ከመንግሥት ዓመታዊ በጀት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ሃብት ለግዥ እንደሚውል መረጃዎች ያመለክታሉ። የግዢ ስርዓቱ በሰዎች የሚፈጸምና በቴክኖሎጂ የተደገፋ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥት በጀት ለምዝበራና ለብልሹ አሰራር እየተጋለጠ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል እንደሚቀር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁንና የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ይህን ችግር ለመፍታት ያስችል ዘንድ በተለይም የመንግሥት የግዢ ስርዓትን በማዘመን ከሰዎች እጅ ንክኪ ነጻ በሆነ በኤሌክትሮኒክ መንገድ መፈጸም የሚቻልበትን ሁኔታ አመቻችቷል። በዚህም በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ የመንግሥትና የህዝብን ሃብት ከብክነት መታደግ እንደሚቻል ታምኖበታል።
በቅርቡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ስራ ላይ ያዋለውን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት በተመለከተ አንድ አካል ከሆኑት ከአቅራቢዎች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት እንደተጠቆመውም፤ የመንግሥት ግዢ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ከሰው እጅ ንክኪ ውጭ በሆነ መንገድ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ መፈጸሙ ከፍተኛ ጠቀሜታው አለው።
በውይይቱ የተሳተፉት የተጎና ኮንስትራክሽኑ አቶ ሄነሪ ነጋሽ፤ የግዢ ስርዓቱን ለማዘመን የተደረገው ጥረት እጅግ በጣም ጥሩና አበረታች መሆኑን ይገልጻሉ። ድርጅታቸውም በዚሁ ስርዓት ውስጥ ገብቶ መሥራት ከጀመረ ከአምስት ወራት በላይ ማስቆጠሩን ነው የጠቀሱት። የግዥ ስርአቱ ለአጠቃቀም ምቹና ከሰዎች ንክኪ ነጻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሙስና ነጻ የመሆን ዕድል እንዳለውና ለአቅራቢዎችም በርካታ ጥቆሞች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በዋናነት ቴክኖሎጂውን መጠቀም ጊዜን ያስችላል። ከሁሉም በላይ የጨረታ ሰነዶችን ለመግዛት ሲባል ይደረጉ የነበሩ ምልልሶችን የሚያስቀር በመሆኑ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። ለወረቀትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውለውን ሃብትም ከብክነት ይታደጋል።
በቀደመው አሰራር በደብዳቤ ይደረጉ የነበሩ ምልልሶችም ለቁጥር የበዙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ እነዚህን አላስፈላጊ ሂደቶች ማስቀረት እንደቻለና ይህም በብዙ ገንዘብ ሊተመን እንደሚችል አብራርተዋል።
አሁን ላይ በኤሌክትሮኒክ በሚደረገው ግዢ ቢሮ ተቀምጦ በኦንላይን ጨረታውን መሳተፍና ውጤቱንም ማወቅ የሚቻልበት የአሰራር ስርዓት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል። ለብልሹ አሰራር ዕድል እንደማይሰጥም ተናግረው፣ እንደ አገርም የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
አቶ ሄነሪ እንዳሉት፤ የኤሌክትሮኒክ የግዢ ስርዓት ገና አዲስ የተጀመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ይህም ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ነው፤ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የኢንተርኔት መቆራረጥ አንዱ ነው። ለዚህም የሚጠቀሟቸው የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች ሂደቱን ፕሮሰስ ለማድረግ ምን ያህል አቅም አላቸው የሚለውን መፈተሽ ከአቅራቢዎች ይጠበቃል። ይህም በቀጣይ ከቴክኖሎጂው ጋር በሚኖር መላመድ እየተቀረፈ የሚመጣ ችግር ነው።
