ትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እቅድ ይዟል። በዚህ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት መካከልም ፤ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል። ከተቋቋመ ሰባ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት እንደሚያስችል የትምህርት ሚኒስትር በተደጋጋሚ እየገለጸም ይገኛል። የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ከሚታወቀው በተሻለና በተለየ መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲመጣ ወሳኝነት እንዳለውም ይታሰባል።
ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮአቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ተወዳዳሪና ብቁ ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን ለማፍራትና ጥራት ያለው የምርምር ውጤት እንዲሰሩ በማድረጉ በኩልም ራስ ገዝነታቸው ይጠቅማቸዋል ተብሏል።
ዩኒቨርሲቲዎች ችግር የሚያባብሱ ሳይሆን በሰላም መኖርን፣ ዴሞክራሲን፣ የሚሰብኩ ተቋማት እንዲሆኑ በተለይ አገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ማወቅ፣ ለችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨት፣ የዓለምንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ቀጣይ አቅጣጫን ለማመላከትም ነጻነትና ራስ ገዝነት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።
ይህንን ለማረጋገጥ በመንግሥት ቁርጠኝነት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት እንዲሸጋገሩ በተወሰነው መሰረት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይታወቃል። በዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ የማድረግ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ እና አጽድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አስተላልፏል።
እኛም ራስ ገዝነት ለዩኒቨርሲቲዎች ብሎም ለማህበረሰቡ አልፎም ለተማሪው እንደ አገርም በትምህርት ጥራቱ ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው ለውጥ በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆኑት ከዶክተር ሰለሞን አብርሃ ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ይሆናሉ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ሰለሞን፦ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ወይም በሌላ ስሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነት ማለት ተቋማቱ የአስተዳደራዊ፤ የአካዳሚክ፤ የምርመር፤ የሰው ሃብት አስተዳደር፤ የፋይናንስ ጉዳዮቻቸውን ነጻነት ኖሯቸው በዛው ልክ ደግሞ ተጠያቂነትም እንዳለባቸው አውቀው የሚተገብሩበት ሥርዓት ነው፡፡
አንድ ተቋም ተቋማዊ ነጻነት ተጎናጽፏል ወይም ራስ ገዝ ሆኗል ብለን ስናስብ በዋናነት ከአካዳሚና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ነጻነት ኖሯቸው ይህንንም ከተጠያቂነት ጋር በመያዝ የተሻለና ውጤታማ ስራን እንዲሰሩ የማስቻል ጅምር ነው፡፡
አስተዳደራዊ ነጻነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የራሳቸውን አደረጃጀት እና መዋቅር የመዘርጋት ስልጣን ይሰጣቸዋል፤ በዚህ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮቻቸውን ጨምሮ በመዋቅራቸው ውስጥ የሚያስፈልጓቸውን የአመራር እና የአስተዳደር አካላትን በራሳቸው መመደብ እንደሚችሉ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡
በሌላ በኩልም ፋይናንሻል አቅማቸውን በጀታቸውን በአግባቡ የመጠቀም እድል ይፈጥርላቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችን የመሻር፤ የመሾም፤ ሀብት የመፍጠር ፤የውስጥ መመሪያዎችንና አስተዳደራዊ ስርዓቶችን የመዘርጋት ነጻነት ይኖራቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ሀብታቸውን በአግባቡ ከመጠቀም ብሎም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች የመቅጠርና ሥርዓቱን እንዲሁም ደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የመወሰን አቅም ይፈጥርላቸዋል። በተለይም ለዩኒቨርሲቲው ብሎም ለአገር ይጠቅማል፡፡ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ይሰራል ብለው ያመኑበትን ባለሙያ በድርደር እስከ መቅጠር ድረስ የሚደርስ ነጻነት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡
ከተማሪዎች ቅበላ ጀምሮ አስመርቆ እስከማውጣት ድረስ ያለው ሂደት ጤናማ ብሎም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ተማሪዎችን አወዳድሮ እስከመቀበል ድረስ ያለውን ውሳኔ የማንንም ድጋፍ ሳይጠይቁ የመወሰን አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡
ተቋማት ራስ ገዝ በሆኑ ቁጥር ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ምን ዓይነት የትምህርት ሥርዓት መከተል እንዳለባቸው ገበያውም በሚፈልገው ልክ የመወሰን ከዛም አልፎ የሚያስትምሩበትን ቋንቋም እስከ መወሰን ድረስ እድል ይኖራቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በቦርድ ይተዳደሩ ነበር፡፡ በዛም አንዳንድ ጉዳዮቻቸውን በቦርድ የማስወሰን አካሄድም እንደሚከተሉ ይታወቃል ፤ አሁን ራስ ገዝ መሆናቸው ምን ይጨምርላቸዋል?
