ትምህርት ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ የመለወጫ ትልቁ መሳሪያ ነው። ትምህርት ሲባል ግን እንዲሁ ዝምብሎ ትምህርት አይደለም። ጥራት ይፈልጋል።ጥራት ያለው ትምህርት ለማረጋገጥ ደግሞ ተማሪዎች በስነ ምግባር የታነፁ መሆን ይኖርባቸዋል። በርካታ ሀገራትም በተማሪዎቻቸው ስነ ምግባር ላይ ገና ከህፃንነታቸው ጀምሮ ትኩረት አድርገው በመስራታቸው ራሳቸውን ከድህነት አውጥተው ወደ ሀብት ማማ ወጥተዋል።
ስነ ምግባር የሁሉም ነገር መሰረት እንደመሆኑ በትምህርት ላይ ያለው አስተዋፅኦም ቀላል አይደለም። ምክንያቱም በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ነው ነገ ሀገርን ሊቀየር የሚችለው። መልካም ስነ ምግባር ያለው ተማሪ ነው አስተማሪውን ሊያከብር የሚችለው። ስነ ስርዓት ያለው ተማሪ ነው ወላጆቹን የሚያከብረው። የዛሬ መልካም ስነ ምግባር ተማሪ ነው የልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ፈጠራ ባለቤት የሚሆነው።
አሁን ለሚታየው የትምህርት ጥራት ጉድለት አስተዋፅኦ እያደረጉ ካሉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የተማሪዎች የስነ ምግባር ችግር ነው። ለተማሪዎች ስነ ምግባር ጉድለት ችግር ደግሞ በየደረጃው የሁሉም አስተዋፅኦ አለበት። ከመንግስት ጀምሮ የትምህርት አመራሩ፣ መምህራን፣ ወላጆችና ራሳቸው ተማሪዎች ለስነ ምግባር ጉድለት የራሳቸው አበርክቶ አላቸው።
የተማሪዎች የስነ ምግባር ግድፈት ችግር እየተባባሰ መጥቷል። ይህ ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ የመጣው የስነ ምግባር ግድፈት አንድ ቦታ ላይ መፍትሄ ካልተበጀለት ነገ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ሀገሪቷን በብቃት የሚመራና ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያሻግር ዜጋ እስከማሳጣት ያደርሳል። ሀገሪቱን ከድህነት አላቆ ወደ ብልፅግና ማስገባትም አይቻልም።
በዚህ ቴክኖሎጂ በላይ በሚፈልቅበት የዲጂታል ዘመን ደግሞ ስነ ምግባር ትልቅ ሚና አለው። ምክንያቱም በስነ ምግባር የታነፀ ተማሪ ብቻ ነው የሳይንስና የፈጠራ ስራዎችን ሊያፈልቅ የሚችለው። ስነ ምግባር ያለው ተማሪ ነው በርካታ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶችን የሚያወጣው። መልካም ስነ ምግባር ያለው ተማሪ ነው ሀገሩን በተለያዩ ሳይንሳዊ ግኝቶች ከግዜው ጋር ሊያራምድና ሊያሻግር የሚችለው።
ሳይንስና ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት የተማሪዎችን ስነ ምግባር ማሻሻል ወሳኝ መሆኑ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባዘጋጀው አንድ መድረክ ላይ ተጠቁሟል። በዚሁ መድረክ ላይ በተማሪዎች የስነ ምግባር መንስኤና መፍትሄዎች ላይ የሚያተኩር ጥናት ይፋ ሆኗል።ጥናቱ በዋናነት ለተማሪ የስነ- ምግባር ግድፈት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ አራት ዋና ዋና መንስኤዎች ጠቁሟል። በተለይ መልኩ ደግሞ ወላጆች፣ መምህራንና ራሳቸው ተማሪዎች ለተማሪዎች ስነ- ምግባር ግድፈት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
መምህራን ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን ድጋፍ ያለማድረጋቸውና ሞያዊ መርሆችን ተከትለው ትምህርትን ለተማሪዎቻቸው መስጠት አለመቻላቸው ለተማሪዎች ብልሹ ባህሪ አንዱ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። በራሳቸው በተማሪዎች በኩል የሚታዩ ያልተገቡ ባህሪያትም በትምህርት ቤት ውስጥ የስነ ምግባር ግድፈት እንዲኖር እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ወላጆችም ለተማሪዎች ባህሪ ጉድለት የራሳቸው ሚና እንዳላቸውና በተለይ ደግሞ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው መጥፎ ስነ ምግባርን በመውሰድ በትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚያንፀባርቁ በጥናቱ ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቱም በራሱ ለተማሪዎቹ ምቹ ሳይሆን ሲቀር ለተማሪዎች የስነ ምግባር ግድፈት ምክንያት እንደሚሆን ጥናቱ አሳይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች በስነ ስርዓት ሲታነፁ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎችን ለመስራት እንደሚበረታቱ በጥናቱ ተመላክቷል። ሆኖም የስነ ስርአት ጉድለት በተማሪዎች በኩል ሲኖር ለሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ተነሳሽነት እንደማይኖራቸው ተገልጿል።
የተማሪዎች የስነ ምግባር ጉድለት ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ የመጣ ችግር መሆኑ አያጠያይቅም። ከዚህ አኳያ በተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ መስራትና በተለይ ደግሞ ተማሪዎች ወደ ሳይንስና ፈጠራ ስራ እንዲሳቡ ለማድረግ የስነ ምግባር ችግሮችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ባለድርሻ አካላትም የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል። ይህም የስነ ምግባር ግድፈት በትመህርት ቤቶች አካባቢ እንዲቀንስ ያስችላል። የስነ ምግባር ግድፈቶች በቀነሱ ቁጥር ደግሞ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ በማፍራት ሀገርን መቀየር ይቻላል።
የስነ ምግባር ግድፈት ችግር እንዳለ ሆኖ ግን ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተማሪዎች የተለያዩ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህም በቅርቡ የተካሄደው የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽን ጥሩ ማሳያ ነው። ነገር ግን ደግሞ ተማሪዎች በትምህርት ቤት የሚያሳዩት የስነ ምግባር ግድፈት ሲቀረፍና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሲወጡ ወደ ሳይንስና ፈጠራ ስራ ይሳባሉ። በሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ይዘው የሚወጡ በርካታ ተማሪዎችንም ማፍራት ይቻላል፡፡
የተማሪዎች የስነ ምግባር ግድፈት ሲባል ሁሉንም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ህጎችንና ደምቦችን መጣስ ያጠቃልላል። ተማሪዎች ይህን አለማድረጋቸው ደግሞ በአጠቃላይ መማር ማስተማሩን ስራ ያውከዋል። በእንዲህ ሁኔታ የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስቀጠል ደግሞ አይቻልም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታዲያ ጥናቱ በቅድሚያ ወላጆች የልጆቻውን ስነ ምግባር በመከታተል ረገድ አስተዋፅዋቸው አነስተኛ መሆኑንና ለልጆቻቸው ግዜ እንደማይሰጡ አመላክቷል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ያወጣውን ህግ መተግበር ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁሟል። በሶስተኛ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተማሪዎች መተዳደሪያ ደምብ ወቅቱን የዋጀና ከግዜው ጋር የሚሄድ አለመሆኑን አሳይቷል።በተመሳሳይ ኩረጃም እንደ አንድ የተማሪ የስነ ምግባር ችግር ጎልቶ የወጣ መሆኑንም አመላክቷል።
ከነዚህ የጥናቱ ግኝቶች በመነሳት እንደመፍትሄ ሆነው የተወሰዱት ባለድርሻ አካላት በተለይ ደግሞ የትምህርት አመራሮች ከቅጣት ይልቅ ተማሪዎችን ቀና ምላሽ በመስጠት የተማሪዎችን ስነ ምግባር ችግር መቀነስ እንደሚችሉ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት ቤት ህጎችን ማሻሻል እንደ ሁለተኛ መፍትሄ የቀረበ ሲሆን የትምህርት ቤት አመራሮች ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት ከማባረር ይልቅ ተማሪዎች ላይ ግዜ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።ወላጆችም ለልጆቻቸው ግዜ ቢሰጡና ቀርበው ቢነጋገሩ ለተማሪዎች ስነ ምግባር መሻሻል የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጥናቱ እንደመፍትሄ አስቀምጧል።
እንግዲህ ይህ ጥናት የተማሪዎች ስነ ምግባር ነገ ለምንፈጥራትና በምንፈልገው ልክ መገንባት ላሰብናት ኢትዮጵያ ሀገራችን ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን አሳይቶናል። በተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ ከወዲሁ ካልተሰራ በቀጣይ አደጋው ምን ያህል የከፋ እንደሚሆንም አስቀምጧል። ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተማሪዎች የስነ ምግባር መሻሻል የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። መንግስትም ቢሆን የስነ ምግባር አስፈላጊነትን በመረዳት በዚህ ረገድ ለሚሰራው ስራ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ ይገባል።
ዞስካለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015