በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ 12ሺ829 ቅርንጫፎች ያሏቸው 109 የፋይናንስ ተቋማት አሉ።በአሁኑ ሰአት የእነዚህ ተቋማት ሀብት 2ነጥብ9 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።በትርፋማናት ረገድም 37 ቢሊዮን ብር በላይ አትራፊ ሆነዋል።ከዚህም በተጨማሪ በመላ አገሪቱ ያሉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብሎም የሸሪአን ህግ ተከትለው የሚሰሩ ባንኮች ከፍተኛ የሆነ ተቀማጭ ገንዘብ አላቸው፡፡
ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በሸሪአ አገልግሎት 172 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሆኗል።ይህም በሸሪዓ ላይ የተመሰረቱ የፋይናንስ አገልግሎቶችና ፖሊሲዎች ውጤታማ እየሆኑ ስለመምጣታቸው የሚያመላክት ስለመሆኑም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኙ አሃዛዊ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በዛሬው ዕትማችን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ያሉበትን ደረጃ እና የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ አገር እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ፤ በሀገራዊ የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ እየተወሰዱ ስለሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችና የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውናል፤ እኛም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው እውነታ በሀገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ቀውስ ተከስቷል ?
አቶ ሰለሞን፡- በእኛ ሀገር የፋይናንስ ሴክተር ቀውስ አልተከሰተም /የለም።ቀውስ የሚባለው ውጪ አገር ያለው ወይንም አሜሪካ የምሰማው ነው።ይህ ማለት ግን ወደ እኛ አይመጣም ማለት አይደለም።እንዳይመጣ ዝግጅት አድርገናል/እያደረግንም ነው።ለዚህ በዋንነነት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር መገንባት ‹‹ሪስክ ማኔጅመንት ›› ያስፈልጋል።በዚህ ላይ በደንብ መሥራት ይጠበቅብናል።‹‹ሊኩዲቲ›› ላይ በተመሳሳይ በሚገባ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርብናል።
በብድር አሰጣጥ ላይም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።ይህም ማለት የማይመለሰው ብድር አምስት ከመቶ በላይ እንዳይወጣ የመከታተል ሥራ መስራት ይኖርብናል።እነዚህ እጅግ በጣም ወሳኝ ከሚባሉ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።በጥቅሉ ሲታይ ግን የፋይናንስ ሲስተማችንና ሥርዓታችን ችግር የለበትም። ነገር ግን ወደፊት የፋይናንስ ችግር ቢፈጠር ብለን የተቀማጭ ዋስትና ‹‹Deposit insurance›› ሥራ ተጀምሯል ።ስለዚህ ለአደጋ የተጋለጠ የ ፋይናንስ ሥርዓት የለንም፤ በዚህ አግባብ ከተሰራ በኢኮኖሚ ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎች ማስተካከል ቀላል ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቱ ፋይናንስ ተቋሞች ቀውስ ውስጥ አልገቡም ማለት ነው?
አቶ ሰለሞን፡- የእኛ ተቋማት ቀውስ ውስጥ አልገቡም።ቀውስ ማለት ትርጉሙ እንዲህ ቀላል አይደለም።ቀውስ ማለት የአንድ የፋይናንስ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሲቃውስ እና ለመቆጣጠርም አደገኛ ሁኔታ ላይ ሲደረስ ነው።የፋይናንስ ተቋማት ሲወድቁ ቀውስ ተፈጥሯል ይባላል።ይህ በእኛ አገር አልተከሰተም። ይህን ትርጉም ከተረዳን የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሴክተር ቀውስ ውስጥ አለመግባቱን ማረጋገጥ እንችላለን ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀውሶች የሉም ለማለት ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ሰለሞን፡- በእኛ በኩል ይህንን አስረግጠን የምንናገርበት ብዙ መንገድ እና ሳይንሳዊ ልኬቶች አሉ። ለምሳሌ አትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው አይታመምም።ሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ ከታመመ እና በሽተኛ ከሆነ አደገኛ ነው።የፋይናንስ ሥርዓቱን እንደዛ አይነት ሁኔታ ከገጠመው የፋይናንስ ሥርዓቱ ተቃውሷል ማለት ነው።አንድ ወይንም ሁለት የፋይናንስ ተቋማት ችግር ሊገጥማቸው ይችላል።ችግር ቢገጥማቸው እንኳን የተለያየ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡
መሰል ችግሮች ማጋጠማቸው የተለመደ ነው። የአንዳንዶቹ ችግሮች በፍጥነት የሚስተካከሉ ይሆናል።አንዳንዶቹ ደግሞ በሂደት የሚስተካከሉ ናቸው።በመሆኑም ይህ ችግር ተከሰተ ማለት ፋይናንስ ሥርዓት ተቃወሰ ማለት አይደለም።ጠቅለል ሲደረግ ቀውስ አለ ማለት ህዝብ በሙሉ ታሟል እንደማለት ይሆናል። ስለዚህ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ችግር ውስጥ እስካልገቡ ድረስ እና ትርፋማ ሆነው እስከሄዱ ድረስ ቀ ውስ አለ ብሎ መነገር አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ አለመመጣጠኖች ምን ተብሎ ይገለፃል?
አቶ ሰለሞን፡– አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማይክሮ አለመመጣጠን እና የፋይናንስ ተቋማት ቀውስ ትርጓሜው የተለያየ ነው።አለመመጣጠን በብዙ ነገር ሊገለጽ ይችላል።በተለያዩ ደረጃ የምንፈልገውን ላናገኝ እችላለን።ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ፣ ባላንስ ኦፍ ፔይመንት፣ የንግድ ሚዛን አለመጣጣም እና ግሽበት በሚፈለገው ደረጃ ላይደረስ ይችላል።ይህ ሆኗል ማለት ግን ሥራ የሚጠይቅ ነገር ቢኖርም የፋይናንስ ቀውስ ስለመከሰቱ አመላካች ሆኖ ሊጠቀስ አይችልም።እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ሂደት ይጠይቃል።ይህን ለማቃለል እየተሰራበት ነው።
ነገር ግን የፋይናንስ ሴክተሩ ከዚህ አለመመጣጠን ይጎዳል የሚለውን ለመጥቀስ ካልሆነ በስተቀር የፋይናንስ ቀውስ ነው ማለት ፈፅሞ አይታሰብም።ሌላው ቀርቶ አሜሪካ ውስጥ ቀውስ የለም።ሦስት ባንኮች ወድቀው ነበር፤ እነርሱንም ታድገዋል።በመሆኑም ቀውስ የሚለው፤ በእኔ በኩል ቀውስ የሚለው በራሱ መነሳት የለበትም የሚል እምነትና አረዳድ አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር የወጪ እና ገቢ ምርት አለመመጣጠን አለ። ይህ ቀውስ ባይባልም፤ እንደ ብሄራዊ ባንክ ችግሩን ለማስተካከል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሰለሞን፡- የውጪ እና ገቢ ምርት አለመመጣጠን የሚታይ ነገር ነው ።አለመመጣጠኖች አሉ።ይህ የሆነው ግን ከተፈጥሮ አደጋዎችና አለመረጋጋት ስለወጣን ነው። ቀደም ሲል ደግሞ የአንበጣ መንጋ እና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ነበርን። በዚህም የተነሳ አቅርቦትና ፍላጎት የተመጣጠነ አልነበረም። በፋይናንስ ረገድ የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ነበር። ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፤ አቅርቦቱ ደግሞ በዚያው ልክ አላደገም።አሁን ከነበረው ቀውስ ወጥተን ወደ መደበኛ ሥራችን ገብተናል።ነገር ግን አሁንም ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ማየት ይገባናል።የዓለም ነባራዊ ሁኔታም የሚያመጣብን ግሽበት ይኖራል።ትልቁ ነገር ግሽበትን ለመቀነስ ሥራ እየተሠራ ነው።ይህንን የምንሰራው ደግሞ ሳይንሱን ተከትለን እና ጥናቶችን መሰረት አድርገን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግሽበትን ለመከላከል ምን ዓይነት ሥራዎች ናቸው የሚከናወኑት?
