ትምህርት ቤቶች የነገ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች መፍለቂያዎች እንደመሆናቸው መጠን ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት በመስጠት በንድፈ ሀሳብ የሚሰጡ ትምህርቶች ወደ ተግባር እንዲለውጡ በማድረግ ተማሪዎች የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳበሩና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲሰሩ በማበረታታት ማገዝ አለባቸው። አሁን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከምንመለከታቸው አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ለፈጠራና ለምርምር ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶችን ለዚህ ማሳያ አርገን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በየዓመቱ የግልም ሆነ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቤቶቹ የተሰሩ የፈጠራና የምርምር ሥራዎችን በክፍለ ከተማ ደረጃ ለውድድር እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ ከእነዚያ ውስጥ የተሻሉትና በውድድሩ ያሸነፉት የፈጠራ ሥራዎች ደግሞ በከተማ ደረጃ እንዲወዳደሩ በማድረግ የፈጠራ ሥራዎች በመደገፍ እንዲበረታቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በክፍለ ከተማ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ውድድር በቅርቡ ደግሞ በከተማ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት 8ኛው ከተማ አቀፍ ‹‹በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የዳበረ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል አውደ ርዕይ ተካሄዷል፡፡ በአውደ ርዕዩ ከመንግስትና ከግል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎችና መምህራን የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል።
የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል ተማሪ በረከት ጌቱ አንዱ ነው። የቤተል ሕዳሴ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ የሚናገረው ተማሪ በረከት በርከት ያሉ የፈጠራ ሥራዎችን ይዞ ቀርቧል። በረከት የባዩሎጂ፣ የኬሚስትሪ፣ የአይ ሲቲ እና የፊዚክስ ትምህርት ዘርፎች የሚመለከቱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ሰርቶ ለእይታ አቅርቧል፡፡ በኮምፒዩተር ለመቆጣጠር የሚቻል ታንክ፣ ዘመናዊ የማስተማሪያ ዘዴ መጠቀም የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎች ለእይታ ካቀረባቸው ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ተማሪ በረከት በተለይ በፊዚክስ የትምህርት ዘርፍ ከሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች አንዱን ስንመለከት የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሮቦት ነው፡፡ ሮቦቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ በተለይ የአእምሮ ውስንነት ላለባቸው (ለኦቲዝም) ህሙማን ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው የሚናገረው፡፡
