“ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርም፤ የዓባይም ባለይዞታና ባለቤት ናት” -አቶ ዳኛው ገብሩ ተስፋው የታሪክ ምሁር

የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ዳኛው ገብሩ ተስፋው ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት ደቡብ ጎንደር ጥናፋ ወረዳ፤ ቀደም ሲል ደራ ገብረመስቀል፣ በአሁኑ ወቅት ወለላ ባሕር በመባል በሚታወቅ ቦታ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም የቄስ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን “ሀ” ብለው ጀምረዋል፡፡

የቄስ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በአካባቢያቸው ወዳለ መደበኛ ትምህርት ቤት በመግባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በወቅቱ የተሻለ ግንዛቤ አዳብረው የመጡ ስለነበረም የተወሱ ክፍሎችን መዝለል የቻሉበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።

እንግዳችን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ደቡብ ጎንደር ውስጥ በሚገኘው በደብረ ታቦር ዳግማዊ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። በአገር ውስጥ የተለያዩ ኮሌጆች ገብተው የመማር እድልም አግኝተዋል፤ በዚህም በተለያዩ ሙያዎች ለመመረቅ በቅተዋል።

ትምህርታቸው በኮሌጅ ትምህርት ብቻ እንዲወሰን ያልፈለጉት አቶ ዳኛው ገብሩ፣ ወደ ባህር ማዶ በመሻገር ሞስኮ እስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በታሪክ ትምህርት በተለይም በማኅበረሰብ ተመራማሪነት ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት፤ እንደዚሁም የሶስት ልጆች አያት የሆኑት እንግዳችን አቶ ዳኛው፣ ዘጠኝ ያህል መጻሕፍትን በመጻፍ ለንባብ አብቅተዋል። ከዘጠኙ መጻሕፋቸው ውስጥ ሁለቱ የሚያጠነጥኑት በትምህርት ላይ ሲሆን፣ የቀሩት ደግሞ በታሪክ እና ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ነው፡፡

ከጻፏቸው መጻሕፍት “ቀይ ባሕር” እና “በሰላም ውስጥ ያለ ጦርነት” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቁት በውሃ ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ሌሎች ያልታተሙ ስራዎች አሏቸው። አብዛኛውን የስራ ጊዜያቸውን ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ያሳለፉት አቶ ዳኛው ገብሩ፣ ለትምህርቱ ዘርፍ የተለየ ፍቅር አላቸው።

ከዚህ የተነሳ ስራቸውን የጀመሩት በመምህርነት ነው፤ አሁንም የሚሰሩት ከትምህርት ጋር የተያያዘ ስራ ነው። እስከመጨረሻው መስራት የሚፈልጉት ከትምህርት ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያለው ስራ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ማንበብንና መጻፍን አጥብቀው የሚወዱ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑትን የዘጠኝ መጻሕፍት ደራሲና የታሪክ ምሁሩን አቶ ዳኛው ገብሩን በተለይ ከቀይ ባሕር ቀጣና ጋር አያይዞ የዛሬ እንግዳው አድርጎ አቅርቦላችኋል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- በርከት ያሉ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅተዋል፤ ይዘታቸው ምን ይመስላል?

አቶ ዳኛው፡– ለንባብ ያበቃኋቸው ዘጠኝ ያህል መጻሕፍትን ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የሚያጠነጥኑት በትምህርት ላይ ነው። የተቀሩት ደግሞ በታሪክ እና ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ነው። ከጻፍኳቸው መጻሕፍት ውስጥ በተለይ ሁለቱ በውሃ ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። እነዚህም መጻህፍት አንዱ “ቀይ ባሕር” በሚል፣ ሁለተኛው “በሰላም ውስጥ ያለ ጦርነት” በሚል ርዕስ ያሳተምኩት ነው። ለጊዜው ለንባብ ያበቃሁት ዘጠኝ መጻሕፍትን ይሁን እንጂ ገና ያልታተሙ ስራዎችም በእጄ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቀይ ባሕር የሚለው መጻፍዎ በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ በስፋት ትንተና የሚያደርግ ነው፤ ስለመጻፉ ማእከላዊ ጭብጥ የተወሰነ ነገር ቢነግሩን?

