ሰዎች ለሚኖራቸው እንቅስቃሴ ያስፈልጉኛል ብለው በጥንቃቄ ሊመርጧቸው ከሚገቡ አልባሳት መካከል አንዱ ጫማ ነው፡፡ አንድን ጫማ ለመምረጥ የጫማው አይነት፣ ጥራት ፣ ምቾት እና ዋጋ ከግምት ውስጥ ይገባሉ ፡፡ አብዛኛው ሰው እነዚህን መመዘኛዎች የሚተገብረው ከቤት ውጪ በሚኖረው እንቅስቃሴ የሚጠቀመውን የጫማ አይነት ለመምረጥ ሲፈልግ እንጂ በቤት ውስጥ አብዝቶ የሚያደርጋቸውን ጫማዎች ለመግዛት ሲፈልግ አይደለም።
በዛሬው የፋሽን ገጻችን መቀመጫውን በአሜሪካ ኮሎራዶ አድርጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘውን የቤት ውስጥ ጫማ አምራች ኩባንያ የቤት ጫማ ማምረት ተሞክሮ እንቃኛለን፡፡ በኢትዮጵያም ትክክለኛውን የክሮክስ ጫማ ብቻ የሚሸጡ መደብሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
የጫማው ኩባንያ ክሮክስ ይባላል፤ የክሮክስ የእለት ተእለት ጫማ ሃሳብ አመንጪዎች ሶስት ጓደኛሞች ናቸው። እነሱም ስኮት ሲማንስ ፣ ጂዮርጅ እና ሊንዶን ሀንሰን ይባላሉ፡፡
መረጃዎች እንዳስታወቁት፤ የጫማ ሀሳባቸው መነሻ ዲዛይን የጀልባ ቅርጽ ይመስላል፤ ጫማዎቹም ምቾት ያላቸው ፣ የማይከብዱ እና ሰዎች በየእለቱ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ አይነት ተደርገው የሚመረቱ ናቸው፡፡ የክሮክስ የቤት ውስጥ ጫማ አምራች የተመሰረተው እ.አ.አ በ2002 ሲሆን፣ በየእለቱ የሚያገለግሉ ጫማዎችን ለወንዶችና ለሴቶች እንዲሁም ለህጻናት እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ ኩባንያው ጫማዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው በፍሎሪዳ የጀልባ ትርኢት ላይ ሲሆን፣ በወቅቱም 200 ጫማዎችን ሸጧል፡፡
ኩባንያው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በገበያው ላይ ስሙን ለመትከል እና ተቀባይነት ለማግኘት የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ መቆየቱን ከኩባንያው ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ መረጃው እንዳመለከተው፤ ስለውበቱ እና አይነቱ አሉታዊ የሆነ አስተያየት የሚሰጡ ቢኖሩም፣ ሰዎች ግን ጫማውን ለእለት ተእለት ተግባር በእጅጉ ሲፈልጉት ይስተዋላል፡፡
ቆመው ሲሰሩ የሚውሉ ሰራተኞች፣ ምግብ አብሳዮች ፣ አትክልተኞች ምቾት የሚሰጥ ጫማ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የክሮክስ ጫማም ይህን ምቾት በሚገባ እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ መሆኑ ይገለጻል፡፡ የክሮክስ ምርት በገበያ ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ሲሆን፣ ኩባንያውም እ.አ.አ በ2005 አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ጫማዎችን በማምረት 75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባት የቻለም ነበር፡፡
መረጃው እንዳመለከተው፤ የክሮክስ ጫማ በይበልጥ እውቅናን ለማግኘት ከተጠቀማቸው የሽያጭ መንገዶች ውስጥ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ካላቸው ታዋቂ ሰዎች ጋር አብሮ መስራት አንዱ ነው፤ ጫማዎቹን በተለያየ የዲዛይን አማራጭ እና የቀለም አይነት በማስተዋወቅ ያከናወናቸው ተግባሮችም እንዲሁ ሰዎችን ከአንድ በላይ የክሮክስ ብራንድ ጫማ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አድርጓቸዋል ፡፡
ሌላኛው የሽያጭ መንገዱ የክሮክስ ተጠቃሚዎች የሚገዟቸውን ጫማዎች በራሳቸውን መንገድ ዲዛይን እንዲያደርጉት እና ልዩነት እንዲሰማቸው የሚያስችሉ ዲዛይኖችን ማስተዋወቁ መሆኑንም መረጃው ይጠቁማል። ደንበኞችም ኩባንያው ከሚያመርታቸው ምልክቶች ስሞች እና ፊደላት የሚወዷቸውን በመጠቀም ጫማቸውን ማስዋብ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠሩም ሌላው ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ሌላኛው ምክንያቱ ለየት ያለ ዲዛይን ያላቸውን የክሮክስ ጫማዎች በማምረት ደንበኞችን ለመሳብም የሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ ምርቶቹን በትልልቅ የፋሽን ትርኢት ዝግጅቶች እና ፕሮግራሞች ላይ በመገኘትና ራሱንም በማስተዋወቅ አዳዲስ ደንበኞችን ሲያፈራ የኖረም ነው፡፡
