እንደመነሻ …
ዛሬም በርካታ ጉዳዮች መፍትሄ ከሚያገኙበት፣ ጥብቅ ቋጠሮዎች ላልተው ከሚፈቱበት ስፍራ ላይ ነኝ። በዚህ ቦታ የብዙ ሰዎች ዕንባ ታብሷል፡፡ የአይታመኔ ታሪኮች መጨረሻ አምሯል፡፡ የብዙሃኑ ፈታኝ ሕይወት ተቀይሯል፡፡
ዛሬ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ግቢ የሚገኙ ነፍሶች ትናንትን በሻካራማ መንገዶች አልፈዋል። አብዛኞቹ የተስፋ መቁረጥን ስሜት አሳምረው ያውቁታል። ጥቂት የማይባሉትም በሸክማቸው መክበድ ሰው ሆነው መፈጠርን እስከ መጥላት የደረሱ ናቸው ፡፡ በወቅቱ በርካቶቹ ሰማይ የተደፋባቸው ያህል ተሰምቷቸው ያውቃል፡፡
ከእነዚህ ነፍሶች ጥቂት የማይባሉት በከፋ ችግር፣ በህመምና ባይተዋርነት ሲሰቃዩ ነበር፡፡ የትናንት ጨለማ አልፎ ዛሬ እስኪነጋም ከጎናቸው የቆመ ‹‹አይዟችሁ ›› ባይ ወገን አልነበራቸውም፡፡ ሁሉም በሚባል ሁኔታ በሰው መሀል ሆነው ሰው በማጣት ተሰቃይተዋል፡፡ እንደ ሰው ወግ አጉራሽ፣ አልባሽ፣ አስታማሚ ደጋፊን ተርበዋል፡፡
ከጎናቸው ዕንባቸውን የሚያብስ፣ ብሶታቸውን የሚያደምጥ አለመኖሩ ለብዙ ችግሮች ሲዳርጋቸው ነበር፡፡ የዛሬን አያድርገውና ትናንትን እያንዳንዳቸው በሆነባቸው ሁሉ አዝነዋል ፣ ተክዘዋል ፣ አምርረው አልቅሰዋል፡፡
ዛሬ እነዚህና ሌሎች በመልካም ልብና በቸር እጆቿ በምትታወቀው ወይዘሮ ሙዳይ መሪነት ዕንባቸው ታብሷል፡፡ ታሪካቸው ተቀይሯል፡፡ ካሉበት፣ ከወደቁበት፣ ለማንሳት የሚፈጥነው የግቢው ቅንነት በብዙ ፈተናዎች መሀል እያለፈ ደግፏቸዋል፡፡ ቀድሞ በሁኔታዎች ክፋት የጠሉትን ማንነት ሽሮም ‹‹ሰው›› መሆናቸውን መስክሯል፡፡
ዛሬም በሙዳይ ደጃፍ ጨቅላ ህጻናት ፣ በዘንቢል፣ በጨርቅ ተጠቅልለው ይጣላሉ፡፡ የተቸገሩ፣ ያዘኑ፣ ቀን የጨለመባቸው ወገኖች ዕለት ከዕለት ከግቢው ይደርሳሉ። በኤች አይ ቪ የተያዙ፣ በከፋ ህመም የተፈተኑ፣ በማጣት መንጣት ሆድ የባሳቸው ሁሉ መጠጊያ ማደሪያቸው የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ነው፡፡ እያንዳንዳቸው በውስጣቸው የያዙት አይነኬ ታሪክ አላቸው፡፡ የአብዛኞቹ ሕይወት በመልከ ብዙ ሚስጥር የተሸበበ ነው፡፡ እነዚህ ባለታሪኮች በአንድም በሌላ ምክንያት እግራቸው ወደ ሙዳይ ግቢ አድርሷቸዋል፡፡
