በቀደሙት ዘመናት ሆነ ዛሬም ዓለምን ከምንም በላይ ዋጋ ካስከፈሉት ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ጽንፈኝነት እንደሆነ ይታመናል። በቀጣይም የሰው ልጅ ብሩህ ነገዎችን ሊያጨልም ይችላል ተብሎ የሚሰጋውም ይሄው የአስተሳሰብ መዛነፍ እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ የጋራ ግንዛቤ አለ።
ዥንጉርጉር በሆነው ዓለም ውስጥ ለአንድ አስተሳሰብ ግዝፈት ሰጥቶ እሱን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ የማየት፤ ከዚያም አልፎ አስተሳሰቡን በኃይልም ሆነ በተለያዩ መንገዶች በሕዝቦች ላይ ለመጫን የሚደረገው ይህ አይነቱ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ በተለይም ብዝሃነት በሰፈነበት ማህበረሰብ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።
ጽንፈኝነት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሰረት ይዞ ላለፉት መቶ ዓመታት ዓለማችንን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ባለፈ፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ላይ ለመጫን በስውርም ይሁን በግልፅ የተካሄዱ ጦርነቶችና ከዚሁ ጋር ተዳምረው የሄዱ ሴራዎችን መጥቀስ ይቻላል።
አፍሪካ ውስጥ የጸረ-ቅኝ ግዛት ትግል ስኬት እያስመዘገበ በመጣበት ማግስት ፤አፍሪካውያን በብዙ መስዋዕትነት የተጎናጸፉትን የፖለቲካ ነጻነት በአግባቡ ሳያጣጥሙ ፤በተለያዩ ጽንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ተጠልፈው ዛሬም ድረስ የግጭትና የሁከት ማዕከል ሆነዋል። የአህጉሪቱ የነጻነት አባቶች ተስፋ ያደረጓትን አፍሪካ እስከ ዛሬ መፍጠር ሳይቻልም ቀርቷል።
በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ያለው እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም አንድ ዓይነት ቋንቋ ተናጋሪ፤ የጋራ ባህል እና ሃይማኖት ባለቤት የሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ ሳይወድ በግድ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በፈጠሩት ግራ መጋባት ብሔራዊ ማንነቱን አጥቶ ተለያይቶ ለመኖር ተገድዷል። በዚህም ለተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ተዳርጓል።
በመካከለኛው ምስራቅ የብዙ ዘመናት ሀገረ መንግስት ታሪክ ባለቤት የሆኑትና ለዓለም አሁነኛ ስልጣኔ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው እንደ ሶሪያና ኢራቅ የመሳሰሉ ሀገራት ፤ ዓለም አቀፍ ሴራ በወለዳቸው ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ተጠልፈው የወንድማማችነት ፍቅራቸውን እና ብሔራዊ ክብራቸውን አጥተው፤ ሀገራዊ ህልውናቸው ዛሬም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ይገኛል።
”እኔ ካልኩት በቀር ሌላ ምርጫም አማራጭም የለም ፤ ያለው አማራጭ መቀበል ወይም አለመቀበል ነው ፤ከዚህ ውጪ ሊኖር የሚችለው አሸንፎ መውጣት ፤ ወይም ተሸንፎ ለአሸናፊው አስተሳሰብ መገዛት ነው ” በሚለው የተዛነፈ አስተሳሰብ ላይ መሰረቱን ያዋቀረው ጽንፈኝነት፤ በኛም ሀገር ትልቁ ሀገራዊ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል፣ እያስከፈለንም ያለው ዋጋ በቀላሉ ሊሰላ የሚችል አይደለም።
መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በውይይትና በድርድር በሚያምን ሕዝብ የተገነባችና ለሁሉም እኩል የሆነች ሀገር በትናንቱ መሰረት ላይ ለመገንባት የያዘውን አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ የአቅመ ቢስነት መገለጫ በማድረግ ሀገርና ህዝብን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ያስከፈሉ በጽንፈኛ አስተሳሰቦች የተነዱ የጥፋት ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለስደት ተዳርገዋል። የሕዝቦችንን ተቻችሎ በአንድነት የመኖር ባህልን ጨምሮ ሀገረ መንግስቱን ስጋት ላይ የጣሉ ብዛት ያላቸው ክስተቶች ተፈጥረዋል፤ ዛሬም ቢሆን ሀገራዊ የግጭትና የጉዳት ዜናዎቻችን ጽንፈኝነት የወለዳቸው ናቸው።
በሀገሪቱ ጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖች በየወቅቱ መልካቸውን እየቀያየሩ ሕዝባዊ አጀንዳዎችን ሳይቀር በመጥለፍ ሀገርን ሰላምና ዕረፍት በመንሳት ዜጎች በብዙ ተስፋ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለው የጀመሩትን ለውጥ እንደቀደሙት የለውጥ ተሞክሮዎች ለማምከን በግልጽ ፣ በአደባባይ ፣ በስውር የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ አስፈጻሚ እስከመሆን በደረሰ ባንዳነት እየተንቀሳቀሱ ነው።
በሀገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ ባልታየ መንገድ የሃይማኖት ስፍራዎችን እና ሃይማኖታዊ /መንፈሳዊ አጀንዳዎችን ለጽንፈኛ አስተሳሰባቸው ማስፈጸሚያ እስከ ማድረስ በደረሰ ሴራ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ኃይሎች በቃችሁ ለማለት ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው።
እንደ ሀገርና ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበሬታን ያተረፍንባቸውን ማህበራዊ እሴቶቻችንን እያቀለሉ፤ የሀገርን ሰላም ጨምሮ ሀገረ መንግሥቱን ስጋት ውስጥ በመጨመር፤ ጽንፈኛ አስተሳሰባቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን ሕሊና ቢስ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከእስካሁኑ የከፋ ዋጋ ሳያስከፍሉን ነቅተን በአግባቡ ልንታገላቸው ይገባል። ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነትና ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርም ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም