው።
በትምህርት ሚኒስትሩ በኩል የተጠራው ሕዝባዊ የትምህርት ንቅናቄ አላማው ይሄው ነው። እነዚህን ትምህርት ቤቶች ወደ ደረጃ ማምጣት፤ ለመማር ማስተማሩ አመቺ እንዲሆኑ ማስቻል፤ ለዚህ የሚሆነውም አቅም አሰባስቦ መንቀሳቀስ ነው ።
በዚህ ንቅናቄ የመሳተፍ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ነው፤ በተለይም የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት በላይ ሀገራዊ ኃላፊነት የለም እና በንቅናቄው በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
የአንዲት ሀገር ሁለንተናዊ መሰረት ትምህርት ከመሆኑ አንጻር ጥሪው ሀገራችንን በጠንካራ መሰረት ላይ እንገንባ የሚል ድምጸት ያለው ነው። የተማረ ዜጋ ካልተፈጠረ ነገ፤ ከነገ ወዲያ የሚፈራ ሀብት ለትውልድ የመተላለፍ ዕድሉ ጠባብ ነው። የተማረና የሰለጠነ ዜጋ ካልተፈጠረ ከልማት ይልቅ ጥፋት ይበዛል። ሆነው ያየናቸውም ሊያስተምሩን ይገባል።
ነገ ባለሀብት መሆን የሚፈልግ ሰው የተማረና የሰለጠነ ዜጋ ካልተፈጠረለት ባለሀብት መሆን አይችልም። ቢሆንም በብዙ ውጣ ውረድ ያፈራው ሀብት የጥፋቱ ሰለባ ስላለመሆኑ መተማማኝ የለውም። በዚህ የተነሳም ትምህርት ቤቶችን መገንባት የነገን መዳረሻ ማሳመር ጭምር ነው።
ልጆቹ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱለት የማይፈልግ የለም፤ ልጆቹ ሥቃይና መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈልግ የለም። ስቃይና መከራ እንዳይደርስባቸው፣ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ፤ የሰለጠነ ዜጋ ያላት አገር መፈጠር ያስፈልጋል፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በትምህርት ነው። በእውነቱ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለትምህርት አስፈላጊነት ማውራቱ በራሱ ምን ያህል እንደተጎተትን የሚያሳይ ነው።
በሕዝባዊ ንቅናቄው ጥሪ የተደረገው ለሁሉም ዜጋ ነው። በተለይም ተምረው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ቀድመው አርዓያ ሊሆኑ ይገባል። መንግሥት በነጻ አስተምሯቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ምን ባደርግ ነው ለውጥ የሚመጣ ማለት አለባቸው። ታዋቂ ሰዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸውና ይህን ንቅናቄ ሊያስተባብሩና ሊያስተዋውቁ ይገባል።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እስከዛሬ በነበረው አሰራር ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነው ተገኝተዋል። ይህ ምናልባትም በአንድ ጊዜ የሆነ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ነው። በዚህም ምክንያት ያለፈው ሥርዓትና ትውልድ ሊወቀስ ይችላል። ከዚህ መማር ያለብን አሁን የተጠራውን ንቅናቄ ካልሰራንበት እኛም በቀጣዩ ትውልድና ሥርዓት እንደምንወቀስ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር ጥናት አድርጎ ችግሮችን በዓይነት በዓይነት ዝርዝሮ ለመንግሥትና ሕዝብ አሳውቋል። ስለዚህ ነገርየው የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። የአንዲት ሀገር ዕድገትና ሥልጣኔ መጓዝ የሚችለው የተማረ ዜጋ ሲኖር ብቻ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ነገ መድረስ ያለባቸውን ነገር በጉጉት ይጠብቃሉ። ባለሀብቶች ሌት ከቀን የሚሰሩ ለዕለቱ የሚበላ ይቸግረናል ብለው አይደለም፤ ለቀጣይ ትውልድ ነው።
እኛ ተራ ግለሰቦች እንኳን ቤት ለመሥራትም ሆነ ለመግዛት የምንመኘው ለአንድ ጉሮሯችን አይደለም፤ ለልጅ ልጆቻችን ጭምር ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ሀገር ሰላምና ልማት ሲኖራት ነው። ያ የሚሆነው ደግሞ የተማረና የሰለጠነ ዜጋ ሲኖር ነው። የበለጸጉ ናቸው የምንላቸው አገራት የቅንጦት ነገሮች ላይ የደረሱት ከዘመናት በፊት ትምህርት ላይ ስለሰሩ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር ያሳወቀንን አስደንጋጭ መረጃዎች ልብ ልንል ይገባል። ልብ ብለንም ለንቅናቄው የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አለበለዚያ በልጆቻችን የነገ ዕጣ ፋንታ ላይ እየፈረድን እንደሆነ ለደቂቃዎች ልንዘናጋ አይገባም። ነገዎቻችንን እያለምን እንደሆነ ጭምር።
ከዛሬ 40 ዓመት በኋላ ዓለም ምን ላይ እንደምትደርስ መገመት ቀላል ነው፤ በቀደመው አካሄዳችን ለመጓዝ ከወሰንን ፤ በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ትውልድ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም ፤ ይህንን እውነታ ዛሬ ላይ ሆነን ለመቀልበስ እያንዳንዱ ዜጋ የልጆቹን ነገ እያሰበ ለንቅናቄው ስኬት የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ ይገባል!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2015