እንዲህ በሆነ ጊዜ ፊት የሚነሳቸው፣ በር የሚዘጋባቸው አይኖርም፡፡ መከፋታቸውን የሚያ ውቁ፣ መቸገራቸውን የሚረዱ ልበ ቅኖች አቅፈው ይደግፏቸዋል፡፡ ውሎ አድሮ ያለፈ ታሪካቸው ይቀየራል፡፡ የከፋ ሕይወታቸው ይለወጣል፡፡ እነሱም ከቁስላቸው አገግመው ለሌሎች መፍትሄ ለመሆን የፈጠኑ ይሆናሉ፡፡
ከሙዳይ አንደበት…
ዛሬም ከወይዘሮ ሙዳይ ጋር ብርቱ ወግ ይዘናል። ጨዋታችን ብዙ ታሪኮችን የሚያውሳ ፣ በርካታ የሕይወት ገጠመኞችን የሚዳሰስ ነው። ወይዘሮዋ ካለፉት ታሪኮች እያስታወሰች በትዝታ ታወጋኛለች። በምሰማው እየተገረምኩ በዝም ታ ማ ዳመጤን ይዣለ ሁ፡፡
እየሰማሁት ባለው እውነት ያለፈ ታሪካቸውን የቀየሩ፣ ሕይወታቸውን የለወጡ በርካቶች መሆናቸውን አውቄያለሁ፡፡ በአብዛኞቹ የሕይወት ገጠመኞች መሀልም የሙዳይ በጎ አድራጊ ሰፊ እጆች አርፎበታል፡፡ ታሪክ በራሱ ጊዜ ቢያልፍም ‹‹ነበር›› ብሎ ይወሳ ዘንድ ግድ ነውና ከብዙዎቹ መሀል የጥቂቶቹን ልንመዝ፣ ልናስታውስ ወደናል፡፡ እነሆ! ከእውነታዎቹ አንዱ ፡፡
ከሲታዋ ሴት
ማንም ከሰዎች መሀል ተቀምጣ ቢያያት ስለእሷ የተለየ ቅጥነት ለማወቅ አይቸገርም፡፡ ይህች ሴት ከተለመደው አካላዊ አቋም ወጣ የሚያደርጋት ብዙዎች አይተው የሚደነቁባት ከሲታ ሰውነቷ ነበር፡፡ ቀጭን ነች፡፡ ‹‹ቢይዟት ትሰበራለች›› ይሏት አይነት ነፍሰ ስስ ፡፡
በአጋጣሚ ሴትዬዋን ያያት ሁሉ ከመገረም አልፎ ‹‹ክው›› ብሎ መደንገጡ አይቀሬ ነው፡፡ ከአካሏ የተጣበቀው ቆዳዋ ስጋ ይሉት አንዳች ነገር ያለበት አይመስልም፡፡ በግልጽ የሚነበበው ዘርዛራ አጥንቷ አንድ ሁለት ብሎ ይቆጠር ይመስላል፡፡
የሚገርመው ጉዳይ አብራት የምትኖር ልጇም ከእሷ ጋር መምሰሏ ነው፡፡ እሷም እንደ እናቷ ድርቅ ያለ ሰውነት ፣ ክስት ያለ አቋምና ገጽታን ይዛለች፡፡ ከሲታዎቹ እናትና ልጅ አይለያዩም፡፡ ክፉ ደግ ቀናትን፣ አስቸጋሪ ጊዚያትን አብረው ተሻግረዋል፡፡
ሙዳይ ዛሬም ይህችን ሴት የምታስታውሳት የተለየ ቅጥነቷን ከሰዎች ግርምታ ጋር አያይዛ ነው፡፡ ዓመታት ቢያልፉም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ዛሬም ድረሰ አትዘነጋም፡፡ በአጽም የቀረ የሚመስል አቋሟ፣ እንደ እንጨት የደረቀ ሰውነቷ፣ የተጎሳቆለ ማንነቷ አሁንም ትዝ፣ ትውስ ይላታል፡፡
በጎ አድራጊዋ ሴትዬዋን በግቢው ከሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ጋር አዛምዳ ማኖር ጀምራለች፡፡ እንዲህ መሆኑ ግን በታሰበው መንገድ አልቀጠለም፡፡ የነዋሪው ሰላም መናጋት፣ የግቢው ዝምታ መደፍረሰ ይዟል፡፡ የተለየ ባህርይዋ፣ ተደባዳቢነቷ ብዙዎችን አውኳል። ሙዳይ በየጊዜው በምታየው ፣ በምትሰማው ጉዳይ ተቸግራለች ፡፡