ከደህንነት ጋር በተያያዘም እንዲሁ ስጋት ነበረኝ ያሉት አቶ ሄነሪ፤ ስጋታቸውም የአቅራቢው ሰነድ ሶስተኛ ወገን ዘንድ ይደርሳል የሚል እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ላይ ግን ባገኙት ስልጠና መሰረት በኢንሳ በኩል የሚደረግ ጥበቃ ስለመኖሩ መረዳት እንደቻሉና ስጋታቸውም የተወገደላቸው መሆኑን አጫውተውናል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የዋይ ኮንስትራክሽኑ አቶ ይደሰት ተስፋዬ ነው። አቶ ተስፋዬ ቴክኖሎጂው ሲተዋወቅ አንስቶ የመጀመሪያው ተመዝጋቢ እንደነበርና በዚህም ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል። እሱም እንደ አቶ ሄነሪ ቴክኖሎጂው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራል።
አቶ ይደሰት እንዳለው፤ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርአቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማቃለል የቻለ ነው። መንግሥት ወደዚህ ስርዓት ከመግባቱ አስቀድሞ አንዳንድ የውጭ ድርጅቶች ቴክኖሎጂውን ሲጠቀሙበት ነበር፤ ለወደፊት የተሻለ አበርክቶ እንደሚኖረውና ሰዎች እኩል ዕድል እንዲኖራቸው በማድረግ በኩልም ሰፊ ድርሻ አለው።
‹‹አንዳንድ ጊዜ ጨረታ ላይ ሰፊ የኩባንያ ፕሮፋይል ያላቸው ይገጥማሉ›› የሚለው አቶ ይደሰት፤ እነዚህን ፕሮፋይሎች ለመለየት ብዙ ጊዜ ይወስድባቸው እንደነበር ይናገራል። የግዢ ስርዓቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኤሌክትሮኒክ መሆኑ ሥራውን በእጅጉ ማቃለል የቻለና ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥ ሆኗል ይላል።
አልፎ አልፎ እንደ ችግር የሚታዩ ሂደቶች ቢኖሩም የኤሌክትሮኒክስ ግዢ የጎላ ጠቀሜታ አለው ሲል ገልጾ፤ ይህን የግብይት ስርአት ሁሉም ሰው በቅድሚያ አምኖ መቀበል እንዳለበት ተናግሯል። በተለይም ሁሉም ሰው እኩል ዕድል አግኝቶ መወዳደር የሚችልበት ስርዓትና የተሻለው ሰው የሚመረጥበት በመሆኑ ትልቅ ዕድል ነው ብሏል።
ከደህንነት ጋር በተያያዘም አሁን ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለበት አቶ ይደሰት አስታውቆ፣ ምናልባት በቀጣይ አንዳንዶች ቴክኖሎጂው ይበልጥ ሲገባቸውና ዕውቀቱን እያገኙ ሲሄዱ ክራክ አድርገው የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ስጋት እንዳለውም ገልጸዋል።
አቶ ይደሰት እንዳብራራው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አቅራቢዎችን በአንድ አሰባስቦ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠቱ እጅግ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው። በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በርካታ ቁጥር ያላቸው ቢሆኑም፣ እስካሁን ወደ ስርዓቱ የመጡት ጥቂቶች ናቸው። አሁን ላይ በርካቶች እየመጡ ነው፤ በቀጣይም ይመጣሉ። ለዚህም የግዢና ንብረት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ኃላፊነት ወስዶ በቴክኖሎጂው ዙሪያ እየሰጠ ያለው ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እጅግ ጠቃሚና የሚበረታታ ነው።
