በሀገራችን ቀደም ሲል የእጅ ጥበበኛው የሚያበረታታው አልነበረም፤ ኑሮውንም በመገለል ነበር የሚመራው። ይህ ሁኔታ ሙያውን ለማቆየትም ሆነ ለማሳደግ ሳያስችል ኖሯል። ሙያተኛውም በሙያው ተገቢውን ጥቅም ሳያገኝበት ዘመናት አልፈዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች ተቀይረዋል። የእጅ ጥበበኛው ወቅቱ ከሚጠይቀው ፋሽን ጋር ለመራመድ ሌተቀን እየተጋ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእጅ ሥራ ሙያ ክህሎት በትምህርት እንዲታገዝ የማድረጉ ጥረት እየተጠናከረ መጥቷል። የእጅ ጥበብ ሙያተኞች ምርቶች በእጅጉ ተፈላጊ እየሆኑ ናቸው። ባሙያዎችም ሙያቸውን ለማሳደግ ያላቸው ፍላጎትም እየጨመረ ይገኛል። ባለሙያዎቹ በልምድ የቀሰሙትን እውቀት በትምህርት በመደገፍ የእጅ ሥራ ሙያ እንዲያድግ የራሳቸውን አበርክቶ በማድረግ ላይ ናቸው። በተለያዩ አውደ ርዕዮች፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና በሌሎች ቦታዎች ላይ የምናያቸው የእጅ ሥራ ውጤቶችን ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ማጠቀስ ይቻላል።
ፋሽን ዲዛይነር ወጣት ነጻነት ተስፋዬ በእጅ ስራ ሙያ ውስጥ ትገኛለች። ፋሽን ዲዛይነር ነጻነት የእጅ ሥራ ሙያን የተማረችው ከእናቷ ነው። በልጅነቷ እናቷ የሚሰሩትን የእጅ ጥበብ እያየች ስላደገች የሙያው ባለቤት ለመሆን አልተቸገረችም። ሙያውን ከልጅነት ጀምሮ እያደገችበት ስለመጣች በፍላጎት ነው የምትሰራው።
‹‹እናቴ የእጅ ሥራዎችን ሠርታ በመሸጥ ነው ያሳደገችኝ›› የምትለው ዲዛይነር ነጻነት፤ ለሙያው ፍቅርና ፍላጎት ያደረባት ያኔ ገና ከልጅነቷ አንስቶም ነው። እናም የእናቷን ሙያ ሊያሳድግላት የሚያስችላትን ትምህርት ለመማር ፍላጎቱ ስላደረባት የፋሽን ዲዛይኒንግ ሙያ ተምራ በምትወደው የእጅ ሥራ ሙያ ላይ ተሰማርታለች።
ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ ቀደም ሲል እናቷ በክር ግብዓት ተጠቅመው ሲሰሩት የነበረው የእጅ ስራ ሙያን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሙያው እንዲያድግ ባላት ፍላጎት ያላትን ክህሎትና በዘርፉ ያገኘችውን እውቀት ተጠቅማ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ከዘመኑ ጋር የሚራመዱና የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያሟሉ ዲዛይኖችን በመሥራት የግል ጥረቷን እያደረገች ነው። በአሁኑ ጊዜም በተለያየ ዲዛይን ከምትሰራቸው አልባሳት ቲሸርት ይጠቀሳል።
አልባሳቱንም ክር በመጠቀም ነው የምታዘጋጃቸው። በተጨማሪም በዚሁ በክር ግብዓት በተለያየ ዲዛይን የተዋቡ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ ብርድ ልብስ፣ ቀሚሶች፣ መደረቢያዎች፣ ኮፍያዎች በመሥራት ላይ ስትሆን፣ ከሀገር ባህል (የሀበሻ ልብስ) ጋር በመቀላቀል የምትሰራቸው የተለያየ የአልበሳት አይነቶች መኖራቸውንም ዲዛይነር ነጻነት ትገልጻለች።
የሀበሻ ቀሚሶቹን በሚፈለገው ዲዛይን ከሠራች በኋላ በሚፈለገው ቦታ ልክ ጥልፍ እንደሚሰራበት ሁሉ ቲሸርት የሚሰራበትን ክር በመጠቀም የሚፈለገው ዲዛይን በማውጣት እንደምትሰራም ገልጻ፤ ከእጅ ሥራ ሙያው በተጨማሪም የተለያዩ አልበሳት ዲዛይን በማድረግ እንደምትስራ ትናገራለች። ዲዛይነር ነፃነት እነዚህ ሥራዎቿን ለገበያ ለማቅረብም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠቅሟታል። ቴሌግራም፣ ፌስቡክ፣ ኢንስቲግራም እና ቴክ ቶክ የመሳሰሉትን የማህበራዊ ሚዲያ ቻናሎች አማራጮቿ እንደሆኑ ገልጻለች።
በተጨማሪ ደግሞ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ላይ በማቅረብ ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረገች ነው። በዚህም አሁን ላይ ምርቶቿን የሚፈልጉ ደንበኞች በውጭ ሀገር እንዳሉ ተረድታለች፤ ከሀገር ውስጥ ደንበኞቿ መካከልም ብዙዎቹ ሥራዎቿን ካዩ በኋላ በትእዛዝ እንድታቀርብላቸው ይጠይቋታል።
አልባሳቱን ለመሥራት የምትጠቀምበት የጨርቅ ክር ግብዓት ጥራት በደንበኞቿ እያስመሰገናት መሆኑን ጠቅሳ፣ እስካሁንም ለገበያ ያቀረበቻቸው አልባሳት በጣም ጠንካራና ረጅም ጊዜ ማገልገል የሚችሉ መሆናቸውን ከደንበኞችዋ በምታገኘው ግብረ መልስ አረጋግጣለች።
ዲዘይነሯ እንደምትለው፤ አሁን ላይ ምርቶቿን በተቻለ መጠን ህብረተሰቡን በማይጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበች ነው። የአንድ ቦርሳ ዋጋ 1ሺ500 እስከ 3ሺ500 ትሸጣለች። ምርቶቹ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል፤ የህብረተሰቡም ፍላጎቱም በጣም ከፍተኛ ነው፤ ብዙ ትእዛዝም እየተቀበልን ነው፤ ብዙ ደንበኞች ቦርሳዎቹን ከሀገር ባህል አልባሳት ጋር ለመጠቀም ይመርጧቸዋል ትላለች።
ዲዛይነር ነፃነት እንደገለጸችልን፤ አልበሳቱን በተለያየ መልኩ ዲዛይን አድርጎ በብዛት ለማምረት ጊዜ ይወስዳል፤ ሥራውም ያደክማል። በመሆኑም ብዛት ያለው የሰው ኃይል ይፈልጋል። በብዛት የሰው ኃይል ይዞ ለመሥራት የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ለጊዜው ከሁለት የቤተሰቧ አባላት ጋር በመሆን ነው ሥራውን እየሰራች የምትገኘው። አቅሙ ቢኖር ግን ዘርፉ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
‹‹ምርቶቿን ባልተለመደ መልኩ ለየት ባለ ፋሽን ስለምሰራቸው ተጠቃሚዎቹ በዚያው ልክ ይወዷቸዋል። ለተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ዝግጅቶች ጨምር ስለሚፈልጓቸውም በትዕዛዝ ያሰራሉ›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ በተለይ ፋሽን የሚከተሉ ሰዎች ሥራዎቿን ወደው እንደሚገዟት ትናገራለች።
ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ እነዚህን ምርቶች ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተረፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት ይቻላል። ምርቶቹን ለመስሪያ የሚሆኑ ጥሬ እቃ ከውጭ ለማስመጣት የሚጠይቀው ቀረጥ ውድ ስለሆነ በሚመለከተው በኩል በቅናሽ እንዲገባ ቢደረግ በግብዓቱ ላይ እሴት እየጨመሩ ወደ ውጭ መልሶ በመላክ ሀገሪቱን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።
እሷ እንዳለችው፤ ህብረተሰቡ ምርቶቹን ገዝቶ ለመልበስ በጣም ይፈልጋል፤ አሁን ላይ ያለው አቅርቦትና ፍላጎት ግን አይጣጣምም። ጥሬ እቃ ከውጭ የሚገባበት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ የምርቶቹ ዋጋ በዚያው ልክ ውድ እንዲሆን ያደርገዋል። ጥሬ እቃው በሀገር ውስጥ የሚገኝበት ሁኔታ ቢኖር ዋጋውም ይቀንሳል። ህብረተሰቡም የሚፈልገውን ምርት በሚፈልገው ዋጋ ማግኘት ይችላል።
ወጣቷ ለሙያው ክብርና ሙያውም እንዲያድግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ትናገራለች። ለሙያው እድገትም የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም ትገልጻለች። ‹‹ለቲሸርት መስሪያ በሚውለው ክር በተለያየ ዲዛይን የሚሰሩትን እነዚህን አልባሳትን የማምረቱ ሙያ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ላይ ብቻ መቅረት የለበትም የምትለው ዲዛይነሯ፣ ሙያውን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ነው የምትገልጸው።
በተለይ ወጣቱ ትውልድ ይህንን ሙያ ተምሮ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁማለች። ሙያውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግም ሆነ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ሥራ ለመስራት በእሷ በኩል ዝግጁ መሆኗን ትናገራለች። ሙያውን ለሌሎች ማስተላለፍ የምትችልበትን ትምህርት ቤት በመክፈት ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠርም ፋሽን ዲዛይነር ነጻነት አስበዋለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም