በኢትዮጵያ ዜጎች በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ከሆነ ወዲህ በርካቶች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በግልና በቡድን የተደራጁ ግለሰቦችም አረጋውያንና በህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን፣ ልዩ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተጎዱ ሴቶችንና ህፃናትን ያለምንም የልፋት ዋጋ ሙሉ አልያም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ሲያግዙና ሲረዱ ማየት እየተለመደ መጥቷል።
የክረምት ወቅት ለአብዛኛው የአገራችን ተማሪዎች የዕረፍት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወጣቶች ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ተግባር ለመፈፀም በበጎ ስራ ላይ የሚሰማሩበትና ይህንንም ባህል ከመለማመድ አልፈው እንዲዳብር የሚተጉበት ሊሆን ይገባል።
በርካታ ወጣቶች የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካኝነት ጊዜያቸውን ለሌሎች ሲሰጡና ወገኖቻቸውን በሚጠቅም ተግባር ላይ ሲያውሉ፣ በሀገራቸው ዕድገት ላይ ገንቢ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ማየት አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል። በዘንድሮ የክረምት ጊዜያትም በተለያዩ የአገራችን ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች በበጎ ስራ ላይ እንደሚሰማሩ ይጠበቃል። ችግኝ መትከል፣ ደም መለገስ፣ በከተሞች የትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ ማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ ወዘተ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሚያከናውኗቸው የተለመዱ ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህን አጠናክሮ በመቀጠል ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት በሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉ ላይ የማይፋቅ የራስን አሻራ ማኖር ነውና በዋጋ የማይተመን የመንፈስ ርካታንም ያጎናፅፋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዚህ በተሻለ መልኩ መጎልበትና ባህል ሊሆን የሚገባ መልካም ተግባር ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ አሁን የተጀማመሩ መልካም ተግባራትን ይዞ ለበለጠ ውጤትና ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር የማድረግ አቅም አለው። ሀሳቦችን በማንሸራሸርና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር የሰላም እሴቶችን ለማዳበርም ትልቅ ሚና አለው። የበጎ አድራጎት ሥራ በእርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋልና የሚሰጠው ማኅበራዊ መስተጋብርም የጎላ ነው።
ለዚህ ደግሞ በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ ብቻ እንዳይወሰኑ የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር የግድ ነው። ወጣቶች ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመዘዋወር እግረ መንገዳቸውን አንድነታቸውንና የባህል ዕሴቶቻቸውን የሚያጋሩበትና የሚያጎለብቱበት ሁኔታ መስፋት ይኖርበታል። ይህም ቋንቋ፣ ባህል፣ የአሰራር ዘይቤ እንዲሁም የተለያዩ የባህል እሴቶችንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አንዱ መንገድ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህ ህሳቤ ዕውን እንዲሆን ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን በባለቤትነት የሚመራው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካለት ሁሉ በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል፡፡
ሁሉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ከፌደራል እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት በባለሙያዎች የታገዘ የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮችን በማስፋት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተዘጋጀውን ራሱን የቻለ መመሪያና መተዳደሪያ ደንብ ወጣቶች እንዲያውቁ የማድረግ ሥራን ቀደም ብሎ ማከናወን ተገቢ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መገለጫው ብዙ ነውና ከተለመዱት የማኅበረሰብ አገልግሎቶች የዘለለ አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው። ይህም አሁን በአገራችን ላይ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ቀዳሚ ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማህበራዊ ሚዲያና ድረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሄርን ከብሄር፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት በማጋጨት ዕድገቱን ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን መታገል ይገባዋል፡፡
ይህን ተግባር ማከናወን የሚቻለው ደግሞ ወጣቱ እኩይ ተግባራትን ተቀብሎ ከማራገብ ታቅቦ ትክክለኛውን ሀገራዊ የፍቅር መስመር እንዲይዙ ስህተታቸውን ነቅሶ በማውጣት ማረም ሲችል ነው። ስለሆነም ከግጭት፣ ከትርምስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አንደሌለው በአንክሮ መምከር እና ማስተካከልን ወጣቱ እንደ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊቆጥረው ይገባል። ከሌላው ማኅበረሰብ ይልቅ ለመረጃ ቅርብም ነውና በሶሻል ሚዲያው በሚነዙ አሉባልታዎች ዙሪያ እውነተኛውን ነገር ፈልፍሎ ማጋለጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2015