ዶክተር ሰለሞን፦ልዩነቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመንግስት ተቋማት በመሆናቸው በጀታቸውንም ሙሉ በሙሉ የሚያገኙት ከመንግስት ነው፤ በቦርድ ይተዳደሩ እንጂ የራሳቸው የሆነ የፋይናንስ የሰው ሃብት የግዢ አስተዳደር አልነበራቸውም ። የሲቪል ሰርቪስ የሚወጣ የሰው ሃብት አስተዳደር ነው የሚከተሉት። በገንዘብ ሚኒስቴር የሚወጣ የግዢና የፋይናንስ ሥርዓትን ነው ሲከተሉ የኖሩት። ይህ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ብሎም ተቋማቱ ካላቸው ልዩ ባህርይ አንጻር ምቹ ሆኖ አልተገኘም። ምቹ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ተቋማቱ ለቆሙለት የትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ስራ እንቅፋት ፈጥሯል። በመሆኑም ተቋማቱ ተቋማዊ ነጻነትን ተጎናጸፉ ስንል የራሳቸው የሆነ የፋይናንስ የግዢ ሥርዓት እንዲኖራቸው እድል ሰጥቷል ማለት ነው። አዋጁም ጸድቋል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ወደራስ ገዝ የሚመጡት ተቋማት የራሳቸው የሆነ በቦርድ የሚጸድቅ የፋይናንስ የግዢ የሰው ሃብት አስተዳደር ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ እንደ ተቋም ትልቅ ነጻነትን የሚፈጥር ነው።
ተቋማቱ ተማሪን አስተምረው ያስመርቃሉ፤ የምርምር ስራን ይሰራሉ፤ ብዙ ዓይነት ውስብሰብ ስራዎችን በኃላፊነት ይሰራሉ፤ ከዚህ አንጻር አሁን ያለው የግዢ የፋይናንስ ስርዓት ውጤታማ እንዲሆኑ አላስቻላቸውም። በመሆኑም ተቋማቱ ራስ ገዝ ሲሆኑ ብዙ ነገሮች ስለሚቀሉላቸው በዛው ልክ ውጤታማም የሚሆኑበት እድል የሰፋ ይሆናል።
በጠቅላላው ከዚህ በኋላም በቦርድ የሚመሩ ቢሆኑም ቦርዱ ትልቅ ስልጣንና ኃላፊነት የሚሰጠው አቅምና ብቃት ያላቸውን ሰዎች የሚያካትት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ተቋማት ራስ ገዝ በመሆናቸው ብዙ ነገሮቻቸውን በራሳቸው የመወሰን እድልን አግኝተዋል ፤ ነገር ግን ከፍ ያለ ነጻነት ለብልሹ አሰራር ብሎም በአገር ደረጃ ወጥ የሆነ አካሄድ እንዳይኖርስ አያደርግም በዚህ ላይ ምን ታስቦበታል ?
