ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለሀገራት ዕድገትና ልማት እንዲሁም ባህልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። የአንድን ማኅበረሰብ እሴቶችና የተከማቸ እውቀት ማስተላለፊያ መንገድም ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በትምህርት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው የሚለውንም መርህ የዓለም ሀገራት የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን የዓለም ሀገራት በሙሉ ትምህርትን ለለውጥ ተጠቅመውበታል ለማለት ብዙም አያስደፍርም።
የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አብሮ የሚቀያየር ስለመሆኑም ይናገራል፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ለሚታየው ስብራት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈላጊውን “ከፍተኛ ደረጃ” የሚያሟሉት አራቱ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። ይህንን ለመለወጥ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ “በኃላፊነት ይሳተፉበታል” የተባለው ይህ ዘመቻ ወላጆችን፣ የቀድሞ ተማሪዎችን እና መምህራንን የሚያሳትፍ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶችን ጥራት እና ደረጃ የማሻሻል ሥራ በአምስት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የማዳረስ ዓላማ ያለው መሆኑንም ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው በተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው። እርሳቸው በአጽንኦት ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፤ የትምህርት ቤቶችን ጥራት የሚመለከት ነው።
በሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ባሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግምገማ ማድረጉን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ በተገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ ትምህርት ቤቶቹ በአራት ደረጃዎች እንደተመደቡ ገልጸዋል። ግምገማው የተደረገው፤ ትምህርት ቤቶች በሚጠቀሟቸው ግብዓቶች፣ በመማር ማስተማር ሂደቶቻቸው እንዲሁም ተማሪዎቻቸው በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች ላይ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ግምገማ ከተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል “ከፍተኛ” የተባለውን “ደረጃ አራት” ያገኙት፤ አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የሚፈለገውን ደረጃ ያሟሉት በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያላቸው ድርሻ 0 ነጥብ 001 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፣ ሌሎቹ ትምህርት ቤቶች “የተጠበቀውን ደረጃ ያላሟሉ” መሆናቸውን ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።
በዚሁ ግምገማ በተገኘው ውጤት፤ ከአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 85 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት “ፍጹም ከደረጃ በታች” መሆናቸው መረጋገጡን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ደግሞ 70 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚጠበቀው “ደረጃ በታች” ማስመዘገባቸውን አክለዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች፤ በግምገማው በ“ደረጃ አንድ” እና “ደረጃ ሁለት” ምድብ የተቀመጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር የእነዚህ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል፤ “ህብረተሰቡን በማስተባበር” ጥገና እና እድሳት እያደረገ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። በዚህ አይነት መልኩ 8 ሺህ 700 ገደማ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት እንደተደረገላቸውም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የትምህርት ባለሙያ እና በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አማኑኤል ኤሮሞ እንደሚናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን አመላካች ነው የሚባለው የተማሪዎች ውጤት ነው። በተማሪዎች ውጤት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ሚና ያላቸው አራት አካላት ናቸው ይላሉ። ተማሪው ፣ወላጅ ፣መምህር ርዕሰ መምህር እና የትምህርት ቤቱ ምቹ ሁኔታ ናቸው፤ እነዚህ አካላት ናቸው በተማሪ ትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ ሚና ቀድመው የሚጫወቱት ሲሉ ያክላሉ።