ጫማው በተለያየ ዲዛይን እና አይነት ተመሳስሎ የሚሰራ መሆኑን መረጃው ጠቅሶ፣ ሰዎች ኩባንያው የሚያመርተውን ትክክለኛውን የክሮክስ ጫማ የበይነ መረብ መገበያያ ዘዴዎችን በመጠቀም ከየትኛውም ሀገር ሆነው እንደሚገዙም ተመልክቷል ፡፡
ከአካባቢ ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን፣ የክሮክስ ኩባንያ በይበልጥ እውቅና ያተረፈው እና በርካታ ተጠቃሚዎችን ያፈራው የኮቪድ 19 ወረረሽኝ በተስፋፋበት ወቅት መሆኑን ፎርብስ መጽሄት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ጊዜው በዓለም ያሉ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበት ብዙ ሰዎች ስራቸውን ትተው ቤት ውስጥ ለመቀመጥ የተገደዱበት ወቅት መሆኑ ለኩባንያው የቤት ጫማዎች ገበያ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ነበር ፡፡
በዚያን ወቅት ሰዎች ለስራ ቦታቸው የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ አይነት ጫማዎች አስቀምጠው፣ በቤት ውስጥ የሚደረጉ ምቹ ጫማዎችን ወደ መፈለግ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያው ወረርሽኙ በተስፋፋበት እ.አ.አ በ2021 ብቻ 115 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የክሮክስ ጫማዎችን መሸጥ ችሏል፡፡ ኩባንያው ለተለያዩ ሆስፒታሎች ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ እነዚህን ጫማዎች በወቅቱ በከፍተኛ የስራ ውጥረት ውስጥ ለሚያሳልፉ የሆስፒታል ሰራተኞች ማበርከቱም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
ጫማዎቹ ምቾት እንዳላቸውና በዚህም የደንበኞች ምርጫ መሆኑ ቢገለጽም፣ በአንዳንድ ሰዎች ግን እንደሚተችም ይገለፃል፡፡ ከዚህም አልፎ ኩባንያው በተለያዩ ምክንያቶች እ.አ.አ በ2006 ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ገጥሞት፣ በርካታ ሰራተኞቹን አባሮም እንደነበርም ከድረገጽ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የኩባንያው ኃላፊ አንድሪው ሪስ ሰዎች ክሮክስን ሊጠሉትም ሊወዱትም ይችላሉ፤ እኛ ግን እንዲወዱት ለማድረግ ብዙ ምክንያቶችን እናስቀምጣለን በማለት በአንድ ወቅት ከፎርብስ መጽሄት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው ቀደም ሲል ደርሶበት ከነበረው ኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ መሆን እንደቻለም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
በ2023 እንዲሁ አጠቃላይ የተጣራ ገቢው 792 ሚሊዮን ዶላር መድረሱም ኩባንያው በድረ ገጹ የለቀቃቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ85 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ምርቶቹን ለገበያ ያቀርባል፡፡ ዋና መገለጫውም ‹‹ ሁሉም ሰው ምቾት ይገባዋል ›› የሚል ሲሆን፣ አካታችነት ፣ ቀጣይነት እና ማህበረሰብ ተኮር እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰራም ይገልጻል ፡፡
አሜሪካ ፣ ካናዳ ፣ አውስትራሊያ ፣ ጃፓን የክሮክስ ብራንድ ተጠቃሚዎች በብዛት የሚገኙባቸው ሀገራት ናቸው ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እና ተደራሽ ማድረግ የቻለ በመሆኑም አብዛኛዎቹ የክሮክስ ጫማዎች በተለያዩ ሀገሮች ይመረታሉ፤ ቬትናም ፣ ቻይና እና ጣልያን በስፋት ከሚመርትባቸው ሀገሮች መካከል ይጠቀሳሉ ፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም