አዕምሮ ኢንተርፕረነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት የ30 ዓመት ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ኩባንያ ነው። ኩባንያው 51 አባላት ያሉት ሲሆን፣ 47ቱ በኩባንያው የሰለጠኑ ናቸው። ኩባንያው ወደ ተቋም የመቀየር ዓላማ ያነገበ ነው፤ ዓላማውን ዕውን ለማድረግ ከፍለው ከሚሰለጥኑ ሰልጣኞች በተጨማሪ በተለያዩ አማራጮች የስልጠና እንዲሁም የማማከር አገልግሎት ለሚፈልጉም አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።
ኩባንያው ከፍለው ከሚሰለጥኑት በተጨማሪ መለወጥ ለሚፈልጉ ሰዎች በተለያዩ አማራጮች የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) ስልጠናን በመስጠት ብዙዎችን ከህልማቸው ማገናኘት መቻሉን ይገልጻል። ላለፉት ሦስት ዓመታት 167ኛ የደረሰ የዩቲዩብ ፕሮግራምን ጨምሮ በአሀዱ ሬዲዮ የስኬት መንገድ በሚል ርዕስ የኢንተርፕረነሺፕ ስልጠናን አጠናክሮ እየሰጠ ይገኛል።
ዶክተር ወረታው በዛብህ የአዕምሮ ኢንተርፕረነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማህበር መሥራች ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው፤ የቦርድ አባልና ዋና ሥራ አስፈጻሚም ሆነው ይሠራሉ። በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነቶች ዶክትሬት ዲግሪ አላቸው። አማርኛን ጨምሮ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ሩሲያኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ።
ራዕይ ያላቸው ሥራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት እያደረጉ ካሉት እንቅስቃሴ አስቀድሞ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ነበሩ። ከመምህርነታቸው በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ፒያሳ ካምፓስ ዲን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ፋይናንስ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ዶክተር ወረታው ሠርተዋል።
በዚህ ወቅት የሕይወታቸውን መንገድ የቀየረ አንድ ክስተት መፈጠሩን ዶክተር ወረታው ያስታውሳሉ። ጊዜው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ የሚባል ተቋም ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ እርሳቸውን ጨምሮ አምስት መምህራንን የኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠና ለተማሪዎች እንዲሰጡ ይፈልጋል። በቅድሚያ ግን አምስቱ መምህራን ተማሪዎቹን ማሰልጠን የሚያስችላቸውን ስልጠና ለ15 ቀናት እንዲያገኙ ተደረገ።
ስልጠናውን ባገኙ ማግስት ዶክተር ወረታው የሕይወት መንገዳቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው በግልጽ መረዳት ቻሉ። በ15 ቀናት ስልጠና ያገኙት ዕውቀት ሚሊዮኖችን መፍጠር የሚያስችላቸው እንደሆነ ይረዳሉ። ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነቶች መሠረቶቹ የቢዝነስ ሰዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ቱሪስቶችና ሌሎች እንደሆኑ በመረዳት እነዚህን ሰዎች የመፍጠር እልህ ከስልጠናው ማግኘት እንደቻሉ ነው ዶክተር ወረታው የገለጹልን።
ከስልጠናው በኋላ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት ብቻ ይኑረኝ። ማዕረጎቹ አያስፈልጉኝም በማለት መምህር ብቻ ልሁን በማለት ቢሮውን አስረክበው የጊዜ ነፃነታቸውን አረጋገጡ። ይህን የጊዜ ነፃነት በመጠቀምም ተንቀሳቅሰው የተግባር ትምህርቶችን ተከታተሉ። ‹‹እኔም የራሴ አለቃ ነኝ፤ ተቆንጥሮ የሚሰጥ ሥራ ሠርቼ ራሴን ቤተሰቤንና ሀገሬን መለወጥ አልችልም›› በሚል እልህ ከላይ ታች ማለትን ከስልጠናው ማግስት ጀመሩ። ተስፋ ሳይቆርጡ ብዙ ጊዜ ወድቀው መነሳታቸውም ለዚሁ ነው።
የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) ስልጠና የሰጣቸው ተቋም ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ በወቅቱ በጥሩ ደመወዝ የቀጠራቸው ሲሆን፤ ከስልጠናው ጋር በተያያዘም ሁለት ጊዜ ኡጋንዳ በመጓዝ በኢኮኖሚና ማህበራዊ በኩል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ይናገራሉ። ከሁሉም በላይ ግን ኡጋንዳ ካምፓላ 40 ሰልጣኞችን ለማሰልጠን ሄደው ከፍለው ለመሰልጠን የተዘጋጁት 200 ሰዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያን ወክለው ኡጋንዳ ላይ 40 ሰልጣኞችን ሲያሰለጥኑ ያገኙት ግብረመልስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) ማሰልጠኛ ተቋም መክፈት እንዳለባቸው ነው። ይህ ሃሳብ እዚያው ኡጋንዳ ላይ ተጠነሰሰ።
የሃሳብ ጥንስሳቸውን መሬት ለማሳረፍ ሲነሱ አስቀድመው ከተቀጣሪነት መውጣትና ወድቀው ለመነሳት ወስነው ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ጥለው የወደቁ ቢሆንም፣ ወድቀው ሳይቀሩ በብዙ ብርታት ተነስተዋል። ‹‹ማንኛውም ፍሬ ሳይበሰብስ እንደማይበቅል፤ ሳይበቅል እንደማያፈራ ሁሉ፤ እኔም እንደ ፍሬዋ በብዙ ነገር ተፈትኜ ብዙ ጊዜ ወድቄ ለመነሳት ወስኜ ሁሉንም አልፌዋለሁ›› ይላሉ።
‹‹ኢንተርፕረነርሺፕ ሲስፋፋ ኢትዮጵያ ትፋፋለች፤ የኢትዮጵያ ሀብት ከአንገት በላይ ያለው/አእምሮ/ የልጆቿ አካል ነው›› የሚሉት ዶክተር ወረታው፤ ይህን ለማድረግ ትልቁ መሣሪያ የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) ልማት እንደሆነም በጽኑ ያምናሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተገባ ነገር እንዳይስፋፋ የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) መስፋፋት አለበት። ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ከልጆቿ አንገት በላይ ያለውን አካል (አእምሮ) መጠቀም ሲቻል እንደሆነም ይናገራሉ።
እርሳቸው ወደ ዘርፉ በገቡበት ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ አንድም የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) መጽሐፍ አለመኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ወረታው፤ ሰባት መጽሐፍቶችን በግላቸው በጋራ ደግሞ ስድስት በድምሩ 13 መጽሐፍቶችን እንዲሁም ሰባት ማሰልጠኛ ተንቀሳቃሽ ምስል (በሲዲ) አዘጋጅተው አንድ ሚሊዮን ባለራዕይ ዜጎችን ለማፍራት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጸዋል። መጽሐፍቶቹ በተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በኦሮሚኛና በትግርኛ የተዘጋጁ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ፈጠራ ካልተስፋፋ ያልተገባ ነገር እንደሚስፋፋም አስረድተዋል።
ዛሬ ላይ የሥራ ፈጠራ (የኢንተርፕረነርሺፕ) ለማስፋት መንግሥትን ጨምሮ በግለሰብ ደረጃም ብዙ አማራጮች እየመጡ እንደሆነና ይህም እንደሚበረታታ የጠቀሱት ዶክተር ወረታው፤ አዕምሮ ኢንተርፕረነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማህበር የማሰልጠንና የማማከር ሥራውን በስፋት እየሠራ እንደሆነ ይገልጸሉ። በዚህም በእስካሁን ቆይታቸው በርካታ ባለራዕዮችን መፍጠር እንደቻሉም ተናግረዋል።
በተለያየ ጊዜና ቦታ የሚሰጡትን ስልጠናና የማማከር ሥራ ሳይጨምር በመደበኛው ዙር ብቻ እየከፈሉ ለሚሰለጥኑ ሰልጣኞች አንድ ሺ ጊዜ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፣ በስልጠናው ተጠቅመው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን ማገዝ የቻሉ ኢትዮጵያውያን በርካታ መሆናቸውንም አብራርተዋል። ሩቅ ሳይሄዱ በቅርብ ካሉት እርሳቸውን ጨምሮ የኩባንያው አባል የሆኑ 47ቱ አባላት የዚህ ውጤት መሆናቸውን እና ስኬታማ እንደሆኑ ተናግረዋል። አብዛኞቹም የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው ለብዙዎቸ ሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት በርካቶች እንደሆኑም አመልክተዋል።
በማዕከሉ ስልጠና ያገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለራዕይ ሰልጣኞች ስለመኖራቸው የጠቀሱት ዶክተር ወረታው፤ እነዚህ ሰልጣኞች አሁን ላይ የማይታዩ ነገር ግን ወንዝ ሆነው የሚፈስሱ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ። ምናልባትም ፍሬያቸው የሚታየው ወደፊት እንደሆነ ገልጸው፤ ኩባንያው ከሁለት ሰዎች ጀምሮ እንደሚያሰለጥንም አመላክተዋል።
‹‹አሜሪካ በአምስት ኢንተርፕረነሮች ነው የተቀየረችው›› የሚሉት ዶክተር ወረታው፤ እነዚህን ሀገር የመቀየር አቅም ያላቸውን አምስት ኢንተርፕረነሮች ለማግኘት በርካቶችን ማሰልጠን የግድ መሆኑን ይገልጸሉ። እነዚህ ሰዎች ሲገኙ ኢትዮጵያ ድህነት፣ ስደት፣ ረሃብና ጦርነት አጀንዳዎቿ አይሆኑም ይላሉ።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የታደለች ሀገር ናት፤ እንደ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋ የታደሉ ሀገራት በዓለም የሉም ሲሉ ዶክተር ወረታው ይገልጻሉ። ባለራዕዮቿና ህልም ያላቸው ልጆቿ ጥቂቶች መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ሠርቶ ከመብላት ውጪ ወደፊት መጓዝ አልተቻለም ወደኋላ ቀርተናል ይላሉ። ሌሎች ያደጉ አገራት ተሞክሮ የሚያመለክተው ሠርቶ ከመብላት ባለፈ ማትረፍረፍ፣ ለትውልድ ጥሎ ማለፍ የሚል ነው። እኛም ይህን ማድረግ ይጠበቅብናል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለዚህም ሀገር የሚቀይሩ ኢንተርፕረነሮች መፈጠር ይኖርባቸዋል፤ ኢንተርፕረነሮች ሲፈጠሩ ትላልቅ ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ቦታዎች፣ ሆቴሎች፣ የትምህርትና የሕክምና ተቋማትና ሌሎችን መገንባት ይችላሉ። ተቋማቱን ለትውልድ አስተላልፈው እነሱ ግን ያልፋሉ። ለዚህም በሀገር ደረጃ ብዙ መሠራት አለበት።
ብዙ መደፈን ያለባቸው ክፍተቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ የመጀመሪያውና ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ የመቶና የሁለት መቶ ዓመት ዕቅድ የሌላት መሆኑን ትልቅ ክፍተት ሲሉ ገልጸውታል። የዛሬ መቶና ሁለት መቶ ዓመት የሕዝቡ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል፤ ስለዚህ «ምን እመግበዋለሁ፣ ምን ይሠራል፣ መኖሪያውስ ወዴት ይሆናል» የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ እቅዶችን አቅዶ የመንቀሳቀስ ክፍተት ከእያንዳንዱ ቤት አንስቶ እስከ ቤተመንግሥቱ እንደሚታይ ዶክተር ወረታው አመልክተዋል። ይህን ችግር ለመፍታት የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል። ሥራ ፈጣሪዎች በዕቅድ እንደሚመሩ ጠቅሰው፣ እርሳቸውም የፈጣሪን ፈቃድ በማስቀደም የ30 ዓመት ዕቅድ አዘጋጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራሉ።
«ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር የተሰጣት ታላቅ ሀገር ብትሆንም እንደታላቅነቷ ሕዝቦቿ አላደጉም ዛሬም ረሃብና ጦርነት መገለጫዎቿ ናቸው» የሚሉት ዶክተር ወረታው፤ ይህም ራእይ ያለው ካለመሆን ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ወንዞች በከንቱ እየፈሰሱ፣ መሬቱ እያለ መጠቀም አለመቻሉን ጠቅሰው፣ ሁሉን የተሰጣት ኢትዮጵያ የሕዝቦቿ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር ግን መወሰዱንና ሕዝቡ በማይጠቅመውና በማይመለከተው ጉዳይ እየገባ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን እያጠፋ እንደሆነ ነው ያብራሩት። ለዚህም ቁልፉ ችግር ኢትጵያ ውስጥ የፈጠራ ጥበብ ክህሎቶች የዳበሩ አለመሆናቸውንና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ መንቀሳቀስ አለመቻሉን ያመለክታሉ።
