ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከሰሞኑ ደጋግሞ በሰፈራችን መታየት አብዝቷል። ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ መጮሁን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ሰዓቱ የሰፈራችን ሰዎች ወደ «በተስኪያን» የሚሄዱበት ነው። በእኛ ሰፈር ያሉ ሰዎች በሙሉ ‹‹በተስኪያን›› ሳይሄዱ በፊት ምንም አይነት ሥራ አይጀምሩም። ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል እየተነሳ ስለሚጮህ የሰፈራችን ሰዎች ከሰሞኑ ‹‹በተስኪያን›› መሄዱን ትተውታል።
ልክ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል በሰፈራችን የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ‹‹በተስኪያን›› መሄዳቸውን ትተው የይልቃል አዲሴን ንግግር ለማዳመጥ እየተቻኮሉ ወደ ዋርካው ስር ይሰባሰባሉ። ዛሬም የሆነው ይኸው ነው።
ይልቃል አዲሴ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው ዛሬም ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ስር እስኪሰባሰቡ ድረስ “ሳይማሩ መተርጎም ሳይበጡ ማከም የሚያስከትለው ችግር እንደ ሄለሞክ መርዝ አደገኛ መሆኑ ተገማች ነው።” እያለ ዲስኩሩን በጩኸት ይናገር ነበር። የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታ ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ፣ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ ‹‹እህ.. እህህ…›› ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ ኒኮሎ ማኪያቪሊን THE PRINCE በተሰኘው ፍልስፋና አዘል መጽሐፉ ‹‹የውርስ ግዛቶችን እንደማስተዳደር ቀላል ነገር የለም። የውርስ ግዛቶችን ለማስተዳደር በቀደምት አያቶች የተቋቋሙትን ተቋማትና ሕግጋት (ደንቦች) መንከባከብና ለወቅቱ የሚስማማውን ሕግ ማውጣት ብቻውን በቂ ነው።›› ሲል አመላክቷል። …ይህ እውነታ አለው። በዚህ ወቅት በሥልጣኔ ማማ ላይ የተቀመጡ ምዕራባውያን፤ በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ በአውሮፓ ይሄን የማክቪሊን ፍልስፍና መተግበር ጀመሩ። የአባቶቻቸውን ውርስ አጥብቀው ያዙ። ለማይክሮ ሴኮንድም እንኳን አልለቀቁትም። ውርሱን እንዲሁ መሬት ላይ አልጣሉትም። የአባቶቻችውን ውርስ ለመተግበር መጀመሪያ ህዳሴ (Renaissance) ቀጥሎም አብርሆት (Enlightenment) ከዚያም የኢንዱስትሪ አብዮት (Industrial Revolution) በማለት የአባቶቻቸውን ሀገር በቀል ትምህርት በመጠበቅና በማስጠበቅ እውቀታቸውን ለልጆቻቸው አስተማሩ። ይህ አካሄዳቸው ዛሬ ላይ ሁሉ ነገራቸውን ቀላል አድርጎላቸዋል።
በእኛ ሀገር ግን የሆነው የዚህ ተቃራኒ ነው። ሀገር በቀል እውቀቶችን በማጥላላትና ክፉ ስም በመለጠፍ የአሁኑ ትውልድ የፈረንጅ እውቀትን ብቻ በመቃረም ጊዜውን እንዲያጠፋ አደረግነው።
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን አቁሞ እንደማሰብ አለና እንደገና ይጮህ ጀመር። ‹‹ሀገር በቀል እውቀቶችን መናቅ የጀመረው የቀደመው ትውልድ በሽታ ተስፋፍቶና አድጎ በአሁኑ ትውልድ ክፉኛ ተጋብቷል። በመሆኑም የዛሬው ትውልድ አሁን ላይ ከውጭ የተዋሳቸውንም እውቀቶች ጭምር ንቆ ሲጥል እየያን ነው።
ጥሩም ይሁን መጥፎ የሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው የተማሩ አዋቂዎች ሊቀመጡባቸው የነበሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት የሐሰት ሰነድ በአሰሩ ግብዞች ተወረሩ። ከዚህ በላይ ውድቀት አለ?›› ሲል እጁን እያወራጨ ተሰብሳቢውን ጠየቀ። ምላሽ የሰጠው ግን አልነበረም።
‹‹በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት እግር እንጂ ጭንቅላት አይጠይቅም›› አለ ይስማከ ወርቁ .. እውነቱን ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሐሰት የትምህርት ማስረጃ ከሌላቸው ሰዎች በምንም ተሽለው አይታዩም። ለዚህ አይደል ወንድም ጋሼ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንም ቢሆኑ ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ ‹‹የብቃት ምዘና ፈተና ወይም ሲኦሲ›› መውሰድን እንደ ግዴታ ማስቀመጡ።
‹‹ከዚህ ቀደም ከአባቶቻችን የወርስናቸውን አስተምሮዎች እና አስተሳሰቦች በገንዘብ እንደማይገዙ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ከዚህ ቀደም የትምህርት ማስረጃን አይደለም በገንዘብ በተገቢው መንገድ እንኳን ተምሮም ማግኘት የምጥ ያህል ከባድ ነበር። አሁን ግን አይደለም ትምህርት ቤት ተገኝተን ይቅርና ባናገኝም በፈለግነው ቁመት እና ወርድ የፈለግነውን የትምህርት ማስረጃዎች ማሠራት እንችላለን። ለዚያውም ሕጋዊ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ።›› ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው::
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ፤…ንጉሥ እና ቅዱስ ላልይበላ ድንጋይን በድንጋይ የማቅለጥ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነጭ አባይን እና ጥቁር ዓባይን ካርቱም ላይ ገድበውት ነበር። ካርቱም የሚለው ቋንቋም አገውኛ እንደሆነ እና ትርጓሜውም ማገድ ወይም ማቆም መሆኑን አሰፋ አሊ ዑመር ቁስለኛዋ ሀገር በተሰኘው መጽሐፉ ጠቅሶታል። በዚህ ዘመን ከታች ወደላይ የሆነን የውጪዎች የኪነ ሕንጻ ጥብበ ስናሳድድ ከላይ ወደ ታች የሆነውን የእኛን አባቶች የኪነ ሕንጻ አሠራር ረሳነው።
ከዚህ ቀደም እኔ የማውቀው ‹‹ሰውየውን ስጡን የሚመጥነውን ወንጀል እኛ እንፈልግለታለን›› ነበር የሚባለው። አሁን ደግሞ ‹‹የምንፈልገውን ብር ስጡን እኛ የፈለገውን ዲግሪ እስከተቀያሪ (ተጠባባቂ) ዲግሪ መርቀን እንሰጠዋለን›› ሆኗል።
እነኚህ ሰዎች ሐሰተኛ ዲግሪ ለመያዝ ያላቸውን ጉጉት ስመለከት….
አንችን ብሎ ደግሞ ልሂድ ባይ ጀርመን፤
እዚህ አርፈሽ ነግጅ ቃሪያ እና ጎመን። የሚለው የአዝማሪ ግጥምን ዝፈንላቸው ዝፈንላቸው ይለኛል።
በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተሰገሰጉ ቂሎች በገዙት የሐሰት የትምህርት ማስረጃ ‹‹ምን ታመጣላችሁ!›› እያሉ እቁብ እና እድር ሊያስተዳድሩበት ይችላሉ። ነገር ግን ወንዝ አያሻግራቸውም። ይሄን ደግሞ በተግባር ተመልክተናል። አንዳንድ ባለዲግሪዎች ከውጭ ሀገር ከመጡ ሰዎች ጋር ‹‹እንዴት ዋላችሁ? እንዴት አደራችሁ?›› ብለው ለማናገር እንደተቸገሩ ሰምተናል፤ አይተናልም።
ኢንግሊሽ (English) የሚለውን ‹‹እንጃልሽ››፤ ጂ-ሜል (Gmail) የሚለውን ደግሞ ‹‹ግመል›› ብለው ያነበቡ ባለዲግሪዎችና ማስተሮች መኖራቸውን ተመልክተናል። ከእንደዚህ አይነት ንግግሮች ጋር ተያይዞ ለአንድ ሰሞንማ በማኅበራዊ ሚዲያው ሐሜቱ ቀልጦ ነበር ።
እኔ የምለው በርካታ የተማሩ ሰዎች ከሥራ ውጭ በመሆናቸው የቤተሰብ ጥገኛ ሆነው ሳለ የሐሰት የትምህርት ማስረጃ ይዘው ሀገርን የሚያጎሳቁሉ አካላትን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ አጣርቶ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ምን አጣን? የሐሰተኛ የትምህርት ሰነድ ይዘው በሥራ ላይ የተቀመጡ ሰዎችን በሕግ አለመጠየቅ አሁን ላይ በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ የሚነሳውን ሥራ አጥነት ችግር መቅረፍ እንዳንችል ከማድረጉም ባሻገር ተተኪው ትውልድ ለትምህርት የሚኖረውን አመለካካት የተንሻፈፈ እንዲሆን ያደርጋል።
አሁን ላይ እየተመለከትን ያለው ነገር ደግሞ እጅጉን የሚያስፈራ እየሆነ ነው። የሐሰተኛ የትምህርት ሰነድ ማሠራት እንደብልጥ አለማሠራት ደግሞ እንደ ጅል ሲያስቆጥር ተመልክተናል።
በእኛ ሰፈር እና እድር እየሆነ ያለውን ነገር ስመለከት መጀመሪያ እና መጨረሻው ይምታታብኛል። ይህን ስል የአንድ የፍርድ ቤት ውሎ ትዝ አለኝ።
አንድ ዐቃቤ ሕግ ዳቦ ቤት ያለውን አንድ ግለሰብ በፅዳት ጉድለት ፍርድ ቤት ያቆመዋል። ዳቦ ቤቱም ምን እንዳጠፋ ዐቃቤ ሕጉ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፤ ‹‹ዳቦ ቤቱ ለሕዝብ ዳቦ አቅራቢ ሆኖ ሳለ ቤቱ በሸረሪት ድር ተሞልቷል። ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ማናቸውም ተቋማት ደግሞ ከሸረሪት እና መሰል ቆሻሻዎች ፅዱ ሊሆኑ እንደሚገባ በተለያዩ ጊዜያት በወጡ መመሪያዎች እና አዋጆች ተመላክቷል። ይሁንና ዳቦ ቤቱ በሀገሪቱ የወጡ መመሪያዎችን እና አዋጆችን በመተላለፍ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥን ተቋም በሸረሪት ድር ሲወረስ እየተመለከተ በቸልተኝነት አልፏል። ይህም በሕግ ያስጠይቀዋል ክቡር ፍርድ ቤት!›› አለ።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕጉን መከራከሪያ ነጥብ ካዳመጠ በኋላ ተከሳሽን ለተከሰስክበት ነገር መልስ አለህ ብሎ ይጠይቀዋል። ተከሳሽም ‹‹ክቡር ፍርድ ቤት እኔ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ማናቸውም ተቋማት ንጽሕናቸው ካልተጠበቀ በሕግ እንደሚያስጠይቅ አላውቅም። ስለዚህ ሳላውቅ ላጠፋሁት ጥፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሊሰጠኝ ይገባል እንጂ ወንጀል ሆኖ ልጠየቅ አይገባም›› ሲል ተከራከረ።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም ‹‹ተከሳሽን ሕግ አለማወቅ ከጥፋተኝነት አያድንም›› ሲል የሦስት ዓመት እሥራት ፈረደበት። ይሄን የተመለከተው ተከሳሽም ‹‹ማንኛውም ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ንጽሕና ሊጠበቅ ይገባል ከተባለ፤ ሐሰተኛ ዲግሪና ማስተርስ የሚቸበችቡ የትምህርት ተቋማትስ ለምን ዝም ተባሉ፤ከሸረሪቱና ከቆሻሻው በላይ የእነሱ አታላይነትና አጭበርባሪነት ሀገር አይጎዳም ወይ ብሎ? ዳኛውን አፋጠጣቸው እርስዎ። ዳኛውም ለጊዜው የሚመልሱት መልስ አልነበራቸውም።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግሩን ቀጠለ … አሁን ላይ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ሪጅስትራሮች ኦርጅናል የትምህርት ማስረጃ እየቸበቸቡ መሆኑን በፖሊስ ሳይቀር ተደርሶባቸዋል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እነዚህ ሐሰተኛ ሰዎች መቀመቅ መውረዳቸው አይቀሬ ነው።
‹‹ደንበጫ ሲሄድ መሸብኝ፤
ገና ዳሞት አለብኝ›› …አለ ባለቅኔው….።የሐሰት ሰነድ ይዘው ለሕዝብ አገልግሎት እንሰጣለን በሚሉ ሐሰተኛ የሙያ ባለቤቶች ላይ ተገቢው ማጣራት ተካሂዶ የእርምት እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ሀገራችንን ወደ ኋላ ማስቀረቱ ሳይታለም የፈታ ነው። ብሎ ንግግሩን የጨረሰው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ወደ መቀመጫው ተመለሰ።
ይህን ተከትሎ ወፈፌው ይልቃል አዲሴም ጉሮሮውን እየጠራረገ ንግግሩን ከአቆመበት ጀመረ። ‹‹የተማረ ማለት ሁሉም የሚያየውን የሚያይ ሳይሆን፤ ለሁም የተደበቀን ማየት የሚችል ነው። ይህ በትምህርት እና ሥልጠና የሚመጣ ነው። የሐሰት የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ግለሰቦች ይሄ ችሎታ የላቸውም።
ተበድሮ ቅቤ ታርዞ ጎፈሬ እንዲሉ የእኛ ሰፈር የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዲግሪያቸው የተገዛ በመሆኑን እንኳንስ ማንም የማያየውን ሊመለከቱ ይቅርና ሁሉም የሚያየውን እንኳን በቅጡ አይመለከቱትም።
ይህን ተከትሎ በርካታ ግለሰቦች እና ቡድኖች አሠራርን መተቸት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ሰዎች የሚጎዱህ አንድም ስለሚፈሩህ አሊያም ስለሚጠሉህ ነው እንዳለው ማኪያቬሊ እውቀት የሌላቸው ግለሰቦች በእውቀት ላይ ተመሥርተው ትችት በሚያደርጉ ግለሰቦችን ማሳደድ ይጀምራሉ። ሀገርም አይሆኑ ሆኖ ይበጠበጣል።
ያለምግብ መጋቢ ያለውሃ ዋናተኛ እንዲሉ ያለእውቀት ለሕዝብ አገልግሎት እንሰጣለን ከሚሉ ሐሰተኛ ባለዲግሪዎችና ማስተርሶች እድገትን፣ ብልጽግናን፣ ሰላምን፣ ተባብሮ መሥራትን መጠበቅ የዋህነት ነው። ምክንያቱም መኑ ዘደመሮ ለብርሃን ምስለ ጽልመት (ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው) እንዲሉ የጥበበኛ እና የተማሩ ሰዎች መገለጫዎችን ስለምን ካልተማሩ እና የትምህርት ማስረጃን ከገዙ ሰዎች እንጠብቃለን። ምክንያቱም እነኝህ ሰዎች ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ናቸውና።
ከሰሞኑ ከሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር ተያይዞ አንድ ጓደኛዩ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ። በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ወደ ሚሠራበት መሥሪያ ቤት 10 ሰዎች ይቀጠራሉ። ይሁንና ኃላፊው የተቀጠሩትን ሰዎች የትምህርት ማስረጃ ሕጋዊነት ይጠራጠራል። ይህን ተከትሎ አንድ ጋዜጠኛ ጓደኛውን ስለሁኔታው እንዲያጣራ ይነግረዋል። ጋዜጠኛውም ከተቀጠሩት 10 ሰዎች አራቱ የሐሰተኛ ሰነድ እንዳቀረቡ ለኃላፊው ይነግረዋል። የሥራ ኃላፊውም ‹‹አራቱ ብቻ ከሆኑ ችግር የለውም›› ብሎ አረፈው።ችግራችን እዚህ ደረጃ ደርሷል።
በአጠቃላይ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለ ጉዳይ ነው። በየቦታው ሰው የሚያማርሩ፤ ሙስና የሚጠይቁ ፤በአገልግሎት አሰጣጥ ሕዝብን የሚያስለቅሱ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባለቤቶች ናቸው። የወሰዱትም ዲግሪ በሙስናና በሌብነት ስለሆነ ለሚሰጡት እያንዳንዱ አገልግሎትም በምትኩ ጉቦና ምልጃን ይሻሉ። ስለዚህ ጎበዝ እነዚህን ሌቦች መንጥሮ ማውጣቱ የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015