ዶክተር ሰለሞን፦ ተቋማቱ አሁንም የመንግስት ተቋማት ናቸው። የመንግስት ዩኒቨርሲቲ መሆናቸው ይቀጥላል። በዚህም የመንግስት ተጠያቂነቱም ይቀጥላል ማለት ነው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ራስ ገዝ የሚለው ሥርዓት ነፃነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚሰጥ እንጂ ነጻነትን ብቻ ሰጥቶ ልቅ የሚያደርግ አይደለም፡፡
በመሆኑም አደረጃጀቱ በግልጽ ይቀመጣል፤ ሕጎችና ሥርዓቶች ይኖራሉ፤ በእነዚህ ሕግና ሥርዓቶች የሚመራ እንጂ የግል ተቋም አይደለም፤ ቀጣይም የሕዝብ ተቋም ናቸው፤ ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል። በመሆኑም ለእያንዳንዱ ውሳኔ ተጠያቂነት እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ግዢ በቦርድ ጸድቆ ይፈጸማል ማለት ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ልቅ ይተዋል ማለት አይደለም። ሌላውም እንደዛው ነው። በመሆኑም ነጻነቱ በዛ ብሎ መሰጠቱ ለአሰራር እንዲያመች፤ ሰበባ ሰበቦች እንዳይበዙ የሚያደርግ እና የምንፈልገውም የትምህርት ሥርዓት አሳሪ በሆኑ የተንዛዙ አሰራሮች እንዳይጠለፍ ለማድረግ እንጂ አሰራሮች ልቅ እንዲወጡ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሆነው የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩ ከሆነ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምን ይለያሉ?
ዶክተር ሰለሞን ፦ በተቋማቱ ላይ የሚደረገው የመንግስት ኢንቨስትመንት ይቀጥላል። ግን ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከተልኳቸው ጋር በተያያዘ ሀብት እንዲያመነጩ ይጠበቃል። ይህ ማለት ደግሞ ገንዘብ ማመንጨት ሲችሉ ወጪዎቻቸውንም መሸፈን ይጀምራሉ ማለት ነው። በመሆኑም ተቋማቱ የሕዝብ ተቋማት መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ተማሪዎችን እያስከፈሉ ትምህርት መስጠታቸው አንዱ የገቢ ምንጫቸው ነው። በዓለም አቀፍ ያሉ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችም ከመንግስት የሚደረግላቸው ድጎማ እንዳለ ሆኖ ከተማሪ የሚያገኙት ክፍያ እንዲሁም የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ የሚያገኟቸው ሀብቶች ስራዎቻቸውን ይደጉማሉ፡፡
ሀብት ያመነጫሉ ሲባል ግን ቀጥታ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ገብተው ከነጋዴ ጋር ይወዳደራሉ ማለት አይደለም። ከሚሰጣቸው ተልዕኮ አንጻር ነው የሚሰሩት፤ ለምሳሌ ከሚሰጧቸው ተልዕኮዎች አንዱ የመማር ማስተማር ስራ ነው፤ ሲያስተምሩ ገንዘብ ያገኛሉ በሌላ በኩል ደግሞ የምርምር ስራዎችን ያከናውናሉ ይህንን ሲያደርጉ ገንዘብ ያገኛሉ። የማህበረሰብ አገልግሎት ሲሰጡ ሲያማክሩ ገንዘብ ያገኛሉ፤ ይህ ደግሞ ሀብት የማመንጨት ሂደቱ ነው። ያመነጩትን ሀብት ደግሞ ለትምህርት ጥራት ለምርምር ሥራ ያውሉታል ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ሌላው በተቋማቱ ራስ ገዝ መሆን ላይ የሚነሳው ነገር የፍትሐዊነት ነው፤ መክፈል የሚችል ብቻ የሚማርባቸው ተቋማት እንዳይሆኑስ የታሰበው ምንድን ነው?
ዶክተር ሰለሞን፦ ተቋማቱ የመንግስት እንደመሆናቸው መጠን ሥራቸው ፍትሃዊነትን የማረጋገጥ ሥራ ነው። አንድ ተቋም ራስ ገዝ ሲሆን ተማሪን ፈትኖ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ይቀበላል። በዚህም ተማሪዎች ሲገቡ ተወዳድረው አቅም ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፤ ግን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አቅሙ ኖሮት ደግሞ ከፍሎ መማር የማይችለውን ተማሪ የማስተማር ጉዳይ የመንግስት ኃላፊነት ይሆናል። መንግስት ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ተማሪዎቹ ነጻ የትምህርት እድልን የሚያገኙበትን ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ይሰራል።
በመሆኑም አቅም ኖሮት መክፈል የሚችል ይከፍላል፤ መስፈርቱን አሟልቶ የመክፈል አቅም የሚያንሰውን ደግሞ መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ያስተምራል፡፡በመሆኑም ተቋማቱ ራስ ገዝ ሆኑ ማለት ወደግል ተቋምነት ተቀየሩ ማለት አይደለም። ተደራሽነታቸውን የማረጋገጡ ስራ እንዳለ ሆኖ ፍትሀዊነትንም የማረጋገጥ ስራው በዛው ልክ ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል?
ዶክተር ሰለሞን ፦ በነገራችን ላይ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ ጅምሩ ቀደም ባለው ጊዜ በእኛም አገር የነበረ ነው። አሁን ባለንበት ዘመን በጣም ትልልቅና ብዙ የምርምር የቴክኖሎጂ ሽግግርን እያደረጉ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የሆኑ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ስራ በራሱ ከፍ ያለ ነጻነትን የሚፈልግ ነው። ለምሳሌ ምርምር ሲካሄድ የተለያዩ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፤ ግብዓቶቹ ደግሞ በአስቸኳይ የግዢ ሥርዓት መፈጸም ሊኖርባቸው ይችላል። ነገር ግን አሁን ያለው የፋይናንስና የግዢ ሥርዓት ይህንን የሚፈቅድ አይደለም ። በመሆኑም እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ሊሆኑ የሚችሉት ራሳቸውን ማስተዳደር ሲችሉ ብቻ ነው። ዛሬ ላይ ቆመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ልንጠራቸው የምንችላቸው ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ ናቸው። የውጤታማነታቸው ምስጢርም ይኸው ነው።
ለምሳሌ እነ ሀርቫርድን ጨምሮ የስቴት ዩኒቨርሲቲዎች የመንግስት ናቸው። ግን ደግሞ ራስ ገዝ አስተዳደርን ስለሚከተሉ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ላይ ሁሌም ከላይ የሚታዩ ናቸው። በመሆኑም ራስ ገዝ ማድረግ የዓለም ተሞክሮም እንደሚያሳየው በትምህርት ጥራት ፤ በምርምር ስራዎች ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ነው።
እኛም ከመሬት ተነስተን አይደለም ዩኒቨርሲቲዎቻችን ራስ ገዝ ሊሆኑ ይገባል በማለት ወደ ስራ ይገባነው። ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ከፍ ያለ ሥራ ተሰርቷል፤ አሁን በመንግስት ደረጃ 51 ዩኒቨርሲቲዎች አሉን ፤ በግል 5 እንዲሁም 325 አካባቢ የግል ኮሌጆችም አሉን። በመሆኑም ይህ ተደራሽነት ጥሩ ቢሆንም የዛሬ አምስት ዓመት የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ሲካሄድ የተገኘው ውጤት የሚያሳየው ተደራሽነቱ አበረታች ቢሆንም የትምህርት ጥራቱ ላይ ግን ችግር እንዳለ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ምን መሰራት አለበት ለሚለው ፍኖተ ካርታው ካስቀመጠው ምክረ ሃሳብ አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ማድረግ ነው፡
በመሆኑም የዚህን የጥናት ውጤት በመያዝ ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ ገዝ የሚሆኑበትን አሰራር የማመቻቸት ሂደት ነው የተጀመረው። ራስ ገዝ የመሆን ጉዳይም ከጥናቱ ጋር አብሮ የመጣ ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
የዓለም ተሞክሮ የሚያሳየንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻነት ለአካዳሚክ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንዳለው ነው። ሌላውና የሚገርመው ነገር ራስ ገዝ በአገራችን ዛሬ የተጀመረ አሰራር አይደለም ፤ በንጉሱ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ራስ ገዝ ሆኖ ነው የተቋቋመው ፤ በዛን ወቅት የነበረውን ተሞክሮም መለስ ብለን ስናየው በትምህርት ጥራት ላይ የነበረው ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም ፤ ሆኖም ከመንግስት ለውጥ ጋር በተያያዘ በዛ መልኩ መቀጠል ባለመቻሉ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በጠቅላላው ግን ራስ ገዝ አንዱ የትምህርት ሚኒስቴር የሪፎርም ስራ አካል ነው፡፡
ከራስ ገዝነት በተጓዳኝ ጥናቱን መሰረት በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን በሚና የመከፋፈል ሥራ ይሰራል። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በሙሉ የሚሰጡት ትምህርትም ሆነ ደረጃቸው ተመሳሳይ ነው፤ ነገር ግን አንድ ዓይነት መሆን አይጠበቅባቸውም ። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቹ በትኩረትና በተልዕኮ ሊለያዩ ይገባል፤ ይህም ሲባል የተወሰኑት ምርመር ሌሎቹ አፕላይድ ሳይንስ የተቀሩት ህክምና ከዚህ የሚተርፉት ደግሞ የመማር ማስተማር ሥራውን ከምርመሩ ጋር አዋህደው ይቀጥሉ ተብሎ ዩኒቨርሲቲዎቹን የመለየት እንዲሁም ካላቸው አካባቢያዊ ሁኔታና ጸጋ እንዲሁም ከኋላ ታሪካቸው በመነሳት ትኩረት እንዲያገኙ ሆኗል። በዚህ መነሻነትም ከዚህ በኋላ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ሥራን አይሰሩም፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የራስ ገዝ የመሆን ጉዞውን እንዲጀምር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመረጡ ተነግሯል ሌሎቹስ መቼ ነው የሚገቡት?
ዶክተር ሰለሞን፦ አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካለው ልምድ ከእድሜውና ከሌሎች ነገሮች አንጻር ተመራጭ ሆኗል። በነገራችን ላይ አዋጁ አንድ ተቋም ምን ሲያሟላ ራስ ገዝ እንደሚሆን በግልጽ አስቀምጧል፤ ከዚህም ውስጥ ያለው ታሪካዊ ዳራ ፡፡ አቅሙ የሰራተኞች ብዛትና የስራ ዘርፍ ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ቢሆን ራሱን የማስተዳደር አቅሙ ምን ያህል ነው? የሚሉት ነገሮች ሁሉ ታይቶ ነው የሚመረጠው። በዚህ መስፈርት መሰረት አሟልቶ የተገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የምንላቸው ስምንት ያህል ተቋማት ወደ ራስ ገዝነት ይገባሉ። ቀስ በቀስም ዩኒቨርሲቲዎች አቅማቸው እየታየ ወደ መስመር ይገባሉ። ነገር ግን በሁለት አመት ውስጥ አስር ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ ሆነው ይወጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ዘንድሮ የሚጀመረው የተማሪዎች የመውጪያ ፈተና ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ዶክተር ሰለሞን ፦ 280 ሺ ለሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ለመስጠት ዩኒቨርሲቲዎቹ ከፍ ያለ ዝግጅትን እያደረጉ ነው። ከሐምሌ 3 እስከ 8 ቀን 2015 ዓም ደግሞ ፈተናው ይሰጣል። በዚህ ዓመት የሚመረቅ ተማሪ ሁሉ የመውጪያ ፈተናውን ይወስዳል ማለት ነው፡፡
ተማሪን ፈትኖ ማስገባት ብሎም የተማረውን ምን ያህል አውቋል ብሎ ደግሞ መጨረሻ ላይ ፈትኖ ማስወጣት እኛ አገር አሁን ይጀመር እንጂ ሌሎች አለማት ይሰሩበታል። ዋናው ዓላማውም ተማሪዎች የሚፈለግባቸውን ወይም ሊያውቋቸው የሚገቡ መሰረታዊ እውቀቶች ይዘዋል ወይ? የሚለውን መለካት ነው። ተማሪዎች ሶስትም አራትም አምስትም ከዛ በላይም አመት በትምህርት ያሳልፉ መጨረሻው ግን በተማሩት ትምህርት በኩል ያሉትን መሰረታዊ ነገሮች ያውቃሉ ወይ የሚለውን የምንለካበት ነው። ተማሩ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሲያልፍና እውቀቱ ተመዝኖ ሲታይ በትምህርት ጥራት ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው በአንድ ሙያ ተምሮ ሲወጣ ስለተማረው ትምህርት ጽንሰ ሃሳብ ምንድነው? የሚለውን ነገር ከማወቅ ጀምሮ የዛ ሙያ ባለቤት ነው ሊያስብለው የሚችለውን ነገር አውቋል ወይ? የሚለው ሲለካና ሲረጋገጥ ያኔ ወረደ ስለምንለው የትምህርት ጥራትም ተጨባጭ መረጃን እንይዛለን ማለት ነው፡
በጠቅላላው አንድ ተማሪ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብቶ ሲማር ከእውቀት፤ ከብቃት፤ ከክህሎት አንጻር አውቋቸው እንዲወጣ የሚፈለጉ ነገሮች አሉ፤ እነዚህን ነገሮች በሚገባ ጨበጠ ማለት ደግሞ ኢንደስትሪው ላይ ሲገባ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለት ነው፡፡
በመሆኑም የመውጪያ ፈተናው ጠቅለል ያለ ተማሪዎች በተማሩት ሙያ ዘርፍ ላይ ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮችን አውቀዋል ወይ ?እውቀቶችን ጨብጠዋል ወይ? የሚለውን የሚለካበት ሥርዓት ከመሆኑ አንጻር ለትምህርት ጥራቱም የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሌላው እንግዲህ ዶክተር በትግራይ ክልል የትምህርት ዘርፉን ወደነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች ነበሩና አሁን ላይ ምን ውጤት አለ ?
ዶክተር ሰለሞን፦ የፕሪቶሪያውን ሰላም ስምምነት መሰረት ጦርነቱ ቆሟል። የሰላም አንዱ መገለጫው ደግሞ ትምህርት በመሆኑ በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደሥራ መግባታቸው አንዱ ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ማሳያ በመሆኑ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ወዲያውኑ ኮሚቴ አዋቅረን መቀሌ በመሄድና የአራቱንም ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች በመጠራት ያሉበትን ሁኔታ፤ የደረሰባቸውን ጉዳትና ሊደረግ በሚገባውን ነገር ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እነሱም አለ ስለሚሉት ነገር ሪፖርት አቅርበውልን አይተናል፡፡
እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም አክሱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል የሚል መረጃ ስለነበረን በቦታው ላይ ቅኝት የሚያደርግ ቡድን በመላክና ሁለት ሳምንት እንዲቆዩ በማድረግ የትምህርት ክፍሎቹን አዲሱ አመራር እንዲረከበው የማድረግና የጽዳት ስራዎች ተሰርተው ወደ ስራ እንዲመለስ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል፡
በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችላቸው ቁመና ላይ እየደረሱ ነው። በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ምግባቸውም ማደሪያቸው እንዲሁም የጤና ሁኔታቸው ሁሉ ክትትል የሚደረገው በመንግስትና በተቋማቱ በመሆኑም በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች ሲገቡ እነዚህ ነገሮች ተሟልተው ሊጠብቋቸው ስለሚገባ ባለፉት ወራቶች ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከአካባቢው አመራሮች ጋር በመሆን እየተሰራ ያለው ይህ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር የሚያስችላቸው ቁመና ላይ ናቸው ወይ መሰረተ ልማቱ ምን ይመስላል የሚለውን የማረጋገጥ ስራውም በዋናነት እየተሰራ ነው። በተወሰኑት ማለትም እንደ ራያ ዩኒቨርሲቲ ያሉትም ዝግጅታቸውን አጠናቀው ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡
መከላከያ ትግራይን ለቆ በወጣበት ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ላይ በየዩኒቨርሲቲው ያሉ ተማሪዎችን ማስወጣት ነበረብንና በወቅቱ ከ20 ሺ በላይ ተማሪዎችን ከትግራይ አስወጥተናል። እነዚህን ተማሪዎችም በጊዜያዊነት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉም ሆኗል። መመረቅ የነበረባቸውም ተመርቀዋል፤ የሚቀራቸውም እየተማሩ ነው። ነገር ግን ከትግራይ ያልወጡ የአካባቢው ተማሪዎች ቁጥራቸውም ከ20ሺ በላይ የሚሆነው እዛው አሉ። እነዚህን ተማሪዎች ሁለት ዓመት በጦርነቱ ምክንያት አልተማሩም በመሆኑም አሁን ላይ ትምህርታቸውን ካቆሙበት እንዲቀጥሉና ዩኒቨርሲቲዎቹ ደግሞ ዝግጁ ሲሆኑ የአዲስ ተማሪ ቅበላም የሚጀምሩበት ሁኔታ ታስቧል፡፡
አሁን ላይ ራያ ዩኒቨርሲቲ እዛ አካባቢ ያሉትንና ሌላ ቦታ ያልተመደቡትን ነባር ተማሪዎቹን ጠርቶ ምዝገባ እያደረገ ነው። መቀሌና አዲግራትም ከአንድ ወር በኋላ ወደ ስራ የሚገቡ ሲሆን አክሱም ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ሁለት ወር ወደመማር ማስተማር ስራው ይገባል። ሁሉም ግን ለነባር ተማሪዎቻቸው ጥሪ ከማስተላለፍም በላይ ባሉበት ሆነው ምዝገባቸውን እንዲጨርሱም አድርገዋል። በዚህም ያላቸውን የተማሪ ቁጥርና ሊያደርጉ የሚገባቸውን ዝግጅት አውቀዋል፤ ጊዜው ሲደርስ ጠርተው ያስገባሉ።
በወቅቱ ተፈናቅለው የመጡ መምህራን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስራቸውን እንዲጀምሩ ተደርጓል። ነገር ግን አሁን ላይ ሁኔታዎች እየተስተካከሉ በመሆኑ ወደ ቀድሞ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተመልሰው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻም ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ?
ዶክተር ሰለሞን፦ አዎ እንግዲህ በተለይም ከተነሳንበት አንጻር ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ይሆናሉ ወይም ይሁኑ ሲባል እንደ አገር ያለው ወይም የሚኖረው ፋይዳ በጣም ሰፊ ነው። በተለይም ብቁ የሰው ኃይል በማዘጋጀት ለአገራችን ኢንደስትሪዎች አቅም የሚጨምር ሥራ ያሰራል። ይህ ደግሞ ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል። ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ችለው ብቃት ያለው መምህር ቀጠሩ ማለት ብቃት ያለው ተማሪን የማውጣት እድላቸውም ሰፋ ማለት ነው። በዛውም ብቃት ያለው ምርመር ይደረጋል፤ ቴክኖሎጂዎችም ይወለዳሉ። ማህበረሰቡም ተቋማቱ በዚህ አካሄድ የግል ተቋም ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውንም ሃሳብ ማውጣት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ሰለሞን፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015