ግብር መክፈል በግለሰብም ይሁን በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ በጋራ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ቀዳሚ ግዴታ ተደርጎ ይቆጠራል። ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ከግዴታነትም ባሻገር የዜጎች ሃላፊነትን በአግባቡ የመወጣትና የኩራት ምንጭ ተደርጎ ይቆጠራል።
በዜጎች መልካም ፍቃድና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የህዝብን ሥልጣን የያዘ መንግሥት ደግሞ ነዋሪዎች በንግድና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚከፍሉትን ግብር በአግባቡ የመሰብሰብ ተመሳሳይ ሃላፊነት አለበት። ከግብር የሚገኝን ገቢ ከመሰብሰብ ባሻገርም ለሀገር እድገትና ግንባታ በእቅድና በሃላፊነት ሊጠቀምበት ይገባል።
በሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ቃልኪዳን አስረው የሚኖሩ ህዝቦች እና ቃል ኪዳን ገብቶ ሥልጣን የያዘ መንግሥት በመተማመንና በጋራ ሉዓላዊ አንድነቷ የተከበረ ሀገር መገንባት እንደሚችሉ ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳብና ተግባር በዓለማችን ላይ ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር የኖረ ወደፊትም የሚቀጥል ነው።
ይህንን እውነት ወደ አገራችን ስናመጣውም ተመሳሳይ የምናገኘው ነገር ነው ። ዜጎች ከጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ጀምሮ ለሀገሪቱ ነገሥታቶች ሲገብሩ ቆይተዋል። በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን የመሩ ነገሥታትም ከዜጎች ግብርን በመሰብሰብ ሀገርን ሀገር ለማድረግ ጥረዋል።
ይህም ሆኖ ገቢን በመሸሸግ ግብርን ባለ መክፈል ግዴታውን የማይወጡ ዜጋ ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ሁሉ፤ ከህዝብ የተሰበሰበውን ግብር በአግባቡ ለሚጠበቅበት ዓላማ ለማዋል ያልቻሉ ነገሥታት /መሪዎችም የመኖራቸው እውነታ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ። ከዚህ አንጻር ግብር ከፋዩም ሆነ ግብር ሰብሳቢው፣ ከፍተኛ የአገር ሃላፊነት እንዳለባቸው ፣ ይህን ሃላፊነታቸውን በታማኝነትና በፍፁም ቅንነት መፈጸም ከሕግ ያለፈ የሞራል ግዴታች እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ሌላው ግብርን የተመለከተ የሚነሳው የሚጣለው ግብር ተመን ፍትሃዊነት ነው። መንግሥታት ግብር የመጣል ሃላፊነትና ግዴታ በተገቢው መንገድ አሳውቆ ፣ የዜጎችን ገቢ ታሳቢ ያደረገ ፍትሀዊ ገቢ የመጣሉ ጉዳይ ነው። በዛሬው አጀንዳዬ ርእሰ ጉዳይም በዋናነት ከሰሞኑ የወቅቱ ትኩሳት ወደሆነውና ተግባራዊ እየተደረገ ወደሚገኘው “አዲሱ የግብር ተመን ማሻሻያ ሕግና አተገባበር” ላይ ነው።
መንግሥት በይፋዊ የመረጃ አውታሮቹ “መገናኛ ብዙሃን” ይፋ እንዳደረገው የግብር ተመን ማሻሻያ እንጂ አዲስ ሕግ እንዳላፀደቀ አስታውቋል። ይህ ማለት ቀድሞ “የአፈር፣ የጣሪያና ግድግዳ” ተብሎ በሕግ የተወሰነው ተመን ላይ የዋጋ ማስተካከያ ከሚደረገው ውጪ እንደ አዲስ እንዲከፈል የተቆረጠ ወይም የተጨመረ የግብር አይነት የለም።
በግልፅ እንድንረዳው የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤን ሃሳብ ቃል በቃል እንዲህ እናስቀምጥ “የክፍያ መጠኑ አሁን ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ እና እንቅስቃሴን መሠረት ያደረገ ነው፤ አሁን እየተሰበሰበ የሚገኘው የቤት ኪራይና የቤት ግብር ደንብ ከ45 ዓመት በፊት የነበረ ደንብ ነው። የግብር መጠኑ ጥናት ተደርጎ የግብር ስሌት ምጣኔው ቀድሞ የነበረው ሳይነካ ፤ የገንዘብ መጠኑ ነው ማሻሻያ የተደረገበት” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን።
በተቃራኒው ከነዋሪዎችና ከኢኮኖሚ ባለሙያ ዎች ደግሞ የሚነሱ ተቃራኒ ሃሳቦች እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን ሃሳቦች ለማንሳት ልሞክር። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች “የቤት ግብር ተመን ማሻሻያ ወቅቱን ያላገናዘበ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ነው” የሚል አስተያየት አላቸው። ማህበረሰቡም በተመሳሳይ ግብር ላለመክፈል ማንገራገር ሳይሆን አቅምንና ወቅታዊ ሁኔታን ያላገናዘበ አዲስ ተመን መሆኑን በተደጋጋሚ በማንሳት ቅሬታውን እየገ ለጸ ነው።
እነዚህን ከመንግሥትም ሆነ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ሃሳቦች በአግባቡ ማየት ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግሥት አገሪቱ እያመነጨች ባለው ኢኮኖሚ ልክ ግብር መሰብሰብ ይኖርበታል። ዜጎችም በሚጣልባቸው ግብር የተነሳ ለኢኮኖሚ ቀውስ የሚዳረጉበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ፤ ሁለቱም ሀገርን የሚጎዳ ስለሆነ ።
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃል መረዳት እንደሚቻለው “በአዲስ አበባ ያለቁና አገልግሎት እየሰጡ ካሉ 800 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ቤቶች ውስጥ 182 ሺህ ቤቶች ብቻ ነበሩ በግብር ሥርዓት ውስጥ የነበሩት። የቤት ግብር የሚሰበሰበው የማይከፍለው ከሚከፍለው የሚበልጥ በመሆኑ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማድረግ ነው”።
ይህን ጥሬ ሃቅ ወስደን ከተመለከትነው ገቢያቸውን እና ንብረታቸውን በሃቅ አስመዝ ግበው ግብር ከሚከፍሉት ዜጎች በላይ የሆኑ ሀብት ሸሽገው የመንግሥትን ገቢ የሚያሳጡ አካላት እንዳሉ ነው። ይህ እውነታ በማስረጃ ከተደረሰበት መንግሥት ማስተካከያ መውሰዱ እና ሃላፊነቱን መወጣቱ ተገቢ ይሆናል። ከዚህ ጎን ለጎን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች አዲስ በወጣው ተመን ምክንያት ተጨማሪ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ ከህብረተሰቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን እና ማስተካከያዎችን ማድረግ ተገቢ ነው።
ለማጠቃለል በህብረተሰቡ ዘንድ በግብር ዙሪያ ያሉ የተዛቡ መረጃዎችን በማጥራት ሂደት ውስጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ፤ እየተስተዋለ ያለው ችግርም የዚሁ ክፍተት አንድ አካል እንደሆነ ይሰማኛል። መንግሥትም ሆነ ህብረተሰቡ የየራሳቸውን ሃላፊነት ሳይዛነፍ መፈፀም በጥቅሉ ታላቂቱን ኢትዮጵያ ለመገንባትና ለትውልድ ለማሻገር ያግዛል እላለሁ። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015