አቶ ሰለሞን፡- በዚህ ላይ ብዙ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ።በደፈናው የሚጠቀስ ሳይሆን ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ነው።አንደኛው በሞኒተሪው በኩል በጣም ብዙ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዳይገባ ይደረጋል።ሁለተኛው በ‹‹ፊሲካል›› በኩል ደግሞ የበጀት ጉድለቱን ለመቀነስ መስራት ነው።ፊሲካል ዲሲፕሊን የሚባለው ይህ ነው።ሞኒተሪ ፖሊሲው ባለን መሣሪያ ተጠቅመን እና ፊሲካል ዲሲፕሊን ካለ ሌላው ነገር አቅርቦት ላይ ያለው ጉዳይ ነው።ዝናብ ከዘነበ እና ሰራተኛው ከተሰማራ፤ አርሶ አደሩ በቂ ምርት ካመረተ ብሎም ኢንዱስትሪዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ከተነቃቁ ችግሮቻችንን እናልፋቸዋልን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ጤናማ አካሄድ እየተከተሉ ነው ለማለት መለኪያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ሰለሞን፡- በአገሪቱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት በጤናማ አሰራር ውስጥ ናቸው ለማለት ሳይንሱ የሚስያስቀምጣቸው መለኪያዎች አሉ።አንደኛው በቂ ካፒታል አላቸው ወይ የሚለው ነው።በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በቂ ካፒታል አላቸው።ሁለተኛው ‹‹አሴት ኳሊቲ›› ነው።በዚህ ረገድም ቢሆን ባንኮች አምስት ከመቶ በታች ናቸው ጣሪያው ላይ እንኳን አልደረሱም፡፡
ሌላው ‹‹ሊኩዩዲቲ›› ነው።በዚህ ረገድም ከአንድ ባንክ ውጪ ሁሉም ጤናማ መስመር ላይ ናቸው። ይህም አንዱ ባንክ ቢሆን ትርፍ ገንዘብ አለው።ነገር ግን ከአንዱ ቅርንጫፍ ወደ ሌላው ጋር ሲታይ ክፍተቶች ይታያሉ።የአንድ ባንክ አንድ ቅንጫፍ ወይንም የተወሰኑ ቅርንጫፎች ላይ ችግር ሊኖር ይችላል።ይህ ማለት ግን የፋይናንስ ተቋማትን አጠቃላይ ምስል አይሰጥም፡፡
በመሆኑም የፋይናንስ ቀውስ አለ ብሎ መናገር አይቻልም።በዘገባዎችም ቢሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።ይህ የአንድን አገር ምስል ከሚያሳዩ ውስጥ ቀዳሚው ነው።የውጭ ኢንቨስተሮችንም ሊያርቅ የሚችል ስለሆነ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል። ሌላኛው ልኬቱ የትርፋማነት ህዳግ ነው።በዚህ ዓይን ከታየም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፋይናንስ ሴክተሮች ትርፋማ በመሆን ይታወቃሉ።በትርፋማነተቻው ከታየ ከልክ በላይ ነው።በፋይናንስ ሴክተሩ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል።በዚህ የትርፍ መስመር ውስጥ ያሉትን ቀውስ ውስጥ ገብተዋል ከተባለ ይህም ስህተት ይሆናል።
በመሆኑም በጣም ትርፋማ በመሆናቸውም በጣም ጤናማ ናቸው የሚለውን ድምዳሜ ይሰጠናል።ከማይክሮ ፋይናንስ ጋር በተያያዘ ትንንሽ ችግሮች አሉ።በተለይም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸው አሉ።እነዚህ ድጋፍ የሚፈልጉ በመሆናቸው ድጋፍ የሚደረግላቸው ይሆናል።የልማት ባንክንም የተወሰነ ከመደገፍ በስተቀር የንግድ ባንኮች ምንም ችግር የሌለባቸውን መሆኑን መጥቀስ ይቻላል።በዚህ ዓይን ሲታይ ትርፋማነታቸው እና ጤናማነቱ አስተማማኝ ነው የሚል ምስል ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡- የንግድ ባንኮች ትርፋማ ከመሆን ባሻገር አካሄዳቸው እና በመካከላቸው ያለው ውድድር እንዴት ገለጻል?
