ጦርነት እና የተፈጥሮ አደጋ ገፍቷቸው ከአገራቸው ተሰደው ወደ አጎራባች አገራት ስለሚሰደዱ ሰዎች ሲነሳ አፍሪካውያን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በተለይ ተደጋጋሚ የጦርነት ስጋት የሚንዣብብበት ምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ቁጥር በየጊዜው በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሲሆን፤ በምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች መዳረሻ ከሆኑት አገራት መካከል አንደኛዋ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት።
በኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገቡ ስደተኞች ጋር ተያይዞ ከሚሠሩ ተቋማት ዋነኛው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ድርጅት ነው። ተቋሙ መቼ ተቋቋመ ከሚለው ጀምሮ እየሠራ ያለውን ስራ በሚመለከት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ወደ መሃል ከተማ እየገቡ ስለሚሠሩት ሰደተኞች ሕጋዊነት ጉዳይ አንስተን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛን ጠይቀን ምላሻቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንዴት እና መቼ ተቋቋመ ከሚለው እንጀምር
አቶ ተስፋሁን፡– ተቋሙ መቼ እና እንዴት ተቋቋመ የሚለውን ለመመለስ በአጠቃላይ ከስደተኛ ጋር በተያያዘ የአገራችን የህግ ሁኔታ እና የተቋማዊ ምላሽ ምን ይመስላል? የሚለውን መለስ ብሎ ማየት አስፈላጊ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል እና በማስተዳደር የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላትና ምናልባትም ለሺህ ዓመታት የተለያዩ ግጭቶችን በተለይም ጦርነትን ሸሽተው የሚመጡ ሰዎችን በማስጠለል የምትታወቅ ነች። ይህ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ ከመውጣቱም በፊት የነበረ ሂደት ነው።
ይህ መልካም እና ቀና ተግባር በሕግ ማዕቀፍ መደገፍ የጀመረው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1951 ዓ.ም ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው የስደተኞች ኮንቬንሽን (Refugee convention) ማዕቀፍን ተቀብለው ካፀደቁ ቀዳሚ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ1967 የስደተኞች ፕሮቶኮል (Refugee protocole) እንዲሁም 1969 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የስደተኞች አስተዳደር ዲክላሬሽ አዋጅንም ተቀብላ አፅድቃለች:: እነዚህ ሁሉ ህጋዊ ማዕቀፎች ባሉበት ሁኔታ በተለይም ከ1950ዎቹ ጀምሮ በሶማሊያ እና በሱዳን በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው የመጡ ሰዎችን ስታስተዳደር ነበር።
በዛ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር፤ በኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት ለመክፈት የመጡበት ጊዜ ነበር። እርሱን ተከትሎ ደግሞ በኢትዮጵያ ያሉ ሁኔታዎችን ለመደገፍ በወቅቱ የአገር ግዛት ልዩ ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ በጋራ ሲሰራ ነበር። ይህ ጥንስስ ቀስ በቀስ ሔዶ አሁን ያለውን አገራዊ ተቋም እንዲመሰረት ሆኗል። ስለዚህ ተቋሙ በተለያየ ስያሜ በተለያዩ ተቋማት ስር ሆኖ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የነበረ ተቋም ነው።
ነገር ግን እንደ ተቋም እራሱን ችሎ ሕጋዊ ሰውነት ይዞ የተቋቋመው በ2011 ዓ.ም አገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ነው። በዛ ጊዜ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በሚል በሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል። እንደገና በ2013 ዓ.ም በወጣው የአስፈፃሚ ተቋማትን መልሶ የማቋቋሚያ አዋጅ ደግሞ ስያሜውን በመቀየር የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በሚል ራሱን ችሎ ተቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፡- ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾችን በተመለከተ የምትሠሩት ሥራ ምን ይመስላል?
አቶ ተስፋሁን፡– ስደት ከሚለው ጋር ተያይዞ የሚምታቱ ሶስት ዓይነት መፈናቀሎች አሉ። በቅድሚያ እነርሱን ግልፅ እናድርግ። የመጀመሪያው መፈናቀል አንድ ኢትዮጵያዊ ወይም የማንኛውም አገር ዜጋ ለትምህርት፣ ለሥራ ወይም ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከአገሩ ወደ ሌላ አገር በሚሔድበት ጊዜ ፍልሰት (ማይግሬሽን) ይባላል። ይህ ከቀዬ መሰደድ ቢሆንም ዓላማውም ሆነ ግፊቱ መልካም ነው።
ኢትዮጵያውያን በዚህ እና በሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ከአገር ከወጡ በኋላ ሲመለሱ ከስደት ተመላሽ ይባላሉ። ሌላው ደግሞ ተፈናቃይ ነው። በጦርነት ወይም በተፈጥሮ ችግር ምክንያት ከአንድ የአገሪቷ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚደረግ ጊዜያዊ ወይም ዘላቂ መፈናቀል ነው። ይህ ተፈናቃይ ይባላል። ሶስተኛው ደግሞ ስደት (Refugee) የሚባለው ነው። ስደት የምንለው ከኢትዮጵያ አንፃር የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ በአገራቸው ጦርነት ወይም ግጭት በመከሰቱ እና በግላዊ ማንነታቸው በመሳደዳቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ስደተኞች ይባላሉ።
አሁን ለእነዚህ ስደተኞች ምላሽ መስጠት የእዚህ ተቋም ሥራ ብቻ ነው። የሚደግፍ እና በየዘርፉ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የለም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ላይ ያግዛል። የክልል መንግስታት መሬት ከመስጠት ጀምሮ ፀጥታ ላይም ብዙ ያግዙናል። ሌሎችም ተቋሞች ለምሳሌ ኢሚግሬሽን የሰነድ ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ያግዛል። በዋነኛነት ግን ከጥንስሱ ጀምሮ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም ነው።
ውጭ ጉዳይም ሆነ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ብዙ ተቋማት የሚሰሩት ኢትዮጵያውያን ተመላሾች ላይ ነው። እኛም በተወሰነ መልኩ ብንሠራም በዋናነት የእኛ ኃላፊነት አይደለም። ስደት እና ፍልሰት ተደባልቀው ስለሚታሰቡ እና በአማርኛ ቋንቋ ደግሞ ለሁለቱም ስደት የሚል ቃል ስለምንጠቀም ብዙ ጊዜ ይምታታል እንጂ፤ የስደት ጉዳይ የዚህ ተቋም ሥራ ነው። የፍልሰት ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ በጣም በርካታ አባላት ያሉት በርካታ ተቋማትን የሚያስተባብር እና በርካታ ሥራ የሚሠራ በብሔራዊ ደረጃ ምክር ቤት አለ። ስለዚህ እኔ መግለፅ የምችለው ስደትን ወይም Refugee የተመለከተ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙን ለብቻው በሕግ በ2011 ዓ.ም እንዲቋቋም የገፉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ተስፋሁን፡– ይህንን በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን። አንደኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ቁጥር በጣም እየገፋ በመምጣቱ ነው። በ2019 ዓ.ም የስደተኛው ቁጥር በጣም ጨምሮ ወደ 800 ሺህ የተጠጋበት ጊዜ ነበር። ከዛ በፊት በነበረው በዓለም ደረጃ የሚሠራበት ሁኔታ አልነበረም። በሌላ በኩል የስደተኛን ጉዳይ ዘላቂ በሆነ መልኩ ልማትን እና ሰብዓዊ ድጋፍን ባቀናጀ መልኩ ሁሉን አቀፍ ምላሽ መሰጠት አለበት የሚለው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
እ.አ.አ በ2016 ኒዮውርክ በተካሔደ ስብሰባ ላይ በጣም ከፍተኛ ተሳትፎ ተደርጎበት በዓለም ደረጃ በአገራት መሪዎች የተካሔደ ከፍተኛ ጉባኤ ነበር። የስደት ጉዳይ ዓለም አቀፍ ጉዳይ በመሆኑ ይህንን መልኩን በሚመጥን ደረጃ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል የሚል ሰፊ ውይይት ተደርጎ፤ ብዙ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል። ኢትዮጵያም እንደ አገር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በ2016 በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት በዘጠኝ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ቃል ገብታለች።
በቃሏ መሠረት የስደተኞች ጉዳይ አጠቃላይ ምላሽ ለመስጠት ማዕቀፍ ያስፈልገዋል የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል። ይህንን መነሻ በማድረግ በአገራችን በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ከእነዚህ መካከል የምላሹን ጉዳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ብቻ ላይ ያተኮረ ሳይሆን የልማት አቅጣጫዎችንም ያማከለ እንዲሆን ማድረግን ያካተተ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለስደተኞች የሚሰጠው ምላሽ ለስደተኞች ብቻ ከሆነ ዘላቂ ስለማይሆን ለስደት ተቀባይ ማህበረሰብም ዕርዳታው ያስፈልጋል የሚል ነው።
ይህ ከፍተኛ የአቅጣጫ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ስደተኞችን የሚያስተዳድሩ ክልሎች ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር በኢትዮጵያ ደረጃ ራሱ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ የሚባሉ ናቸው። እነዚህ ክልሎች ካላቸው ትንሽ ሀብት አቋድሰው ለስደተኞች የሚያካፍሉ ከሆነ፤ እነርሱንም የሚያግዝ መሆን አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል። ኤጀንሲው በመምሪያ ደረጃ በሚሰራበት ጊዜ መጀመሪያ ሥራው ጊዜያዊ ድጋፍ ላይ ብቻ ነበር። ከጊዜያዊነት በተጨማሪ ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ተቋሙ መቀየር ነበረበት። በተጨማሪ ወቅቱ በአገር ደረጃ የተቋማት ሪፎርም ሲካሔድበት ነበር።
ስለዚህ ተቋማትን በአዲስ መልክ የሚያቋቁመው የአስፈፃሚ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጅ ሲወጣ፤ ከዋና መምሪያነት ወጥቶ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሆኖ እንዲወጣ ገፊ ምክንያት ሆኗል ማለት ነው። ስለዚህ ተቋሙ በተናጥል የተቋቋመበት ምክንያት አንደኛው የስደተኞች ቁጥር መጨመር፣ በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው ትኩረት እና ኢትዮጵያም በዓለም ደረጃ የገባቻቸው ቃልኪዳኖች ጊዜያዊ ምላሽ ላይ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሔ ላይም ያተኮሩ ስለነበሩ እነርሱን በሙሉ ባቀናጀ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞች በኢትዮጵያ አሉ። በዋነኛነት ወደ 400ሺህ የሚጠጉት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ናቸው። ከደቡብ ሱዳን በመቀጠል የሶማሊያ 320 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች አሉ። ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራ፣ ሱዳን እና በአነስተኛ ቁጥር ጎረቤት ካልሆኑ አገራትም ጭምር የመጡ ከ26 አገራት የተወጣጡ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በተቋቋሙ የስደተኛ ጣቢያዎች በርካታ ስደተኞች ያሉት ጋምቤላ ሲሆን፤ በመቀጠል ሱማሌ ከዛም አፋር እንዲሁም አማራ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ስደተኞችን እያስተዳደሩ ያሉ ክልሎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ስደተኛን የማስተዳደር ሂደት ውስጥ ሥራዎችን ስታከናውኑ እያጋጠማችሁ ያለው ችግር ምንድን ነው?
አቶ ተስፋሁን፡- በኒውዮርኩ የ2016 ዓ.ም ጉባኤ ላይ ዋናው የተቀመጠው አቅጣጫ የስደት ጉዳይ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነው የሚል ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ በርካታ ስደተኞችን የሚያስተዳድሩ አገራት ራሳቸው በልማት ወደኋላ የቀሩ እና ብዙ ችግሮች ያሉባቸው አገሮች ናቸው። ስለዚህ ያደጉ እና የበለፀጉ አገራት እነዚህን ብዙ ሳይኖራቸው ብዙ ስደተኞችን እያስተዳደሩ ያሉ አገራትን የመደገፍ ሞራላዊም ሕጋዊም ግዴታ አለባቸው የሚለው ነው።
ስለዚህ በጣም መሠረታዊ ሆኖ የወጣው የጋራ ኃላፊነት እና የጋራ ተጠያቂነት የሚል መሠረታዊ መርህ መጥቷል። ይህ ደግሞ ለስደተኞች በሚሰጥ ምላሽ ላይ የተለያዩ አካላት ምላሽ መሰጠት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ከዚህ አንፃር የተለያዩ አካላትን መለየት ይቻላል። የመጀመሪያዎቹ ለስደተኞች ምንጭ የሚሆኑ አገራት ናቸው። ሁለተኛዎቹ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አገራት ሲሆኑ፤ ሶስተኞቹ ከተቀባይም ከምንጭም የተለዩ ያደጉ አገራት ናቸው። አራተኞቹ ደግሞ ደጋፊ አካላት ናቸው። ለምሳሌ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ስደተኛ ሲመጣ፣ ደቡብ ሱዳን ራሷ ኢትዮጵያ፣ አሜሪካን እና የዓለም ባንክ ይህንን ችግር ከመፍታት አንፃር ኃላፊነት አለባቸው።
ከኢትዮጵያ አንጻር ኮቪድ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር ከጎረቤት አገር ጦርነት ሸሽተው ለሚመጡ ሰዎች ከለላ በመስጠት ለገባነው ቃል ኪዳን እና ለኖረው ታሪካችን ታማኝነትን አሳይተናል። ነገር ግን አሁን ካለው ስደተኛ አንፃር ከደጋፊ አገራት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኘው ድጋፍ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም። ምክንያቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጀት እየቀነሱ እና ትኩረታቸውን ወደ አዳዲስ ግጭቶች እየሆነ ነው። ለምሳሌ የዛሬ ዓመት አካባቢ ትኩረት የሚሰጠው ለአፍጋኒስታን ጉዳይ ነበር።
አሁን ደግሞ የዩክሬን ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ምክንያት የሚፈለጉ ድጋፎች ወደ አፍሪካ ፣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲባል እያነሰ እየሔደ ነው። የሚሰጠው ድጋፍ እያነሰ ስደተኛው ግን እየጨመረ ነው። ተፈጥሯዊ እድገቱ እና በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ አዳዲስ ግጭቶች የስደተኛው ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው። የድጋፉ ቁጥር ግን በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ነው። እናም እነዚህ ነገሮች ጫናውን የበለጠ ወደ ተቀባይ አገራት እያደረጉ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ አገራት ስደተኞች መሃል ከተማ ሥራ ከመስራት በተጨማሪ በልመና ላይ ተሰማርተው ይታያሉ። ይህ የሆነው ተገቢው ድጋፍ ባለመገኘቱ ነው?
አቶ ተስፋሁን፡- ከላይ ኢትዮጵያ ኒውዮርክ ላይ በ2016 ቃል ኪዳኖችን እንደገባች ገልጫለሁ። ኢትዮጵያ ከገባቻቸው ዘጠኝ ቃል ኪዳኖች መካከል አንዱ ከሚኖሩት ስደተኞች ለ10 በመቶዎቹ በከተማ የመኖር ፍቃድ መስጠት ነው። ይህም ስደተኞች ከተማ መኖር ይችላሉ ተብሎ ሲታመን ከተማ እንዲኖሩ ይፈቀዳል። በአዋጃችንም በዝርዝር ከተቀመጡ ጉዳዮች አንዱ ሕጋዊ አካሄዱን ተከትለው ሥራ የማግኘት መብት አላቸው።
በእዚህ አግባብ መሠረት በብዛት ከኤርትራ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች የተወጣጡ የከተማ ስደተኝነት ፈቃድ ይዘው የሚኖሩ 80 ሺህ ስደተኞች አሉ። ነገር ግን አዲስ አበባ ያሉት እነዚህ ብቻ አይደሉም። ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ወይም በህጋዊ መንገድ መጥተው ነገር ግን እንዲሁ እየኖሩ ያሉ ሌሎች በሕግ ቋንቋ ስደተኛ ተብለው ያልተመዘገቡ ግን ዝም ብለው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች አሉ። የእነዚህን ጉዳይ የሚመለከተው የውጭ ዜጎች ቁጥጥር ኢሚግሬሽን ነው። በዚህ ላይ ከኢሚግሬሽን ጋር እየሠራን ነው።
በዋናነት ሕጋዊዎቹን በሚመለከት 80 ሺ የሚሆኑት ከተማ የመኖር ፍቃድ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሙሉ መረጃቸው እና መገኛቸው የታወቀ ነው። ከሥራ ጋር በተያያዘ በህጋዊው መንገድ ሥራ ለመስራት ይፈቀድላቸዋል። መጀመሪያ ሥራ ስላገኘሁ ይፈቀድልኝ ብለው ያመለክታሉ። እኛ ህጋዊ ስደተኛ መሆናቸውን አጣርተን መረጃቸውን አገናዝበን ለስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የድጋፍ ደብዳቤ እንጽፋለን። እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት እፈልጋለሁ የሚልን አጣርቶ ተገቢ ነው ብሎ ሲያስብ የሥራ ፍቃድ ይሰጣቸዋል። ከዛ ውጭ ግን የታክሲ አገልግሎትም ሆነ የፀጉር ቤት ሥራ የመሳሰሉትን ለመሥራት ሕጋዊ የሆነውን ሂደት ተከትለው ወይም ይህን ሂደት ሳይከተሉ እንዲሁ ፍቃድ ሳያገኙ የሚሠሩ ስለመኖራቸው መታወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ለዚህ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?
አቶ ተስፋሁን፡- ሕጋዊ ስደተኞችን በተመለከተ የእኛ ኃላፊነት ነው። የመጡት ስደተኝነት ፈቃድ ሳይጠይቁ ከሆነ ግን ጉዳዩ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ይሆናል። አንዱ ግልፅ ማድረግ ያለብን ስደተኝነት የሚገኘው አንድ ሰው ወደ ኢትዮጵያ በገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚመለከተው የእኛ ተቋም ቅርንጫፍ ወይም ለፖሊስ ፅህፈት ቤት ለጣቢያ ሔዶ ‹‹እኔ በዚህ ምክንያት ከአገሬ የተፈናቀልኩ በመሆኑ ጥገኝነት መጠየቅ እፈልጋለሁ። ›› ሲል የመጣበት ምክንያት አሳማኝ መሆኑ ተረጋግጦ በሕግ በተቀመጠው የስደተኝነት ትርጓሜ ውስጥ የሚያርፍ መሆኑ ታይቶ እና ተጣርቶ የስደተኝነት እውቅና ይሰጠዋል። ከዚህ ውጭ እንዲሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የሚኖሩ እና ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠሩ ጥገኝነት የመጠየቂያ ጊዜያቸው ያለፈ ከሆነ ጉዳዩ የእኛ ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ሚሊየን ስደተኛ በጣም ብዙ ነው። ይህንን ያህል ሕዝብ ማስተዳደር ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር ጫና አልፈጠረባትም?
አቶ ተስፋሁን፡- የስደተኞች ምላሽ ላይ የመንግስት ሚና እነርሱን መመዝገብ፣ ማስተዳደር፣ መሬት ማዘጋጀት እና መሬት ላይ እንዲሰፍሩ ፍቃድ መስጠት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሕግ አግባብ መሠረት የሥራ ፍቃድ፣ ስልክ ማውጣት፣ መንጃ ፍቃድ ማውጣት የመሳሰሉትን የሚጠይቁ ከሆነ እርሱን በሕግ አግባብ ማመቻቸት የመንግስት ሚና ነው። ከዚህ ውጭ የእነርሱን ጤና፣ ትምህርት እና ምግብን በሚመለከት የተባበሩት መንግስታት ተቋማት ኃላፊነት ነው።
ስለዚህ ትምህርት ጤና እና የመሳሰሉትን አብዛኞቹን የሚሸፍነው በተባበሩት መንግስታት ዩ ኤን ሲ ኤች አር አማካኝነት ነው። ምግብን በተመለከተ ወጪውን የሚሸፍነው የዓለም ምግብ ድርጅት ነው። መንግስት ላይ ጫና እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል። አንዳንዴ ከዓለም ድርጅቶች ድጋፍ መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚደርሳቸው የምግብ ድርሻ አንዳንዴ ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ያጋጥማል።
አዲስ ዘመን፡- ቀጠናው አካባቢ የሚፈጠር ቀውስ ኢትዮጵያ ላይ የፈጠረው ጫና ካለ እና ከስደተኛ ቁጥር ጋር በተያያዘ ያለውን ለውጥ በሚመለከት ያብራሩልኝ።
አቶ ተስፋሁን፡– የእኛን ሥራ ለየት የሚያደርገው፤ ምላሽ የምንሰጠው አገር ውስጥ ለተፈጠረ ጉዳይ ሳይሆን ሌሎች አገሮች ላይ ለተፈጠረ ችግር ነው። ስለዚህ ጎረቤት አገር ላይ ግጭት ሲፈጠር የሰዎች መፈናቀል ይከሰታል። ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ለእነሱ ምላሽ በመስጠት እንጠመዳለን። በቅርቡ ለምሳሌ የካቲት ወር አካባቢ በሶማሊያዋ ላስአንኦድ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሶማሊያውያን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል። በኢትዮጵያ ከሶማሊያ ለመጡ 91ሺ ስደተኞች ምላሽ እየሰጠን ነው። እነዚህ ስደተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድን አቋቁመን ምዝገባውን አከናውነን፣ ድጋፉንም ከተለያዩ ተቋማት በማሰባሰብ ምላሽ እየሰጠን ነው። ልክ እርሱ መልክ መያዝ ሲጀምር ደግሞ የሱዳን ግጭት ተከሰተ።
የሱዳን ግጭትም በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ሰዎችን ሊያፈናቅል የሚችል እንደሆነ ይታወቃል። በአንድ በኩል ሱዳን ትልቅ አገር ነች፤ ብዙ ሕዝብ አላት። ከሕዝቧ ሌላ ብዙ ስደተኞችም የሚኖሩባት ናት። ብዙ ኢትዮጵያውያንም በሱዳን ይኖራሉ። ስለዚህ ዓይነተ ብዙ ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሊሰደድ እንደሚችል በማሰብ ከፍተኛ ዝግጅት አድርገናል። በሁለት የኢትዮጵያ በሮች ሱዳናውያን ተሰደው እየመጡ ነው። በዋነኝነት በአማራ ክልል በመተማ እና በቤንሻንጉል ክልል ኩርሙክ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በኩል የሚገቡ አሉ። የተወሰኑ ደቡብ ሱዳናውያን ደግሞ በጋምቤላ በኩል የመግባት ሁኔታ አለ።
በሶስቱም ቦታዎች ዝግጁ የሆነ ቡድን አለ። ኢትዮጵያውያንን ሳንቆጥር ወደ 7ሺህ የሚሆኑ የሌሎች አገር ዜጎች አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ጥገኝነት እየጠየቁ ነው። አሁንም እንደ አዲስ ጦርነቱ እያገረሸ ስለሆነ፤ ቁጥሩ ከዚህም የባሰ ሊሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ። ጦርነቱ ከቀጠለ ሰው መፈናቀሉ እና መሸሹ የማይቀር ነው። ጦርነቱን ተከትሎ ደግሞ ከሚመጡባቸው መዳረሻዎች መካከል አንዷ መዳረሻ ኢትዮጵያ ስለሆነች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ አንፃር ያለው መሠረታዊ ችግር በ2023 ዓ.ም ስንጀምር ከዓለም አቀፍ ተቋማት የነበረው በጀት በጣም ትንሽ ነበር። ያችኑ በጀት ተጨማሪ 91ሺ ከሶማሊያ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 7ሺህ ከሱዳን ለማስተናገድ ተጠቅመንበታል።
ይህም ሥራችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ከሆኑ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምላሹ ፈጣን እንዲሆን እና በተቻለ መጠን ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ወንድማማችነትን በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራን ነው። እንደጥሩ ተሞክሮ ለማንሳት ያህል የሶማሊያው ግጭት ሲፈጠር ከአዲስ አበባ በጣም ሩቅ ነው። የመጀመሪያው ምላሽ ሰጪዎች እዛው አካባቢ ያሉ ሕዝቦች ናቸው። ያው ሁሉም በቋንቋም በሃይማኖትም መወራረስ ብቻ ሳይሆን አብረው የኖሩ ስለሆኑ ካለችው ላይ ትንሽም ቢሆን እያካፈሉ ሲኖሩ ነበር።
ሱማሊያ እንደምናውቀው ላለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ድርቅ ያጠቃው፤ ዝናብ ያልዘነበበት አካባቢ ቢሆንም ያለቻቸውን እያጋሩ ያቆዩዋቸው መሆኑ በተቋም ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ሳይቀር የሚያኮራ ነው። እኔም ይህን ማድረግ እችላለሁ የሚል መንፈስን የሚፈጥር ነው። ይህንን የሕዝቦችን ቀናነት እንደተቋም በማንፀባረቅ ለማስቀጠል እናስባለን። የተቋማችን መሪ ቃልም ኢትዮጵያዊ እጆች ለሰብዓዊነት የሚል ነው። ታሪካችንን የመቀጠል እና የማስቀጠል ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሚጨምሩት ካለ መልዕክት ማስተላለፍ ይችላሉ።
አቶ ተስፋሁን፡– የዛሬ አራት ዓመት እ.አ.አ በ2019 ዓለም አቀፍ መድረክ ተካሂዶ ነበር። መድረኩ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መድረክ የሚባል ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የመድረኩ ተባባሪ ሆና ከሌሎች አራት አገራት ጋር ሰብሳቢ ነበረች። በጣምራ ሰብሳቢነት ግንባር ቀደም ተደርገው ሊጠቀሱ የሚችሉ ቃል ኪዳኖችን ገብታለች። ትምህርት፣ የሥራ ዕድል፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የስደተኞች መብት አስተዳደር ከገባቻቸው ቃል ኪዳኖች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው።
ቃል ኪዳኖችን ተከትሎ በ2011 የስደተኞች አዋጅ እንደ አዲስ ወጥቷል። በዛ አዋጅም ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ እስከገቡ እና እስከተዳደሩ ድረስ መንጃ ፈቃድ የማግኘት፣ የባንክ የሒሳብ ቁጥር የማውጣት፤ በሕጋዊ መንገድ ሥራ የማግኘት ዕድሎች አላቸው። በተጨማሪ ልደት፣ ሰርግ እና ሞት እንደማንኛውም ዜጋ በወሳኝ ኩነት እንዲመዘገብ የሚፈቅድ አዋጅ አውጥታለች። እርሱን ተከትሎ ተቋማችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎች ሰርቷል። በቀጣይ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ በታኅሳስ ወር አካባቢ የመጀመሪያው የዓለም የስደተኞች መድረክ ማጠቃለያ እና የሁለተኛውን መድረክ ማስጀመሪያ ይካሄዳል።
ይህ መድረክ በዓለም ደረጃ በአገራት መሪዎች ደረጃ የሚካሔድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቃል በገባችባቸው ቃል ኪዳኖች ዙሪያ ያገኘቻቸውን ግኝቶች፣ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች እና በቀጣይም ልትወስዳቸው ያሰበቻቸውን አዳዲስ ቃልኪዳኖች የምታስተዋውቅበት እና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ጥረታችንን አይቶ ድጋፍ እንዲያደርግ አስፈላጊው ጥሪ የሚቀርብበት ነው። መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን ዝግጅት በመደረግ ላይ ሲሆን፤ ሰኔ ስምንት የመጀመሪያው መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመድረኩ በርካታ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች፣ ኤምባሲዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ኃላፊዎችም የተገኙበት ሲሆን፤ እስከ አሁን በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች ምን ይመስላሉ፤ በቀጣይስ ምን ምን ጉዳዮች ላይ ቃል እንገባለን በሚለው ላይ ቃል አቅጣጫ የያዝንበት ነው።
በውይይቱም ላይ አገራችን ለታሪኳ እና ለቃሏ ታማኝ ስለመሆኗ በርካታ ሥራዎችን ስለመስራቷ፤ ነገር ግን የዓለም አቀፍ ድጋፍ በሚፈለገው ደረጃ እና ቃል በተገባው ልክ አለመሆኑ ብዙ ተግዳሮቶች እንዲያጋጥሙን አድርጓል የሚለውን ትኩረት ተሰጥቶት አጀንዳ ሆኗል። በተለይ አገሪቷ እንደሚታወቀው ተፈጥሯዊም የሆኑ በርካታ ፈተናዎችን ያለፈችበት ጊዜ ነው። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎችም ውስጥ ሆና ለተቸገሩ ከለላ መሆኗን ቀጥላለች። በቀጣይም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ጥረቷን የሚደግፉ እና የሚያጠናክሩ እገዛዎችን እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋሁን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም