ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ግስጋሴ መሠረታዊ አቅም አድርጋ የምትጠቀመው የሰው ኃይሏን እና የተፈጥሮ ሃብቷን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ሃብት በባሕሪው አላቂ እንደመሆኑ በአግባቡ እና በቁጠባ ሊጠቀሙበት ካልተቻለ የሚፈለገውን ሀገራዊ ፋይዳ ሳያበረክት አለሁ እያለ ማምለጡ አይቀሬ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ በተለይም በከበሩ ማዕድናት የበለጸገች ናት፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ኢትዮጵያ በወርቅ፣ በኦፓል፣ በጀሶ ድንጋይ፣ በድንጋይ ከሰል፣ በዕምነበረድ፣ በፖታሽ፣ በታንታለም፣ በብረት፣ በነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ፣ እና ሌሎች ማዕድናት የታደለች አገር ናት፡፡ በዚህ መልኩ በጥናት የተለዩ ብቻ ሳይሆኑ፤ ገና በጥናት እየተለዩ ያሉ በርካታ ማዕድናት ስለመኖራቸውም ነው የሚገለጸው፡፡
ይሄንን ፈጣሪ ያደላት ሃብቷ ደግሞ አላት ከመባል የዘለለ በአግባቡ አልምቶ መጠቀምን በእጅጉ የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ከለውጡ ማግስት እንደ ሀገርም ዘርፉን እንደሚመራው ተቋምም ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈው፤ አቅጣጫዎችም ተቀምጠው ወደሥራ ተገብቷል፡፡
ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መካከል የወጪ ንግድ ማዕድናትን በዓይነትም በመጠንም ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ፤ ለሀገር ውስጥ የማዕድን ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ማዕድናትንም በሀገር ውስጥ መተካት አቅጣጫዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ሥርዓት መዘርጋት ቁልፍ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ መሠረትም፣ የማዕድን ዘርፉ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት የሀገራዊ ልማቱ አቅም እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ ይሄን ሚናውን እንዲወጣ ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሳደግ ሲሆን፤ ለዚህም የማዕድን ምርቱን ማሳደግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ለአብነት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ እና የባሕላዊ አምራቾችን በመደገፍ ጭምር በ2012 በጀት ዓመት ይመረት የነበረውን ሦስት ነጥብ ሁለት ቶን ወርቅ በ2022 በጀት ዓመት ወደ 137 ቶን የማድረስ፤ በዚሁ ልክ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ድርሻውን የማሳደግ ዕቅድ ተይዟል። ከዚህ አኳያ በማዕድን ዘርፉ ላይ የተወሰዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አበረታች ውጤት እያሳዩ ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪን እያስገኙም ጭምር ነው፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ ዘርፉን በእጅጉ እየተፈታተነው የሚገኘው የማዕድናት ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ሲሆን፤ ይሄም በሀገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች ላይ ጎልቶ የሚስተዋል ነው፡፡ ሂደቱም ሀገር ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረጋት ይገኛል፡፡
ለምሳሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀደም ሲል በባሕላዊ መንገድ እንኳን እየተመረተ በሳምንት እስከ አስር ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረግ ነበር፡፡ በክልሉ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እየተበራከተ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በሳምንት ሁለት ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ያልተቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡
ይሄ ሐቅ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ አይደለም፤ በኦሮሚያም፣ በደቡብም፣ በጋምቤላም፣ በሲዳማም፣ በሁሉም ክልሎች ያለ ነው፡፡ ይሄ ሕገወጥ ተግባር ደግሞ በተለያየ ቪዛ ወደ ሀገር ውስጥ በገቡ የውጪ አገር ዜጎች፣ እንዲሁም ለግል ጥቅማቸው በሚለፉ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት ጭምር የታገዘ፤ በሕጋዊ የኢንቨስትመንትና ንግድ ሽፋን የሚደረግለትም ነው፡፡
በዚህ መልኩ በሚፈጸም ሕገወጥ የማዕድናት ዝውውር ታዲያ ሀገር እንደ ሀገር ካላት ሃብት ተጠቃሚ እንዳትሆን ብቻ ሳይሆን፤ ሂደቱ ጥቂት ሕገወጦችን ማዕከል አድርጎ የሚዘወር እንደመሆኑ በሕጋዊ መንገድ በዘርፉ የተሠማሩ አካላትንም የልፋታቸውን እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ክልሉ በ2014 በጀት ዓመት 2ሺ300 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ ሦስት ሺ ዘጠኝ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ አቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም፤ በክልሉ በተንሰራፋው ሕገወጥ የማዕድን ማውጣትና ኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት በበጀት ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ከ482 ኪሎ ግራም መሻገር አልቻለም፡፡
ይሄ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ እና ሀገር ዋጋ እየከፈለች ስለመሆኑ አንድ ማሳያ እንደመሆኑ፤ ችግሩን መከላከል እና ከመሠረቱ ምንጩን ማድረቅ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትም ይሄንን ለመግታት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ ሲሆን፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በሕገወጥ የወርቅ ማውጣት እና ኮንትሮባንድ ግብይት ላይ የተሠማሩ የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ፣ ተባባሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ይሄን ተከትሎ በተወሰደ ሰፊ ኦፕሬሽንም መጠኑ ከፍ ያለ የወርቅ ማዕድን ከየሱቁ፣ ከየመኖሪያ ቤቱና ሌሎችም ስፍራዎች እየተያዘ ይገኛል፡፡ ይሄ ርምጃ ሕገ ወጦችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደረገ ጅምር ተግባር ሲሆን፤ በሕገወጦች ከሀገርና ሕዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ ለኮንትሮባንዲስቶች ሲሳይ ሲሆን የቆየው የሀገር ሃብትም ወደ ብሔራዊ ባንክ ቋት እንዲመለስ ዕድልን የሰጠ ነው፡፡
በዚህም በክልሉ አሁን ላይ በሳምንት ከአስር ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ እንዲገባ አስችሏል፡፡ ይሄ ጅምር ከወዲሁ ያሳየው ውጤት ደግሞ ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማስቻል አኳያ ሕገወጥ ተግባሩን መቆጣጠር እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱን ማዘመን ተገቢ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም ሀገር ከማዕድን ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሉ ርምጃዎችን የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015