መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ ካሉ ከ49 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ86 በመቶ በላይ የአንደኛ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ እንዲሁም ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ-ልማቶች በተሟላ ደረጃ የላቸውም።
ለምሳሌ፣ በአገሪቱ ካሉት ትምህርት ቤቶች 33 ነጥብ ሁለት በመቶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 55 ነጥብ67 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት አላቸው። 37 በመቶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 43 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የመፀዳጃ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው።
29 ነጥብ አራት በመቶ አንደኛ እና መካከለኛ 74ነጥብ አምስት በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ የተቀሩት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የትምህርት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ ፈታኝ አድርጎባቸዋል።
ይሄ ደግሞ ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ እንዲማሩ ያስገደዳቸው ከመሆኑም በላይ፤ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሚጠበቅባቸውን እውቀት፣ ክህሎትና የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንዳይችሉ አድርጓል።
ከዚህ አኳያ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ጥናት እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳዩ ሲሆን፤ በ2014 ዓ.ም የተደረገው አገራዊ ፈተና ውጤትም ለዚሁ ማረጋገጫ የሰጠ ሆኗል።
ይሄ የጥራት ችግር ለመንሰራፋቱ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም፤ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ ያለመሆንን የሚመለከተው እና የአገራችንን ትምህርት ቤቶች ደረጃ አልባ ያደረገው የትምህርት ቤቶች ግብዓትና መሰረተ ልማት አልቦነት ነው።
ይሄ ሃቅ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ነገን እውን ለማድረግ አቅደው እየተጉ ያሉትን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞን የሚፈትን ነው። ምክንያቱም ትምህርት ለሰው ልጆች የእውቀትም፣ የክህሎትም፣ የሥነ ምግባርም፣ በጥቅሉ ከፍ ያለ የሰው ልጅን ምሉዕነት የመፍጠሪያ አውድ እንደመሆኑ፤ ይሄንን ምሉዕነት መፍጠር የማይችሉ ትምህርት ቤቶችን ይዞ የብልጽግናውን ግብ ለማሳካት የሚደረገውን ጉዞ በብቃት የሚያሳልጥ ትውልድ መፍጠር አይቻልም።
በመሆኑም ይሄንን ጉዞ ለማሳለጥ፣ ለዚህ የሚሆን ትውልድን በትምህርት ቤቶች ለመፍጠር ካስፈለገ፤ የእነዚህን ትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፤ በተገቢው ግብዓትና መሰረተ ልማት ማደራጀት እጅጉን አስፈላጊ ነው።
ይሄንንም መንግሥት በተለይም ዘርፉን የሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር ተገንዝቦ እንቅስቃሴ ጀምሯል። ይሁን እንጂ ይሄንን ችግር መፍታት እና እነዚህን ትምህርት ቤቶች የሚፈለገው ደረጃ ላይ የማድረስ ሥራው በመንግሥት አቅም ብቻ በሚፈለገው ጊዜና ሁኔታ እውን ማድረግ አይቻልም።
ይሄን በተመለከተ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ችግሩን በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት ቢታሰብ ከሦስት አስርት አመታት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” እንዲሉ፤ ይህን ሰፊ ችግር መፍታት የሚቻለው ሥርዓት ዘርግቶ በዘላቂነት ሰፊውን ሕዝብ እና ልዩ ልዩ የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ቀጥተኛ ተሣትፎን ያረጋገጠ ንቅናቄ በማድረግ ሊሆን ይገባል።
ከዚህ አንፃር ትምህርት ሚኒስቴር አገር አቀፍ ንቅናቄ የማድረግ እቅድ የያዘ ሲሆን፤ በዚህ ንቅናቄ መሰረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚሰሩ የውስጥም የውጪም ተቋማትና ድርጅቶች፣ በትውልድ ቦታቸው፣ በተማሩበት ቦታ፣ በሚሰሩባቸውና በሚኖሩባቸው አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በሚችሉት መንገድና መጠን አስተዋጽኦ በማድረግ አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ሁኔታ አመቻችቷል።
የዚህ ንቅናቄ ተጠባቂ ውጤትም፣ በማኅበረሰብና በልዩ ልዩ አካላት አስተዋጽኦና ጥረት እያደጉ የመጡ መሠረተ ልማታቸውን (ንጹሕ ውሃ፣ መፀዳጃ ክፍሎች፣ በቂ መማሪያ ክፍሎች፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ፤ የስፖርት ሜዳ፣ መጻሕፍት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ ቤተ-ሙከራ፣ ወዘተ.) ያሻሻሉ ትምህርት ቤቶች በብዛት እንዲኖሩ ማድረግ ነው።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ንቅናቄ ዋና ዓላማ አድርጎ ከተነሳባቸው ጉዳዮች መካከል፤ ትምህርት ቤቶችን ከሦስቱ አበይት ጉዳዮች አንፃር በመገምገምና ችግሮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ትምህርት ቤቶች ያለባቸውን ክፍተቶች በመፍታት የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው። ከእነዚህም መካከል፣ በስታንዳርድ መሰረት የተሟላ ቤተ መጻሕፍት፣ የቤተ-ሙከራ አገልግሎት እንዲሁም የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከላት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የንቅናቄው ንቁ ተሳታፊ በመሆን የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ለማሻሻል፤ እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሂደት በባለቤትነት በመደገፍ የነገ አገር ተረካቢ ትውልዶች በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በሥነምግባርና በሞራል ተገንብተው የሚወጡባቸውን ትምህርት ቤቶች የመፍጠር ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015