የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን ዓባይን የራሳቸው ንብረት አድርገው ከመመልከት ባለፈ ከፈጣሪ የተሰጠን ስጦታ ነው በማለት እነሱም አምነው የግብጽንም ሕዝብ እስከማሳመን ደርሰው ነበር። በዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ምንም መሥራት የለባትም ብቻ ሳይሆን ካለ ግብጽ ፈቃድም መንቀሳቀስ የለባትም የሚልም እምነት አዳብረው ቆይተዋል።
ይህን ሃሳባቸውን ሥጋ አልበሰው እውነት ለማድረግ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ደግሞ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን ነው። በታሪክ ተዘግቦ እንደምናገኘው በ1902 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም የነበሩት ስምምነቶች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው ወይም የኢትዮጵያን ስምምነትና ይሁንታ ያገኙ ሳይሆን ከቀኝ ገዥዎች ጋር የተደረጉ ስለነበሩ ነው።
በዚህም ዓይነት ግብጻውያን በልበ ሙሉነት የሕዳሴው ግድብ ሊሠራ እንደማይገባ ሲወተውቱ ቆይተዋል። በቻሉት መጠንም የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ ያልሞከሩት ሴራ፤ ያልደረሱበት ቦታ አልነበርም። ነገር ግን ሁሉም ነገር ሳይሳካ ቀረና ግድቡም ተጠናቆ አንደኛውን፣ ሁለተኛውን፣ ሶስተኛውን እና አራተኛውንም ሙሌት ማጠናቀቅ ተቻለ። ይህም ሆኖ ግብጻውያን ግድቡ ከተጀመረም በኋላ በየደረጃው ተቃውሟቸውን ከማሰማት ብሎም ከማስፈራራት ተቆጥበው አያውቁም። ነገር ግን ያልታሰበው ሆነና የሕዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን ትብብርና ተሳትፎ ዛሬ ላይ ደርሶ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በቃ።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት ትሰጥ የነበረው ውሃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈርም ነበር። በዚህ ዓይነት የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ግብጻውያን ከሺህ ዓመት በላይ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። የእነሱ ተጠቃሚነት ዛሬም ባይቋርጥም ኢትዮጵያ ግን የውሃ ሀብትን በመጠቀም ረገድ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በቅታለች። ለመሆኑ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን በማድረግ ሂደት በነበሩት ውጣ ውረዶች እንደ ሀገር ምን ተጠቃሚነት ተገኘ ስንል በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ያላት የውሃ ሀብት እና ተጠቃሚነት እንዴት ይገለጻል?
ፕሮፌሰር መኮንን፡- ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ በሚጠበቀው ደረጃ ሥርዓቱን ጠብቆ ለመጪውም ትውልድ በሚጠቅም መልኩ እየተገለገልንበት አይደለም። የውሃ ሀብት በባህሪው ከተፈጥሮ፤ ከአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች እየቀነሰ የሚመጣ ነው። በመሆኑም ይህንን ከፍተኛ ጥቅም ያለውና ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባ ሀብት በአግባቡ እያበለጸጉ መጠቀም ይጠበቃል። በርግጥ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር በበርካታ ችግሮች ውስጥ መሆናችን ይታወቃል።
ዛሬም ድረስ ለአብዛኛው ሕዝብ በምግብ ራስን መቻል፤ የንጽህና መጠበቂያ እና ንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘት፤ ኤሌክትሪክ አቅርቦትና ሌሎችም እንደ ቅንጦት የሚታዩበት ነው። በጥቅሉ በድህነት ውስጥ እየኖረ ያለው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። ይህንን ችግር ለመሻገርም በመንግሥት በኩል እንደ ሀገር ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል። ተስፋ የምንጥልበትና ብዙ እየተሰራበት ያለው የግብርናው ዘርፍም ከውሃ አቅርቦት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
