ከተመሰረተ ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያገኘው ነው። ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ በመባልም የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያም ተሸልሟል። በ2007 ዓ.ምህረትም እንዲሁ በአገር አቀፍ የላቀ ሳይንሳዊ ፈጠራ መስክ የወርቅ ኒሻንና ዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ድርጅት እኤአ የ2015 የምርጥ ሥራ ፈጠራ (ኢንተርፕረነር) ዘርፍ አሸናፊ እንዲሁም “የአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ ቴክኖሎጂ” ተሸላሚ ሆኗል።
አቶ ከበደ ላቀው የኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። አቶ ከበደ ኩባንያው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለውጤት እንደበቃ ይናገራሉ። ያን ሁሉ አልፎም በአሁኑ ወቅት ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መፍትሔ በመሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያበረከተ ይገኛል።
የኩባንያውን ምርት ወደ ገበያ ለማስገባት ብርቱ ትግል ጠይቋቸው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ከበደ፤ ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ከአስር ዓመታት በላይ እድሜ ማስቆጠሩንና የፈጠራ ሃሳቡን ለማስፋት፣ ተጨባጭ ለማድረግና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል ረዘም ያሉ የድካምና የሙከራ ዓመታትን ማሳለፉን ይናገራሉ።
ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደቻሉ የሚናገሩት አቶ ከበደ፤ የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆናቸው ችግሩን በቅርበት ያውቁታል። ለዚህ መፍትሔ መሆን ሲያስቡ ብልጭ ያለላቸው ሃሳብ የአርሶ አደሩን ችግር መቅረፍ የሚችለው የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ መሆኑን ተገነዘቡ። የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያውን ዕውን ለማድረግ ብልጭ ያለላቸውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የተለያዩ ሃሳቦችን አውጥተዋል፤ አውርደዋል። በዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችንም አድርገዋል።
ለምነቱን ያጣ መሬት ምርታማ መሆን የሚችለው ማዳበሪያ ሲጠቀም እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ ከበደ፤ ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ግብርናውን ሊጠቅም የሚችልና በዘርፉ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል ሃሳብ ይዞ የመጣ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ይህን ሃሳብ ዕውን ለማድረግ ጉዟቸው ረጅምና አድካሚ እንደነበር በማስታወስ በተለይም ከመደበኛው ትምህርታቸው በተጨማሪ ሰፊውን ጊዜያቸውን በጥናትና ምርምር በማሳለፍ በኦን ላይን የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲሁም ቴክኒካል ድጋፎችን ከሳይንቲስቶች የማግኘት ዕድል እንደነበራቸው አጫውተውናል።
በአሁኑ ወቅት ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ጠቃሚ ነው ያሉትን በአገር ውስጥ መመረት የቻለውን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ይዘው መቅረብ የቻሉት አቶ ከበደ፤ ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ የአፈር ማዳበሪያን ተክቶ የሚያገለግል እንደሆነና በአጠቃቀሙ ላይ ብቻ ልዩነት እንዳለው ነው የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት፤ ምርቱ አዲስ እንደመሆኑ ወደ ማህበረሰቡ ወስዶ ለማስተዋወቅና ለማለማመድ ፈተናው እጅግ ከባድ ነበር። ይሁንና ምርቱ ራሱን በራሱ ፈትኖ፣ አስተዋውቆና በረጅም ጊዜ ቆይታ ወደ ገበያ መግባት ችሏል።
‹‹መጀመሪያ ሃሳብ ብቻ የነበረው ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ሃሳቡ ተሸጦ ውጤት በማምጣት ህልሙን ዕውን ማድረግ የቻለ ምርት ነው›› የሚሉት አቶ ከበደ፤ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን ለማምረት በዋናነት በተፈጥሮ የሚገኙ የእንስሳትና የዕጽዋት ተረፈ ምርቶች ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ኩባንያው ማዳበሪያውን ለማምረት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ የሚገኙ ጥሬ ዕቃዎችን ነው የሚጠቀመው። ይህም የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቅ ባለመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማዳበሪያውን ለማምረት የሚጠቀሟቸው ቀመሮች /ፎርሙላዎች/ በሙሉ ፓተንትድ መሆናቸው ኢኮግሪንን ለየት ያደርገዋል። ኢኮግሪን ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የአእምራዊ መብት እውቅና የተሰጠው ብቸኛ ካምፓኒ ነው።
ተፈጥሯዊ ከሆኑ ግብዓቶች የሚመረተው ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው፣ ለአጠቃቀም ምቹ፣ የሆነና የአፈር ማዳበሪያን ተክቶ እንዲሁም በተጨማሪነት ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ነው። በሰሜን ሸዋ አካባቢ አሌልቱ ቶሎፋ በሚባል ቦታ የሚመረተው ማዳበሪያው፣ ቦታው የተመረጠበት ምክንያት አንደኛ ከአየር ንብረትና ከጥሬ ዕቃ ግብዓት ግኝት በተያያዘ በጥናት ላይ በመመስረት ነው። ማምረቻ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት መገኘቱ ግብዓቶችን ከሁሉም ክልሎች ለማምጣት እንዲሁም ምርቱን ለሁሉም ክልሎች በቀላሉ ለመላክ የሚያስችል አማካኝ ቦታ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው።
‹‹የምርት ሂደቱ ሁለት ነገሮችን ይፈልጋል›› የሚሉት አቶ ከበደ፤ አንደኛው ጥሬ ዕቃዎችን መሰብሰብና ለሚፈለገው አገልግሎት ግብዓት እንዲሆን የማዘጋጀት ሂደት መሆኑን ይጠቁማሉ። ሁለተኛው የተዘጋጁትን የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎች ወደ መጨረሻው ሂደት ማስገባትና የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት መሆኑን ጠቅሰው። በዚህ ሂደት የኢኮግሪን የመጨረሻው ውጤት ተፈጥሯዊ የሆነ ፈሳሽ ማዳበሪያን ማውጣት እንደሆነና ለዚህም የተለያዩ ዘመናዊና ማንዋል ማሽኖችን ይጠቀማል ብለዋል።
የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ እንዳሉት፤ ኢኮ ግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሁሉንም አይነት ንጥረ ነገሮች አሟልቶ የያዘ፣ ለሁሉም የሰብል አይነቶች ተስማሚ የሆነና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን የሚያሳድግ ነው። የሰብሉን በሽታ የመቋቋም አቅም የሚያጎለብት ሲሆን፣ በተለይም ከሰው ሰራሹ ማዳበሪያ የማይገኙትንና በአነስተኛ መጠን የሚፈለጉትን ንጥረ ነገሮች አካትቶ የያዘና በሶስት አይነት መንገዶች ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ነው።
ሰው ሰራሽ የሆነውንና ዩሪያና ዳፕ የተባለውን ማዳበሪያ የተጠቀመ አንድ አርሶ አደሩ ኢኮግሪንን በተጨማሪነት ቢጠቀም ምርትና ምርታማነቱን ከማሳደግ በተጨማሪ የመሬቱን ለምነት በመመለስ ለማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ በሂደት እየቀነሰ ይሄዳል። ከዚህ በተጨማሪም ሰብሉ በሽታ እንዲቋቋም በማድረግ ለኬሚካል የሚወጣን ወጪ ይቀንሳል። ይህም በአንድ ጊዜ ሁለትና ሶስት ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ ነው። ከወጪ አንጻርም እንዲሁ ኢኮግሪን በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ የሚመረት በመሆኑ ከመደበኛው ማዳበሪያ ይልቅ ዋጋው ተመጣጣኝ ነው። ኢኮግሪን ተፈጥሯዊ በመሆኑ ከጤና አንጻር የሚሰጠው ጠቀሜታ ሶስተኛው ጥቅም ሲሆን፤ ሰዎች ጤናው የተጠበቀ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የተለያዩ ሰብሎችን እንዲጠቀሙ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
ለማንኛውም እርሻ ስራ ኢኮግሪን እጅግ ተስማሚና ውጤታማ እንደሆነ ያነሱት አቶ ከበደ፤ በተለይም የአበባ እርሻዎች ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን በመጠቀም እጅግ ውጤታማ እንደሆኑ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት፤ ኢኮግሪን ወደ ውጭ የሚላኩ አበቦች መጠናቸውና ጥራታቸው እንዲጨምር አድርጓል። ብዙ ጊዜ የአበባ እርሻ መሬት መታከምን የሚፈልግ ቢሆንም ኢኮግሪን በሂደት መሬቱን እያከመላቸው ነው የሚሄደው። በመሆኑም አብዛኞቹ የአበባ እርሻዎች ኢኮግሪንን በመጠቀም ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሻስ ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ግብዓት በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ የተመረተ እንደመሆኑ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንደልብ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፤ አገሪቷ ለማዳበሪያ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ በሂደት ማስቀረት ያስችላል ያሉት አቶ ከበደ፤ በተለይም በጊዜ ሂደት የመሬትን ለምነት እየመለሰ የሚሄድ በመሆኑ የሚኖረው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው። በቀጣይም ምርቱን በማስፋት በመላው አገሪቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ፋብሪካው መሰረተ ልማቱ በተሟላለት አካባቢ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና በሚፈለገው ልክ መስፋት የሚችል መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ፤ የማምረት አቅሙም በዚሁ ልክ ማደግ እንደሚችል ነው የተናገሩት። በቀጣይም ምርቱን በየክልሎች በማምረት አርሶ አደሩ ተፈጥሯዊ የሆነውን ማዳበሪያ ከደጁ ማግኘት እንዲችል ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩና የማስፋፊያ ቦታ መጠየቃቸውን አስታውቀዋል።
ኢኮግሪን ዛሬ ላይ እንዲደርስ ቤተሰብ፣ ጓደኛና የተለያዩ ሰዎች ሚና እንዳላቸው ያመለከቱት አቶ ከበደ፤ በተለይም እርሳቸው የሕይወታቸውን ሰፊ ጊዜ እንደወሰደባቸው ይናገራሉ። ሃሳቡ በልጽጎ ፍሬያማ እንዲሆን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ በርካታ ሰዎች ድርሻ ያላቸው መሆኑንም ጠቅሰው፣ ሃሳቡ ብዙ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብና ዕውቀት፣ የፈሰሰበት ብዙዎች ዋጋ የከፈሉበት ድምር ውጤት መሆኑን ያብራራሉ።
ስኬት የሚለካው በተለያየ መንገድ እንደሆነ ያነሱት አቶ ከበደ፤ በሃሳብ ደረጃ የነበረውን ኢኮግሪን ዛሬ ላይ ፈሳሽ ማዳበሪያ የሚል ምርት እንዲኖር ማድረግ በራሱ አንድ ስኬት ነው ይላሉ። ይሁንና ኢኮግሪን በብርቱ ተፈትኖ ያለፈ ሃሳብ በመሆኑ እንዳይቀጭጭ የሁሉንም እገዛ ይፈልጋል ብለዋል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የአፈር ማዳበሪያ በየጊዜው የሚገጥመው እጥረትና የዋጋ ንረት አርሶ አደሩን ለምሬት የሚዳርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መፍትሔው ራስን መቻል ነው የሚሉት አቶ ከበደ፤ በተለይም አርሶ አደሩ ራሱን በማገዝ ከውጪ የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ በተፈጥሮ ማዳበሪያ የመተካትና ኢኮግሪንን የመሰሉ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ አምራቾችን በማስፋትና በማስተዋወቅ ሁሉም ሰው የመፍትሔው አካል ሊሆን እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
እሳቸው እንዳሉት፤ አገር በቀሉ ኢኮግሪን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች በተለይም ኦሮሚያ ክልል በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአማራ ክልል ምርቱ እየተለመደ መጥቷል። በቀጣይም ምርቱን ከመጠቀም ባለፈ አጠቃቀሙን ማስረዳትና ማስተዋወቅ ሰፊ ሥራን ይጠይቃል። በተለይም አርሶ አደሩ ምርቱን በውጤታማነት መጠቀም እንዲችል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል። ከዚህ ባለፈም ኢኮግሪን አገር በቀል ምርት እንደመሆኑ የአገር ሃብት እንደመሆኑ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውም ሰው የኔ ብሎ ሊቆምለት ይገባል።
ኢኮግሪን በአገር ውስጥ የሚመረት ከመሆኑም በላይ የጥሬ ዕቃ ውስንነት የሌለው በመሆኑ ምርቱን በተፈለገው መጠን ማምረት ይቻላል። የማሸጊያ ጥሬ ዕቃው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማሸጊያ ጀሪካን ለማምረት የሚስችለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ሌሎች ሁኔታዎች ምቹ ከሆኑ የማምረት አቅም ውስንነት አይኖረውም። ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያ ሥራ እየሠራ ሲሆን፣ ስራው ሲጠናቀቅም በወር እስከ ስድስት ሚሊዮን ሌትር የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል።
ኩባንያው በተለያየ መንገድ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ አንደኛ ጥሬ ዕቃውን በማቅረብ፣ ሁለተኛ በማምረት፣ ሶስተኛ ምርቱን በመሸጥ ሥራ ላይ ለተሰማሩ 300 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ በቀጥታ ከቀጠራቸው በተጨማሪ ምርቱ በስፋት በሚፈለግበት ወቅት ተጨማሪ የቀን ሠራተኞችን ይቀጥራል።
ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር እንደ ኩባንያ ችግር ፈቺ የሆነና አገር በቀል የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ መቻል እንዲሁም ከትርፍ በላይ አርሶ አደሩ ላይ ውጤት ለማምጣት እየተጋ ያለ ኩባንያ ስለመሆኑ የተናገሩት አቶ ከበደ፤ አቅም ለሌላቸው አርሶ አደሮች ምርቱን በነጻ በመስጠት እንደሚያስተዋውቅም ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ስልጠና ይሰጣል። አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች መንግሥት ለሚያደርገው ጥሪም ምላሽ ይሰጣል።
‹‹ስራ ፈጣሪዎች ሁልጊዜም ችግር ፈቺ ናቸው›› የሚሉት አቶ ከበደ፤ ማንኛውም ችግር የሚነሳው ከአካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም በትውልድ አካባቢያቸው ሰሜን ሸዋ አካባቢ ቤተሰባቸውን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን ችግር በማስተዋል እነሆ መፍትሔ በማለት ተፈጥሯዊ የሆነ ፈሳሽ ማዳበሪያ ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል። ኢኮግሪን፤ ለሁሉም አይነት የሰብል አይነቶች ማለትም ለቤት ውስጥ አበባ፣ ለልዩ ልዩ የአትክልት፣ እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎ ለመሳሰሉት ጥራጥሬ ሰብሎች፣ ለፍራፍሬና ለማንኛቸውም አይነት ችግኞች ልማት መጠቀም ይቻላል። ምርቱም ከአንድ ሌትር ጀምሮ እስከ 200 ሌትር ተዘጋጅቶ ይቀርባል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015