ከዚህ በኋላ በእሷ ማንነት በግቢው ከሌሎች ጋር ማኖር አይቻልም፡፡ እውነቱን ስታውቅ መፍትሄ ያለችውን አማራጭ ሞከረችና ተሳካላት፡፡ ከቀበሌ ሰዎች ጋር ተማክራ ለእሷ የሚሆን ማረፊያ ክፍል አገኘች፡፡ ከግቢው አውጥታ፣ የሚያስፈልጋትን አሟልታ በነጻነት ማኖር ጀመረች፡፡
አሁን ሴትዬዋ ከግቢው ውጭ ድጋፍ ከምታደርግላቸው ሰዎች መሀል አንዷ ሆናለች፡፡ ይህች ሴት ባሻት ጊዜ አንድ ሳምንት ምግብ ይሉትን አትቀምስም። አንዳንዴ ደግሞ ጠርሙስ ሙሉ አረቄ ግጥም አድርጋ ትጠጣለች፡፡
አሁንም ከሰዎች አትስማማም፡፡ የቀረቧትን ትጣላለች፡፡ ያገኘችውን ሁሉ እየተሳደበች፣ ትውላለች። ልጇን ጨምሮ በእጇ የገቡትን መደብደብ ልማዷ ነው። ሙዳይን ለማግኘት ሰበብ የምትሻው ሴት ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ታስጠራታለች፡፡ እሷን ማየትና ማግኘት ባሻት ጊዜ ከአፏ አትነጥላትም፡፡ ተደጋጋሚ መልዕክት ሲደርሳት ከስራ ጊዜዋ ቀንሳ ካላት ሰዓት ሸራርፋ ካለችበት ትደርሳለች፡፡ ስታገኛት ግን ምክንያቷ ሁሉ ያንስባታል፡፡
ስለ እሷ ስራ ብትፈታም፡፡ አትጨክንባትም ተረጋግታ እንድትኖር መክራ አጽናንታ ትለያታለች፡፡ ባመማት በደከማት ጊዜም ፈጽሞ አትርቃትም፡፡ ሁሌም ለልጇ እንድትኖር ትመኛለች፡፡ ስለጤናዋ አትሰለችም፡፡ መቼም ቢሆን ሀኪም ቤት ለመውሰድ ትፈጥናለች ፡፡ መድኃኒቷን ለመግዛት ትሮጣለች፡፡
የሀኪሙ ውጤት
አንድ ቀን ሙዳይ ይህችን ሴት ለማሳካም ከአንድ ሆስፒታል ወስዳ በወቅቱ ጥሩ ስም ከነበረው ሀኪም ዘንድ ታቀርባታለች፡፡ ሙሉ ምርመራ ያደረገላት ሀኪም ስራውን እንደጨረሰ የሚለው የሚናገረው ጠፋው፡፡ ሴትዬዋን የቱን መርምሮ የቱን እንደሚተው ጨንቆታል፡፡ በእሷ ውስጠት ኩላሊት ፣ ጉበት፣ ሳንባ ይሏቸው ክፍሎቿ በሙሉ አልቀዋል፡፡
ይህ አይነቱ እውነት ያልተለመደና ያልታሰበ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ችግር ይዛ በሕይወት መቆሟ፣ ያስደንቃል። ዶክተሩ በግርምታ ውስጥ ሆኖ ለሙዳይ የደረሰበትን የምርመራ እውነት አሳወቃት፡፡ ከዚህ የህክምና ውጤት በኋላ ሳምንት ትቆያለች ያለ አልነበረም፡፡ እሷ ግን ከነችግሮቿ በሕይወት መኖር ቀጠለች፡፡
ሙዳይ ባለችበት ሆና የሴትዬዋን ውሎ አዳር ትከታተላለች፡፡ እንደቀድሞው ግን በጠራቻት ቁጥር ወደእሷ አትሮጥም፡፡ ከራሷ መክራ ከመሄድ ታቅባለች። ሴትዬዋ ይህን ስታውቅ ሙዳይን የማግኘት ጉጉቷ ጨመረ። በየቀኑም መልዕክተኞች እየላከች መጥታ እንድታያት ጎተጎተች፡፡
አሁን ሙዳይና ያቺ ሴት ከተያዩ ቆይተዋል። ለአፍታ እረፍት የሌላት ወይዘሮ በየቀኑ ወደእሷ መሄዱን ካቆመች እንደዋዛ ጊዚያት ተቆጥረዋል፡፡ እንደልማዷ ሰዎችን መላክ ባታቆምም ሙዳይ ጉዳይዋ እየበዛ፣ ጊዜዋ እያጠረ ነውና ሀሳቧን መሙላት አልሆነላትም፡፡ ይህ እውነታ ሁለቱን በአካል ሳያገናኝ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ከሁለት ዓመታት በኋላ…
አንድ ቀን የሙዳይ የእጅ ስልክ ደጋግሞ አቃጨለ። ድንገት አንስታ የደዋዩን ማንነት ጠየቀች፡፡ ከስልኩ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ሳታያት የቆየችውን ሴት ድምጽ ጎልቶ ተሰማት፡፡ እስከዛሬ ሰዎችን ስትልክ የቆየችው ሴት ዛሬ እንዲደወልላት ስልክ ለምና በድምጽ እያወራቻት ነው፡፡ ደዋይዋ እየደጋገመች ሙዳይን ትጠይቃለች፡፡ ስላመማት፣ ስለጨነቃት በአካል መጥታ እንድታያት ትማጸናለች፡፡
ሙዳይ የእሷ ቃል በጆሮዋ በደረሰ ጊዜ እስከዛሬ ተስምቷት በማያውቅ ሁኔታ ውስጧ ተረበሸ። እስካሁን የምትሻውን ሁሉ እየላከች የፍላጎቷን ስትሞላ ቆይታለች፡፡ ወደእሷ ላለመሄዷ የራሷ በቂ ምክንያትም ነበራት፡፡ አሁን ግን ይህን ጉዳይ ሰበብ እያደረገችው አይደለም፡፡ ‹‹ተነስተሸ ሂጂ›› የሚል ቃል ሹክ እያላት ነው። ተማጽኖዋን፣ ልመናዋን መናቅ አልሆነላትም፡፡ የእጇን ስራ ጣለች፡፡ ከምትሄድበት ቀረች፡፡ ጊዜው እየመሽ ነው። አልተዘናጋችም፡፡ ጊዜ ሳትፈጅ መኪናዋን አስነስታ እሷ ወደምትገኝበት ሰፈር ከነፈች፡፡
“ልጄን አደራ! ‘
በስፍራው ስትደርስ እስከዛሬ ወደ እሷ ስትልካቸው የነበሩትን ሰዎች አገኘች፡፡ ሁሉም ሙዳይ ዛሬ ሞልቶላት በመምጣቷ ተደስተዋል። ሰላም ብላቸው ወደውስጥ ስትዘልቅ ታማሚዋን አገኘቻት፡፡ ዛሬም እንደቀድሞው ፊቷ እንደገረጣ፣ አጥንቷ እንዳገጠጠ፣ አፏ እንደደረቀ ነው። ታማሚዋ ገና ስታያት ‹‹እንኳን መጣሽልኝ›› በሚመስል አቀባበል ፈገግ ለማለት ሞከረች፡፡
በወቅቱ ነፍሰጡር የነበረችው ሙዳይ ይህ ገጽታዋ ውስጧን ረበሸው፡፡ ስለ እሷ በቅርበት ብታውቅም ሁለት ዓመታትን ሳታያት ቆይታለች፡፡ ዕለቱን የልቧን ማወቅ፣ የፍላጎቷን መረዳት ብትፈልግ በለመደችው የፍቅር ስሜት ወደታማሚዋ ቀረበች። ህመሙ ብሶባታል፡፡ አቅም እንዳነሳት ጉልበት እንደከዳት ያስታውቃል፡፡ ይህ የገባት ሙዳይ ወደግል ሆስፒታል ልትወስዳት መምጣቷን ነገረቻት፡፡
ታማሚዋ በግድ ፈገግ እያለች የምትለውን ሁሉ ሰማች፡፡ አሁን ሙዳይ ልብሷን እንድትለብስ፣ ከአልጋው እንድትነሳ እያገዘቻት ነው፡፡ እሷም እንደምንም ራሷን አበርትታ ለመቆም፣ ለመራመድ እየሞከረች ነው፡፡ በድንገት ግን ያልታሰበው ሆነ ፡፡
ታማሚዋ ከሙዳይ እጅ አምልጣ ሸርተት ብላ ወደቀች፡፡ ሁኔታው ያስደነገጣቸው ከወደቀችበት ሊያነሷት ፈጠኑ፡፡ የታሰበው አልሆነም የወደቀችው ሴት ዳግም አልተነሳችም፡፡ በአንድ አፍታ ትንፋሽዋ በህቅታ ተቋጭቷል ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት በሙዳይ ጆሮ ውል ያለው ቃል በህሊናዋ ተመላለሰ፡፡ ታማሚዋ በጭንቅ ውስጥ ሆና ለሙዳይ ይህን የአደራ ቃል ትደጋግም ነበር ፡፡ ‹‹አደራ !ልጄን አደራ››
ሽሽት …
ሙዳይ የሴትዬዋን ድንገቴ ሞት አምኖ መቀበል ተስኗታል፡፡ የሁኔታው አስደንጋጭነት ያስደነበራቸው የአካባቢው ሰዎች ሟችን እንስተው እንደወጉ ማስተካከልና መገነዝ አልፈለጉም፡፡ ለአመታት መታመሟን፣ ያለቅጥ መክሳት፣ መቅጠኗን ያውቁ ነበርና ሊቀርቧት አልፈለጉም፡፡ ሙዳይን አጋፍጠው ሸሹ፣ራቁ፡፡
ሙዳይ ምርጫ አልነበራትም፡፡ ለመውለድ አንድ ሳምንት ቢቀራትም፡፡ ቀድሞ ያጋጠማትን ተመሳሳይ ተሞክሮ ተጠቅማ በድፍረት ሟችን ለመገነዝ ጎንበስ ቀና አለች፡፡ ያሰበችው ተሳካ፡፡ አካሏን አስተካክላም ‹‹አደራ›› ወዳለቻት ልጇ ፊቷን ዞረች፡፡ ትንሽዋ ልጅ ሁሉም ጉዳይ መጠናቀቁ የገባት ይመስላል፡፡ ልብሶቿን ሰብስባ ከሙዳይ ጉያ ተወሸቀች፡፡ እንደልጅ አልተረበሸችም፣ ስታለቅስ፣ ስትተክዝ አልታየችም፡፡
ወይዘሮ ሙዳይ ዛሬ ላይ ሆና ያንን ቀን ስታስታውስ በዓይኖቿ ትኩስ ዕንባ ያለማቋረጥ ይወርዳል፡፡ ያቺ ሴት ከዓመታት በኋላ አጣድፋ የጠራቻት አንድም ለስንብት፣ አንድም ለአደራ ቃል መሆኑ ሲገባት በሆነው ሁሉ ትገረማለች፡፡
በወቅቱ እንደቃሏ ልጇን ተቀብላ ቀብሯን በወጉ ፈጽማለች፡፡ ይህ ታሪክ ዛሬን በትዝታ ስታወጋው ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን አይጠፋትም፡፡ በእሷ ህሊና ደግሞ ዘወትር ከምታስባቸው፣ ሁሌም ከማትዘነጋቸው አስገራሚ እውነታዎች መሀል አንደኛው ሆኗል፡፡ የከሲታዋ ሴት ታሪክና አሳዛኙ የሕይወቷ መጨረሻ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015