የስምንት አመቷ ሙሪዳ ሁሴን በተለምዶ አሜሪካ ጊቢ በሚባለው አካባቢ ነዋሪ ናት። ከአካል ጉዳት ጋር ነው የተወለደችው ይህች ታዳጊ ከወገቧ በታች ያለው የአካል ክፍሏ አይንቀሳቀስም፡፡ መቆምም ሆነ መቀመጥ አትችልም፡፡ ራሷን ችላ ለመፀዳዳት ስለምትቸገር ዳይፐር ለመጠቀም ትገደዳለች።
እንዲህ አይነት የህፃናት የአካል ጉዳት በተለይም ለእናቶች ፈታኝ ነው። በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙት የሙሪዳ ወላጅ እናትን ወይዘሮ ፈትያ ከማል ይህ ፈተና ቀላል አይደለም። ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ እንደሚባለው እንኳን ያልሆነላቸው እኚህ እናት በልጃቸው አካል ጉዳት ምክንያት አሁን ላይ ሥራ ፈተው ለመቀመጥ ተገደዋል። ወይዘሮ ፈትያ ቀደም ሲል በየሰው ቤት እየዞሩ ልብስ በማጠብ፣ እንጀራ በመጋገር፣ በርበሬና ሽሮ በማዘጋጀት ኑሯቸውን ይገፉ ነበር። አሁን ግን ይህንንም ተሯሩጠው ለመሥራት ተቸግረዋል። አለኝ የሚሉት ኑሮ መደጎሚያ ገቢም የላቸውም።
ወይዘሮ ፈትያ አካል ጉዳተኛ ታዳጊ ልጃቸው መቀመጥ ስለማትችል አዝለዋት እንደሚውሉ ይናገራሉ። ታዳጊዋ ሙሪዳ እንደማንኛውም ልጅ መጫወት ትፈልጋለች፣ ትምህርት ቤት መሄድም ትሻለች፡፡ ግን የአካል ጉዳቷ እንደ እኩዮቿ ተሯሩጦ መጫወት ስለማይፈቅድላት ልጆች ሲጫወቱ ማየትን ትመርጣለች። ነገር ግን ራሷን ችላ መቀመጥ ስለማትችል እናት ሁልጊዜ ወደ ውጭ አውጥተው መደገፍ ወይም አዝለው መቆም ይኖርባቸዋል።
“ልጄ መጫወት ባትችልም ልጆች ሲጫወቱ ማየት ትፈልጋለች፡፡ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈውም አዝያት በመቆም ጨዋታቸውን እንድታይ በማድረግ ነው” የሚሉት እናት ሁሌም ይህን ካላደረጉ አካል ጉዳተኛ ልጃቸው እንደምታስቸግራቸው ይናገራሉ። ይሄን ችግራቸውን ግን በቅርብ የሚያውቁ ጎረቤቶች እንጂ ሌሎች ሰዎች እንደማይረዷቸውም ያስረዳሉ። በዚህም ዘወትር የሚመለከቷቸው ሰዎች፣ አላፊ አግዳሚው ሳይቀር ሥራ ፈት አድርገው እንደሚቆጥሯቸው ነው የሚናገሩት።
የእኚህን እናት ችግር ቀርበው ያልተረዱ አንዳንዶች ልጃቸው አካል ጉዳተኛ መሆኗን ሲረዱ ከጀርባቸው ላይ አውርደው ለምን አስቀምጠው ጨዋታ እንድታይ እንደማያደርጓት ይጠይቃሉ። ይህ ግን የሚሆን አይደለም፣ ወይዘሮ ፈትያ ልጃቸውን አዝለው ረጅም ሰዓት ማሳለፍ አለባቸው። በድካም የዛለ ወገባቸው ይንቀጠቀጣል፡፡ በመቆም ብዛት እግራቸው ያብጣል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮም ይህ ከኩላሊት ጋር የተያያዘ መዘዝ አምጥቶባቸዋል።
ያም ሆኖ ልጃቸውን አዝለው በመቆም የዕድሜ እኩዮቿን ጨዋታ ስትመለከት ማየት እናት እጅግ የሚደሰቱበት ነገር ነው። ታዳጊዋ ሙሪዳም እናት በሚከፍሉት ዋጋ ሰውነቷ ባይታዘዝላትም እንደታዘለች በደስታ ለመዝለል ትሞክራለች፣ በሳቅ ትፈነድቃለች።ለወይዘሮ ፈትያም ይህ የልጃቸው ደስታ ትልቅ የህሊና እርካታና ደስታ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። ይህ የወይዘሮ ፈትያና የልጃቸው የየዕለት ኑሮ ውጣ ውረድ ነው። የእናትና ልጅ የዕለት ጉርስ የሚሸፈነውም ይሄን ችግራቸውን ቀርበው በሚያውቁ በጎ ሰዎች መሆኑንም እናት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፈትያ በቅርቡ ለእሳቸውና ለአካል ጉዳተኛ ልጃቸው ቀጣይ ሕይወት ተስፋ የሚሆን ነገር አግኝተዋል፡፡ ይህ ተስፋ ‹‹እናት ዙበይዳ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ የሚገኙ እናቶችን የሚደግፍ ነው፡፡ በቅርቡም ወደ እነ ወይዘሮ ፈትያ ጎራ ብሎ ችግራቸውን በማጤን ዘላቂ የሆነ እፎይታን ሊቸራቸው ቃል ገብቷል፡፡
ድርጅቱ ለአካል ጉዳተኛዋ ሙሪዳ የሚሆን ዊልቸር እንደሚለግስ ገልጿል፡፡ ዊልቸሩን በ11 ሺህ ብር እያሰራላት እንደሆነም ለእናት አሳውቋቸዋል። “ልጇ ዊልቸሩ ተሰርቶ ሲመጣላት ራሷን ችላ መቀመጥ ትችላለች፡፡ ልጆች ሲጫወቱም እዚሁ ላይ ሆኖ የማየት ዕድል ታገኛለች” ሲሉም ወይዘሮ ፈትያ ተስፋቸውን ይናገራሉ።