ውይይቱን የመሩት የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የመንግሥት ግዢ ስርዓትን በማዘመን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርአትን ተግባራዊ ለማድረግ ለሶስት ዓመታት ጥናት ተካሂዷል። ከጥናቱ በኋላ በ2014 በጀት ዓመት በዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት ነው ሥራው የተጀመረው። በ2015 ደግሞ 74 የፌዴራል ተቋማት ወደ ትግበራ እንዲገቡ ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል 70 የፌዴራል ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ግዢያቸውን በኤሌክትሮኒክ መፈጸም ችለዋል። የቀሩት 95 ተቋማት በአሁኑ ወቅት በስልጠና ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ስልጠናውን አጠናቀው ለ2016 በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ስርዓቱ ይገባሉ።
‹‹በ2016 በጀት ዓመት 169 የፌዴራል ተቋማት ከተለመደው ግዢ ወጥተው ዘመናዊና ዓለማቀፋዊ በሆነ መንገድ ግዢያቸውን በኤልክትሮኒክ የሚፈጽሙ ይሆናል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ያደጉ አገራት ዘመናዊ የግዢ ስርዓቱን ላለፉት 50 ዓመታት ሲጠቀሙበት እንደነበር አስታውሰዋል። በቀጣዩ በጀት ዓመት ማንኛውም የመንግሥት ግዢ ከኤሌክትሮኒክስ ግዢ ውጭ እንደማይፈጸም አስገንዝበዋል።
‹‹የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ምንም አይነት የሰው ኃይል ሳያስፈልግ መተግበሪያውን በራሱ ኦዲት ማድረግ ስለሚያስችል ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የፀዳ የግዥ ሥርዓት እንዲኖር ያስችላል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በግዥ ሰበብ የሚፈጸመውን ሌብነት ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ በተለይም ሰኔ ላይ የሚፈጠርን የግዢ ግርግር ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀርና እጅግ ውጤታማ እንደሆነ አስረድተዋል።
በፌዴራል ተቋማት የጀመረው ይህ የኤሌክትሮኒክ የግዢ ስርአት ወደ ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንደሚወርድ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከከልሎች የሲዳማ ብሔራዊ ከልላዊ መንግሥት ወደ ስልጠናው መግባቱን ጠቁመዋል። በትግበራው የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ የለማውን ሶፍትዌር በቀጣይ ለሁሉም ክልሎች ተደራሽ በማድረግ መጠቀም እንደሚቻል ነው ያስረዱት።
በአንድ አገር አንድ የግዢ ስርዓት ነው ሊኖር የሚገባው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ልክ የተናበበ አንድ አገራዊ ኢኮኖሚ ለማድረግ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ክልሎች ወደዚሁ ስርዓት እንደሚገቡም አስታውቀዋል። ከ2017 ዓ.ም በኋላ ወደ ወረዳ፣ ዞንና ቀበሌ በማውረድ በቀጣይ አራትና አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር የግዢ ስርዓቱ ሙሉ ለሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚተካ እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ሀጂ ማብራሪያ፤ ከተቋማቱ በተጨማሪ አቅራቢዎችም በዚሁ የግዢ ስርዓት ውስጥ መግባት አለባቸው። አንድ ጊዜ በፌዴራል ተቋም የተመዘገቡ ማለት ለክልል፣ ለዞን፣ ለወረዳና ለቀበሌ ማገልገል ይችላሉ። በቀጣዮቹ ዓመታት የቀደመው የግዢ ስርዓት በሥራ ላይ የማይውል በመሆኑ ከወዲሁ በግዢው ስርዓት ውስጥ በመግባት ተመዝግበው እንዲጠባበቁና ዕድሉን እንዲጠቀሙ አመላክተዋል። ለዚህም እንዴት መመዝገብ እንዳለባቸው ስልጠና ተዘጋጅቶ እየወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከስልጠናው በተጨማሪም በአካል ሄደው መረዳት የሚችሉበት መንገድ መፈጠሩን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በዚህ መሰረት አቅራቢዎች በሙሉ የአሰራር ስርዓቱን አውቀውና ተረድተው ወደ ሥራው እንዲገቡ ተደርገዋል። ትግበራው ሀምሌ ላይ ሲጀመር ለ74 ተቋማት 100 አቅራቢዎች ብቻ ተመዝግበው ነበር። አሁን 15 ሺ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች እና አንድ የውጭ አገር አቅራቢ ወደ ትግበራው ገብተዋል። ይህም በግዢ ወቅት የሚፈጸም ሌብነትን ሙሉ ለሙሉ ከማስቀረት ባለፈ ለዓለም አቀፋዊ የግዢ ስርዓት ዝግጁ መሆን መቻሉን ማሳየት ያስቻለ ነው።
አንድ አቅራቢ ባልተመዘገበበትና ፈቃድ ባላወጣበት ሁኔታ መወዳደር እንደማይችልም አቶ ሀጂ አስታውቀዋል። የዓመቱን ግብር ገብሯል ወይስ አልገበረም የሚሉና የተለያዩ ሂደቶችን ለማወቅ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከባንክ፣ ከቴሌ ብር፣ ከኢንሹራንስና ከንግድ ሚኒስቴርና የተገናኘ ስለመሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ይህም የሰውዬውን ማንነት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አካሄዱ የሰለጠነና ኢትዮጵያን ካደጉ አገራት ተርታ የሚያሰልፍ እንዲሁም ሌብነትን የሚያስቀር መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የክልል የመንግሥታት ከወረቀት የግዥ ሥርዓት ተላቀው የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓትን እንዲከተሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ በ2017 በጀት ዓመት ክልሎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥርዓቱ እንደሚገቡ አስገንዝበዋል። የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ብልሹ የግዢ አሰራርን በመቅረፍ የመንግሥት በጀት ለታለመለት አገልግሎት እንዲውል እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከፌዴራል የመንግሥት ተቋማት በተሻለ የግል አቅራቢዎች ግዥዎቻቸውን በኤሌክስትሮኒክ እየፈጸሙ እንደሆነም ጠቅሰው፣ የመንግሥት ተቋማትና አቅራቢዎች ግዥዎቻቸውን በኤሌክስትሮኒክ የግዥ ስርአት በማድረግ በግዥ ሰበብ የሚፈፀምን ሌብነት መቀነስ ይገባቸዋል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ሌብነት በተንሰራፋበት በዚህ ወቅት የኤሌክትሮኒክ ግዢ ፍቱን መድሃኒት ነው። ግዢ ሲባል ቀድሞ የሚመጣው ሌብነት የሚለው ነው። ሁሉም ነገር ግልጽ በሆነ መንገድ መሄድ ከቻለ ሌብነት በራሱ ጊዜ ይጠፋል። ግልጽነቱ ጊዜና ቦታ የማይገድበው ሲሆን፣ የአንድ ሚሊዮን ብር ጨረታን አሜሪካና አውሮፓ ሆኖ መከታተልና መመልከት ይቻላል። ግልጽነቱ በዚህ ልክ የሰፋ በመሆኑ በመንግሥትና በህዝብ መካከል እንዲሁም በንግዱ ማህበረሰብና በህዝብ መካከል ተቋርጦ የነበረውን እምነት ማስቀጠል ይቻላል።
ተቋማት ግዥዎቻቸውን በኤሌክትሮኒክ ስርአት ሲያደርጉ ከአምስት እስከ 25 በመቶ የሚሆን በጀት ከምዝበራ ማዳን እንደሚቻል የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በትንሹ አምስት በመቶ ያህሉን ማዳን ቢቻል እንኳ እስከ 40 ቢሊዮን የሚደርስ የመንግሥትና የህዝብ ሃብትን ከብክነት ማዳን እንደሚቻል አመላክተዋል።
በአገር ደረጃ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል ታስቦ ከአስር ዓመቱ አገራዊ የልማት ዕቅድ ከተያዙ ስትራቴጂክ ግቦች አንዱ የሆነው የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለስልጣን የመንግሥት ግዢን ወረቀት አልባ፣ ግልጸኝነትና አሳታፊነትን ወደሚያሳድገው ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ (Electronic Goverenment Procurement /e-GP) ስርዓት እንዲሸጋገር እያደረገ ይገኛል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2015