የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ፤ ረጅም የጋራ ታሪክ የሚጋሩ፤ ተመሳሳይ ባህልና ኃይማኖት ያላቸው ናቸው።የትግራይ እና የአማራ ሕዝብ ትስስር ከጉርብትና ያለፈ በደምና በስጋ የተሳሰሩ፤ ተመሳሳይም ስነ ልቦናን የሚጋሩና ኢትዮጵያን አጽንተው ያቆዩ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው፡፡
የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የአገሪቱ ሉአላዊነት ለመዳፈር የሚመጡ ባዕዳን ወረራዎችን በጋራ መክቶ በማስቀረትና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እንዳይደፈር የደምና የአጥንት መስዋዕትነት የከፈሉ ሕዝቦች ናቸው።በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ስልጣንና ስልጣኔ አመጣጥ ሂደት ላይም ተመጋጋቢ፣ ተወራራሽ ፣ እንዲሁም ተዛማጅነት ያላቸው አካሔድ የነበራቸው ሕዝቦች ከመሆናቸውም ባሻገር ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የኖሩም ናቸው፡፡
ሁለቱ ሕዝቦች በተጎራባች አካባቢያዊ አቀማመጥ የሚኖሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ኢትዮጵያዊ በመሆናቸውም ተመሳሳይ ባህል፤ ልማድና ወግ የሚጋሩም ናቸው።አብዛኛው ሕዝብም የሚተዳደረው በግብርና በመሆኑም ኢኮኖሚያዊ መሰረታቸውም ተመሳሳይ ነው፡፡
በተለያዩ የውሸት ትርክቶች እነዚህን ሕዝቦች ለማጋጨትና ለመለያየት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል።በተለይም ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ምክንያት ሁለቱ ሕዝቦችም እጅግ ውድ የሚባል ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።በጦርነቱ ምክንያትም በሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ተከስቷል።ይህ ደግሞ ከሁለቱ ሕዝቦች አልፎ እንደ አገር ያስከፈለው ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ሆኖም መንግስት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶርያ በተደረገው ስምምነት አማካኝት ተቋጭቶ በምትኩ ሰላም ሰፍኗል።ይህንኑም ተከትሎ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራ የልዑካን ቡድን በመቀሌ በመገኘት ጉብኝት አካሂዷል።በተመሳሳይም በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ ልዑክ በባህርዳር ከተማ በመገኘት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርጓል፡፡
ይህ በጎ ጅምር ነው።የሁለቱ ርዕሰ መስተዳድሮች ጉብኝት ለጊዜው ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት የሚያድስና ፍጹም ሰላማዊ ወደ ሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም እንዲያድግ በር የሚከፍት ነው።ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላም እንደአገር የሰፈነው ሰላምም የሁለቱን ክልል ሕዝቦች የበለጠ የሚያቀራርብና ዘመናት የተሻገረውን አብሮነት የሚያድስ ነው።የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ዘርፈ ብዙ መስተጋብሮች ያሉትና ለዘመናት ተሳስሮ የኖረና ወደፊትም አብሮ የመኖር እጣ ፈንታ ያለው በመሆኑ የሁለቱ መስተዳድሮች ጉብኝት ወዳጅነቱ ዘላቂ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የአማራም ሆነ የትግራይ ሕዝቦች የጦርነት አስከፊነት በሚገባ የሚገነዘቡ ሕዝቦች ናቸው። በታሪክ በተደጋጋሚ ጦርነት ባስተናገደው የሰሜኑ ክፍል ሁለቱም ሕዝቦች የሚኖሩ እንደመሆኑ ከጦርነት የሚገኝ አንዳች ትርፍ እንደሌለ ለሁለቱም ሕዝቦች ነጋሪ አያስፈልጋቸውም።ከጦርነት ሞት፤ አካል መጉደል፤ መፈናቀልና ስደት እንዲሁም መታረዝ እንጂ የሚገኝ ጥቅም እንደሌለ ሁለቱም ሕዝቦች በውል ያውቁታል፡፡
ሁለቱን ሕዝቦች ወደ ግጭት ሊያስገባ የሚችል አንዳችም ምክንያት አይኖርም።የሚነሱ ጥያቄዎች ሲኖሩም የአገሪቱን ህጎች ተከትለው የሚፈቱ በመሆናቸው በሁለቱም ክልል የሚገኙ አመራሮች በሳልና አንድነትን ለሚያጸና ተግባር ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን ሁለቱ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸው የቆየውን የርስ በዕርስ ግንኙት ማጠናከር፤ የንግድ ልውውጥን ማጠናከር፤ ከፋፋዮችን ለመመከት በጋራ መቆም ብቻ ነው፡፡
የተፈጠሩም ሆነ ወደፊት ለሚፈጠሩ ችግሮች በምንም አይነት መልኩ ከትግራይና አማራ ሕዝቦች አቅም በላይ አይደሉም። በአጠቃላይ የትግራይ እና የአማራ ሕዝቦች በጋራና በሰላም መኖር ለኢትዮጵያ ቀጣይ አንድነትና ህልውና የሚኖረው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት እስከ አሁን ከነበረው በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015