አፍሪካውያን በብዙ መስዋእትነት የጸረ-ቅኝ ግዛት ትግላቸው ውጤት ማምጣቱን ተከትሎ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የሚያስችላቸውን ድምጽ ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ቆይተዋል። ይህ ድምጻቸው ዛሬም ቢሆን በዓለምአቀፍ መድረኮች በተጠናከረ እና ከፍ ባለ ድምፀት መደመጡ እንደቀጠለ ነው ።
የአህጉሪቱ ሕዝቦች ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት፤ አምራች ዜጋ እና የማደግ ፍላጎት አንጻር ፤ ካሉበት ኋላቀርነትና ድህነት ፈጥነው መውጣት የሚያስችል ዕድል ባለቤቶች ናቸው። በተለይም ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ አቅም በፍጥነትና በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ከቻለ ነገዎቻቸው ብሩህ ስለመሆናቸው ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም፡፡
አፍሪካውያን ከቀደመው የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት የወረሷቸው የግጭት እርሾዎችና እርሾዎቹ የሚፈጥሯቸው ግጭቶች፤ ግጭቶቹ የፈጠሯቸው አለመረጋጋቶች ባላቸው አቅም ወደ ልማት ፊታቸውን እንዳያዞሩ ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል።
«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንደሚባለው ግጭቶችን እንደ አንድ የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው መጠቀም የሚሹ ኃይሎች፤ ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ ከማድረግ ባለፈ፤ ግጭቶች ከዚያም ባለፈ ጦርነቶች የአህጉሪቷ ሕዝቦች መገለጫ እንዲሆኑ አድርገዋል።
ከብዙ ጥረት በኋላ አንጻራዊ ሰላም ውስጥ የሚገኙ የአህጉሪቱ ሕዝቦችም ቢሆኑ ያላቸውን አቅም አስተባብረው ፊታቸውን ወደ ልማት ለማዞር የሚያደርጓቸው ጥረቶች፤ በዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ተገቢውን እውቅ እና በቂ ድጋፍ ባለማግኘቱ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በተለይም ዓለምአቀፍ ሥም የያዙ ትላልቆቹ የፋይናንስ ተቋማት እና ያደጉት ሀገራት፣ አፍሪካውያኑን የማደግ መሻት እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ብዙ ተስፋ ቢጣልባቸውም፤ በብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የተሞሉ የፋይናንስ አቅርቦታቸው የአህጉሪቱ ሕዝቦች የሚጠብቁትን ያህል ሊረዷቸው አልቻሉም።
እንዲያውም አፍሪካውያኑ የሕዝቦቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ለሚያስችሉ ግንባታዎች የወሰዷቸውን ብድሮች/ በብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የተሞሉ / በመክፈል ከዓመት ዓመት ትንፋሽ በሚያሳጥር የብድር ክፍያ ጫና ውስጥ እንዲያልፉ ተገደዋል።
ይህ ደግሞ ለልማታቸው በዋነኛነት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን እንኳን በአግባቡ መገንባት እንዳይችሉ፤ በዚህም ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ መልኩ አልምተው የሕዝቦቻቸውን ሕይወት እንዳይለውጡ ተግዳሮት ፈጥሮባቸዋል።
ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም ያደጉት ሀገሮች ፤ የአፍሪካውያንን የማደግ ፍላጎት እውን እንዲሆን በማገዝ ሂደት ውስጥ ትልቅ አበርክቶ ቢጠበቅባቸውም፤ ከቃል ባለፈ እስካሁን ያላቸው አስተዋጽኦ የችግሩን ያህል የገዘፈ እንዳልሆነ ይታመናል።
በአብዛኛው በእነዚህ ሀገራት ፍላጎት ከተገዙት ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት አፍሪካውያን ብዙ ቢጠብቁም፤ ሆኖ ያገኙት ግን ያሰቡትን ያህል አይደለም፤ እንዲያውም እነዚህ ተቋማት በብዙ መስዋዕትነት ያገኙትን ብሔራዊ ነፃነታቸውን የሚፈታተኑ ሆነው አግኝተዋቸዋል።
ይህንን ከስድስት አስርት አመታት ያዘለቀ እውነታ «የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የባለብዙ ወገን ልማት ባንኮችን ሞዴል ማሻሻል» በሚል ርዕስ በፈረንሳይ ፓሪስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ አፍሪካውያን መሪዎች አደባባይ በመውጣት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው።
መሪዎቹ፤ አፍሪካውያን እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ የመልማት ህልማቸውን ተጨባጭ የማድረግ አቅም እንዳላቸው፤ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም ያደጉት ሀገራት አፍሪካውያንን በሚጠበቀውና በሚገባው መልኩ እየደገፉ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ለእነርሱ ፍላጎት የተገዙት ዓለምአቀፍ ገንዘብ ተቋማትም ቢሆኑ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ከመሆን የዘለለ እንደተጠበቁት እንዳልሆኑ አስታውቀዋል።
መሪዎቹ የተሻለች ዓለም በመፍጠር ሂደት ውስጥ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም ያደጉት ሀገራት ለአፍሪካውያን ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከትና ከዚህ የሚመነጨውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያርሙ፣ በአንድም ይሁን በሌላ /በግልጽም ይሁን በስውር አፍሪካውያንን ያጎበጡ ጫናዎቻቸውን እንዲያነሱ ጠይቀዋል።
ይህ የአፍሪካውያን መሪዎች ለሕዝቦቻቸው ብሩህ ነገዎች በአደባባይ ያሳዩት ቁርጠኝነት፤ የቀደሙት አፍሪካውያን አባቶቻችን ከነፃነት ማግስት ጀምሮ ሲመኟት የቆዩትን፤ ይህም ትውልድ ሆና ማየት የሚሻትን በልጆቿ የበለጸገች አፍሪካ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል፤ ይህንን ቁርጠኝነት አጠናክሮ መቀጠልም የእያንዳንዱ አፍሪካዊ መሪ ኃላፊነትና ግዴታ ጭምር ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015