እኛ ኢትዮጵያውያን ስለነጻነታችን ከፍ ያለ የተጋድሎ ታሪክ ያለን፤ ለዚህም ብዙ ዋጋ እንደከፈልን ታሪካችን የሚዘክረው፣ ዓለምም የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው። የዚያኑም ያህል ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመነጋገር መፍታት ባለመቻላችን የከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎች የመጥፎ ገጽታችን መገለጫ በመሆን አንገት እያስደፉን ስለመሆኑም ለመናገር የማይከብድ የታሪካችን አንድ አካል ነው።
የሩቁን ዘመን ትተን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ያለውን ታሪካችንን ብንመለከት በአገራዊ የውስጥ ችግሮቻችን ዙሪያ ቁጭ ብለን መነጋገር ባለመቻላችን፣ ለአገር ተስፋ የነበረውን የ60ዎቹን ትውልድ አጥተናል ፤ ትውልዱ ይዞት የተነሳው ትልቅ አገራዊ ራዕይ መክኖ እንደአገር የመረረ የልብ ስብራት ውስጥ አልፈናል። ታላቂቷን ኢትዮጵያ የማይመጥን ጥቁር ታሪክ ለመጻፍ ተገደናል።
በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሰረተው፣ በሴራና በኃይል ከተገነባው የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚመነጨው ይህ ዘመኑን የማይዋጅ የፖለቲካ ባህላችን የሚገራው አጥቶ 60ዎቹንና ሰባዎቹን ተሻግሮ ያለፉት ስድስት አስርት ዓመታትም ሰላምን መንገድ ትተው አመጽንና ነፍጥን በመረጡ ኃይሎች ሴራና ግፍ ያልተገቡ ዋጋዎች እንድንከፍል አስገድዶናል። በተለያየ መንገድ ለውጥ ፈላጊ ዜጎቻችችን ህልምም ተፈታትኗል።
አስተሳሰቡ ካልተገባ የዜጎች መስዋእትነት ባለፈ እንደ አገር ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለመውጣት የነበረውንና እስከዛሬ ድረስ ያለውን የህዝባችን መሻት ፤ ፍሬ አፍርቶ በዘመናት መካከል ስለ ነጻነታችን የከፈልነው መስዋእትነት ቶሎ እንዳያፈራ አድርጓል ፤ ዛሬም አገር ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት እንዳታዞር ተግዳሮት ሆኗል። ፈጥነን ካላረምነው በቀጣይም ይህ ትውልድ አገራዊ ብልጽግናን ለማምጣት ለሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ትልቁ ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ ትውልድ ተሻጋሪ ችግር ለመውጣት ከሁሉም በላይ አገራዊ ፖለቲካችን ዘመኑን የሚዋጅ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ መላው ሕዝባችንን የሚመለከት ቢሆንም፤ ከሁሉ በዋነኛነት የወቅቱ ፖለቲከኞቻችን የፖለቲካቸው የአስተሳሰብ መሰረት ከትናንቱ፣ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን አሮጌ አስተሳሰብ ፣ በሁለንተናዊ መልኩ የጠራ መሆኑን በኃላፊነት መንፈስ ሊገመግሙና ለዚህ የሚሆን ታማኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ትውልድ ላይ የሚዘሩት የትኛውም አይነት የፖለቲካ ዘር የቀደሙት ትውልዶች በብዙ ተስፋ ላደረጉት ፣ ከዚያም ባለፈ ለተስፋቸው ለከፈሉት ዋጋ ከበሬታ የሚሰጥ ፤ ሕዝባችን እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ የቀደመውን ትልቅነቱን መልሶ ለመጨበጥ በየዘመኑ ሲያልመው የነበረውን ህልሙን እውን ማድረግ የሚያስችል መንፈሳዊ ፣ ሥነልቦናዊና እና አእምሯዊ አቅም የሚገነባ ሊሆን ይገባል።ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ ከተመሰረተው ፣ ከሴራ እና ከኃይል ከተገዛው ያረጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሳቸውን ሊጠብቁ፤ ከዚህ ይልቅ መጪውን የሀገሪቱን እታ ፈንታ ብሩህ ሊያደርግ ለሚችለው ልዩነቶችን በውይይትና በድርድር መፍታትን መሰረት ላደረገው የፖለቲካ አስተሳሰብ ራሳቸውን ሊያስገዙ ፤ለዚህ የሚሆን ዝግጅት ሊፈጥሩ ያስፈልጋል።
በዘመናት ብዙ መስዋእትነት ከፍለን ቀና ብሎ የሚያስኬድ የነጻነት ታሪክ ባለቤት የሆነውን ያህል ፤ እኛም ሆንን መጪውን ትውልድ አንገት ከሚያስደፋ ኋላ ቀርነትና ድህነት ተላቀን የበለጸገች ሀገር ባለቤት ለመሆን፤ እንደ ሕዝብ ፖለቲካችንን ዘመኑን በሚዋጅ ተራማጅ አስተሳሰብ ልንገራው፤ ትውልድ ተሻጋሪ መሰረት እንዲኖረው አድርገን ዛሬ ላይ ልናዋቅረው ይገባል።ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ እንደ አገር በችግሮቻችን ዙሪያ ተነጋግረን መግባባት ላይ ለመድረስ፤ በዚህም ከመጣንበት የግጭት አዙሪት ወጥተን ሰላማዊና የበለጸገች አገር ለመፍጠር ያስችለን ዘንድ ላዋቀርነው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮ ስኬት ባለን አቅም ሁሉ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የኮሚሽኑ ተልእኮ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላደል በመፍጠር የበለጸገች አገር እና ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመፍጠር ካለው የማይተካ ስትራቴጂክ አስተዋጽኦ አንጻር ልንረዳው ይገባል። ይህ ከግጭት አዙሪት ለመውጣት ጊዜው የሰጠን መልካም ዕድልም ነው። ስለሆነም ለራሳችንም ሆነ ለመጪው ትውልድ መልካም ሕይወት ስንል በኃላፊነት መንፈስ ልንጠቀምበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015