እነዚህ ሁሉ እቅዶች እውን ሊሆኑ የሚችሉት ግን ውሃን ብቻ ሳይሆን ከውሃ የሚገኘውንም የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ በማልማት መጠቀም ሲቻል ነው። በተጨማሪ ዛሬ ላይ በስፋት እየተሄደባቸው ያሉት ከተሞችን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችም በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እና በቂ ውሃ የሚጠይቁ ናቸው። እንደ አጠቃላይ የውሃ ሀብትን መጠቀም በተለይም ትልልቅ ወንዞችን እየገደቡ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ማመንጨት መቻል ለኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሉዑላዊነትም መጠበቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
ይህም ሆኖ በየዘመኑ የነበሩ የሀገሪቱ መሪዎችም ሆነ ሕዝቡና ምሁራን፤ የውሃ ጥቅምን በአግባቡ ተረድተውት የነበረ ቢሆንም ያሉትን ተግዳሮቶች በአግባቡ መረዳት የተቻለው አገልግሎት ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ሲጀመር ነበር። በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመሥራት ታቅዶ በአሜሪካውያን ጥናትም ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል።
ንጉሱ፣ በወቅቱ ብድር እንዳይገኝ ከማድረግ ጀምሮ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸው ስለነበር ሊሳካላቸው ባለመቻሉ «እኛ ባይሳካልን ወደፊት ልጆቻችን ይሰሩታል ይቀመጥ» ብለው ነበር ጉዳዩን በእንጥልጥል ያቆዩት። እነዚህ በጣም ከፍተኛና የተወሳሰቡ ሴራዎች ኢትዮጵያ ብዙ የተዘፈነለትን ዓባይን አልምታ አቅም ፈጥራ ወደ ሌሎች ወንዞችና የውሃ ሀብቶቿ እንዳታማትር እንቅፋት ሆኖባት ቆይቷል።
ዛሬም ድረስ ግብጽና ሱዳን በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ልማት እንዳይከናወን እንደ ሀገራቸው ፖሊሲ በማድረግና ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሠሩ ይገኛል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጀመር እነዚህን በስውርና በተለያየ አካሄድ አሻጥር ሲሰሩ የነበሩ ሴረኞችን ግልጽ አውጥቷል።
በርግጥ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት እንደሚቻል ይታወቃል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዘላቂ የሆነው መፍትሔ የሚገኘው ከውሃ በምናመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚወሰን ይሆናል። ይህም ሆኖ ትልልቅ ግድቦችን በመሥራት ኃይል ለማመንጨትና ለመስኖ ለማዋል በአግባቡ እንዳንጠቀም ፍላጎቱ ቢኖርም የተለያዩ ተግዳሮቶች ነበሩብን። ከዚህም ውስጥ የአቅም ውስንነት ቀዳሚው ነበር።
አቅም ስንል በዚህ ረገድ በጥቅሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ የቴክኖሎጂና ከፍተኛ የበጀት እጥረት ነበረብን። ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት እንደ አማራጭ ሲወሰድ የነበረው ወደ ውጭ መመልከት ነበር። ከውጭ ሀገራት የሚጠበቁ አቅሞች በተለይም ብድር ደግሞ በቀላሉ የማይገኝ ሲሆን ቢገኝም ይዞት የሚመጣው መሰናክልም ነበር።
እናም ይህንን ህልም እውን ለማድረግ የነበሩትን ክፍተቶች ማስታረቅ ይጠበቅ ነበር። በአንድ ወገን የራስን የፋይንስ አቅም፤ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ በማሳደግ በራስ አቅም መገንባት ሲሆን ፤ ሁለተኛው በዲፕሎማሲው ጫና ፈጥሮ የሚተባበርና ድጋፍ የሚያደርግ አጋር ማግኘት ነው። ሁለተኛው መንገድ ለረዥም ዘመናት ተሞክሮ ያልተሳካ በመሆኑ አማራጭ የተደረገው ዛሬ የተደረሰበትን ውጤትም ሊያስገኝ የቻለው የራስን አቅም አሟጦ መጠቀም ነበር። ይህም ቢሆን ግን ረዥምና ውስብስብ ሂደቶችን ያለፈ አሰልቺና ፈታኝ ነበር ለማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለማልማት፣ ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር ያላት አቅም እንዴት ይታያል ?
ፕሮፌሰር መኮንን ፡– ኢትዮጵያ ይህንን የሚያህል የውሃ ሀብት ተሸክማ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ማካሄድ የጀመረችው ዘግይታ ነበር ለማለት ይቻላል። በ1970 ዎቹ ዓ.ም በአሁኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የወቅቱ አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ከተመሰረተ በኋላ በርካታ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች መውጣት ጀምረዋል። በወቅቱ በቴክኖሎጂው ግቢ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ይጻፉ የነበሩ ጥቅሶች ምን ያህል ቁጭት እንደነበር የሚያመላክቱ ነበሩ።
በተለይም እንደ መፈክር በየቦታው ተጽፎ የነበረው «የውሃ ሀብታችን ለሀገራችን ብልጽግና ይውላል» የሚለው እስከ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ጥቅስ ለመሆን በቅቷል። ከዛም በኋላ በዘርፉ ትምህርት የሚሰጡና ምርምር የሚያደርጉ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፉ መምጣትና የተለያየ ፕሮግራሞች መከፈት በሰለጠነ የሰው ሀብት ረገድ ያሉትን ክፍተቶች እያጠበባቸው መጥቷል። ከመስኩ ስፋትና ከሚጠበቀው የሰው ኃይል አኳያ ግን ዛሬም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ዓባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያን ተስማምተው ለመጠቀም መሰናክል የሆነባቸው መሠረታዊ ጉዳይ ምንድን ነው ?
ፕሮፌሰር መኮንን ፡- የኢትዮጵያ 70 በመቶ የውሃ ሀብትና ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያሉት በዓባይ ተፋሰስና ወደ ትልቁ ናይል በሚገቡ ወንዞችና አካባቢው ነው። ግብጻውያን «የናይል ውሃ የመኖርና ያለመኖር እጣ ፈንታችንን የሚወስን ነው» እንደሚሉት ሁሉ በአንጻሩ የኢትዮጵያ የማደግና ያለማደግ፤ የመልማትና ያለመልማት እጣ ፈንታም የሚወሰነው በዚሁ ነው። ይህንን በመገንዘብ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ተቀራርበው እንዲነጋገሩ እና መተማመንና ህብረት እንዲፈጥሩ የናይል ቤዝን አንሼቲቭ የሚባል ወደ ሥራ ገብቶ ስምምነት ተፈጥሮ ብዙ ሲሰራበት ነበር።
ይህ ሲደረግ የነበረውም ታላላቅ በሚባሉት ሀገራት በሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ነው። በወቅቱም የነበሩት ደቡብ ሱዳንም ራሱን ችሎ ሲጨመር አስራ አንድ ሀገራት ተቀራርቦ የመነጋገር ፕሮጀክት የመቅረጽ ተግባራት ሲያከናወኑ ነበር። ይህ የተጀመረበት ዋነኛ ምክንያትም የተፋሰሱ ሀገራት የሚካፈሉት የዓባይ ወንዝ ብዙ ውዝግቦችን እንደሚያስነሳ ስለሚታወቅ ሊፈጠር የሚችለውን እሰጥ እገባ በማስቀረት በትብብር ለመሥራት ሲባል ነበር።
በዚህም ውስጥ ሊተገበር የታሰበው ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ እነዚህን የጋራ ውሃዎች በትብብር፣ በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ አጠቃቀም እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያም በዚሁ ማሕቀፍ ውስጥ በመሆን የሕዳሴው ግድብ እንዲጀመር ለማድረግ በቅታለች። ግብጻውያን የሕዳሴው ግድብ እውን መሆን እነሱ ላይ ምንም ተጽእኖ እንደማያመጣ ይልቁንም ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ለጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋቸው ቢያውቁም ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም።
ምክንያታቸው ደግሞ ለዘመናት የዘለቁበትን የበላይነታቸውን የሚያሳጣና ኢትዮጵያን ተከትለው ሌሎች ሀገራት ይጠቅመናል የሚሉትን መሥራት ጀምረው የግብጻውያን የበላይነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ ነበር።
አዲስ ዘመን ፡- የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተጀመረበት ወቅት እና ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ የግብጽና ግድቡን ሲቃወሙ የነበሩ ሀገራት ምላሽ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር መኮንን፡- በዓባይ ግድብ ላይ ዛሬ በመጠናቀቅ ላይ ያለው የሕዳሴው ግድብ ሲጀመር ቀድሞ ከነበረው ሙከራ ሙሉ ለሙሉ በተለየ አካሄድ ነበር። ከዚያ በፊት የተደረጉት ሙከራዎች በገንዘብም በቴክኖሎጂም በሰው ሀብትም ረገድ ምንጭ ሊደረግ የነበረው ከውጭ በመጠበቅ ነበር። ይሄኛው አካሄድ ግን በይፋ ምንም ዓይነት ነገር ርዳታ ሳይጠየቅ ሙሉ ለሙሉ የራስ አቅምን በመጠቀም እውን ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር።
በሌሎች በርካታ ሀገራት በኩል ጅምሩ ከግብ የማይደርስ በእንጥልጥል የሚቀር ነው የሚል ጠንካራ ግምትም ነበራቸው። በአንጻሩ በኢትዮጵያውያን በኩል በግልባጩ የአንድነት የህብረት ማጠንከሪያና በራስ መተማንን ያጎነጸፈ ለመሆን ቻለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዛሬም ድረስ የዘለቀው የመንግሥት ጥሪን ተከትሎ ለሕዳሴው ግድብ እየተደረገ ያለው የሕዝብ ድጋፍ እንደ ታሪክ ተሰንዶ ሊቀመጥ የሚገባው አኩሪ ተግባር ነው።
እ.ኤ.አ በ2010 ብዙዎቹ የናይል ቤዚን ፕሮግራሞችም እያለቁ ሲሄዱ የጋራ ማሕቀፍ የሚባለውን ዶክመንት ለማዘጋጀት በቁ። በዛው ዓመት በግንቦት ወር ስምምነቱን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ ዑጋንዳ በኢንተቤ የፈረሙ ሲሆን፣ ከአምስት ቀን በኋላ ኬንያም ፈረመች። እንዲህ እንዲህ እያለ ቆይቶ በቅርቡም ደቡብ ሱዳን ፈርማ በምክር ቤቷ ለማጽደቅ በመብቃቷ ለኮሚሽን ምስረታው ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው። ይህም ሆኖ ግን የግብጽ መንግሥት ገና ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተመሰረበት ጊዜ አንስቶ ሥራውን ያስቆሙልኛል አልያም ያስተጓጉሉታል ያላቸውን የተለያዩ ጠንካራ ዘመቻዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
እ.ኤ.አ በ2015 «ፕሪንስፕል ኦፍ ዲክላሬሽን» የሚባል ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ተስማምተው ፈርመዋል። እዚያ የስምምነት ዶክመንት ውስጥ የተቀመጠው ሃሳብ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት እንደምትችል ነገር ግን ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎችና መመሪያዎችን እየተጠበቁ እና በትብብር መቀጠል እንዲቻል ማረጋገጫ የሚሰጥ ነበር። ኢትዮጵያ በዛ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኗ የግድቡን ሥራ ብትጀምርም በግብጻውያን በኩል ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መቅረብ ጀመሩ።
ግድቡን እንደ ማስያዣ በመጠቀም ነገር ግን የእነሱን የተለየ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ውሎችን በማንሳት እንዲተገበሩ መወትወታቸውን ቀጠሉ። ከአሜሪካ ጋር በመተባበርም በዓባይ ተፋሰስ ወንዞች ላይ ምንም ሥራ እንዳይካሄድ የሚያደርግ እና ሌሎች ድብቅ ሴራዎችን የያዙ ውል እስከ ማዘጋጀት ደርሰውም ነበር።
በአንጻሩ ደግሞ በወቅቱ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ሁኔታ የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ ከፍተኛ አቅም እየተፈጠረ የነበረበትና ሕዝቡም ከመንግሥት ጎን በመቆም ትልቅ ተሳትፎና ትኩረት የሰጠበት ነበር። ድርድሩን ሲያደርጉ የነበሩትም ኢትዮጵያውያን ይቀርብላቸው የነበረውን የሀገርን ጥቅም የሚነካ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
በተጨማሪ ግብጻውያን ጉዳዩን ለተባበበሩት መንግሥታት ምክር ቤትም በተደጋጋሚ ሲያቀርቡት ነበር። በአንድ ወቅት ግብጻውያን 63 ገጽ አቤቱታ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በሶስተኛው ቀንም ኢትዮጵያ 79 ገጽ የያዘ ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥታለች። የተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤትም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት ወስዳችሁ ተደራደሩበት የሚል ምላሽ ሰጥቷቸዋል።
ጉዳዩ አፍሪካ ህብረትም ከመጣ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ድርድሮች ቢካሄዱም ሊሳኩ አልቻሉም፤ ምክንያቱም ሱዳንና ግብጽ ከላይ እንደተገለጸው ለዘመናት የቆየውን አቋማቸውን መቀየር ባለመፈለጋቸው ነበር። አቋማቸው ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በፍጹም የተቃረነ ውሃ መቀነስ የለበትም፤ የተፈጥሮ ፍሰቱም መቀየር የለበትም የሚል የራሳቸውን የበላይነት የሚያስጠብቅ ብቻ ነበር። ኢትዮጵያ ደግሞ በግዛቷ ውስጥ የሚመነጩ ውሃዎችን ከመጠቀም የሚያግድ ምንም ዓይነት ሕግ ባለመኖሩ በእነሱ በኩል የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሳትቀበል ለመቆየት ተገዳለች።
ከዚህም በኋላ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥና ካይሮ የተጀመረ ውይይት የነበረ ቢሆንም ሊሳካ አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ግብጻውያን ለዘመናት ከዘለቀው ሃሳባቸው የማይላቀቁ በመሆኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
በተለያየ መንገድም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝና መላውን አረብ ሀገር የሚመለከት እንደሆነ ለማስመሰል ያልሞከሩት ቀዳዳ ያልሄዱበት መንገድ አልነበረም። ይህ ሁሉ ሲሆን የግብጽ ባለሥልጣናትና ተደራዳሪዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲገልጹ የነበሩት ኢትዮጵያ ፈቃደኛ አለመሆኗን ነው።
በኢትዮጵያ በኩል ግን በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥም በመሆን በርካታ ድርድሮች እየተደረጉ የግድቡ ሥራ አልተቋረጠም ነበር። በመንግሥት በኩል የተሰጠውም ትኩረት ሕዝቡም ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ ሳይቀዛቀዝ በመቀጠሉ ግድቡ ውሃ ወደመያዝ ለመሸጋገር ቻለ። ያንንም ተሻግሮ አራቱ ተርባይኖች ሥራ ለመጀመር የበቁ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ ሲጀመር የተገባው ቃል እውን ሆኖ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የጎረቤት ሀገራትም ከግድቡ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
ዛሬ ላይ ከግድቡ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለሱዳን ለታንዛንያ የሚቀርብበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል። በቅርቡም ተጨማሪ ተርይባኖች ወደሥራ የሚገቡ ሲሆን፣ ይህም የሕዳሴው ግድብ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንጂ ማንንም ለመጉዳት አለመሆኑ የሚረጋገጥበት መሆን ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ባለፈ ለኢትዮጵያ ምን ትሩፋት ይዞ መጥቷል ለማለት ይቻላል ?
ፕሮፌሰር መኮንን፡- የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ እንደተ ፈተኑበት ሁሉ ውጤቱም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ሲጀመር ግድቡ ግዙፍ በመሆኑና ብዙ ወጪና አቅም የጨረሰ ነው። ከአስር ዓመት በፊት ግድቡን በሚቃወሙ አካላት በኩል የሌሎች ሀገራት ድጋፍ ካልታከለበት አይጀምሩትም ቢጀምሩትም አይጨርሱትም የሚል ምልከታ ነበር።
ይልቁንም ለዚህ በሚል ከሕዝቡ የሚሰበሰበውም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የትም ባክኖ ይቀራል ብለውም ነበር። ትኩረታቸውንም አድርገው ሲሰሩ የነበሩት ድጋፍ ያደርጋሉ ብለው በገመቷቸው ሀገራት ላይ ነበር። ቀስ በቀስ ወደተግባር ሲገባና ግንባታው እውን እየሆነ ሲመጣ እነሱም ዘመቻቸውን በዛው ልክ እያጠናከሩ ለመሄድ ተገደዱ።
ውጤቱ ግን ኢትዮጵያ ካለ ማንም ድጋፍ መሥራት እንደሚቻል በተግባር ያሳየችበት ለመሆን በቅቷል። ግብጻውያን በቀጣናው በአንጻራዊነት ያላቸውን እድገትና የተሻለ የጦር ኃይል የሚመጣጠን ሀገር ኢትዮጵያ መኖሯን ያመላከተም ነው። በኢትዮጵያውያን በኩልም በራስ አቅም በራስ ጥረት ብዙ መሥራት ፤ መልማት እንደሚቻል ለሕዝብም ለመንግሥትም ማረጋገጫ የሰጠ ሆኗል።
ለጎረቤት ሀገራትም ቢሆን ኢትዮጵያ ልማት እንጂ ሌሎችን መጉዳትን ማዳከምን መዳረሻው ያደረገ አላማ እንደሌላትም ህያው ምስከር ለመሆን በቅቷል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምክር ቤት የተናገሩት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። «ጎረቤቶቻችን እየተቸገሩ ማየት አንፈልግም፤ ካጠራቀምነው ራሱ እንልክላቸዋለን» ብለው ነበር።
የኃይል አቅርቦቱ ለሀገር እድገት ያለው ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት ያሳድጋል። ከሕዳሴው ግድብ የሚገኝ ገቢ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ይረዳል። ቱሪዝምና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። ከምንም በላይ በሌሎች ወንዞች ላይ ለሚከናወኑ ግድቦችም ይሁን ለሌሎች ትልቅ አቅም የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ይቻላልን ያቀዳጀ ነው።
ከዚህም በላይ የትኛውም ሀገር ይሁን ቡድን አቅም የሌለውና ደሃውን ወዳጅ ተባባሪ ማድረግ አይፈልግም። የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያን በወዳጅነት የሚቀርቧትን አካላት እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። የሕዳሴው ግድብ እውን መሆን ከምሥራቅ አፍሪካ ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውንም እይታ የሚነካ ነበር።
አሜሪካ ትልቋ የግብጽ ተባባሪ እንደመሆኗ በአሁኑ ምርጫ ባሸነፉት የቀድሞው ፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ በኩል ጠንካራ ጫና ሲደረግም እንደነበር እናስታውሳለን። ያንን ጫና በመቋቋም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድም ጥቅም ማስጠበቅ መቻል ትልቅ ድል ነው።
እዚህ ላይ ግንዛቤ መደረግ ያለበት እንደ ሀገር የሚደረጉ ውሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ መሆናቸውን እና ብዙ እንደተለፋባቸው ነው። እንደዚህ ያሉ ሀገራዊ ስምምነቶች ሲካሄዱ በጽሑፍ ከሰፈረው ጀርባ የሚኖሩ አጀንዳዎችን ሴራዎችን መገንዘብ ይጠበቃል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ያልፈረመችበትና የማትቀበለውም ቢሆን ግብጻውያኑ የሚያነሱት ለእነሱ ብቻ ጥቅም የሚሰጣቸውን ውል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ለምሳሌ ግብጻውያን ደግመው ደጋግመው የሚያነሱት ለዘመናት የኖረውን ፍሰት አናስተጓጉልም የሚል ስምምነት እንዲደረግ የሚያቀርቡት ጥያቄ አለ። ይህንን መቀበል ማለት በዓባይ ገባር ወንዞች ላይ ምንም አይነት ልማት አናከናውንም እንደማለት ነው።
ይህ የመጪውን ትውልድ የልማት ጥያቄ መዝጋት እንደማለት ነው። ዛሬ ላይ የመጪውን ትውልድ ተጠቃሚነት የሚያጓድል የሀገርን ሉዑላዊነት የሚነካ ስምምነት ቢደረግ ከዓመታት በኋላ ተስቦ መውጣቱ አይቀርም። በመሆኑም በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የተደረጉ የስምምነት ሂደቶች እንደ አጠቃላይም በቀጣይ በሌሎች ጉዳዮች በሚካሄዱ ሀገራዊ ስምምነቶች ላይ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ትምህርት የተወሰደባቸው ናቸው ለማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር መኮንን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም