የትምህርት ጥራት ከብዙ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከልም ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ያላቸው ምቹነት ይጠቀሳል፡፡ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያመለከቱትም ይህንኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ249 ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኞቹ ለመማር ማስተማር አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች የሏቸውም፤ በዚህ የተነሳም ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ እንዲማሩ ተገደዋል።
በሀገሪቱ ካሉ ትምህርት ቤቶች 86 በመቶው የአንደኛ ደረጃ፣ 71 በመቶው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካሉ ትምህርት ቤቶች 99 በመቶ የሚሆኑት ለመማር ማስተማር ውጤታማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ደረጃ አያሟሉም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ስኬት ካላቸው ቁመና አንጻር በአራት ደረጃዎች እንደሚከፈሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ደረጃ አራት ላይ ያሉት ለመማር ማስተማር ሂደት የተሟላ ቁመና ያላቸው ናቸው፤ ደረጃ አንድና ሁለት ላይ ያሉት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ የሌላቸው ሲሆኑ ደረጃ ሶስትም ከእነዚህ ብዙ የተለየ አይደለም፡፡ በዚህ ልኬት በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው።
ለራሱ እና ለሀገሩ፣ ብሩህ ነገዎችን መፍጠር የሚችል ትውልድ ለማፍራት ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ማድረግ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሀገራዊ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በዘርፉ ያለው ሀገራዊ እውነታ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በተጨባጭ ያመላከተ ነው፡፡
በሀገሪቱ ዛሬም ቢሆን በርካታ ህጻናትና ወጣቶች ዳስ ውስጥ፣ ሌሎች በርካቶች በዛፍ ጥላ ስር የሚማሩበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ አልተለወጠም፡፡ ስም ጥር፣ ተዋቂና አንጋፋ፣ ብዙ ምሁራንን ያፈራ የሚባለው ትምህርት ቤት አይነቶቹም ቢሆኑ አሁን በወጣው መረጃ መሰረት ”ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት በራብ ይሞታል” እንዲሉ አይነት ናቸው፡፡ ለመማር ማስተማሩ ሥራ ምቹ የሆኑት ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ መገኘታቸው በትምህርቱ ዘርፉ የተከሰተውን ትልቅ ስብራት ይጠቁማል፡፡
አቅሙ አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ የችግሩ ሰላባዎች መሆናቸው የችግሩን ግዝፈትና ስር የሰደደ መሆን ከመጠቆም ባለፈ፤ ችግሩ በመንግስት አቅም ብቻ ሊፈታ እንደማይቻል ያመላክታል፤ ችግሩን የመፍታቱ ሥራ መላውን ሕዝብ፣ ባለሀብቶችን፣ አጋሮችን፣ ወዘተ በስፋትና በንቃት ማሳተፍን እንደሚጠይቅ ያስገነዝባል፡፡
የሀገሪቱና ሕዝቦቿ እጣ ፈንታ በተማሩ ዜጎቿ እውቀትና ክህሎት ላይ ያረፈ ነው፡፡ የየትኛውም ያደገ ሀገር ተሞክሮም የሚያመለክተው ይሄንኑ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ህጻናትና ወጣቶች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ በሚገባ ከተሰራ ሀገር ከዜጎቿ የምትጠብቀውን የዕውቀትና ክህሎት አዝመራ ታጭዳለች፤ በሚገባ ካልተሰራ ደግሞ ባለችበት ትዳክራለች ወይም የቁልቁሊት ጉዞዋን ትቀጥላለች፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናትና ወጣቶች በዚህ ዘመን ለመማሪያ አይደለም ለመቆያም በማይመጥኑ የመማሪያ ክፍሎች በተባሉ መጠለያዎች፣ ጥቂት የማይባሉትም ዳሶች ውስጥ ለመማር ተኮልኩለው እንዲታዩ መፍቀድ በዜጎችና በሀገር እጣ ፈንታ ላይ መፍረድ ይሆናል፡፡ ችግሩን ለመፍታት አለመረባረብ መላውን ሕዝብ፣ ባለሀብቶች፣ በተለይ በትምህርት ላይ የሚሰሩ አጋሮችን ተጠያቂም ያደርጋል፤ ራስን ከተጠያቂነት ለማዳን የትምህርት ቤቶችን ደረጃና ግብዓት ለማሟላት ዛሬ ይፋ የሚደረገውን ንቅናቄ መቀላቀል ይገባል፡፡
አሁን ካሉት የሀገሪቱ የትምህርት ተቋማት ብርቱ፣ ሀገር ሊለወጡ የሚችሉ ዜጎችን መጠበቅ ፍጹም የዋህነት ነው፡፡ ለራሱ፣ ለሀገሩ፣ ብሩህ ነገዎችን መፍጠር የሚችል ትውልድ ለማፍራት ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ማድረግ ለነገ የማይባል ዛሬውኑ የሚጀመርና በዘላቂነት የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡
የትምህርት ቤቶቹ ደረጃ እንዲጠበቅ መሥራት በነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ማካሄድ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ዛሬ ለትምህርቱ ሥርዓት የሚውለው ሀብት ነው በመጪው ዘመን ውጤታማ ዜጎችን ማግኘት የሚያስችለው፡፡ ለዚህም መንግስት በሚያካሂደው ንቅናቄ ላይ የራስን የኢንቨስትመንት ድርሻ ማኖር ይገባል፤ ይህ ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው የሚጀመረው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2015