የአንድን ሀገር እጣ ፈንታ ብሩህ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ትምህርት ነው። ከዚህ የተነሳም ሀገራት ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። በሚያገኙት ውጤት መሰረትም ነገዎቻቸው ላይ መናገር የሚያስችል ድፍረት ይጎናጸፋሉ። እንደሀገር የቆሙበትንም መሰረት በየጊዜው እያጸኑ ከትናንት ዛሬ ላይ የተሻለች ሀገር ይገነባሉ።
ዓለማችን ወደ አንድ መንደርነት እየተጓዘች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ ዘመኑን በመዋጀት እንደሀገር ዓለም የደረሰችበት ደረጃ ደርሶ አብሮ ለመራመድ የትምህርት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ከሆነ ውሎ አድሯል። በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች የማደግ መሻታቸውን እውን ለማድረግ በትምህርቱ ዘርፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቁ አቅማቸው እንደሆነ ይታመናል።
የእነዚህ ሀገራት አሁነኛ የፖለቲካ ነጻነት ሆነ የነገ ህልሞቻቸው የሚጸኑት ትምህርት ሊፈጥራቸው በሚችላቸው በእውቀት የበለጸጉ ዜጎቻቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ነው። ለዚህ ደግሞ ለትምህርትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው የመንቀሳቀሳቸው እውነታ ብሄራዊ ነጻነታቸውን ከማስጠበቅ ተለይቶ የሚታይ አይሆንም ፤ ብዙ መስዋእትነትን የሚጠይቅ ነው።
ሀገራችንም እንደሀገር ብሔራዊ ክብርን ከማስጠበቅም ሆነ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማምጣት ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የረጅም ታሪክ ባለቤት ናት። በየወቅቱ ሀገሪቱን ያስተዳደሩ መሪዎች በተለይም ዘመናዊ ትምህርትን በማስፋፋት ሀገርን ትልቅ የማድረግ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። የድካማቸውን ያህል ባይሆንም ያገኙዋቸው ውጤቶች የነበራቸው ሀገራዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በተለይም በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን /ከ1930ዎቹ ጀምሮ ዘመናዊ ትምህርትን በመላው ሀገሪቱ ለማዳረስ የተደረጉ ጥረቶችና የተመዘገቡ ስኬቶች፤ ለሀገር ተስፋ የሆነ ትውልድ በማፍራት በተጨባጭ የታዩ ናቸው። ሀገርንም በዓለም አቀፍ መድረኮች ማስጠራት የቻሉ ስመጥሩ የሀገር ባለውለታዎችን በብዛትና በጥራት ማፍራት አስችለዋል።
በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት በትምህርት ጥራት ላይ የነበረው ክፍተት እንዳለ ሆኖ ፤ እንደሀገር ለትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በተለያዩ ውጪያዊና ውስጣዊ ምክንያቶች በጥራት በኩል የነበሩ ክፍተቶች በጊዜ ሄደት ውስጥ እየሰፉ መጥተው አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ የትምህርት ስርአት አደጋ ውስጥ ከተውታል። ይህ ደግሞ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል።
ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት መንግስት በዘርፉ ሀገራዊ ስትራቴጂ ቀርጾ መንቀሳቀስ ጀምሯል። በተለይም የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በሁለንተናዊ መልኩ ብቁ የሆነ ሀገር ገንቢ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ ነው። የፖሊሲ አቅጫዎችን ቀርጾም ወደ ተግባር ለመግባት ሰፊ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በቅርቡ የሚጀመረው በህዝባዊ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ጉዳይ ነው።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ስኬት ካላቸው ቁመና አንጻር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአራት ይከፈላሉ። በደረጃ አራት ላይ የሚገኙት ለመማር ማስተማሩ ሂደት የተሟላ ቁመና ያላቸው ናቸው። በደረጃ አንድ ና ሁለት ላይ የሚገኙት ምንም አይነት የተመቸ ቁመና የሌላቸው ሲሆን፤ ደረጃ ሶስት የሚባሉት ብዙም ከነሱ የተለዩ አይደሉም።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሀገሪቱ ካሉ 49 ሺህ 395 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 99 ከመቶ የሚሆኑት ለመማር ማስተማር ውጤታማነት የተቀመጠውን ደረጃ የሚያሟሉ አይደሉም። ደረጃ አራት ላይ የሚገኙት ደግሞ በቁጥር ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ከቁጥር ባለፈ ስለሀገራዊ የትምህርት ጥራት የሚናገረው ብዙ እንደሆነ ይታመናል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስለትምህርት ጥራት ማውራት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደሚባለው አይነት እንደሚሆን አመላካች ነው። ይህንን መሰረታዊ ችግር ሳይፈቱ ስለጥራት ማውራት ትርጉም የሌለው ጮኸት መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታ በመነሳት መንግስት በቅርቡ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ የሚጀምረው ብሔራዊ ንቅናቄ የሚኖረውን ሀገራዊ ፋይዳ በሚገባ ተረድቶ መንቀሳቀስ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
የንቅናቄው ስኬት ለመጪው ትውልድም ሆነ ለምንመኘው ሀገራዊ ብልጽግና ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ተረድቶ በኃላፊነት መንቀሳቀስ በነገዎች ተስፈኛ ከሆነ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። ለዚህ ስኬት ደግሞ ሁላችንም ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015