እንደ አገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የጀመርናቸው ጥረቶች በብዙ ልፋትና ርብርብ ፍሬ ማፍራት በጀመሩበት፤ ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተው የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ እየሆኑ በመጡበት ማግስት አገርና መንግሥትን ከሁሉም በላይ በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን የማጠልሸት ትርክቶች መሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በቅርቡ የርዳታ ስንዴ ተሰረቀ በሚል የተጀመረው ይህ በመረጃና በበቂ ማጣራት ላይ ያልተመሰረተው ትርክት፤ በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ያልተገባ አቅም ገንብቶ፤ በችግር ውስጥ ያሉ ድጋፍ ፈላጊዎች የሚያስፈልጋቸውን ርዳታ በወቅቱ እንዳያገኙ ትልቅ ፈተና ሆኗል።
የትኛውም ማኅበረሰብ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ፤ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የርዳታ ጥሪ የማቅረብና የመረዳት መብት አለው። ይህ መብቱ በዓለም አቀፍም ሆነ በሞራል ሕግ የተደገፈ ነው። ዋና ዓላማውም በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሕይወት ከጥፋት መታደግና ነገዎቻቸው እንዳይጨልሙ ማድረግ ነው።
እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በየትኛውም የዓለም ክፍል በተለያዩ መንገዶች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ ችግሩን ተቋቁሞ የመሻገሩ እውነታ እንደየአገሩ የኢኮኖሚ አቅምና የአደጋ ዝግጁነት የሚሰላ ቢሆንም፤ የሌሎችን ድጋፍ የመሻቱ እና በአደባባይ ከፍ ባለ ድምጽ የማሰማቱ ሁኔታ ግን የተለመደና ወደፊትም ሊቀጥል የሚችል ነው። በዚህ ሂደትም ብዙ ያደጉም ሆኑ ድሀ የሚባሉ አገራት አልፈውበታል።
ችግሮቹ የሚፈጥሩት ተመጽዋችነት በራሱ ብሔራዊ የልብ ስብራት የሚፈጥር ቢሆንም፤ የርዳታ ጥሪዎች በአደጋ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሕይወት ከማትረፍ አንጻር፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ናቸው። ይህንን አለማድረግ በራሱ እንደ አንድ ትልቅ ወንጀል የሚወሰድ፤ በዓለም አቀፍ ሕግም የሚያስጠይቅ ጭምር ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከተፈጠሩ የሰላም እጦቶች፤ ከኮቪድ፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት እና ከተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በማሳወቅ የርዳታ አቅርቦቶች ለተረጂዎች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ የሚቀርቡበትን የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዚህም ዓለም አቀፉን የምግብ ድርጅት / ወርልድ ፉድ ፕሮግራም / እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ን /ዩ ኤስ ኤይድ/ን ጨምሮ የተለያዩ የርዳታ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ በመግባት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር በራሳቸው ተቋማዊ መዋቅር የርዳታ አቅርቦቶችን ለተረጂዎች ሲያደርሱ ቆይተዋል። በዚህም የብዙ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል።
አገሪቱ ከነበረችበት ተጨባጭ ሁኔታም አንጻር መንግሥት ባልተቆጣጠራቸው አካባቢዎች፤ በርዳታ እህል አቅርቦትና አጠቃቀም ዙሪያም ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በችግሮቹም ዙሪያም በወቅቱ ሰሚ ያጡ ከፍ ብለው ሲደመጡ የነበሩ ድምጾች ነበሩ። የሚመለከታቸው አካላትም ለድምጾቹ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አቅቷቸው ዝምታን መምረጣቸው ይታወሳል።
ይህ እውነት የአደባባይ ምስጢር በሆነበት፤ ከዝምታው በስተጀርባ የተፈጠሩ ጫናዎች አገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ባስከፈሉበት ማግስት፤ መንግሥት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ በስንዴ ምርት ዙሪያ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ትኩረት የሳበ የስኬት ታሪክ ትርክት ውስጥ ሲገባ የተፈጠረው «የስንዴ ተሰረቀ ጩኸት» አንደምታው ለተረጂዎች ከመቆርቆር የመነጨ ስለመሆኑ አጠያያቂ ነው።
በአንድ በኩል 70 ከመቶ የሚሆነው የእርዳታ አቅርቦት በርዳታ ተቋማቱ ተቋማዊ መዋቅር ለተረጂዎች በሚከፋፈልበት፤ ከዚያም በላይ ተሰረቀ በሚባለው የርዳታ አቅርቦት ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ የማጣራት ሥራዎችን ባልሠሩበትና በውጤቱ መስማማትም ሆነ አለመስማማታቸው ባልታወቀበት ሁኔታ «የተሰረቀን ድምጽ» ከፍ አድርጎ ማሰማት ተገቢም፤ ተቀባይነት ያለውም አይሆንም፡፡
በተለይም ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት በተጨባጭ ማስረጃ ያልተደገፈ ሪፖርትን መሠረት በማድረግ ለተረጂዎች ይደርስ የነበረውን የርዳታ አቅርቦት ማቋረጡ ካለበት ዓለምአቀፋዊ ኃላፊነት አንጻር ከፍያለ የሕግና የሞራል ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው። በተረጂዎችም ሕይወት ላይ የመፍረድ ያህል ነው።
ሌሎች የተራድኦ ድርጅቶችም ቢሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት ካለርዳታ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሰፊ ጥያቄዎች ሲነሱ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርቶ፤ አሁን ላይ በተገቢው መንገድ የማጣራት ሂደትን ያላለፈ ሪፖርት በማውጣት አገርና መንግሥትን ባልተገባ መልኩ በመወንጀል ላይ መጠመዳቸው፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር ተጠያቂነትን የሚያስከትል ያልተገባ ተግባር ነው።
በተለይም እንደ አገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል እያደረግናቸው ያሉ ጥረቶች በብዙ መንገድ ተስፋ ሰጪ በሆኑበት፤ ከሁሉም በላይ የበጋ ስንዴ ልማት በብዙ ስኬት የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ትኩረት እየሳበ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን «በርዳታ ስንዴ ስርቆት» ለመወንጀል የሚደረገው እንቅስቃሴ፤ ስኬትን ለማጠልሸት የሚደረግ ሙከራ ቢሆንም መሠረቱ ሐሰት ነውና የሚሳካ አይሆንም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015