አሁን ላይ በሀገራችን የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው (ኦቲዝም) ህሙማን ሰዎች ለብቻቸው ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከል እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን የሚያነሳው ተማሪ በረከት፤ ይሁን እንጂ ህሙማኑ ባሉበት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ የሚያሟሉላቸውን የሮቦት ሞግዚቶች ብንጠቀምላቸው የተሻለ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ <<ይህንን የሮቦት ፈጠራ ለመሥራት ያነሳሳው በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሲቸገሩ ሲመለከት የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅሞ የሚችለውን ቢያደርግ ችግራቸውን በተወሰነ መልኩም ቢሆን መቅረፍ እንደሚችል በማሰቡ መሆኑን ይገልፃል፡፡
የሮቦት ሞግዚቱ የአእምሮ ውስንነት ላለባቸው ወገኖች ከሰዎች የተሻለ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሊሰጥ የሚችል እንደሆነ የሚጠቁመው ተማሪ በረከት፤ ሮቦቱ በአማርኛ፣ በአፍን ኦሮሞ፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንዲያወራና መልስ እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ይናገራል፡፡ የሰዎችን ስሜት (የተለየ ባሕሪ) ተመልክቶ ሙሉ በሙሉ በመቅዳት (ስካን) የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው ወገኖች ከዚያ ስሜት ውስጥ እንዲወጡ የሚያደርጉ ሙዚቃዎችን፣ ፊልሞችና ታሪኮችን በማሳየትና በመንገር እንደሚያጫውት ነው ያብራራው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ለምሳሌ በራሳቸው ላይ አደጋን ሊፈጽሙ ሲሉም ሆነ በሌሎች አካላት አደጋ ሲፈጽምባቸው ለሚመለከተው አካል ደውሎ በማሳወቅ በቀላሉ እንዲጠበቁ የሚያደርግ መሆኑንም ያስረዳል፡፡
ተማሪ በረከት እንደሚለው፤ ሮቦቱ ሌላም ተጨማሪ አገልግሎትን ይሰጣል፤ ለማስተማሪያነትም ያገለግላል፡፡ በተለይ ለሕጻናት በቀላሉ በጨዋታ እያዋዙ ለማስተማር ያስችላል፡፡ ተማሪዎቹ መምህሩ ከሚያስተምራቸው ይልቅ በሮቦት ቢማሩ የመማር ፍላጎታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ይላል፡፡ አሁን ላይ ሮቦቱ ሰላምታ መስጠትና ሲጠሩት ወደ ተጠራበት ቦታ መሄድ እንዲችል ተደርጎ ነው የተሰራ፡፡ ይህ የሮቦት የፈጠራ ስራ ከወዳደቁ ቁሶች የተሰራ ሲሆን፣ የሚሰራውም በባትሪ ነው። ባትሪው አንድ ጊዜ ቻርጅ ከተደረገ ቀኑን ሙሉ አገልግሎት መስጠት ይችላል።
የፈጠራ ሥራዎችን ከልጅነቱ መሞከር ደስ ይለው እንደነበር የሚናገረው ተማሪ በረከት፤ ይህ የሮቦት የፈጠራ ስራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በየጊዜው ለውጦች እያሳየና እያደገ መምጣቱን ይናገራል፡፡ በቀጣይም ይህንን የፈጠራ ስራ እያሻሻለ ለትልቅ ደረጃ እንደሚያበቃውና ሌሎች አዳዲስ ሥራዎችን ለመስራት ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ የፈጠራ ስራዎቹን እንዲህ ባለ በአውደ ርዕይ ማቅረብ ለቀጣይ ሥራዎች ከዚህ የበለጠ እንዲሰራ ሞራልና ጉልበት እንደሆነውም ይገልጻል፡፡
ሌላኛዋ የፈጠራ ባለሙያ ከእቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት የመጣችው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዋ እየሩሳሌም ታደሰ ስትሆን፣ የወዳደቁና የማይፈለጉ ፕላስቲኮች በመጠቀምና በቀላሉ ከሚገኙ ነገሮች የተሰራ እጅ ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች ጸጉራቸውንም ሆነ ገላቸውን መታጠብ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ነው ይዛ የቀረበችው፡፡
ተማሪ እየሩሳሌም እንደምትለው፤ ይህ የፈጠራ ስራ እጅ ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች አገጫቸውን በመጠቀም ማብሪያና ማጠፊያውን ተጠቀመው ገላቸውን መታጠብ ያስችላቸዋል፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ እጅ ለሌላቸው አካል ጉዳተኞች ካለምንም የሰው እርዳታ ሳሙናና የገላ መታሻ እንዲሁም ለጸጉር መታጠብና ማበጠር የሚሆን ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ያሟላ ሲሆን ፀጉራቸውንም ሆነ ገላቸውን በቀላሉ መታጠብ የሚያስችላቸው የፈጠራ ውጤት እንደሆነ ታብራራለች፡፡
የፈጠራ ስራው በቀላሉ ከማይፈለጉ ቁሳቁስ የተሰራ መሆኑን ተማሪዋ ጠቅሳ፣ ኢኮኖሚን ሳይጎዳ ተጠቃሚ መሆን ያስችላል፤ በጥቂት ውጪ የተሰራ ቢሆንም የሚሠጠው ጥቅም ብዙ ነው ትላለች። በቀጣይም ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችንም ለመስራት እቅዳለች። እንደዚህ አይነት አውደ ርዕዮች ሲዘጋጁ ያላቸውን አቅም የሚያሳዩበትና በቀላሉ ለችግሮች መፍትሔ የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ እድል የሚያመቻች መሆኑን ገልጻለች፡፡ አሁን በእንደዚህ መልኩ የቀረበው የፈጠራ ሥራ እየተሻሻለ ለአካል ጉዳተኞች ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ቢደረግለት ከፍ ባለ ደረጃና ጥራት መስራት እንደምትችል ተናግራለች፡፡
የጄኔራል ታደስ ብሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሰኚ አማኑኤል በበኩሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ይዞ ቀርቧል። ከእነዚህ ውስጥ ተንቀሳቃሽ የስልክ ቻርጅ (ፓወር ባንክ) እና የመኪና ሮቦት ይገኙበታል፡፡ ተማሪው የፈጠራ ሥራውን የሰራው ከተለያየ አገልግሎት ከማይሰጡ ቁሳቁስ ሲሆን፤ በተለይ የስልክ ኃይል መሙያው (ፓወር ባንኩ) ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች የሚሰጠው አገልግሎት ላቅ ያለ እንደሆነ ይናገራል። ፓወር ባንኩ አንድ ጊዜ ኃይል ካጠራቀመ በኋላ ሦስት ስልክ ኃይል መሙላት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሶ፣ ከስልክ ባትሪ በተጨማሪም የእጅ ባትሪ ኃይል ለመሙላት እንደሚያገለግል ይናገራል፡፡
ሌላው የፈጠራ ሥራው የመኪና ሮቦት ነው፤ የቤት ውስጥም ሆነ የመንገድ ላይ ቆሻሻን ለማጽዳት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ እንደ ቤት መኪና ሆኖ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ይናገራል፡፡ የመኪና ሮቦቱ አንድ መኪና ሊኖረው የሚገባው ቁስ በሙሉ የተገጠመለት እንደሆነም ነው የሚገልጸው፡፡
ተማሪ ሰኚ እንደሚለው፤ አሁን በአብዛኛው ለመንገድ ጽዳት ተሰማርተው የሚገኙት እናቶች ናቸው፡፡ ይህ የፈጠራ ሀሳብ መነሻ ያደረገው ደግሞ እነዚህን እናቶች ድካም መቀነስን ነው፡፡ የመኪና ሮቦቱን መንገድ ላይ በመልቀቅ እቤት ውስጥ ሆኖ በዘመናዊ መቆጣጠሪያ የመንገድ ጽዳት እንዲያጻዳ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሮቦቱ ቆሻሻን በመሳብ ወደ አንድ ማከማቻ ማድረስ ይችላል፤ በተገጠመለት ሴንሰር አማካይነት ሰውም ሆነ ሌላ ተሽከርካሪ እንዳይገጨው በመከላከል ያለምንም እርዳታ በራሱ የጽዳት አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በሌላ በኩል ቆሻሻን ከማጽዳቱ በተጨማሪ እንደ መኪናም ሆኖ ለሰዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል። አሁን ላይ የተሰራው የመኪና ሮቦት የጽዳት አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ ላይ ለማድረስና ለመመለስ በሰው የሚሽከርከር መሆኑን ጠቅሶ፣ በቀጣይ በሚገጠምለት ሶፍት ዌር አማካይነት በራሱ ቦታው ድረስ በሚሄድ የሚታዘዘውን ትዕዛዝ እንዲፈጽም ለማድረግ ማቀዱን ነው ተማሪ ሰኚ የሚናገረው፡፡
ተማሪ ሰኚ ይህንን የፈጠራ ስራ ለመስራት መነሻ ያደረገው እናቱ ሁልጊዜ ቤት ለማጽዳት የሚደርስባትን ድካም ነው፡፡ ፈጠራውን በቀላሉ ማጽዳት የሚችል ነገር መፍጠር አለብኝ ብሎ እንደጀመረ ጠቅሶ፣ እያሳደገ እስከ መንገድ ጽዳት እንዲደርስ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡ የመኪና ሮቦቱን ፈጠራ ሥራ ለማሳደግና ወደተግባር እንዲገባ ለማድረግ ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት ድጋፍ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ በትልቁ ሠርቶ ለውጤት እንደሚያበቃው ጽኑ እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡
“ይህ የመኪና ሮቦት የሰው ጉልበት ይቀንሳል፤ በቆሻሻ ምክንያት ለተለያየ በሽታ የሚጋለጡ ሰዎችን ከበሽታ ይታደጋል” የሚለው ተማሪ ሰኚ፤ የፈጠራ ውጤቶችን መስራቱ ከውጭ የሚገቡትን በአገር ውስጥ መስራት እንደሚቻል የሚታይበት በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ይላል፡፡ ይህንን የፈጠራ ሥራ ለማውጣት በብዙ ድካምና ልፋት ውስጥ እንዳለፈ በማንሳትም በዚህ ውስጥ ማለፉ ደግሞ ብዙ ትምህርት እንዲያገኝ በማድረግ ብርታትና ጥንካሬ እንደሆነውም ይናገራል፡፡
በጄኔራል ታደሰ ብሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የባይሎጂ መምህር የሆኑት መምህር ስዩም ጥሩነህ በትምህርት ቤቱ በሚገኙ ላብራቶሪዎች ውስጥ በተለይ የኬሚስትሪ መምህራን የተለያዩ ኬሚካሎችን ቀይጠው የሚለዩበት ማሽን ስለሌላቸው ይህንን ችግር መነሻ በማድረግ የፈጠራ ሥራ መስራታቸውን ይናገራሉ። መምህር ስዩም የሰሩት የፈጠራ ስራ አሮጊ የቡና መፍጫ ማሽን በመጠቀምና ዲናሞ በማስገባት የፕላስቲክ የውሃ ኮዳዎችንና ሌሎችንም ቁሳቁስ በአንድ ላይ አቀናጅቶ በመጠቀም ኬሚካሎችን መቀየጥ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ መስራት መቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡
መምህሩ እንደሚሉት፤ የዚህ የፈጠራ ሥራ አገልግሎቱም አንደኛው “ሶዲየም ክሎራይድና ሲልቨር ናይትሬት” አንድ ላይ ቀላቅሎ ሲልቪር ክሎራይድ ለማግኘት የሚደረገውን ሂደት የሚያቀል ነው፡፡ ሁለተኛ አገልግሎቱ ደግሞ በሕክምና ተቋማት ላብራቶሪ ምርመራ ውስጥ ደም፣ ሽንት እና የመሳሳሉትን የላብራቶሪ ምርመራ ለማድረግ አስፈላጊውን ምርመራ የሚካሄደበት የደምም ሆነ ሌሎች የምርመራ አይነቶች ከተሰጡ በኋላ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መመርመር ያለበት የደምም ሆነ የሌሎች ነገሮች የበሽታ መንስኤ በቀላሉ ለመለየት የሚረዳ ነው፡፡
የፈጠራ ሥራው አሁን ላይ በትምህርት ቤቱ ላብራቶሪ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ የሚናገሩት መምህሩ፤ እንዲህ አይነቶች የፈጠራ ውጤቶች ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በእጅ መንካት የማይቻሉ ኬሚካሎችን ቀላቅሎ ለተማሪዎች በተግባር ለማሳየት የግድ የላብራቶሪ ውስጥ መገኘት ያለበት ቁስ ማግኘት ካልተቻለ ከባድ ስለሚሆን ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመፈለግ የግድ ስለሚል ነው፡፡ ይህንን የፈጠራ ሥራ የወጣው ውጪ ዲናሞ ለመግዛት የዋለ ብቻ መሆኑን ተናግሯል
ተማሪ ኤልሮሄ ፊሊሞን፣ ለአለምታዬ ብርሃኑ እና እዩኤል ሞገስ የተባሉት የፋውንቴን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያቀረቡት የፈጠራ ውጤት ደግሞ የግብርና ሥራን የሚያቀልና ዘር የሚዘራ ሮቦት ነው፡፡ የፈጠራው ውጤት አውቶማቲክ የሆነ ዘዴን ተጠቅሞ ዘር ለመስራት የሚያስችል ሲሆን፤ ይህ የፈጠራ ሥራ በቀላሉ እስከ አስር ሄክታር መሬት ድረስ መዝራት የሚያስችል እንደሆነ ተወካያቸው ተማሪ አልሮሄ ይገልፃል፡፡ የፈጠራ ሥራው ዘር ከመዝራት በተጨማሪም ለመስኖ አገልግሎት፣ የተባይ መድኃኒት ለመርጨት፣ ምርቱን ለመሰብሰብ የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ሲሆን በቀጣይም ማረስ እንዲችል የሚያደርጉና ሌሎችም የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች እንደሚገጠሙለት አስረድቶናል፡፡
“ይህንን የፈጠራ ሥራ የጀመርነው በሀገራችን ኋላቀር የሆነውን ግብርና ማዘመን ብንችል ድህነትን ለመቀነስ እንችላለን በሚል ሀሳብ ነው” የሚለው ተማሪ ኤልሮሄ፤ ተግባራዊ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እያሻሻሉ እና እያሳደጉ የመጡት ብዙ ነገር እንዳለም አስረድቶናል፡፡ በቀጣይም የፈጠራ ሥራቸውን ከዚህ የበለጠ አሳድገው ለአርሶ አደሩ እንዲተላለፍና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እንደሚሰሩም ይናገራል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015