ዶክተር አማኑኤል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የጋራ ርዕይ መኖር አለበት፤ ይህንን ርዕይ የሚቀርጸው ደግሞ አመራሩና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ ዋናው ከርዕሰ መምህር እስከ ትምህርት ክፍል ያሉ አመራሮች ቁርጠኝነት ነው። የእነርሱ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ የትምህርት አመራር እውቀት ያላቸው ናቸው ወይ ትምህርት ቤቶችን እየመሩ ያሉት የሚለው በራሱ የሚያጠያይቅ ነው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ባለፈው ሥርዓት በየትምህርት ቤቶቹ ሲመደቡ የነበሩ ርዕሰ መምህራን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ከሙያ ብቃታቸው አንፃር ሲታዩ በትምህርት አመራር እውቀት እና ልምድ ያላቸው አይደሉም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በየጊዜው ይለዋወጣሉ፤ በዚህ መልኩ እየተሰራ ለውጥ መጠበቅ የማይታሰብ ነው።
በሌላ በኩል በአመራሩ፣ በርዕሰ መምህሩም ሆነ በመምህሩ ላይ ተጠያቂነት መኖር አለበት፤ ማለትም ጥሩ ሥራ ከሰሩ መሸለም ከደረጃ በታች ሥራ ከሰራ ደግሞ መጠየቅ አለባቸው፡፡ አሁን በእኛ አካሄድ ይህ አሰራር የለም፤ ጠቅላላ ተማሪ ቢወድቅም እንዴት ሆነ ተብሎ ርዕሰ መምህሩ አይጠየቅም፡፡ በጠንካራ ሥራ ደግሞ ሁሉንም ተማሪ ማሰለፍ ቢችልም የሚያበረታታ አካሄድ የለም፡፡ ይህ አካሄድ መስተካከል ይገበዋል ብለዋል።
በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ትምህርት እና ፖሊሲ ጥናት መምህር እንዲሁም በዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር እንዳለው ፉፋ በበኩላቸው፤ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ጥራት ለማምጣት አሰራሩ በምን ሁኔታ ነው የሚያልፈው የሚለውን ማገናዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፤ በአጭር ጊዜ የሚመጣ ለውጥ የለም፤ ስህተቱ ምን ነበር ብሎ ጥናት እና ምርምርን መሰረት አድርጎ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
እርሳው እንደሚናገሩት፤ በሌላ በኩል በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት ያደረገው ጥራት ላይ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ተደራሽነት ስላልነበረ ይህንን ለመፍታት ሰፊ ሥራዎች ተሰርተው በትምህርት ቤቶች ብዙ ሀብት ወጥቷል፡፡ ነገር ግን የጥራቱ ጉዳይ የተዘነጋ እንደነበር ተናግረዋል።
ተደራሽነቱን እና ጥራቱን ደግሞ አንድ ላይ ማስኬድ ከባድ እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር እንዳለው፣ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥራት የለም ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡ የተደራሽነቱን ያህል ጥራት ማምጣት አልተቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የተማሪው ቁጥር ብዙ በመሆኑ አንዱ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ተማሪ በክህሎትም በእውቀትም ብቁ ለማድረግ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም፡፡
ዶክተር እንዳለው እንደሚገልጹት፤ አሁን የምንሰራው ነገር በዘለቄታ ምን ውጤት ያመጣል የሚለውን ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡ ወደኋላ የሚመልሰን እንዳይሆንም መጠንቀቅ አለብን፡፡ በተመሳሳይ ተደራሽነቱንም የሚገታ እንዳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሆኖ ወደ ሥራ ቢገባ ውጤታማ ያደርጋል።
የአንድ ትምህርት ቤት ማህበረሰብ ሁልጊዜ ከተማሪው ከፍተኛ ውጤት በመጠበቅ መስራት አለበት፡፡ በሌላ ጎኑ ትብብር እና ግንኙነት በመፍጠር በጋራ መሰራት መቻል አለበት፡፡ በትምህርት ቤቶች ትልቁ ቢዝነስ የሚባለው ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ፣ የተማሪዎች የመማር ሂደት በየጊዜው መገምገም ሲሆን፣ እነዚህ ተቀናጅተው በየዕለቱ መሰራት አለባቸው የሚሉት ደግሞ ዶክተር አማኑኤል ናቸው።
ተከታታይ የሆነ የመማር ማስተማር ሂደትን መከታተል ይገባል የሚሉት ዶክተር አማኑኤል፣ ይህ ደግሞ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በክፍል ውስጥ ምን እየተሰራ ነው? የሚለው ላይ ነው ሱሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የጠቀሱት፤ ትልቁ ቁምነገር ያለው በመምህሩ፣ በተማሪውና የመማሪያ መጽሐፉ ላይ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው የመምህራን አቅም መገንባትና ሙያ መሻሻል ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፤ መምህራን ይህን የሙያ አቅማቸውን ሲያጎለብቱ ደግሞ አጀንዳቸው መሆን ያለበት የተማሪ ውጤት ላይ መሆን ይኖርበታል ሲሉም ያክላሉ።
ሌላው አጋዥ ሁኔታዎች የሚባሉት ደግሞ አሉ ያሉት ዶክተር አማኑኤል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ እንዲሁም ምቹ የመማሪያ ክፍሎች እንደሚያስፈልጉ ይናገራሉ፡፡ የወላጆች የነቃ ተሳትፎም የግድ ነው፤ ወላጆች ስለልጆቻቸው ጉዳይ ከትምህርት ቤቱ ጋር በጋራና በቅንጅት መስራት መቻል አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ውጤታማ መሆን እንደማይቻልም ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዋናው አሁን መሰራት ያለበት በትምህርት አመራሩ፣ በመምህሩ ብቃት፣ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ በተማሪዎች ተሳትፎ ላይ እና በወላጆች ተሳትፎ ላይ ነው፡፡ ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ጥቂት የማይባል መምህር ደግሞ ተማሪውን ውጤታማ አደርጋለሁ የሚል ሞራል የለውም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ በቂ ደመወዝ እየተከፈለው አለመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች ለማሻሻል ከተሰራ በትክክል ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ መለካት ያለብን ባላቸው ግብዓት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ምን አይነት ጥሩ መምህር አለ በሚለው ላይ ነው፡፡ ግብዓትን በማሟላት ብቻ የትምህርት ጥራት አይመጣም። ዋናው እና ትልቁ ግብዓት ብቃት ያለው መምህር በመሆኑ እዚህ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ዶክተር አማኑኤል ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን የዕውቀት ደረጃ ለማሻሻል ከተፈለገ ራሳቸው ተማሪዎች የሚማሩትን ጉዳይ ጠንቅቀው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ለማድረግ መስራት እንጂ እንዲሁ ከክፍል ወደ ክፍል ለማለፍ የሚማሩት መሆን የለበትም የሚሉት ደግሞ ዶክተር እንዳለው ሲሆኑ፣ ተማሪው እሰከ አስራ ሁለተኛ ባለው የትምህርት እርከን ውጤታማነቱን እያረጋገጠ የሚሄድ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ በዚህ ሒደት የመማር ማስተማሩ ተግባር የተሟላ ይሆን ዘንድ ትምህርት ቤቶች ትክክለኛ ግብዓትን ያሟሉ መሆን እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው ዶክተር እንዳለው አፅንኦት የሰጡት ጉዳይ፤ የመምህራን የስልጠና ደረጃ ምን ያህል ነው? ያመጣናቸውስ እንዴት አሰልጥነን ነው የሚለው ላይ ነው፡፡ ቅርብ ጊዜ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከሆነው ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ በዘርፉ ብቁ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት የሚችል ተቋም የለም፡፡ ከአመታት በፊት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመምህራን ስልጠና ፕሮግራም ላይ በስፋት ነበሩ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ስልጠና የሚያገኙት የመምህርነት ብቻ ሳይሆን የሥርዓተ ትምህርት ጥናት፣ የምዘና እና ክትትል ሂደት፣ የማጥናት ሁኔታም ነበር፡፡ በዚህም ስልጠና የተሻለ እውቀት ይዘው ይወጡ ነበር፡፡ አሁን ያለው የስልጠና አካሄድ የሚመጥን እና የመምህራንን አቅም የሚያሳድግ አይደለም፡፡
የትምህርት በጀትን በተመለከተ የሥራ ማስኬጃ ተብሎ የሚመደበው እንደሚታሰበው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት አይደለም፡፡ በትምህርት ቤቶች ግብዓት የለም፤ ይህ ከሌለ ደግሞ አሰራር አይኖርም። አሰራር ሳይኖር ደግሞ ጥራት አይመጣም፡፡ ይህንን በተወሰነ መልኩ እንኳ ለመቅረፍ ከላይ እስከታች የበጀት ምደባውን ጨምሮ ያልተማከለ መሆን አለበት፤ ተማሪውን የሚስብ ከባቢያዊ ሁኔታ ለመፍጠር መሰራት የግድ የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው አባባል፤ ሌላው ትልቁ ጉዳይ የትምህርት ቤቶች ከባቢያዊ ሁኔታ ነው። አዋኪ ከሆኑ ነገሮች የፀዱ ናቸው ወይ የሚለውን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ከትምህርት ጋር በፍጹም አብሮ መሄድ የማይችሉ ነገሮች የትምህርት ቤቶችን ዙሪያ ሞልተዋል። እነዚህን ሁኔታዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ የምናስበው ውጤት ሊመጣ አይችልም፡፡
የቤተሰብና የወላጆች ሚና ትልቅ ሊሆን ይገባል የሚሉት ዶክተር እንዳላው፣ አንደኛ የልጆቻቸውን ትምህርት መከታተል በሁለተኛ ደረጃ ከትምህርት ቤቶች ጋር መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡በትምህርት ቤቶች የጎደሉ ነገሮችን ለማሟላት በትብብር መሥራት መቻል አለባቸው፡፡ በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት ኃላፊነት ወስደው ተከታታይነት ባለው መልኩ ለነገ ትውልድ በመጨነቅ ሊሰሩ እና የትምህርት ነገር ግድ የሚላቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉ ጠቃሚነቱ የሚያከራክር አይደለም ፤ነገር ግን በምን መልኩ የሚለው በጥናት ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት። በሌላ በኩል ከላይ እስከ ታች ያለው የትምህርት አመራር በዘርፉ የሰለጠነ እና እውቀት ያለው ሆኖ በጥንቃቄ መደራጀት አለበት፡፡ ይህ አሠራሩን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015