ይህም እናት የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን የሚያስችላቸውን ሥራ ለመሥራት ጊዜ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ ወይዘሮ ፈትያ የሥራ ማግኘት እንዳያሳስባቸው የእናት ዙባይዳ በጎ አድራጎት ድርጅት እገዛ ሊያደርግላቸው ቃል ገብቷል፡፡ ሥራውም እናት ቤታቸው ደጃፍ ሳይርቁ የሚያከናውኑት ነው አነስተኛ ጉሊት ነው። ይህ ደግሞ ከአካል ጉዳተኛ ልጃቸው ሳይርቁ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እድል እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች የአድቮኬሲ እና መብት ጥበቃ ዴስክ ኃላፊንም አቶ ሲሳይ ጥላሁን፣ በአገራችን በእንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ያሉ እናቶች ቁጥራቸው በርካታ መሆኑን ይናገራሉ። እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በተመሳሳይ ሕይወት ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ እናቶች በመዲናችን የተወሰኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው፡፡ አሜሪካ ግቢ የደሀ ደሀ የሚባሉ ወይም ከደህነት ወለል በታች ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሚኖሩበት አካባቢ አንዱ ነው፡፡ በዚህም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የዕለት ጉርስ እስከማጣት የደረሰ አስከፊ ችግር የተጋፈጡ በርካታ ናቸው። የአካል ጉዳተኛ ልጆች ያላቸው እናቶች የሚደርስባቸው ስቃይ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡
መንግስት እንዲህ ዓይነቱን የከፋ ችግር ለመቀነስ የደህነት ስትራቴጂ ከመንደፍ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፣ ይሄን ኃላፊነት የወሰደው ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑን ያስረዳሉ። ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንደ ወይዘሮ ፈትያ ያሉ እናቶችን በአነስተኛ የገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲሰማሩ በማድረግ ይደግፋል፡፡ ከእናቶች በተጨማሪ አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውንም በዳይሬክቶሬቱ በኩል የዊልቸርና ሌሎች ለእንቅስቃሴ የሚረዷቸውን ቁሳቁሶች የሚሰጥበት አሰራር ተዘርግቷል። አሰራሩ ተግባራዊ የሚሆነውም ደረጃውን ጠብቆ ነው፡፡
ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር ሁሉንም አካል ጉዳተኞችና እናቶች ተደራሽ ማድረግ አይቻልም፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በሕብረተሰቡ ተሳትፎ መታገዝ እንዳለበት አቶ ሲሳይ ያነሳሉ። እነዚህ አካላት የደሀ ደሀ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ ማድረግ እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡ “በአዲስ አበባ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታየውን የከፋ ድህነት መቅረፍ ለነገ የማይባል ነው” የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ በሌላው ዓለም ሀብታሞች የተረፋቸውን ምግብና ውሃ ሳይቀር ዝቅተኛው ማህበረሰብ እንዲጠቀም የሚያደርጉበት አሰራር በእኛም አገር መለመድ እንዳለበት አብራርተዋል። አክለውም ችግሩ በአንዴ ስለማይቀረፍም በእንዲህ ዓይነት አማራጮች ድህነትን በማቃለል ተደራራቢ ችግር የሚሆነውን የአካል ጉዳተኝነት ፈተና መቋቋም ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015