የአረፋ በዓል በሂጅራ ዘመን አቆጣጠር በ12ኛው ወር በ10ኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው፡፡ የአረፋ በዓል ሁለት ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከብሮ ይውላል፡፡ አንደኛው ነብዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) አንድያ ልጃቸውን እስማኤልን እንዲሰዉ ከፈጣሪያቸው የወረደላቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ያሳዩትን ቁርጠኝነት ለመዘከር የሚታሰብ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው ዐረፋ የሚለው ቃል በዐረብኛ «አወቀ» እንደማለት ነው፡፡ ይህም የራሱ የሆነ ታሪክ አለው፡፡
አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሃዋ ከጀነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ ዐረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ፡፡ እዚያም «ዐረፍቱከ…ዐረፍቱኪ» ተባባሉ፡፡«አወቅኩህ! አወቅኩሽ» ማለታቸው ነው፡፡ ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የአረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው፤ ይህ በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው።
አረፋ የመረዳዳረት በዓል ነው፡፡ ማንኛውም አቅሙ የቻለ አማኝ ከሚያርደው እንስሳ 1/3ኛውን ለድሃ የማከፋፈል ግዴታ ያለበትና ሁሉም በዓሉን በእኩልነት የሚያሳልፍበት በዓል ነው፡፡ ሙስሊም ዕለቱን አቅሙ በፈቀደ ሁኔታ እንስሳት በማረድ ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር ያሳልፈዋል። ለኢድ አል አድሃ(አረፋ) አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት ሲሶውን ብቻ ለራሱ እንዲጠቀም ነው ኃይማኖታዊ ግዴታው የሚያዘው። ከተቀረው ሲሶው ለዘመድ አዝማድ፣ሲሶው ደግሞ አቅም ለሌለው ደሃ እንዲከፋፈል እስልምና ያዛል።
ከዚህ የተነሳም የአረፋ በዓል በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ በዓል ነው። በዓሉን ከኃይማኖታዊ ትሩፋቱ ባለፈ የቤተሰባዊ እሴት ማጠናከሪያ እና መሰባሰቢያ በዓል አድርገው ስለሚያዩት በተለያየ ምክንያት ተለያይተው የሚኖሩ ቤተሰቦች ይሰባሰቡበታል፡፡ ሕፃናት በበዓል አልባሳት ደምቀው ስጦታ ለጎረቤቶቻቸው በማበርከት ያሳልፋሉ፡፡ እናቶች መኖሪያ ቤቶቻቸውን ያሳምራሉ፤ተወዳጅ እና ጣፋጭ ምግቦች በተለየ ሁኔታ ለቤተሰቡ ያዘጋጃሉ፡፡
በኢትዮጵያ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድም አማኞች በጠዋት ተነስተው፣ በኃይማኖታዊ ንፁህ አልባሳት ደምቀው እና አምረው ወደ መስገጃ አደባባይ እና ወደ መስጂዶች በረድፍ ሲያመሩ ሲታዩ የጎላ ውበት፣ አስደማሚ አንድነት ይንፀባረቃል። ሶላታቸውን በጋራ ሰግደው እና በአንድ ዓይነት መንፈሳዊ ቋንቋ ፈጣሪያቸውን አመስግነው፣እርስ በእርሳቸው የመልካም ምኞት መግለጫ ተለዋውጠው፣ ከልብ የመነጨ ፈገግታ ተመጋግበው፣ ‹‹አብረን ወደ ቤት እንግባ፣ አብረን እንዋል እያሉ›› ሲገባበዙ፣ በአክብሮት ሲጠራሩ ማየትና ማዳመጥ የተለመደ ነው።
በተለይም ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት እስላምና ከርስቲያኑ በመጠራራት በዓሉን በጋራ የሚያከብሩባት ድንቅ ሀገር መሆኗ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለእስልምና ኃይማኖት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተችና በእንግዳ ተቀባይነቷም ዝንተዓለም ስሟ የሚነሳ ሀገር ናት፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ሃበሾችን መሠረት ያደረጉ ከ23 በላይ የቁርአን አንቀጾች፣ በሃበሾች ቋንቋም ከ30 በላይ የቁርአን አንቀጾች እንዲወርዱ፤በተጨማሪም በነብዩ መሐመድ /ሰዐወ/ ስለ ሃበሾች ክብር ከ27 ያላነሱ ነብያዊ ሃዲሶች እንዲነገሩ ምክንያት እንደሆኑ ይነገራል።
በአጠቃላይ ኢድአልአደሃ (አረፋ) የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓል ነው፡፤ በተለይም በኢትዮጵያ የኢድ አልአድሃ (አረፋ) አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በጸጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች፡፡ አረፋን በመሳሰሉ የበዓል ወቅቶች ደግሞ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የክርስትና አምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡ ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው፡፡
ከአረፋ በዓል ዕሴቶች አንዱና ዋነኛው የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ነው፡፡ የእስልምና እምነት በአረፋ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ከሚታረዱ እንስሳት 1/3ኛውን ላጡና ለተቸገሩ ወጎኖች የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችልና የመረዳዳት እሴትንም የሚጨምር ነው፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት በሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህን ወገኖችን አስቦ መዋል በአረፋ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2015