አቶ ዳኛው፡– ያለንበትን የቀይ ባሕር ቀጣና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታውን ስንመለከት የዓለምን ትኩረት በእጅጉ የሚስብ ነው። ትኩረት የሳበበት ምክንያት ሁለት ሲሆን፣ ሁለቱም ውሃ ነው። አንደኛው እንደሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ነው፤ ዓባይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ውሃ ይሁን እንጂ፤ ከስምንት በላይ የሚሆኑ አገሮችን አቆራርጦ የሚሔድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ረጅም ከሚባሉ ወንዞች ደረጃ የሚመደብ ወንዝ ነው። ከዚህ የተነሳ በርካታ አገሮች በዓባይ ላይ ያተኩራሉ። በዓባይ ላይ ፍላጎቱና ተሳትፎውም አላቸው።

በርካታ ሰው የሚያስተውለው ዓባይ የሚመነጭበትን አገርና አልፎ የሚሔድባቸውን አገሮችን ብቻ ነው፤ ነገር ግን ዓባይን በመዳረሻነት የሚፈልጉ ብዙ አገሮች አሉ። ከግብጽ አልፎ በግብጽ በኩል ሳዑዲ አረቢያም አንደኛዋ ፈላጊ ናት። በተመሳሳይ እስራኤልም ውሃውን ትፈልጋለች፤ ሌላው ቀርቶ አልተሳካላቸውም እንጂ ሌሎቹ የሰሜን አፍሪካ አገሮችም እንደ ሊቢያ አይነቶቹ ከዓባይ ውሃ በግብጽ በኩል ቢያገኙ ደስተኞች ናቸው።

ግብጽም ይህን ምኞታቸውን “አሳካላችኋለሁ” ስትል ቃል ስትገባ ቆይታለች፤ በዚህ መልኩ ከራሷም አልፎ በውሀው ጉዳይ ቃል የምትገባ አገር ነች፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት ከቀድሞዎቹ አንዱ የሆኑት የግብጽ መሪ፣ ግብጽ ከእስራኤል ጋር በታረቀችበት ወቅት “የዓባይን ንጹህ ውሃ አብረን እንጠጣለን” በሚል ያሰሙት ንግግር የሚታወስ ነው።

የዓባይን ጉዳይ ብዙ አገሮች አፍጥጠው የሚመለከቱት በውሃ ፖለቲካ ውስጥ ቁጥር አንድ አጀንዳ በመሆኑ ነው፤ እኛም በዚህ ቀጣና ውስጥ የምንገኝ አገር ነን። እሱ ብቻ ሳይሆን በአጋጣሚ ሆኖ ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧ ምክንያት 12 ወንዞቿ ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። አገር አቋርጠው ይሄዳሉ። ከዚህ የተነሳም ጎረቤቶቻችን ተጠቃሚዎች ናቸው። በአንጻሩ እኛ ግን ከጎረቤቶቻችን ብዙ ተጠቃሚዎች አይደለንም። በውሃው ምክንያትም ሁሉም ጎረቤቶቻችን በጥርጣሬ ሲያዩን ኖረዋል። ብዙ ሰው ግብጽን ብቻ በጥርጣሬ የመመልከት እንጂ እርሷ ብቻ አይደለችም፡፡

ሁለተኛው የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው፤ ቀይ ባሕርን ስናነሳ ለአንድ ደቂቃ እንኳ ቢሆን የዓለም አይን የማያንቀላፋበት ቀጣና መሆኑን እናስተውላለን። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም ትኩረትን የሚሹ ወደ አምስት የሚጠጉ ኮሪደሮች አሉ። ከእነዚህ አምስት ትልልቅ ኮሪደሮች መካከል ቀይ ባሕር፣ ከስዊዝ ካናል እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ድረስ ያለው ቦታ ብዙ አገሮች በትኩረት የሚመለከቱትና እጅግ በርካታ ጠቀሜታ ያለው ነው።

አካባቢው ለአንድ ወር ወይም ለአንድ ሳምንት ያህል ቢረበሽ ዓለም በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጉዳይ ልትመሰቃቀል ትችላለች። ከዚህ ቀደም በአንድ ወቅት በ1960ዎቹ አካባቢ በእስራኤልና በአረብ ግጭት ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት የኢኮኖሚ ቀውስ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህ ቀጣና እኛንም ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉ በትኩረት የሚያየው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ታድያ ኢትዮጵያ በዚህ ቀጣና ውስጥ የምትገለጸው እንዴት ነው?

አቶ ዳኛው፡- ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያን ስንመለከት በዓባይ ጉዳይ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያላት አገር ናት። በቀይ ባሕርም ደግሞ ተሳትፎ የነበራትና ያላት አገር ናት፡ የሁለቱም የትኩረት አቅጣጫዎች በዋናነት የሚያርፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የቀይ ባሕርም ሆነ የዓባይ ጉዳይ የችግር መነሻውን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርም የዓባይም ባለይዞታና ባለቤት ናት።

እሱ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ አገሮች ጋር ኢትዮጵያ ስትነጻጸር ተጽዕኖ ልትፈጥር ትችላለች ተብሎ በሌላው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግምት የተሰጣት ናት። ምናልባትም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያላት አገር ናት፤ ከዚህ የተነሳ ዓለም በትኩረት የሚመለከታትና አልፎ አልፎ አንዳንዶቹም በስጋት የሚያይዋት ናት።

ሁለተኛው የሚነሳው ነገር ውሃን በተመለከተ ነው። ውሃ የዓለም ፖለቲካ ቁጥር አንድ አጀንዳ ነው። እንዲያውም ብዙ አገሮች እና ብዙ ምሁራን እንደሚሉት፤ ውሃ ከነዳጅም ከወርቅም የሚበልጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማያዊ ወርቅ ነው። ሌሎቹ ሀብቶች በሌላ ሊተኩ ይችላሉ፤ ውሃ የማይተካ ሀብት ነው። ምናልባትም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሶስተኛው የዓለም ጦርነት የሚነሳ ከሆነ መነሻው ውሃ ነው ብለው ብዙዎቹ ምሁራን በስጋትነት ይተነብያሉ። ምክንያቱ ደግሞ የዓለም ሕዝብ በውሃ ጥማት ውስጥ መኖሩ ነው።

እንደሚታወቀው ከዓለም ክፍል 71 በመቶ የሚሆነው ውሃ ነው። ከዚህ ውስጥ በቀጥታ ለሰው ልጅና ሕይወት ላለው አካል ጥቅም ላይ መዋል የሚችለው የውሃ መጠን ሶስት ነጥብ አምስት በመቶው ብቻ ነው። 96 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆነው ውሃ በቀጥታ ለአገልግሎት የማይውል ነው። ውሃው እንኳ ቢኖር ለጥቅም ማዋል የሚቻለው በከፍተኛ ወጪ ነው።

ዓለም የሚሻኮተውና የሚራኮተው ሶስት ነጥብ አምስት በመቶው ውሃ ላይ ነው። ከሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ከሚሆነው ውሃ ውስጥ ደግሞ 61 በመቶ የሚሆነው ውሃ የሚገኘው ሰው በማይገኝበት ወይም በማይኖርበት በአርክቲክና በአንታርክቲክ ነው። ይህ ማለት ዓለም አፍጥጦ የሚመለከተው ከአንድ ነጥብ አምስት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ባላቸው አገር አቋራጭ ወንዞች ላይ ነው።

ዓለም፤ በውሃ አስተዳደር፣ አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ውስጥ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ አገሮች ይጣላሉ፤ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ አገሮች የሚዋጉት በውሃ ምክንያት ነው። ብዙ አገሮች የሰላም እጦታቸው እና የችግር መነሻቸው ውሃ ነው። ምናልባትም ወደፊት የውሃ እጥረቱ በርካታውን የዓለም ሕዝብ ወደ እልቂት ውስጥ ያስገባዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ስለዚህ የውሃ ፖለቲካ በዓለም ላይ ትልቅ አጀንዳ ነው። እኛም ያለነው በዚሁ የውሃ ፖለቲካ ውስጥ ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ስንመለከት በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ማዕከል የሆነች አገር ናት። የመጀመሪያ የኢትዮጵያን የውጭና የአገር ውስጥ ፖለቲካ ሲወስን የቆየው የዓባይ እና የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ባሳለፈችባቸው በውጭ ፖሊሲ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የውስጥ ችግሯና ግጭቷ አባባሽ እና መነሻው የዓባይና የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እነዚህን ሀብቶቿን በብዛት ሳትጠቀም የዘለቀች፤ በተለይም ዓባይን ሳትጠቀምበት የቆየች ውሃ በመሆኑ ጠላት ጠርቶባታል። እስካሁንም ድረስ ዓባይ ጠላት ሲጠራብን ቆይቷል፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለመጠቀም አቅም አልነበረንም፤ ሲደረግ የነበረውም ሙከራ ጥቂት ነበር። ከዚያ ይልቅ ለወንዛችን ዓባይ ስናዜምለት ቆይተናል። ከዚህ የተነሳ እርሱም ጠላት ሲጠራብን ቆይቷል። ከጠላቶቻችን መካከል ደግሞ ቁጥር አንድ የሆነችው ግብጽ በአገራችን ላይ ችግር ስትፈጥር ዛሬ ላይ የደረሰች አገር ናት። እስካሁንም ድረስ ከግብጽ ጋር የሚያጣላን ጉዳይም ነው፡፡

ሁለተኛው ቀይ ባሕር ነው። ቀይ ባሕር ጥንትም ቢሆን የተወሰነው ክፍል የኢትዮጵያ ይዞታ እንደነበር ይታወቃል። ቀይ ባሕርን ያጣነው አለአግባብ ነው፤ ሰዎች የወደብ ጉዳይን ከሸቀጥ ጋር ቢያመሳስሉትም፤ ይህ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። እኛን ጨምሮ ዓለም በቀይ ባሕር ላይ ያለው ፍላጎት የወደብ ብቻ አይደለም፤ የሕልውናም ጉዳይ ጭምር እንጂ።

እኛ በአሁኑ ወቅት መውጫ ኮሪዶር እንፈልጋለን ስንል የወደብ ጉዳያችን ብቻ ሆኖ ሳይሆን ሕልውናችንንም ጭምር ለማስጠበቅ በማሰብ ነው። ስለዚህ የቀይ ባሕር ጉዳይ የወደብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጠርበት ወይም ደግሞ ላይፈጠርበት የሚችል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህን ባሕር በስህተት አጥተነው ቆይተናል። ቀይ ባሕርን በሸሸነው ቁጥር የአገራችን ሕልውና እየተቃወሰ ይሄዳል።

ቀይ ባሕርን ቀረብ ብለን ስመለከተው በርካታ ጸጋዎች ያሉት ነው። ከጤና ጥቅም አንስቶ እስከ ትራንስፖርት ድረስ ባለው አገልግሎቱ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። አንደኛ ዓለም ተጠቃሚ የሚሆነው ሸቀጦችን እና ጥሬ ሀብቶችን ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ቦታ ለማጓጓዝ ርካሽ የሚባለው የውሃ ላይ ትራንስፖርት ነው። የዓለም ሸቀጥና ጥሬ ሀብት በውሃ ላይ መጓጓዝ ካለበት ደግሞ ዋናው ማዕከሉ ቀይ ባሕር ነው። ምክንያቱም ብዙ ጸጋ ባለበት ኢስያ እና አፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓ መካከል ያለ ስትራቴጂክ ቦታ ነው፡፡

እንደሚታወቀው አፍሪካ ሰፊ ጥሬ ሀብት ያለው አህጉር ነው። ኢስያም ተመሳሳይ ነች፣ ሰፊ የሸቀጥ ዝውውር የሚካሔድበት አህጉር ነው። አውሮፓም ተመሳሳይ ነው። ከዚያ ባሻገር ደግሞ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው የዓለም ሕዝብ የሚኖርበት ቀጣና ነው፡፡

የአፍሪካና የኢስያ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለሸቀጦች ስርጭት ሰፊ ገበያ ያለው አካባቢ ነው። ስለሆነም በንግዱ ስራ አትራፊ መሆን የሚቻለው ዓለም በቀይ ባሕር ላይ ሲጓጓዝ ነው። ነገር ግን ቀይ ባሕር አሁን ያለው በችግር ውስጥ ነው፡፡

ቀይ ባሕር፤ 24 ሰዓት የማያንቀላፉ፣ 24 ሰዓት የሚያንቀላፉና ችግር ጠማቂዎች ያሉበት ቀጣና ነው። እንዲህ ሲባል አንደኛ 24 ሰዓት አፍጥጦ የሚከታተሉ አገሮች አሉ፤ እንደሚስተዋለውም ሁሉም በሚያስብል ደረጃ ተረባርቦ በቀይ ባሕር አካባቢ ከጂቡቲ እስከ ሱማሊያ ድረስ ወደብና የጦር ሰፈር እየተከራየ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ።

ይህ ወደብ ፍለጋ አይደለም። ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለወታደራዊ አቅም ስትራቴጂክ ቦታ የመፈለግና የመያዝ ጉዳይ ጭምር ነው። ምክንያቱም ቀይ ባሕር ላይ በመራኮት ላይ ያሉ አገሮች ወደብ የሞላቸው ናቸው። እነዚህ የማያንቀላፉ አገሮች ናቸው። የአፍሪካንና የኢስያን ኢኮኖሚ ሊቀራመቱ፣ ሰፊ የሆነውን የሰው ጉልበት ሊበዘብዙና ገበያውን ሊጠቀሙ የሚችሉ አገሮች 24 ሰዓት አይናቸውን ከቀይ ባሕር ላይ አይነቅሉም፤ አያሸልቡምም።

ሁለተኛው ደግሞ 24 ሰዓት የሚተኙቱ ናቸው፣ እነዚህም የአካባቢው አገሮች ናቸው ማለት ይቻላል። ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ የመንም እንቅልፋሞች ናቸው። እነዚህ የአካባቢው አገራት እንቅልፋም ባይሆኑ ኖሮ፤ በተናጠል ጥቅማቸውን ማስከበር ባይችሉም፤ ሕብረት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያስከብሩ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለችው ኅብረት እንፍጠር ነው። ሰጥቶ በመቀበል መርህ አንድነታችንን በመፍጠር ጥቅማችንን እናስከብር ነው። ይህንን የተለያዩ አገሮች የሚያዩን በስጋት ነው። የአካባቢው አገራት ቀድሞም ቢሆን ደካማ ናቸው፣ በተናጠል መራመዳቸው ደግሞ የሌሎቹ 24 ሰዓት የማይተኙ አገሮች መረማመጃ መሆናቸው አይቀሬ ነው።

ሶስተኛው ደግሞ ቀጣናው ችግር የሚጠመቅበት ነው፤ በአካባቢው ድሮን ጭምር በመጠቀም ዓለምን የሚያስቸግሩ ቀጣናውንም የሚያምሱ አካላት ያሉበት ነው። ከዚህ የተነሳ ቀይ ባሕር ወንበዴዎች ያሉበት አካባቢ በመሆኑ የተጨነቀ ነው። የመን የፈረሰች አገር ናት፤ በተመሳሳይ ሶማሊያም እንደዚያው ናት። ሱዳንም በትርምስ ውስጥ ነች። ከሁሉ በላይ ቀይ ባሕርን ስናነሳ የአረብና የእስራኤል ግጭት ያለበት አካባቢ ነው። ሁለቱ ደግሞ የበረታ አለመግባባት የሚስተዋልባቸው ናቸው።

በዚህ በችግር ውስጥ ባለ ቀጣና የሚገኙ ሀገራት የሕልውና ስጋት አለባቸው። ስለዚህ እኛም ሸቀጦቻችንና ጥሬ ሀብቶቻችን በሰላም በባሕሩ ላይ እንዲተላለፉ ባለቤት በመሆን ጥቅማችን ማስከበር መቻል አለብን። ሁለተኛው ደግሞ የትኛውም አገር እኛን እንዳይተነኩሰን የራሳችንን ኃይል ቀይ ባሕር ላይ መፍጠር መቻል ይጠበቅብናል።

ቀይ ባሕር ከወደብ በዘለለ የኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም ቀይ ባሕር ላይ መውጫ ኮሪደር ያስፈልገናል በሚል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የወሰዱት ወሳኝ አቋም ነው ባይ ነኝ። ይህ ደግሞ ትክክለኛ ነገር ነው። እኔ በመጻሕፌ ውስጥ ስለቀይ ባሕር ስናነሳ መሽኮርመም የለብንም፤ ባለቤቶች ነን፤ ስለሆነም የተወሰደብንም ቀይ ባሕር ይዞታ መመለስ አለበት፤ ጥያቄ ስናነሳ መላ ኢትዮጵያዊ ሊተባበረን ይገባል እንጂ አንዱ ዘርጣጭ አንዱ ደግሞ ተራማጅ ሊሆን አይገባም ብያለሁ። ምክንያቱም ቀይ ባሕር ላይ ድርሻ የማይኖረን ከሆነ ዘለቄታ ያለው ሕልውና ሊኖር አይችልም።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች የሚኖራት ግንኙነት ምን መምሰል ይኖርበታል ይላሉ?

አቶ ዳኛው፡- አገራችን ሰጥቶ በመቀበል መርህና ፍትሐዊ በመሆን ጥቅም የምታምን ናት። ጎረቤቶቻችንም ሰጥቶ መቀበልን መለማመድ አለባቸው። ጎረቤቶቻችን ከእኛ የሚያገኙት ብዙ ነገር አለ። በዚያው ልክ ልናሳጣቸውም የሚያስችለን በርካታ ነገር አለ። ለምሳሌ ሶማሊያን ብንወስድ ሕልውናዋ የተመሰረተው በኢትዮጵያ ወንዞች በዋቤ ሸበሌና በገናሌ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና በእነዚህ ወንዞች ላይ ያልተጠቀመች ናት። የሶማሊያ ሕልውና በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ሳለ፤ ሶማሊያዎች እኛን ባሕር ሊከለክሉን አይገባም። ሰጥቶ መቀበል ካቃታቸው እኛም ያለመስጠት መብታችን የተጠበቀ ነው።

የዓለምም ሆነ የተፈጥሮ ሕግ ሰጥቶ መቀበልን የሚደግፍ ነው። ራስ ገዟ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ሰጠች ተብሎ የዚያን ያህል ማለቃቀስ አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ስለተዋዋለች የተለያዩ ጠላቶችን በዙሪያቸው እየጠሩ የሚያሰባስቡና ኅብረት የሚፈጥሩበት አካሄድ እራሳቸውን አንቀው እንደመግደል የሚቆጠር መሆኑን ሊረዱ ይገባል።

እንቅስቃሴያቸው የሚጎዳው ኢትዮጵያን ሳይሆን እራሳቸውን ነው። ሶማሊያውያን ከአቅም በላይ እየተንጠራሩ ነው። እስካሁን ድረስ ሕልውናቸውን እያስጠበቀ ያለው የኢትዮጵያ ወታደር ነው። ከዚያ በፊትም ሲያድባሬ “ታላቋን ሱማሊያ መሰርታለሁ” በሚል ሲቃዡ፤ ታናሿን ሶማሊያ ፈጥረው አረፈዋል። አገሪቱ ፈራርሳ ለጎረቤት ጭምር ስጋት የምትሆን ሶማሊያን ትተው አልፈዋል።

ሱማሊያውያን ከቀድሞው መሪያቸው ቅዥት መማር አለባቸው። ጎረቤቶቻችን ደግሞ ሕልውናቸው የተያያዘው ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ ከእኛ መተባበር ግዴታቸውም ጭምር መሆኑን መረዳት አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- ሱማሊያ ከግብጽ ጋር ለመተባበር ሽር ጉድ የማለቷ ነገር ለራሷ ለሱማሊያ አዋጭነቱ የት ድረስ ነው ይላሉ?

አቶ ዳኛው፡– እርግጥ ነው ሶማሊያ ለግብጽ ጥሪ አድርጋለች። ኢትዮጵያና ግብጽ ታሪካዊ ጠላቶች መሆናቸውን የምታውቀው ሶማሊያ፤ ግብጽን ወደምድሯ ጠርታ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት የመሰንዘር ሀሳቧ እራሷን የመጥፋት ሙከራ መሆኑን መረዳት አለባት።

ሶማሊያን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጋት ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ትብብር ነው። ከኢትዮጵያ የምትጠቀመው ውሃ አለ፤ ጠላት በጠራች ቁጥር ኢትዮጵያ የራሷን ርምጃ እንድትወስድ እየጋበዘቻት ነው ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ግብጽ ራሷ እስካሁን ድረስ በብቸኝነት የተጠቀመችበት ዓባይም ሆነ በቀይ ባሕር ላይ ያለውን ይዞታ ለመከልከል የምታደርገው ጥረት ከዚህ በኋላ ግብጽን የማያዋጣት አይደለም። ግብጾች አለኝ የሚሉትን ሕልም እኛ ኢትዮጵያውያን የምንቆጥረው እንደ ቅዠት ነው።

ግብጽ ኢትዮጵያን ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ሞክራለች፤ ይሁንና አለኝ የምትለውን ሰራዊት አራግፋና ትታ የሮጠች አገር ስለመሆኗ ለማስታወስ እንገደዳለን። እንዲያውም በአንደኛው ወቅት ለሰራዊቱ ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ የተበደረችውን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሏ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የወደቀች አገር ናት።

ኢትዮጵያን በቀጥታ ጦርነት ገጥማ የተሸነፈች አገር ናት። የግብጽ ታሪክ ብዙ መሳሪያ የመታጠቅ ነው፤ ነገር ግን ስታሸነፍ ተስተውላ አታወቅም። የግብጽ ስነ ልቦና ሁሌም የተሸነፈና ኢኮኖሚዋም ጦርነትን መሸከም የማይችል ነው። በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያን ጦርነት ትገጥማለች ተብሎ አይታሰብም። በጎረቤቶቻችን ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ደረጃም ሆነ የማሸነፍ ስነ ልቦና ያለው ወታደር ባለቤት የሆነ ከኢትዮጵያ የበለጠ አገር የለም፡፡

አንዳንዶች እንደሚሉት ጠቅላላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠባባቂ ጦር ነው። ክተት ሲባል ከትቶ ኢትዮጵያን ሊያድን የሚችል ሰራዊት ያለው አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ናት። ሌሎች አገራት ተጠባባቂ ጦር ያዘጋጃሉ። ኢትዮጵያ ግን ተጠባባቂ ጦር አያስፈልጋትም፤ ክተት ሲባል ብድግ ማለት የሚችልና ከፍተኛ የማሸነፍ ስነ ልቦና ያለው ሕዝብ ባለቤት ናት።

ግብጾች እኛን ሊጎዱ የሚችሉት በውክልና ጦርነት ነው። እስካሁንም በውክልና ጦርነት ሲያተራምሱን ቆይተዋል። ለዚህ ስራቸውም ከፍተኛ በጀት በጅተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እኛ በውስጥ ጉዳዮቻችን መጠናከርና አገርን ማዳን የግድ የሚለን ነው። አገራችን እንድትድን ከተፈለገ ከውክልና ጦርነት ነጻ መውጣት መቻል አለብን። የውስጥ ጉዳያችንን በውይይትና በንግግር መፍታት ይጠበቅብናል። አገር ከሌለን በአገር ጉዳይ ላይ ልንወያይ አይቻለንም።

አፋሮች፤ “አገሩን የማያውቅ ምድር እየረገጠ ምድርን ይረግማል” የሚል አንድ አባባል አላቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ በምስራቅ አፍሪካ ያለ አንድ የኬንያ ማሳይ የተባለ ታላቅ ጎሳ “ጦርህን ዘቅዝቀህ አታይዝ፤ ምድር ትቆስላለች፤ ምድር ትደማለች” ይላል። እያንዳንዱ አገር ለአገሩ በዚህ ልክ ይቆረቆራል። በሀገራቸው ላይ የውክልና ጦርነት የሚያካሄዱ ኃይሎች የውክልና ጦርነት እንደማይጠቅመን አውቀን ለአገራችን መቆርቆር ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን፡- ለአንደኛው መጻሕፍዎ የሰጡት ርዕስ “በሰላም ውስጥ ያለ ጦርነት” የሚል ነው፤ ምን ማለት ነው ?

አቶ ዳኛው፡- ሁልጊዜ ከግብጾች ጋር ያለን ሁኔታ በሰላም ውስጥ ያለ ጦርነት ነው። ጦርነት መሳሪያ መማዘዝ ብቻ አይደለም፤ ሰላም መንሳትም ጭምር ነው። ጦርነት ማለት ቃታ መሳብ መጨረሻው ነው። ነገር ግን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሒደትን ሰላም መንሳትም በራሱ ጦርነት ነው። ግብጾች ሁልጊዜ ስለወታደሮቻቸው እንደነገሩን፣ በተለያየ ሁኔታ ተጽዕኖ ሊያሳርፉብን እንደሚችሉ እንዳስታወሱን፣ ያላቸው የጦር መሳሪያ ዘመናዊ መሆኑን እንዳሳወቁን፤ የዓባይን ውሃ ብትነኩ በቀጥታ ጦርነት እንገጥማችኋለን ሲሉ እንደፎከሩብን፤ እስካሁንም እንደዛቱብን እዚህ ደርሰናል። ነገር ግን አሳፍረን ከመለስናቸው በኋላ ፊት ለፊት ሞክረውን አያውቁም፡፡

በጠቀስሽው መጻሕፌ ውስጥ ያልኩት ግብጽን ሲነኩት የሚደማውን ስስ ብልት እናውቀዋለን፤ ከዚህ በኋላ ግን ግብጾች ኢትዮጵያን እንነካለን ካሉ ዓባይ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሚያጓጉዘው ንጹህ ውሃ አይኖርም። በርግጥ እኛ መርህ ያደረግነው ፍትሃዊነት ላይ ነው። ከጎረቤቶቻችንም ጋር ቢሆን ጥሩ ነው የምንለው ሰጥቶ የመቀበል መርህን ነው።

በቀጣናው አካባቢ ያሉ አገራት ማንቀላፋታቸውን ትተው በጋራ በመሆን ለጋራ ጥቅም ወደማስከበሩ ቢመጡ መልካም ነው። በቀጣናው ያለነው አገሮች በሙሉ በተናጠል የምናደርገው እንቅስቃሴ ጉልበት የሌለው በመሆኑ በጋራ ለጋራ ጥቅም ወደልማት ፊታችንን ብናዞር የተሻለ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ጎረቤቶቻችን ምንም አይነት ጉልበት የሌላቸው በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ቢተባበሩ ትልቅ አቅም መፍጠር እንችላለን ባይ ነኝ። ጉልበት መፍጠር ከቻልን ከየትኛውም ያደገ አገር ጋር በእኩልነት መደራደር እንችላለን። ማንም አገር ወደቀጣናው መጥቶ በአካባቢው ያለውን የትኛውንም አገር ሊረማመድበት አይችልም። በቀይ ባሕርና በዓባይ ወንዝም ሊፈነጭ አይችልም።

ኅብረት ብንፈጠር ተጠቃሚዎች እንጂ ተጎጂዎች አይደለንም። ለዚህ ትብብር ጎረቤቶቻችን መልካም ፈቃዳቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ ግን በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥም ብትሆን በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ በመሆንዎ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ዳኛው፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You