«ቢዝነስ ላይ ያለው አመለካከት ትክክል አይደለም፤ በተለይም ሀገርን ለትልቅ ህልም ማነሳሳት ከፖለቲከኞቹ ይጀምራል፤ እንዲህ ዓይነቱ መነሳሳት አብዛኞቹ ፖለቲከኞቹ ዘንድ የለም» የሚሉት ዶክተር ወረታው፤ ለዚህም ሕዝቡ በልቶ አደር እንጂ አትረፍርፎ አደር እልህኛ መሆን አልቻለም ብለዋል። የሚገባንን መሥራት አልቻልንም፤ በመሆኑም ሁልጊዜ ተጨማሪ የቤት እጥረት፣ የምግብ እጥረት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እጥረት፣ የመማሪያና የትምህርት ጥራት እጥረት ሌሎችም እጥረቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተደራረቡና እየተነባበሩ መምጣታቸውን ነው ያስረዱት።
ሁሉም ነገር ሞልቶ የተትረፈረፈባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ ሀገሪቱ ሀብቶቿን ተጠቅማ መልማት፣ ማደግና መለወጥ እንድትችል እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት አለበት ሲሉ ገልጸው፣ የዚህ የቤት ሥራ ከቤተሰብ እንደሚጀመርም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቤተሰብ ልጁን ሥራ ወዳድ፣ እውነተኛ፣ ሀሰትን የሚጠየፍ፣ ሀገር ወዳድና የሰው ገንዘብ የማይመኝ አድርጎ ካሳደገው ሀገር መገንባት ከዚያ ይጀመራል። ለመብላት መሥራት የግድ እንደሆነና ‹‹ማንኛውም ሰው ተግቶ መሥራት ከቻለ ካሰበበት መድረስ ይችላል›› የሚለውን በመርህ ደረጃ ትውልዱ ውስጥ ማስረጽ ከተቻለ ለቀጣዩ ትውልድ ተደራራቢ ችግር አይቀመጥም።
ራስን መገንባትና ማልማት ላይ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። በተለይም ከአንገት በላይ (አእምሮ ላይ) ያለው ልማታችን አስፈላጊና ትክክለኛው ቦታ ላይ አልደረሰም። አእምሮ ላይ የሚካሄደውን ልማት ትክክለኛው ቦታ ላይ ለማድረስ አንባቢ፣ ተመራማሪና ሥራ ፈጣሪ ትውልድ መፈጠር ይኖርበታል። ገበሬው የሙያ ትምህርት ያስፈልገዋል፤ አንባቢና ተመራማሪ ሊሆን ይገባል። እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም በበሬ የሚያርስ አርሶ አደር ሊኖር አይገባም። አርሶ አደሩ ነገ ያደገና በትራክተር የሚያርስ፣ በኮምባይነር የሚወቃ፣ ምርቱን በመኪና የሚሰበስብ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግን ፈጥሮ ለአካባቢው ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችልና የመንደሩ አልሚ መሆን አለበት። የአርሶ አደሩ ምርት ሲበዛ የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች ይበዛሉ። ስለዚህ ዓመቱን በሙሉ የሚሠሩ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያስፈልጋሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀጣሪነት አስተሳሰብ እየቀነሰ ስለመምጣቱ የጠቀሱት ዶክተር ወረታው፤ በቀጣይም ተቀጣሪ መሆን የማያዋጣ እንደሆነ ትውልዱ እየገባው እንደሆነም ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ተቀጥሮ መሥራት የቤተሰብን ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። ተቀጣሪውም ቢሆን ተጨማሪ ሥራ መሥራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ መሠረታዊ ፍላጎት አለማሟላቱ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እየተቀየረ መሆኑን ጠቅሰው፣ መፍትሔው በእያንዳንዳችን መዳፍ ውስጥ መሆኑንም አመልክተዋል። በቀጣዩ በጀት አመት መንግሥት አዲስ ሠራተኞችን አይቀጥርም የሚሉ መረጃዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህም የተመረቀ ሁሉ ሥራ እንደማይጠብቀው አውቆ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ወጣቱን የሚያነሳሳ ትልቅ ዕድል መሆኑን አመላክተዋል።
እንደተባለው መንግሥት አዲስ ቅጥር የማይፈጽም ከሆነ ለተማረው ኃይል የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣ የማምረቻ ቦታ ማዘጋጀት፣ ስልጠና መስጠትና ማምረቻ ማሽኖችን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚጠበቅበት ዶክተር ወረታው ያመለክታሉ። እነዚህ ሁሉ የተሟሉለት ወጣት በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ሁሉ መሙላት የሚችል ዕድለኛ ትውልድ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015