በቀደሙት ዘመናት ሆነ ዛሬም ዓለምን ከምንም በላይ ዋጋ ካስከፈሉት አንዱ እና ዋንኛው ጽንፈኝነት እንደሆነ ይታመናል። በቀጣይም የሰው ልጅ ብሩህ ነገዎችን ሊያጨልም ይችላል ተብሎ የሚሰጋውም ይኸው የአስተሳሰብ መዛነፍ እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ የጋራ እሳቤ አለ።
ዥንጉርጉር በሆነ ዓለም ውስጥ ለአንድ አስተሳሰብ ግዝፈት ሰጥቶ እሱን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ የማየት፤ ከዛም አልፎ አስተሳሰቡን በኃይል ሆነ በተለያዩ መንገዶች በሕዝቦች ላይ ለመጫን የሚደረገው ይህ አይነቱ አስተሳሰብ /ጽንፈኝነት /በተለይም ብዝሃነት በሰፈነበት ማህበረሰብ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል ።
ጽንፈኝነት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሰረት ይዞ ላለፉት መቶ ዓመታት ዓለማችንን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ባለፈ፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ላይ ለመጫን በስውርም ይሁን በግልፅ የተካሄዱ ጦርነቶችና ከዚሁ ጋር ተዳምረው የሄዱ ሴራዎችን መጥቀስ ይቻላል።
አፍሪካ ውስጥ ጸረ-ቅኝ ግዛት ትግል ስኬት እያስመዘገበ በመጣበት ማግስት ፤አፍሪካውያን በብዙ መስዋእትነት የተጎናጸፉትን የፖለቲካ ነጻነት በአግባቡ ሳያጣጥሙ ፤በተለያዩ ጽንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ተጠልፈው ዛሬም ድረስ የግጭትና የሁከት ማእከል ሆነዋል። የአህጉሪቱ የነጻነት አባቶች ተስፋ ያደረጓትን አፍሪካ እስከ ዛሬ መፍጠር ሳይቻል ቀርቷል።
በጎረቤት አገር ሶማሊያ ያለው እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም። አንድ አይነት ቋንቋ ተናጋሪ ፤ የጋራ ባህል እና ሀይማኖት ባለቤት የሆነው የሀገሪቱ ህዝብ ሳይወድ በግድ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በፈጠሩት ግራ መጋባት ብሄራዊ ማንነቱን አጥቶ ተለያይቶ ለመኖር ተገድዷል። በዚህም ለተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ተዳርጓል።
በመካከለኛው ምሥራቅ የብዙ ዘመናት አገረ መንግስት ታሪክ ባለቤት የሆኑ፤ ለዓለም አሁነኛ ስልጣኔ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው እንደ ሶሪያና ኢራቅ የመሳሰሉ አገራት ፤ ዓለም አቀፍ ሴራ በወለዳቸው ፅንፈኛ አስተሳሰቦች ተጠልፈው የወንድማማችነት ፍቅራቸውን እና ብሔራዊ ክብራቸውን አጥተው፤ አገራዊ ሕልውናቸው ዛሬም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ይገኛል።
”እኔ ካልኩት በቀር ሊላ ምርጫም አማራጭም የለም፤ ያለው አማራጭ መቀበል ወይም አለመቀበል ነው፤ ከዚህ ውጪ ሊኖር የሚችለው አሸንፎ መውጣት፤ ወይም ተሸንፎ ለአሸናፊው አስተሳሰቡ መገዛት ነው ” በሚለው የተዛነፈ አስተሳሰብ ላይ መሰረቱን ያዋቀረው ጽንፈኝነት፤ በኛም አገር ትልቁ አገራዊ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል። እያስከፈለንም ያለው ዋጋ በቀላሉ ሊሰላ የሚችል አይደለም።
መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በውይይትና በድርድር ላይ የተመሰረተች ለሁሉም እኩል የሆነች አገር በትናንቱ መሰረት ላይ ለመገንባት የያዘውን አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ የአቅመ ቢስነት መገለጫ በማድረግ አገርና ሕዝብን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ያስከፈሉ በጽንፈኛ አስተሳሰቦች የተነዱ የጥፋት ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለስደት ተዳርገዋል። የሕዝቦችን ተቻችሎ በአንድነት የመኖር ባህልን ጨምሮ አገረ መንግስቱን ስጋት ላይ የጣሉ ብዛት ያላቸው ክስተቶች ተፈጥረዋል፤ ዛሬም ቢሆን አገራዊ የእለት ተእለት ዜናዎቻችን ጽንፈኝነት እንደአስተሳሰብ የወለዳቸው ፈተናዎች መገለጫ ናቸው።
በአገሪቱ ጽንፈኝ ግለሰቦችና ቡድኖች በየወቅቱ መልካቸውን እየቀያየሩ ሕዝባዊ አጀንዳዎችን ሳይቀር በመጥለፍ አገርን ሰላምና እረፍት በመንሳት ዜጎች በብዙ ተስፋ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለው የጀመሩትን ለውጥ እንደቀደሙት የለውጥ ተሞክሮዎች ለማምከን
በግልጽ ፣ በአደባባይ ፣ በስውር የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልእኮ አስፈጻሚ እስከመሆን በደረሰ ባንዳነት እየተንቀሳቀሱ ነው።
እነዚህ ኃይሎች በአገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ ባልታየ መንገድ የሃይማኖት ስፍራዎችን እና ሃይማኖታዊ /መንፈሳዊ አጀንዳዎችን ለጽንፈኛ አስተሳሰባቸው ማስፈጸሚያ እስከ ማድረስ በደረሰ መታወር ውስጥ ይገኛሉ። የዜጎችን ሰላም ከዛም አልፎ ህይወት በመቅጠፍ ይህንንም የፕሮፓጋንዳ አቅም መግዣ ለማድረግ በስፋት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።
ለዚህም ከአገር ውጪ ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ በአስተሳሰቡ የተጠለፉ ግለሰቦችን በጋዜጠኝነት ፣ በማህበራዊ አንቂነት … ወዘተ ስም በማሰለፍ አስተሳሰቡን በሕዝቦች ውስጥ ለማስረጽ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። እንደ አገርና ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበሬታን ያተረፍንባቸውን ማህበራዊ እሴቶቻችንን የሚገዳደሩ ተግባራትን እለት እለት በተናበበ መንገድ ሲፈጽሙም ማየትና መስማት የተለመደ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ሕዝብን በሕዝብ ላይ ሆነ ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት ብዙ የሀሰት ትርክቶችን ከመፍጠር ጀምሮ የራሳቸውን የጥፋት ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ በማስረግ የሕዝቦችን ሰላም ከመፈታተን አልፈው አገረ መንግሥቱን ስጋት ውስጥ ለመጨመር ተንቀሳቅሰዋል።
ጽንፈኛ አስተሳሰባቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን ሕሊና ቢስ በሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እነዚህ ኃይሎች በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት እንደአገር ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን እንድንከፍል አስገድደውናል። እነዚህን ኃይሎች ከእስካሁኑ የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍሉን አሁን ላይ በቃችሁ ልንላቸው ይገባል። ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነትና ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል።
ይህን ማድረግ ባለመቻላችን ለሚፈጠር ማህበረሰባዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ሆነ የሞራል ውድቀት ማንም ከታሪክ ሆነ ከህሊና ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም።
ከመርደቂዮስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015