የውጭ ምንዛሪው በገበያ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በሚል ትልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ወይም ገበያ መር መሆኑ እንዲሁም በመንግሥት ሥር ያሉ ተቋማት ወደ ግል መተላለፋቸው፤ የነዳጅ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነትን በተመለከተ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምን ለውጥ ያመጣል ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪና መምህር ከሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ደኑ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- እንደኢኮኖሚ ምሁር የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- ኢኮኖሚ ማሻሻያው የመጣው አዲስ የሽግግር ሁኔታውን ወይም ለውጡን ተከትሎ ነው:: ከዛ በፊት ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ወድቃ ነበር:: እንደውም እንደሚባለው የተወሰኑ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንኳን ለማከናወን የማይቻልበት የበጀት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር:: ይህ ትልቅ ችግር ስለነበር በፍጥነት ያድግ የነበረው ኢኮኖሚ ወርዷል::
ከዚህም በተጨማሪ ከለውጡ በፊት የተለያዩ የሕዝብ ቅሬታዎች በጣም እየተስፋፉ ሔደው ሥርዓት አልበኝነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር:: የሀብት ክፍፍሉም በጣም ለተወሰኑ ወገኖች ያደላ ነበር:: በእርግጥ ዕድገት እንደነበር አይካድም፤ ዕድገቱ ግን ሰፊ እና አብዛኛውን ሕዝብ ያቀፈ አልነበረም:: ከዛ ግን ለውጡን ተከትሎ ኢኮኖሚው ምን ይሁን ተብሎ በጥናት ላይ በመመሥረት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው መጣ:: ሀገር በቀል የተባለው የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችን የሚሽር እና የተለየ ስለሆነ ሳይሆን፤ የኢኮኖሚ ሥርዓቶች እና ማሻሻያዎቹ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመረኮዙ ሆነው የታሰቡ በመሆናቸው ነው::
አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያው ማሻሻያ ምን ያህል ስኬታማ ነው? ምን ምን እንቅፋቶችስ ነበሩ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለተወሰኑ ዓመታት ሲተገበር ነበር:: ነገር ግን የተሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው እንደገና ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ማሻሻያ ስለሚያስፈልግ፤ በቅርብ ማሻሻያ ተደርጓል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያየናቸው አንዳንድ የፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል:: በእርግጥም ገበያ መር ወደ ሆኑ እና በዛ መንገድ ሙሉ በሙሉ የሚሄዱ ርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው::
እነዚህ ርምጃዎች ቀድሞ የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የተወሰዱ ሲሆኑ፤ በዚህም አንዳንድ ችግሮች ተቀርፈዋል:: አንዳንድ ችግሮች ግን ቀጥለዋል:: ይህ የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው:: ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ:: የኮረና ወረርሽኝ ነበር:: ይህ ወረርሽኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም:: እስከ አሁንም ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም::
በኋላም በዓለም ላይ በተለያዩ ሀገሮች ጦርነት መካሄዱ በተለይ አሁንም የቀጠለው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ያለው ተፅዕኖም ይታወቃል:: በዛ ላይ በየጊዜው የሚነሳው ግጭት እየፈጠረ ያለው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም:: ለምሳሌ በተመጣጣኝ ዋጋ ይገኝ የነበረው ማዳበሪያ እና ስንዴ እንዲሁም ሌሎችም ዕቃዎች ይላኩ የነበሩት ከራሺያ እና ከዩክሬን ነበር። እነዚህ ሀገራት ጦርነት ውስጥ ገብተው፤ ምርቶቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ሁኔታ ሲቋረጥ ችግር መፈጠሩ እና ኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደሩ አልቀርም:: ቀስ በቀስ እየሔደ የነበረው የምዕራባውያኑም የኢኮኖሚ ቀውስ የሚዘነጋ አይደለም::
ሌላው በነዳጅ መስመሮች ላይ ከፍተኛ የዝውውር አደጋዎች ሲከሰቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው እጅግ በጣም ከፍተኛ ሆኗል:: በፊት 40 ብር የነበረው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ አሁን ወደ 70 እና 80 ከዛም በላይ ደርሷል:: ስለዚህ እንደኛ የራሳቸው ነዳጅ የሌላቸው ሀገራት ብዙ ፕሮጀክቶቻቸውን ለማስፈፀም ግብዓቶችን ከውጭ ሀገር የሚያስገቡ እና በውጭ ሀገሮች ላይ የሚደገፉ ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ ገብቷል:: የኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው:: ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ? የሚለው በየጊዜው እየታየ የሚለወጥ ነው::
ቀድሞ በተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚታይ ለውጥ በመምጣቱ እና ደህና ደረጃ ላይ በመደረሱ፤ የተሻሻሉትን የበለጠ ውጤታማ ልማድረግ ተጨማሪ የፖሊሲ ለውጦች ስላስፈለጉ በቅርቡ ደግሞ የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል:: ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የወለድ ተመን በአቅርቦት እና ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑ አንዱ ነው። የውጭ ምንዛሪም እንዲሁ ገበያ መር ‹‹ፍሎቲንግ›› ሆኖ እንዲቀጥል የሚል ውሳኔም ተላልፏል:: ማለትም የውጭ ምንዛሪው ከመንግሥት ነፃ በሆነ መልኩ የግድ በ50 ብር ሽጡ እየተባለ ሳይሆን፤ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ የሚወሰነው በአቅርቦት እና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ነው:: ይህ ከማሻሻያው ጋር ተያይዞ የተላለፈ ውሳኔ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በተጨባጭ የውጭ ምንዛሪው ገበያ መር ‹‹ፍሎቲንግ›› የሆነበት ምክንያት ብድር ለማግኘት ነው የሚሉም አሉ:: እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- ብድርን በተመለከተ ከአበዳሪዎች ጋር አበዳሪዎችም የራሳቸው እይታ አላቸው:: በየጊዜው እንደኛ ባሉ ተበዳሪዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል:: ይህ የሚካድ አይደለም:: እነሱ የራሳቸው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍላጎት አላቸው:: ያ እንደተጠበቀ ሆኖ በመግባባት እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ መሠረት ተነጋግሮ አንዳንድ የሚፈልጉ ለውጦችን ማድረግ ተገቢ ነው:: አዳጊ ሀገሮች የሚደርስባቸውን የኢኮኖሚ ቀውስ ከሚያዩ መርዳት ለእነርሱም የኢኮኖሚ መርህ ይጠቅማል::