አቶ ሰለሞን፡- ግልፅ ነው።ይህ ጤናማ ካልሆነማ በዚህ ደረጃ ትርፋማ አይሆኑም።ጤናማ ካልሆነም ውሎ አድሮ የሚታወቅ ነው የሚሆነው።ይህን ደግሞ የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል አለ።በእርግጥ ውድድር ሂደት ነው።የውጭ ባንኮች ሲመጡ፣ በቴክኖሎጂ ሲታገዝ ብሎም የሰው ኃይል አቅማቸው እያደገ ሲመጣ የሚመጣ ነው።ውድድር በአንድ ቦታ የሚገደብ አይደለም።ሁሌም መስራት የሚፈልግ ነው።ውድድር አዳዲስ ምርቶችና አገልግሎቶች ሲመጡ እየዳበረ የሚመጣ ነው።በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ተቋማት መካከል በቂ ውድድር አለ ማለት አልችለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች በፋይናንስ ተቋማት ሲንገራገጩ ባንኮች ብቻ ትርፋማ መሆናቸው ጥርጣሬ አይፈጥርም?
አቶ ሰለሞን፡- ይህ ድሮም ነበር።ብዙ ቦታ፤ ብዙ ችግር ነበር። ነገር ግን እነዚህ ባንኮች ትርፋማ ሆነው የመጡ ናቸው።አሁንም ያንኑ አስቀጥለው ነው እየሄዱ ያሉት። ስለዚህ የባንኩ ዘርፍ ትርፍ ኖሮት የትርፍ ክፍፍል ሲሰጥ ነው የኖረው።በዚህ ረገድ ባንኮች እያተረፉ ያሉት ጤናማ ሥርዓትን ተከትለው መሆኑን ማወቅ ይገባል።ነገር ግን የሚስተካከሉ ነገሮች የሉም ማለት አይቻልም።በመሆኑም ውድድሩ በሂደት እየተጠናከረ ይሄዳል።የፋይናንስ ሴክተር ውድድርም መተባበርም ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ ተቋማትን ወደ ቀውስ ከሚከቱት መካከል የሳይበር ስርቆት ነው።እንደ ፋይናንስ ሴክተር ቴክኖሎጂ የተገነባ የመከላከል ዝግጅታችን ምን ይመስላል?
አቶ ሰለሞን፡– ከሳይበር ጋር በተያያዘ በሚገባ መስራት አለብን። ከማጭበርበር ጋር የሚከሰተውም ችግር ትኩረት የሚፈልግ ነው ፤በችግሩ ዙሪያ መሥራት ያስፈልጋል። የፋይናንስ ደህንነት መረብን የቁጥጥር አቅም ማሻሻል ይገባል ። የቁጥጥር አቅምን ከማሻሻል በተጨማሪ የገንዘብ ተቋማት እራሳቸውን ለማጠናከሪያ ዝግጁ መሆን አለባቸው።ተቋማት የቴክኖሎጂ እና የካፒታል፣ አቅም እና ስትራቴጂያቸውን ማሻሻልና ተፎካካሪ መሆን ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትልቅ አቅም ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት መካከል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተጠቃሽ ናቸው።ከብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ውጪ ሌላ ተቆጣጣሪ የሚፈጠርበትና የሚደራጅበት ጊዜ መቼ ነው ?
አቶ ሰለሞን፡– ይህን በተመለከተ ጥናት ተጀምሯል።በዓለም ባንክ በኩል የሚሰራ ሥራ ስለሆነ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚያጠናቅቁት ነግረውናል።ስራው ተጀምሯል ። ስራው በጣም ሰፋ ነው። የመጀመሪያው ሥራ እንዴት ይዋቀራል የሚለው ነው። በመቀጠል ተጠሪነቱ ለማን ይሆናል የሚለው ነው። ከዚህ በመቀጥል ደግሞ ለውጭ ክፍት ለማድረግ በራሱ ሪፎርም መደረግ አለበት።በዚህም የተነሳ የህግ ማዕቀፎችና እና ሌሎች ነገሮች በሙሉ መታየት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ የጥቁር ገበያ እየተበራከተ እንደሚገኝ ይነገራል። ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው?
አቶ ሰለሞን፡- ከዶላር ምንዛሪ ጋር በተያያዘ መንግሥት ሲወስን በርካታ ነገሮችን በማጥናት ነው።ነገር ግን ችግሮች የሉም ማለት አንችልም።ህግ ወጥ የምንዛሪ ሂደት የለም ማለት አይቻልም።ነገር ግን በየጊዜው ጥናት እየተጠና እና ፖሊሲዎች እየታዩ አስፈላጊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ።ስለዚህ በዚህ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችንም መንግስት በጥልቀት የሚከታተለው እና መፍትሄዎችን እያስመቀጠ የሚሄድበት ይሆናል።መፍትሄው እንደ ችግሩ ሁኔታ የሚታይ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በምስረታ ላይ የነበሩ እስካሁን ድረስ ወደ ሥራ ባልገቡ ባንኮች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ይኖራል?
አቶ ሰለሞን፡- ቀደም ሲል ባንኮች ሲመሰረቱ 500 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ መኖር አለበት።እኛም እነዚህን ባንኮች በአጭር ጊዜ ይህን የገንዘብ መጠን በማስቀመጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ ነው ፍላጎታችን፤ ስናግዝም ነበር። በአሁኑ ወቅ ወደ ምስረታ ልገቡትን ይህን እንዲያሟሉ ጊዜ ሰጥተናል።መስፈርቱን ያሟሉ ወደ ምስረታ እና ሥራ እየገቡ ነው።ይህን ማድረግ የማይችሉት ደግሞ ወደ ሌላ ‹‹ሽፍት›› እያደረጉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ባንኮች ስንት ናቸው?
አቶ ሰለሞን፡– በቁጥር ይታወቃሉ።ዝርዝሮቹ አስፈላጊ ከሆኑ የሚጠቀሱ ይሆናል።ዕድሉን አግኝተው ያልተጠቀሙ መኖራቸውን ግን መጥቀስ ጠቃሚ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መስፈርቱን ያላሟሉ ምን ይደረጋሉ?
አቶ ሰለሞን፡- መስፈርቱን ያላሟሉ ገንዘቡን እንዲመልሱ ነው የሚደረገው።ይህ ካልሆነ ደግሞ ከሌሎች ባንኮች ጋር እንዲዋሃዱ ይደረጋል ።ይህን መጠቀም የማይፈልጉ በሌላ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት የማድረግ መብት አላቸው።በአጠቃላይ ሲታይ ግን አማራጮችን መጠቀም ዕድል አላቸው።ይህም የተሻለ ዕድል ሊሰጣቸው የሚችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መስፈርቱን ያላሟሉ ነገር ግን በጥምረት ለመስራት የወሰኑ ተቋማት አሉ?
አቶ ሰለሞን፡- እስካሁን ድረስ ወደ እኛ መጥተው በዚህ ላይ የተነጋገርነው ነገር የለም።ከዚህም አለፍ ብሎ ስለ አደረጃጀታቸው አልነገሩንም።ነገር ግን እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩ እንዳሉ እናውቃለን።ባንኮቹ አስፈላጊ ንግግር ካደረጉ እና ሂደቱን ካሟሉ በኋላ ወደ እኛ የሚመጡ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፋይናንስ አካታችነትን በተመለከተም በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከባንክ የሚበደሩ ከግማሽ ሚሊዮን አልዘለሉም። ይህን ችግርለማቃለል ሥርዓቶች እየተዘጋጀ መሆኑ ተነግሮ ነበር። በአሁኑ ወቅት ይህ ከምን ደረሰ?
አቶ ሰለሞን፡- ተንቀሳቃሽ የዋስትና ሥርዓት ዘርግተናል። ከዚህ በፊት ተቀባይነት የሌላቸው የቁም እንስሳት እና እህልን ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ ነው። መጋዘን ውስጥ አስቀምጠን ደረሰኝ እንይዛለን።የመሬት አጠቃቀም ሰርተፍኬት የምንለውም አለ።ከዚህ አለፍ ብሎ በርካታ ነገሮች አሉ።ስለዚህ እነዚህን ሁሉ በመጠቀም የውሃ ፍሪጅ፣ ቴሌቪዥን እና የመሳሰሉት አስይዘን የምናበደርበት ሁኔታ ሁሉ ተፈጥሯል።
ከዚህም ባለፈ ኢንተሌክችዋል ፕሮፐርቲ ‹‹Ip›› እና ሃሳብ ጭምር ፋይናንስ የሚደረግብት ሥርዓት ተፈትሯል። ስለዚሀ ሃሳቡ ወይንም ሰርተፍኬት ያለው አካል እንደ ማስያዣ በማሳየት መበደር የሚቻልበትም ሁኔታም አለ ።ይህ ሂደትም ተጀምሮ 70ሺ የሚሆኑ ተመዝግበዋል። ተንቀሳቃሽ ዋስትናን አስይዘው የተበደሩ ሰባ የሚሆኑ አሉ፡፡
ሁለተኛው ከእውቀት ጋር፣ ኮንሱዩመር ፕሮቴክሽን ጋር ተያይዞ የሚሰራ ሥራ አለ።ለግብርና እና ለመሳሰሉት ከአምስት ከመቶ ያላነሰ ብድር እንዲሰጥ ብለን ያወጣናው መመሪያ አለ።ይህንንም ተግባራዊ እያደረግን ነው።አሁን ባለን መረጃ መሠረት አምስት ከመቶ በላይ ሄዷል፡፡ስለዚህ በዚህ ዘርፍ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አለ ብለን እናስባለን።
ክልሎችም እንደዚሁ በክልሎች የአካታችነት ካውንስል የተቋቋመ ሲሆን፤ በትኩረት እየተሰራበት ነው።በፋይናንስ አካታችነት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎችም የተሻለ ከሰሩት ጋር እንዴት መናበብ አለባቸው የሚለውም እየተሰራበት ነው።ይህን ሥራ የበለጠ ለማዘመንና እና ተደራሽ ለማድረግም ሥርዓት ተዘርግቶ በሰፊ እየተሰራበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎንም የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ መነገሩ ይታወሳል።ከምን ደረሰ?
አቶ ሰለሞን፡– አሁን እያጠናቀቅን ነው።አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው።ከረጂ ተቋማት ‹‹ዶነሮች›› አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው።በወራት ዕድሜ ለህዝ እንደራሴዎች ይቀርባል።ስለዚህ እየተፋጠነ ነው ማለት ይቻላል።በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት የሚደርሱ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ፈቃድ ይሰጣቸዋል ተበሎ ይታሰባል ።ከዚህ በላይ ከሄደ ከአቅም በላይ የመሆን ዕድል ሊኖረው ይችላል።ለመማርም ጊዜ አይኖረንም።ስለዚህ አዋጁ ከወጣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ባንኮች ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር ይኖራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን እንዳይውጧቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ እንዲሰሩ የተቀመጠ አሰራር እና አቅጣጫ አለ?
አቶ ሰለሞን፡– ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው አንድ አቅጣጫ አለ።እነዚህ ተቋማት ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉት ነው። ይህ ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ ነው፤ አሁንም እየተከታተልንበት ነው።ለዚህ የሚበጀተው ገንዘብ ቀላል አይሆንም ማለት ነው።ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በአግባቡ አለመጠቀም ይስተዋላል።ከአገር ወጣ ብለው በታሰበው ልክ አቅም ሳይገነቡ የሚመለሱ የፋይናንስ ተቋማት አሉ።
ይህን መከታተልና መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል።ለዚህ ደግሞ የቦርድ አመራር ሰራተኛው እና የየተቋማቱ አመራሮች ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።አሁን ቀድሞ እንደተለመደው መሄድ አይቻልም፡፡ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ። በጀት ተመድቦም በሰፊው መስራት አስፈላጊ ነው።የውጭ ምንዛሬ፣ ፋይናንስ ዘርፍ ተወዳዳሪነት፣ ሥራ ፈጠራ፣ ጤናማ ውድድር ማረጋገጥ ከመንግሥትና ከግል ዘርፎች የሚጠበቅ ነው፤ ለዚህም ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል።
ማን ከማን ጋር መሥራት አለበት፤ ማን ከማን ጋር ቢዋሃድ ያወጣል የሚለውን ከአሁኑ ማሰብ ይገባል።ከውጭ ከሚመጡ ተቋማትም ጋር እንዴት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ማሰብ አለባቸው።ካፒታል፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ እንዴት መጋራት እንደሚቻልም ባንኮቹ ከወዲሁ መሥራት አለባቸው፤ ባንኮቹም ይህን ስራ ጀምረዋል።ነገር ግን በዚህ ላይ አሁንም ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት።
ሌሎችን ሄደው መጎብኘት ፤ እንዴት እንደሚሰራ፣ ቦርዱ እንዴት እንደሚመራ፣ ማናጅመንቱ የሚያስተዳድርበት መንገድና ሥርዓት፣ የህግ ማዕቀፎችን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰው ኃይል አስተዳደር ጭምር ማወቅ ተገቢ ነው።ማንበብ እና መስማት ብቻ ሳይሆን በአካል ሄደው ማየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወደዚህ ሥራ ለመግባት የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን ማሳደግ አለባቸው።ወጪዎችን በመቆጠብ ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር ማሰብ ግድ ይላቸዋል።ለዚህም የሚያግዝ የሰው ኃይል ማሰልጠንና ማፍራት ይገባቸዋል።ቀደም ሲል የነደፉትን ስትራቴጂ ብቻ መጠቀም ሳይሆን መልሰው ማየትና መከለስ አለባቸው።
ከሚመጣው ሁኔታ አኳያ እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎች ታሳቢ የሚያደረጉ ጉዳዮችን በሙሉ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መልሰው ሊያዋቸው ይገባል።በአጠቃላይ መጪውን ጊዜ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረገ ሥራ እና አቅም መገንባት ይጠበቅባቸዋል።በሴክተሩ ላይ የተሻለ ልምድና እውቀት ያላቸውን ሰዎች ይዘው መሥራትም ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበርዎት ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ሰለሞን፡– እኔም አመሰግናለሁ።መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ግን አንድ ነገር ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።በእኛ ሀገር የፋይናንስ ቀውስ አልተፈጠረም፤ አላጋጠመም።በዚህ መልኩ መረዳት እና መገንዘብ ተገቢ ነው።ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም