አንድ ዛፍ ቆርጣችሁ፣
ሁለት ካልተካችሁ፣
የተፈጥሮ ጠላት፣
የደን አሸባሪ፣
የሰው ልጅ አዋኪ፣ የተፈጥሮ ፀሯ- ነፍሰ ገዳይ ናችሁ፡፡ ይላል በ (ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ -1994 ዓ.ም. ጀርመን/ሀምቡርግ) ከተማ የተጻፈና በማህበራዊ ትስስር ሚዲያው ላይ ያገኘሁት ስንኝ፡፡ አዎ የተፈጥሮ ሀብታችን ተመናምኖ በረሃማነት ደረጃ ላይ አደርሶ የነበረበት እውነታም ይኸው ነው፤ አንድ ዛፍ ቆርጠን በምትኩ ሁለት አለመትከላችን፡፡
ዛሬ ላይ የቀደሙት ሁኔታዎች/ለዶክተሩ ግጥም መነሻ የሆነው ልምምዳችን/ እየተቀየሩ ነው ፡፡በተለይም ባለፉት አምስት አመታት የተፈጥሮ ሀብትን ለመንከባከብ በአረንጓዴ አሻራ በኩል እንደአገር እየተሰራ ያለው ሰፊ ስራ የቀደመውን ትርክት እየቀየረው ነው።
የአገራችን የደን ሀብት ታሪክ እንደሚያመለክተው፣ በቀደሙት ዘመናት የምድሪቱ 120 ሚሊዮን ሄክታር 60 በመቶ በሚሆን በደን ተሸፍኖ እንደነበር ነው። የቀደሙት የአገሪቱ ነገስታቶች/ንጉሶች የደን ምንጠራና ገደብ የለሽ አደንን ለመከላከል ይሞክሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ የጅባትን ደንና የወፍ ዋሻን ውኃ-በል (watershed) የደን ክምችት እንዲጀመር ስለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ የወጨጫና የየረር ተራራዎችን በደን በማልማት እንዲሁም ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› በማድረግ አገሪቱን በደን የማልበስ ተግባር በስፋት እንደፈጸሙ ታሪካቸው በስፋት ያወሳል፡፡
የደን ሀብትን ጠቃሚነትን በእጅጉ የተገነዘቡት አፄ ምኒልክም ቢሆኑ አገራቸውን በደኑ መስክ ለማልማት ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› የሚለውን እሳቤ አጽንኦት በመስጠት በዘመናቸው የመጀመሪያውን የደን ሥርዓት መሥርተውም ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የደን ሕግ ለማርቀቅም የውጭ አገር ባለሙያዎችን ቀጥረው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
ይህም ሕግ ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆን ስለመደንገጉም ይታወሳል፡፡ አገሪቱን በደን ለማልማት ካላቸው ቅንነት የተነሣም በፍጥነት የሚያድጉ ዛፎችን ከሌሎች አገሮች በማስመጣት ተክለዋል፡፡ ንጉሡ የደን አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለማቋቋም ካላቸው ፍላጎት የተነሣ የውጭ አገር ዜጋም ቀጥረው ምክር ሲቀበሉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሆኑ ኮነሬል መንግስቱ ኃይለማርያም ከደን ልማት ጋር የተያያዘ የራሳቸው አዎንታዊ ታሪክ ባለቤት ናቸው።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ከደን መመናመንና ከተፈጥሮ ሀብት መራቆት ጋር ተያይዞ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያጋጠማቸውን ቀውሶችና ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በማስረዳትና ባገኙት መድረክ በመሞገት ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አቶ መለስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ከመገንባት ጋር አያይዘው በብዙ የተንቀሳቀሱበት የደን ልማት ዛሬ ለደረስንበት ውጤት የነበረው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ይህንኑ ‘የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ’ በማስቀጠል ረገድም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል ያሳዩትና እያሳዩት ያለው ትጋት በዘርፉ አሁን ላይ እንደአገር ላተረፍነው ከፍ ያለ እውቅና ዋነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡
የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ የዕፅዋቶችና የደኖች መመናመን ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ ያስገቡት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ ፣ መላው የአገራቸውን ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ / የአረንጓዴ ልማት አርበኛ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስኬትን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አገር የምታደርገው ‘የአረንጓዴ ዐሻራ’ ዘመቻ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች ላይ የፈጠረው መነሳሳትና ያሳየው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ትኩረትን የሳበ ብዙዎችም ፈለጋችንን ለመከተል የወሰኑበት ስለመሆኑም እየተነገረ ነው፡፡
መንግስት ከጅምሩ ጀምሮ ”አረንጓዴ አሻራ ለአገራችን ዘላቂ ልማት” ብሎ ሲነሳ ሕዝቡም ቢሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በመውጣት መልዕክቱን በተግባር ስለማዋሉ መቼም ነጋሪ አያሻንም፣ ምክንያቱም በአይናችን ያየነው ሃቅ ነውና፣ ይህ ስራ (የችግኝ ተከላ) ደግሞ ዘንድሮም በስፋት ቀጥሏል እርግጠኛ ነኝ የእኛም መነሳሳት በዛው ልክ ቀጥሏል ብዬ አስባለሁ፡፡
ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ሞዴል የማድረግ እንቅስቃሴው የበርካቶችን ይሁንታና ድጋፍ እያገኘ መሆኑንም በስፋት እያስተዋልን ነው፡፡ የደን ሀብቶቻችን ሊያበረክቱ የሚችሉትን እምቅ ጠቀሜታዎችም ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለልጆቹና ለመጪው ትውልድ በዘመቻው እየተሳተፈ ነው፡፡
በዚህ ረገድም የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ ሲጀመር በ12 ሰዓታት ውስጥ ከ353 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመተከል በዘርፉ የዓለም ክብረወሰን በእጃችን መያዝ ችለናል። ባለፉት አራት አመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከልም ዓለምን ማስደመም ችለናል፡፡ ይህም ለእኛ ትልቅ የሞራል አቅም ሆኗል፡፡
የአገሪቱ የደንና የአየር ንብረት ይዞታ እንዲያገግም ለማድረግ የታለመው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዘንድሮም ቀጥሏል፡፡ በዚህ ዓመትም እንደ አገር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዷል፡፡ ለመርሐ ግብሩም መንግስት በሚችለው አቅም እየሰራ ሲሆን የእኛ የዜጎች ርብርብም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ስኬት አስተማማኝ እንዲሆን የተተከሉትን ችግኞች በባለቤትነት ማስተዳደርና መንከባከብ ያለበት የየአካባቢው ነዋሪ መሆኑ ለማንም የሚሰወር አይደለም። ይህንኑ እውነታ ወደ መሬት ለማውረድ እየተሰራና ውጤት እየተገኘበት ቢሆንም ከምንተክላቸው ችግኞች ብዛት አንጻር አሁንም ትኩረት የሚሻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ከፍ ያለ የባለቤትነት መንፈስ ፈጥሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የሚመራ ቢሆንም፣ የአካባቢ ጥበቃ የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሁም ዜጎች በአጠቃላይ ለመርሀ ግብሩ ስኬት የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል። ተቋማትና አንዳንድ ፍቃደኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ሰራተኞቻቸውን በማስተባበር የሚያደርጉት የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞችን የሚበረታቱና ተጠናክረው በዚህም አመት ሊቀጥሉ ያስፈልጋል፡፡
በዘንድሮ ክረምት የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ-ግብር እንደ አገር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዷል፣ ለዚህም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል፣ ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በአፋር ክልል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተጀምሯል፡፡
የመርሃ ግብሩ ስኬት ከኛ አልፎ መጪዎቹን ትውልዶች ተጠቃሚ ከማድረጉ አኳያ ሁላችንም በዘንድሮው የችግኝ ተካላ በኃላፊነት መንፈስ በመሳተፍ አሻራችንን ማኖር ፤ ከዛም አለፍ ሲል አምናና ካቻምና የተከልናቸውን ምን ደረጃ ላይ ደረሱ ብለን የቀደሙትን በመጎብኘት የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ-ግብርን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ እናሳድግ ! ፡፡
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015