የውጭ ምንዛሪ እና የውጭ ኢንቨስትመንት ጥሩ ሁኔታ እና አቅጣጫ እንዲኖረው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የውጭን ምንዛሪን ገበያ መር ማድረግ አስፈላጊ ነበር:: በሌላ በኩል የእኛ የንግድ ሚዛን ከውጪዎቹ ጋር ሲወዳደር ያለበት ደረጃ የሚታወቅ ነው:: ይህንንም ችግር ለማቃለል እና የተገኙትን ለውጦች የበለጠ ለማሻሻል በጎ ርምጃዎች ተወስደዋል:: እነዚህ ርምጃዎች በጣም ሰፊ እና ጊዜም የሚጠይቁ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ከገበያው እየወጣ መምጣቱ እና የኢኮኖሚ ርምጃዎቹ ምን ውጤት አስገኙ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- የኢኮኖሚ ርምጃ ምን ጊዜም ቢሆን፤ በአጭር ጊዜ ውጤት ላይገኝበት ይችላል:: ነገር ግን አጠቃላይ አቅጣጫው ገበያ መር ኢኮኖሚ በትክክል እስከ ተመራ ድረስ መንግሥት፤ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፍተኛ ደረጃ ከሚቆጣጠረው ኢኮኖሚ የተሻለ መፍትሔዎችን ሊያመጣ ይችላል የሚለው አያከራክርም:: ይህንን የሚያረጋግጡት የኢኮኖሚ ሳይንሱ እና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎች ናቸው:: ስለዚህ እንደውም ቀደም ብለው ኮሚንስቶች ወይም ሶሻሊስቶች የኢኮኖሚ አመራር የነበራቸው ሀገሮች እነቻይናም ሆኑ እነራሺያ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ የተሸጋገሩት ይህንን ጥቅም በማየታቸው ነው::
ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ገበያ መር ኢኮኖሚ የመንግሥትን አመራር ያስወግዳል ማለት አይደለም:: እዚህ ላይ የግድ መታወቅ ያለበት፤ መንግሥት ስትራቴጂክ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ተገቢውን ሕግ እና መመሪያ በማውጣት፤ ሕግ በማስከበር የሀገሪቷን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮችን በመከላከል ያልተፈለጉ ተግባራት የሚቆጣጠርበት ሁኔታ አለ:: ገበያ መር ቢባልም መንግሥት በጣም ያስፈልጋል በሚላቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ኢንቨስት ሊያደርግ ይችላል::
መንግሥት መንገዶች፣ የውሃ አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ፣ የምርምር ሥራዎች፣ ጤና እና ትምህርትን በተመለከተ የማይናቅ ሚና ይጫወታል:: ነገር ግን የግል ዘርፉ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ አቅሙን ገንብቶ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ድርጅቶች በተገቢው መልኩ ሀገርን ጠቅመው ራሳቸውን የሚጠቅሙበት ሕጋዊ መድረክ ይኖራቸዋል:: ይህንን ሁሉ የሚያደርገው መንግሥት ነው:: ስለዚህ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ኢኮኖሚው የሚኖረው ሚና የአመራርነት ነው:: ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት ሚና መምራት ብቻ ነው?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- መንግሥት ኢኮኖሚውን ሊመራ እና ሊያድግ እንዲሁም ሕዝቡ የተረጋጋ ኑሮ ለመምራት የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው:: ስለዚህ ሰላም የማስከበር እና ሃይልን የመጠቀም ዕድል ያለው መንግሥት ጋር ብቻ ነው:: ይህ በየትኛውም ሀገር ያለ ነው:: ዲሞክራቲክ ናቸው ተብሎ የሚነገርላቸው እነ አሜሪካንም ሆኑ፤ የአውሮፓ ሀገሮችም የትኛውም ሀገር ሕጋዊ መንግሥት ሃይልን የመጠቀም እና ሰላምን የማስፈን ሕጋዊ እና ሕገመንግሥታዊ ሥልጣን አለው::
ለኢኮኖሚው መረጋጋት እና ለኢኮኖሚው በተፈለገው ፍጥነት እና ሁኔታ መካሔድ መንግሥት ሕግን የማስከበር እንዲሁም ሕገወጣዊነትን የመከላከል ሚና ይጫወታል። ይህ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ሃላፊነት ነው:: በየጊዜው አዳዲስ ሕጎች የሚወጡት ለዚሁ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተለያዩ የኢኮኖሚ ለውጦች አሉ:: እነዚህ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፤ ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- የኢኮኖሚ ለውጦች አሉ:: እነኚህ ለውጦች እንዴት ናቸው? ሲባል እነኚህ ለውጦች አስፈላጊ እና ጊዜው የሚፈልጋቸው ናቸው:: አንዳንዶቹ እንደውም የዘገዩ ናቸው ማለት ይቻላል:: ይህም ሆኖ እነዚህ ለውጦች ሥራ ላይ በሚውሉበት ጊዜ የሚያጋጥሙ ጊዜያዊ ችግሮች አሉ::
የትኛውም ለውጥ ሲመጣ ችግር ያጋጥማል:: ያ ችግር የሚፈታው እንዴት ነው? ሲባል አብረው የተቀመጡ አካሔዶች አሉ:: ለምሳሌ የኑሮ ውድነት ወይም የዕቃ ዋጋዎች የማሻቀብ ሁኔታዎች ይኖራሉ:: ይህ ሲታይ የተወደዱት ከየት የመጡ ዕቃዎች ናቸው? የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ በአብዛኛው ከውጪ የሚመጡ በየቤታችን የምንጠቀምባቸው ዕቃዎች በየጊዜው ዋጋቸው ንሯል:: ለዚህ መፍትሔው አንደኛ የሀገር ውስጥ ምርት ማሳደግ እና ፍላጎታችንን ማሟላት ነው::
እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በአብዛኛው የከተማው ነዋሪ ችግሮች ናቸው:: በገጠሩ አካባቢ ያለው ሕዝባችን ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የሚነካው ምናልባት የማዳበሪያ ጭማሪ ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው የሚጠቀመው የራሱን ምርት ነው:: እራሱ አምርቶ ያገኘውን የተወሰነውን ለገበያ ያወጣል፤ የተወሰነውን ለራሱ ቀለብ ያውላል:: ገበያ የሚሔደው አንዳንድ ጥቂት ነገሮችን ለመግዛት ነው::
ከገጠሩ የበለጠ የምንዛሪ ተመኑ የሚጎዳቸው በከተማው አካባቢ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎች የሚጠቀሙት ላይ ነው:: ስለዚህ እነዚያን በሀገር ውስጥ መተካት ይጠይቃል:: የዕቃ ዋጋ በሚያድግበት ጊዜ ለተወሰነ የሽግግር ጊዜ ችግርን ለመፍታት አንደኛው ተጠቃሚው ሕዝብ የራሱን የአጠቃቀም ሥርዓት ማስተካከል አለበት:: ይህ የትም ሀገር ያለ የኢኮኖሚ ሳይንስ ነው::
የትም ሀገር እንደበፊቱ መኖር በማንችልበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ መኖር እና ያንን ጊዜ ማሳለፍ መቻል የግድ ነው:: አንዱ ይህ ሲሆን፤ ሌላኛው የሀገር ውስጥ ምርትን በከፍተኛ መጠን ማብዛት ነው:: ለዛ አቅሙ አለ ወይ ሲባል፤ መልሱ አዎ ነው:: ያልታረሰ ብዙ መሬት አለ:: ችግኞችን በማፍላት በመካናይዜሽን ወይም በመስኖ በማልማት ብዙ ምርት ተገኝቷል:: በማሽላውም በበቆሎውም ሆነ በሌሎችም አምርቶ እንደዚህ ማድረግ ይቻላል:: ሌሎችም በርበሬም እንደየ ሁኔታው እንደአመቺነቱ መሠራት አለበት::
ምርትን በተመለከተ እንደየሁኔታው የሚያጠኑ ምሁራን እና የግብርና ተመራማሪዎች አሉ:: አትክልት እና ፍራፍሬዎች ላይም በተሻለ ሁኔታ እየተመረተ ነው:: እዚህ ላይ አንዳንዱን በሽታ ሊያጠቃቸው ይችላል:: በደንብ መመረት ከጀመረ በኋላ አስፈላጊው ጥንቃቄ ከተደረገ የሀገር ውስጥ ምርትን በአጭር ጊዜ አሳድጎ ሕዝቡ ከውጭ የሚያስገባውን ነገር ከሀገር ውስጥ እንዲተካው ማድረግ ይቻላል:: ይህ ሲሆን የዋጋ ንረቱ ይቀንሳል:: ሕዝብም የሚያገኘው የሚፈልገውን ነገር በቀላሉ በአካባቢው ማግኘት ይችላል:: ትልቁ ነገር ይህ ነው:: በጥቅሉ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ እና ምርትን ማበራከት አንዱ ጉዳይ ይህ ነው:: ስለዚህ የውጪ ምርት የመወደድ ችግር መኖሩ ራሱ እንደዕድል ማየት አለብን:: ለሀገር ውስጥ አምራቾች እንደመልካም አጋጣሚ ታይቶ ምርታማነትን በማስፋፋት ማስተካከል ይጠበቃል::
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሁኔታ ላይ እንደገና የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል:: ይህ እንዴት ይታያል ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- በእርግጥ እኛ ነዳጅ የለንም:: ነዳጅ የሚመጣው መንግሥት ብዙ ቢሊየን ብሮችን እየደጎመ ነው:: ይሄ የድጎማ ነገር እስከመች ያስኬዳል የሚለው ያጠያይቃል:: መንግሥት ድጎማ የሚያደርገው ከእኛ እየሰበሰበ ነው:: በተጨማሪ የሕዝቡ አቅም አነስተኛ በመሆኑ ደግሞ የግብር ገቢው ይጎዳል:: ስለዚህ መንግሥት እየተበደረ በብድር ላይ ብድር በብድር ላይ ብድር እያደረገ ይሔዳል::
ይህንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የውጪ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች ድጎማ አንሱ እያሉ ለረዥም ጊዜ ሲጨቀጭቁ ነበር:: አሁን እነርሱ ስላሉ ብቻ ሳይሆን ዕዳን ለመቀነስ እንዲሁም በተቻለ መጠን ደግሞ አንዳንድ የልማት ሥራዎችን ለማጣደፍ የሕዝቡን ኑሮ ለማስተካከል እንዲቻል እና ከድጎማ የሚተርፈውንም ገንዘብ ለሌላ ዓላማ ማዋል ያስፈልጋል::
የነዳጅ ድጎማ እየተቀነሰ ሲመጣ ቀስ በቀስ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ይሔዳል:: ይህንን ለማስተካከል ነዳጅ ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ ወሳኝ ነው:: ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ይቻላል:: እዚህ ላይ ለውጦች እየመጡ ሔደዋል:: ሌሎች በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ነገሮችን በኤሌክትሪክ በመተካት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማስተካከል ይቻላል:: ይህ እየተሠራ መሆኑን እያየን ነው:: የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውሎ አድሮ መልካም አጋጣሚዎችን በመፍጠር ጥንካሬዎችን እያስገኘ በመሄድ የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ እያሻሻለ መሄዱ አይቀርም::
አዲስ ዘመን፡- የቴሌኮምም ሆነ የአየር መንገድ በከፊል መሸጥ የውጪ ነጋዴዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባትን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ:: ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- በመንግሥት እጅ ያሉ ንብረቶች በሙሉ ለሽያጭ ላይቀርቡ እና የተወሰኑት በመንግሥት እጅ እንዳሉ ሊቆዩ ይችላሉ:: ነገር ግን ከኢኮኖሚ ሳይንስ አንፃር የግል ባለሀብቱ የኢኮኖሚው መዘውር ወይም ሞተር መሆን አለበት የሚል ነው:: ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ ይህ ነገር ለረዥም ጊዜ አልነበረም:: እንደውም የግል ዘርፉ አልነበረም ማለት ይቻላል:: ስለዚህ እንዲሁ የሀገርን ኢኮኖሚ ከመበተን መንግሥት ሰብሰብ አድርጎ መምራቱ አይቀሬ ነው:: ስለዚህ በመንግሥት ውስጥ የነበሩ ሀብቶችን ደረጃ በደረጃ ወደ ግል ማዘዋወሩ ችግር የለበትም::
ሰሞኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስር በመቶ ሸጠ:: እርሱ ላይ ሰዎች እየገቡ ነው:: ያንን የገዙት የግድ ሚሊየነሮች አይደሉም:: ሰዎች ከአስር ሺህ ብር ጀምረው እየገዙ ነው:: ይህ ማለት አብዛኛውን ሕዝብ ያቀፈ ዓይነት አሠራር ነው:: ምክንያቱም መግዛት ማለት ባለቤትነት ነው:: ስለዚህ ከመንግሥት ሙሉ ባለቤትነት ወደ ሕዝብ እና ወደ ግለሰቦች ማሸጋገር ማለት ነው::
የግለሰቦች መኖር ራሱ በአሠራሩ ላይ ድምፅ በመስጠት እና ሃሳብ በማቅረብ እነኚህ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ የመንግሥት በነበሩበት ጊዜ ከሚሠራው ሥራ እና ከሚያስገኙት ጥቅም በተሻለ መልኩ እየተጠቀሙ መጥቀም ይቻላል:: ይህ በቴሌ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ትልልቅ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ:: እነዚህ ተቋማት ደግሞ ቀድሞም እንኳ የመንግሥት ቢሆኑም ሕዝቡ የኔ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው ናቸው:: ስለዚህ ደረጃ በደረጃ ሕዝቡ መግባቱ ትክክል ነው:: ነገር ግን ለምሳሌ በተቃራኒው ሕዝቡን የሀገር ውስጥ ግለሰቦችን ሙሉ ለሙሉ አግልሎ ለውጪ ቢሸጥ ኖሮ ቅሬታ ሊፈጥር ይችል ነበር::
