በማደግ ላይ ያሉ አገራት የማደግ ፍላጎታቸውን በሚፈታተኑ መልከ ብዙ ፈተናዎች ውስጥ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። አገራቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከሰቱ ችግሮች እና ችግሮቹ በሚፈጥሯቸው ጫናዎች ሕዝቦቻቸው ብዙ ዋጋ ለመክፈል እየተገደዱ ነው። ይህም ተስፋ ባደረጓቸው ነገዎቻቸው ላይ ጥላ እያጠላ ይገኛል።
በአንድ በኩል አገራቱ የተሸከሙት እዳና እዳውን ለመክፈል ያለባቸው ከፍያለ ጫና፤ በሌላ በኩል በየወቅቱ የሚከሰቱ ዓለም አቀፍ ችግሮች “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” እየሆኑባቸው ሕዝቦቻቸው የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት የሚችሉበትን አቅም እያጡ ነው። ይህ ደግሞ አሁን አሁን ከፍ ባለ የኖሮ ውድነት እየተገለጠ ይገኛል።
አገራቱ ከትናንት የወረሷቸው የእርስ በርስ ግጭቶችና ግጭቶቹ እየፈጠሩት ያለው ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ፣ እነዚህን ቀውሶች በግልጽም ይሁን በስውር የሚያባብሱ ማቆሚያ ያጡ ጣልቃ ገብነቶች የእነዚህን አገራት ሕዝቦች አድጎ የመገኘት ህልም እየተፈታተኑት ነው። በአጠቃላይ ወደ ህልማቸው የሚያደርጉትን ጉዞ ጎታች ተግዳሮት ሆኗል።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እነዚህ አገራት ችግሮቻቸውን አሸንፈው እንዲወጡ የሚያስችላቸውን የፋይናንስም ሆነ ሌሎች ድጋፎች በሚፈልጉት መጠንና ጊዜ ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ለመስጠት አለመቻሉ ፣ አብዛኞቹ ቃል የተገቡ ርዳታዎች በወቅቱ አለመለቀቃቸው ፣ ከዚያ ይልቅ የተለያዩ የማስገደጃ ጫናዎች ይዘው የመምጣታቸው እውነታ አገራቱ እነሱን ታሳቢ አድርገው በሚጀምሯቸው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የጎላ ክፍተት እየፈጠረ ነው።
እነዚህ አገራት የጀመሯቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ለማስፈጸም የሚያስፈልጋቸውን ከፍያለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት፤ ቀደም ሲል የነበረባቸውን እዳ የመክፈል አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ መሆናቸው፤ በብዙ ልፋት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ መልሰው ለእዳ ማቀለያ በመክፈል እየሄዱበት ያለው መንገድ “ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ” ሆኖባቸው፤ የድካማቸውን ያህል መራመድ የሚችሉበትን አቅም መግዛት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ዛሬ ላይ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ትልቁ ስጋት እየሆነ የመጣውን የአካባቢ የአየር ብክለት ለመከላከል የሚያደርጓቸው የተለያዩ ጥረቶች፤ ስጋቱን መከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠር የሚችሉ ቢሆኑምለስራው የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ ከመደገፍ አኳያ ያለው ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ በቀጣይ ለአገራቱ ህዝቦች የከፋ ስጋት ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው።
ችግሩን በመፍጠር ሂደት ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ተሳትፎ የሌላቸው እነዚህ አገራት ፤ ችግሩ እየፈጠረባቸው ካለው አሁናዊም ሆነ በቀጣይ ሊያስከትልባቸው የሚችለው ከፍያለ ተጽዕኖ አሁን እየተፈታተኗቸው ካሉ መልከ ብዙ ችግሮች ጋር ተዳምረው የአገራቱን ሕዝቦች ሕይወት የከፋ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይታመናል። ይህም በብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮች መደመጥ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
እነዚህን መልከ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ነገዎች ብሩህ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ «የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የባለብዙ ወገን ልማት ባንኮችን ሞዴል ማሻሻል» በሚል ርዕስ በፈረንሳይ ፓሪስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ከዚህ በፊት ከእነዚህ አገራት ጋር የገቧቸውን ስምምነቶች መተግበር ይጠበቅበታል::”
አገራቱ ለልማታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሀብት ከተለያዩ ጫናዎች ነጻ በሆነ መንገድ ፤ የኮንሴሽናል ፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ የሚፈታበትን መንገድ ማስፋት ፣ ወደ አረንጓዴ ልማት ሽግግር የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ፣ የዕዳ ቀውስን ማቆም ትኩረት ተሰጥቷቸው ከፍባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊተገበሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015