ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዘመን በላይ ዘመናዊ ግብርና እና ቴክኖሎጂን አጣምራ ባለመጠቀሟ እና ዘመን ወለድ ግኝቶችን መጠቀም ባለመቻሏ ዛሬም አርሶ አደሮቿ በበሬ እያረሱ ሚሊዮኖችን ለመመገብ ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም 22 ከመቶ የሚሆኑት ዜጎች ከድህነት አለመውጣታቸው ሚስጥሩ ደግሞ የግብርና እና የግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ብዙ ሥራ ባለመሰራቱ የመጣ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ግብርናን ማዘመን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ባይካድም ሆኖም የጉዳዩን አሳሳቢነት ያህል ስራዎች በታሰበው ልክ አለመሰራታቸው አሁንም ትልቁ ፈተና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ እና ዋነኛ ማጠንጠኛውና ከአገሪቱ ሕዝብ 80 ከመቶ የሚሸፍነው አርሶ አደሩ ወይንም የገጠር ሕዝብ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም አሁንም ከግብርና ግብአቶች አቅርቦትና ፋይናንስ ጋር የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደር ወደ ዘመናዊ ግብርና ካልገባ እና የግብርና ግብዓት በወቅቱ ካልቀረበለት ጠንካራ መሰረት ያለው መር ኢኮኖሚ መገንባት የህልም እንጀራ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረትም አርሶ አደሮች ግብዓትና ፋይናንስ አቅርቦት ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም፤ ይህም ብዙ ፈተና የበዛበት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በመላ አገሪቱ ከባንኮች ብድር እየወሰዱ ከሚገኙት ዜጎች ግማሽ ሚሊዮን እንደማይሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለመሆኑ የፋይናንስ እና ግብዓት አቅርቦት ኢትዮጵያ ግብርና መዘመን የሚኖረው ሚና እስከምን ድረስ ነው?
ዶክተር ይትባረክ ግርማ በሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና ባለሙያ ሲሆኑ፤ ትልቁ ችግርና ሲታሰብ የበርካቶች አረዳድ ከሰብል እርሻ ጋር የተያያዘ አድርጎ የመረዳት ዝንባሌ መሆኑን በመጠቆም ግብርና ግን አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመለከት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በእንስሳት ሀብት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ብትሆንም በተጠቃሚነት ዓይን ደግሞ በታችኛው እርከን ወይንም በሀብቷ ካልተጠቀሙት የምትመደብ አገር ናት፡፡ ይህ የሆነውም ለግብርና ያለን አረዳድ አሊያም ግብርናን እየተተገበረበት ያለው አካሄድ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን አለመሆኑን ነው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና የሥራ ዕድል በመፍጠር 70 ከመቶ በላይ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በእርሻ እየለማ ያለው መሬት በጣም አነስተኛ ሲሆን ምርታማነቱም በዚያው ልክ ዝቅተኛ ነው፡፡ በሌላ ገፅታው ደግሞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ወጪ በማድረግ የግብርና ምርቶችንና ግብዓቶችን ከሚሸምቱ አገራት ተርታ በቀዳሚነት ትመደባለች። በተመሣሣይ በእንስሳት ሀብት ከበርካታ ዓለማችን ክፍሎች ቀዳሚ ብትሆንም አሁንም ድረስ ለዜጎቿ በቂ ምርት ማቅረብ የማትችል አገር መሆኗን በመጠቆም፤ የዚሁ ሁሉ እክል መነሻው ለግብርና መዘመንና ግብዓት አቅርቦት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ነው ባይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከፍተኛ አቅም ያላት ቢሆንም፤ የተመረጡ ዝርያዎችን መጠቀም ላይ ብዙ ርቀት መጓዝ አልተቻለም፡፡ በአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ዘንድም ያለው አተያይ በርካታ እንስሳትን ከቤት መኖራቸውን እንጂ በመጠቀም ደረጃ የሚኖራቸውን ፋይዳ በቅጡ አለመረዳት መኖሩን ያብራራሉ፡፡
ግብርናው በሰብል እርሻ ዓይን ሲታይም ከእንስሳት ግብርና የተለየ ርቀት አልሄደም የሚሉት ዶክተር ይትባረክ፤ አንድ ዓይነት ሰብሎችን በአንድ መሬት ላይ ለተከታታይ ዓመታት መዝራትም ሌላው ግብርናው ያልተሻገረው ፈተና መሆኑን ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት ባህሉም ደካማ ነው፡፡ በብዛት ዕለታዊ ፍጆታን መሰረት ያደረገ የግብርና ሥርዓት መከተልም አንድ ይህ ዘርፍ ያልተሻገረው ማነቆ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻው ደግሞ ግብርና የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እርሻ የሚለው እሳቤ የገዘፈ ክብደት የሚሰጠው መሆኑና ያለውን አቅም በቅጡ አለመረዳት ነው፡፡
እንደ ዶክተር ይትባረክ ገለፃ፤ ለግብርናው ያለው አረዳድ ብቻ ሳይሆነ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚም የሚቀርበው የፋይናንስና ብድር አቅርቦትም እጅግ በጣም አነስተኛ እና ወደፊት የሚያሻግር አለመሆኑን ነው፡፡ በተለይም አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ያለውን ጥሪት እንደ ማስያዣ በመጠቀም ግብዓቶችን አሊያም ደግሞ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን የሚያገኝበት ስርዓት አለመዘርጋቱ የግብርናው ፈተና ነው፤ አገሪቱም ወደ ላቀ ደረጃ እንዳትሸጋገር ሸብቦ ይዟታል የሚል የፀና እምነት አላቸው፡፡
በተለይም በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ሆነ እና እንስሳት ሀብት ላይ ለሚደርሰው ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች በፍጥነት የሚታደግ የኢንሹራንስ በኢትዮጵያ አለመተግበሩ ግብርና ባለበት እንዲረግጥ አስገድዶታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አርሶ አደሩንና እና አርብቶ አደሩን የሚታደግ ስርዓት መዘርጋት አለመቻሉ እንደ አገር ከፍተኛ ኪሳራ እያመጣ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ግብርናን ለማዘመን የሚሰሩ ጥናታዊ ፅሁፎችም ለግብርና ጠብ የሚል በረከት እያመጡ አለመሆኑን የሚኮንኑት ዶክተር ይትባረክ፤ የምርምር ተቋማት የሚያወጧቸውን ምርምሮችና እና ግኝቶች ወደ አርሶ አደሩ የማድረስና የመተግበር ሂደቱ አዝጋሚ ነው፤ ቢደርስም አተገባበሩ ላይ የጋራ መረዳት አለመኖሩን ያብራራሉ፡፡ በምርምር ተቋማት የሚሠሩ ሥራዎችም ወደ ሕዝብ በፍጥነት አለመድረሳቸው ብቻ ሳይሆንም፤ በአርሶ አደሩ የመረዳትና የመተግበር አቅም ልክ የታሰቡ አለመሆናቸው ነገሮችን የባሳ ጥልፍልፍ ያደርጋቸዋል፡፡
የግብዓት አጠቃቀም እና አቅርቦት ሰንሰለቱም በጣም ከፍተኛ ችግር ያለበት ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ። ከዚህም በተጨማሪ የግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ እና ፍጥነት አለመቅረብ ሌላኛው ራስ ምታት ነው፡፡ አርሶ አደሩ አልፎ አልፎም ቢሆን ትርፍ ምርት አምርቶ ወደሚፈልገው አካባቢ ለማድረስ የገበያ መረጃ፣ መሰረተ ልማትና መሰል እጥረቶች አሉ የሚለው የዶክተር ይትባረክ ሃሳብ ነው፡፡
የሥራ ፈጣሪውና ፋይናንስን ባለሙያው አቶ ያሬድ ኃይለመስቀል በበኩላቸው፤ በሁሉም መስክ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲያድግ ከተፈለገ በግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ሥርዓቱ ሁሉንም ዘርፎች ማዕከል ባደረገ መልኩ ሥራ ላይ እየዋለ አለመሆኑን ይጠቁማሉ።በተለይም የፋይናንስ ተቋማት ብድር አሰጣጥ ሁሉን ያቀፉ ባለመሆናቸው ማደግ የሚገባቸው ዘርፎች በሚታሰበው ፍጥነት አለማደጋቸውን ይገልፃሉ፡፡
በምዕራቡ ዓለም ያለውን ተሞክሮ ለአብነት የሚያነሱት አቶ ያሬድ፤ ዘርፍ ተኮር የሆኑ ባንኮች መኖራቸውን ጭምር ያብራራሉ፡፡ ለአብነትም ግብርናው ለማዘመን ሲባል ለግብርናው ዘርፍ ግብዓት የሚያቀርቡ ተቋማት በብዛት አሉ፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለልም በዚያው ልክ የተቋቋሙ ባንኮች እና ሌሎች የፋይናንስ አማራጮች በብዛት ይገኛሉ። ይህም በየዘርፉ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲመጣ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያም መለመድ አለበት ብለው ከሚያስቧቸው አሰራሮች መካከል የፋይናንስ ተደራሽነት በመላ አገሪቱ ገቢራዊ መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ አገሪቱ ያለፈችባቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና የተለያዩ ሁኔታዎች በዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለማሳደሩም በማስታወስ፤ እነዚህን ግን በሚቀጥሉት ዓመታት ማስተካከል ይቻላል ባይ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ያለው የፋይናንስ ሥርዓት እየተጠናከረ መምጣት እንዳለበት የሚናገሩት የፋይናንስ ባለሙያው፤ ከውጭ ፋይናንስ ጥገኝነት ለመውጣትም ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ሁሉን ተኮር አገልግሎት የሚከተሉ ከሆነ እና ዘመናዊ አሰራሮችን የሚተገብሩ ከሆነ የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የማቃለል ዕድላቸው በእጅጉ የሰፋ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጽያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት አትራፊነታቻው የላቀ ደረጃ ላይ ቢሆንም በሁሉም ዘርፎች ላይ በማገዝና በመደገፍ ላይ ግን የሚቀራቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ለማስተካከል ሲባልም እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የፋይናንስ ተቋማት በአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚኖራቸው ሚና ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ያብራራሉ።በተለይም አካታች የሆኑ የባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና አነስተኛ ገንዘብ ተቋማት በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ በእጅጉ የላቀ ሚና አላቸው።እንደ ምክትል ገዢው ገለፃ ከሆነ፤ በአንድ አገር ውስጥ የሚዘወረው የፋይናንስ ሥርዓት አቃፊነትና ሁሉ አቀፍ መልክ ያለው ከሆነ የምጣኔ ሀብት እንዲመነደግ ብሎም ተወዳዳሪነት እንዲኖርም ያስችላል ይላሉ። እንደ አገር ሁሉም ሴክተሮች ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የፋይናንስ አቅም መጠናከር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ የባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እና ማይክሮ ፋይናንሶች ሚና የማይተካ አለፍ ሲልም የአንበሳው ድርሻ የሚይዙ ይሆናል፡፡ ብሔራዊ ባንክም እነዚህ ተቋማት ጤናማ የገንዘብ ፍሰትና አቅም ብሎም ትርፋማነትን መከታተል ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግሩ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ምሁራኑ እንደሚስማሙት፤ በአሁኑ ወቅት ግብርናው መለወጥ ካለበት ውጤታማ የሆኑ ምርምሮችን ማካሄድ፣ እንዲሁም ልማዳዊ አሰራር መቀየር አለበት፡፡ የተቋማት፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና አርሶ አደሩ ትስስር መጠናከር አለበት፡፡ ወዲህ ደግሞ ግብርናን ለማዘመን የሚያግዙ መሰረት ልማቶች በስፋት ሊከወኑ ይገባል፡፡ ለዚሁ የሚረዱ መስመሮችንና አሰራሮችንም ማጠናከር ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
አርሶ አደሩ ግብርናውን እንዲለውጥ አስፈላጊ ድጋፎችን እና ክትትል ማድረግ ተገቢ እንደሆነና ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድም ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ግብዓቶችን በወቅቱ ማቅረብ፣ ዘመናዊ አሰራሮችን መከተል፣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት እና ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት መትከል የኢትዮጵያን ዕድገት ከሚያፋጥኑትና የሚሊዮኖችን የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት የሚለውጥ እንደሆነም ይመክራሉ፡፡
በተለይም አካታች የሆኑ የባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እና አነስተኛ ገንዘብ ተቋማት በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ በእጅጉ የላቀ ሚና የሚኖራቸው በመሆኑ ለግብርናው ዘርፍ የሚያደርጉት ድጋፍ ሊበረታታ እና በልዩ ሁኔታ ሊታይ እንደሚገባውም ይጠቁማሉ። ግብርና በአጭር ጊዜ በማዘመን ከሚታወቁ እና በግብዓት አቅርቦትን የተፋጠነ አሰራር ካላቸው አገራትም ተሞክሮዎችና ልምዶችን መጋራትም ሌላኛው መፍትሄ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ሆነ እንስሳት ሀብት ላይ ለሚደርሰው ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች በፍጥነት የሚታደግ የኢንሹራንስ አሰራር መተግበር ግብርናውን ለመታደግ ዓይነተኛ መፍትሄ ሲሆን፤ በዚያው ልክ ግብዓቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማቅረብ ቀዳሚው መፍትሄ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015