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቢሆን የሚሸጠው በድርሻ (በሼር) ደረጃ ነው:: መንግሥት ዝም ብሎ አንድን ብሔራዊ ሀብት አይሸጥም:: በተመሳሳይ መልኩ ወደ ሕዝቡ እና ወደ ግለሰብ ሊያስተላልፍ ይችላል:: ሕዝቡ ደግሞ ድርሻ ይገዛል:: ይህ ማለት ሕዝቡ ሲገዛ ገዢው የመምረጥ መብት ይኖረዋል:: የትርፍ ድርሻ የመካፈል መብት ይኖረዋል:: ይህ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት::
መንግሥት ምንም ነገርን በጭፍን አይሠራም የሚሠራውም የሚወስነውም በጥናት ላይ ተመሥርቶ ነው:: ገበያ መር በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ነገሮች መንግሥት ከላይ ሆኖ ወደ ታች የሚያስተላልፈው ሳይሆን በፍላጎት እና በአቅርቦት ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ነው:: ይሄ በመጥፎ መታየት የለበትም:: ዕቃውም ሆነ አገልግሎቱ የሚሸጠው እና የሚገዛው በዚሁ በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው:: የገንዘብ ሽያጭም ተመሳሳይ ነው:: ይህ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ እውነት ነው:: ነገር ግን ሲተገበር የኢኮኖሚዎቹ አቋም በምን ዓይነት የልማት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታሳቢ ማድረግ ደግሞ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ወይም ገበያ መር መሆኑ ተገቢ ነው?
ዶ/ር ብርሃኑ፡- አዎ! በአሁኑ ጊዜ በግሎባላይዜሽን ዘመን አንድ ሀገር ብቻዋን ተነጥላ መኖር አትችልም:: የዓለም ሀገሮች በአብዛኛው በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በፖለቲካ ፣ በማህበራዊ ሁኔታም እየተገናኙ የሚኖሩ ናቸው:: ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአሁኑ ጊዜ ከዓለም ሁኔታ አንፃር የውጭ ምንዛሪ መንግሥት እንደበፊቱ በብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የሚወስነው ተመን ከገበያው ጋር መሔድ አልቻለም::
በተጨማሪ በቂ የውጭ ገንዘብ አቅርቦት ማግኘት ስላልተቻለ የጥቁር ገበያው ዋጋ የመንግሥት ባንኮች ከሚመዘግቡት በጣም በከፍተኛ ዋጋ የጨመረ ነበር:: አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ስላልተመጣጠነ ሰው ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ሄዶ ከፍተኛ የምንዛሪ ተመን በመስጠት ሲገዛ ቆይቷል:: ይህ ርምጃ ተገቢ እና ትክክለኛ ነው::
ስለዚህ በመንግሥት ትዕዛዝ በብሔራዊ ባንክ ተመን መሠረት በየጊዜው ለባንኮች እየተነገረ የሚሰጠው ዝቅተኛ የባንኮች ተመን ዋጋ ቢኖርም፤ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ሰው ከዛ በላይ ለመክፈል ፍላጎት እንዳለው አመልካች ነገሮች ነበሩ:: በግልፅ በአደባባይ እንደታወቀው፤ መንግሥት ሃምሳ ብር አካባቢ እየመነዘረ ጥቁር ገበያው መቶ ደርሶ ነበር:: ያ ደግሞ በዛ ዋጋ ለመግዛት የሚሻ ፍላጎት አለ ማለት ነው::
በርዳታም ሆነ በዕዳ ሽግሽግ ከውጭ ካሉ የልማት ድርጅቶች አጋዥነት የአቅርቦቱን መጠን ከፍ ለማድረግ ተሞከረ:: በተጨማሪ በተለያየ ሁኔታ በሙስናም ቢሆን ጥቁር ገበያም ባይኬድ አንድ ዓይነት የምንዛሪ ተመን እንዲሆን የገበያው ሁኔታ ለቀቅ ይደረግ፤ ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ ይህን አድርግ ብሎ ከሚያዝ በየጊዜው የሚቀያየር ሳይሆን በገበያው ላይ ለማንም በማያደላ ተወዳዳሪነት ባለው ሁኔታ ምንዛሪው ይዳኝ ተብሎ ተወሰነ:: ስለዚህ ካለው ከጥቁር ገበያ ጋር የሚስተካከልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደረገ:: ይሄ ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ሆነው::
አቅርቦቱ እየበዛ ሲሔድ ሰዎች በሚፈልጉት መጠንና ዋጋ በባንክ ማግኘት ከተቻለ ወደ ጥቁር ገበያ ዓይኑን የሚያማትር አይኖርም በሚል ነው:: ይሄ መልካም ቢሆንም ከባንኮች ጋር ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ካሉ አሁንም ገበያውን ይረብሻሉ:: ይህ የታወቀ ነው:: ሕገወጥ ንግድ እና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማካሔድ የሚፈልጉ ካሉ፤ አሁንም ይረብሻሉ:: ባንክ የሚሔዱ ከሆነ በሕጋዊ መንገድ መሆን አለበት:: ትክክለኛ እና አስተማማኝ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማስፈቀድ ይገባል:: በብድር እና በርዳታ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደፈለጉት ከሕግ ውጪ ማከፋፈል አይቻልም:: ሕጋዊ ሰነድ እና እውቅና የሌላቸው ይህንን ያጡ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዳሉ:: ይህንን ምንም ማድረግ አይቻልም::
የጥቁር ገበያውን ደግሞ በቀላሉ ዝም ብሎ ማሰር አይቻልም:: አሁን አማራጭ ተወስዷል:: አማራጩን የሚጠቀሙ አሁንም ቢሆን ከጥቁር ገበያው በተሻለ ሁኔታ በጣም ሕጉን በጠበቀ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ያገኛል:: ምክንያቱም አሁን በቀረበው ሪፖርት ባንኮች ባለፉት ወራት ከ282 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለተጠቃሚዎች አቅርበው፤ ከዚህ ውስጥ ግን እስከ አሁን ድረስ የተወሰደው 28 በመቶ ብቻ መሆኑ ይፋ ተደርጓል::
ከባንኮች የመውሰድ ፍላጎት ለምን ቀነሰ? የሚለው ሲታይ ድሮ በሕጋዊ መንገድም ሄደው ስለሚቆይባቸው እና ስለሚንገላቱ ስለሚያጡ ከጥቁር ገበያ ይገዙ ነበር:: አሁን ግን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግበው የንግድ ፍቃድ ያላቸው አሁንም ገንዘቡን እየተጠቀሙ ነው:: ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለያየ ሁኔታ ለተለያየ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የሚንቀሳቀሱት በጥቁር ገበያው ነው ማለት ነው:: ስለዚህ ይህ ሁሉ በመሆኑ አንዳንድ ነገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ላይስተካከሉ ይችላሉ:: የትኛውም ለውጥ ጊዜ ይወስዳል:: ጊዜ ይፈልጋል:: ዛሬ የተደረጉ ማሻሻያዎች ቢያንስ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ውጤታቸው ላይታይ ይችላል:: ከዛ በኋላ ይታያል::
ጥቁር ገበያው የቀጠለው በሕገወጦች ምክንያት ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ ያ እየተስተካከለ ሲሔድ፤ ሕገወጥ አካሔድን የሚከተሉ ሰዎች በሩ እየተዘጋባቸው ሲሔድ፤ ፍላጎታቸው ይቀንሳል:: በዚህ ጊዜ ሕጋዊው የባንክ የገንዘብ ልውውጥ መንገድ ፈር እየያዘ ይሔዳል ብለዋል:: በሌላ በኩል አንዳንድ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መር እንዳይሆን የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ:: ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ሀገር ሊሆን የሚችል መሆኑን አመልክተዋል::
አዲስ ዘመን፡- በዝግጅት ክፍሉ ስም ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ::
ዶ/ር ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም