አፍሪካውያንን ያገናኘው የፋሽን መድረክ

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ አይደለችም፤ የአፍሪካ ሕብረትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫም ናት። ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ከሚያስተናግዱ ትልልቅ የዓለም ከተሞች መካከልም ትጠቀሳለች። በዚህ በጀት ዓመት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከ20 የማያንሱ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገዷም ይህንኑ ያመለክታል።

በሳምንቱ ከተካሄዱ መድረኮች አንዱ ‹‹አፍሪካ ታከብራለች›› (Africa Celebrates) የተሰኘው አንዱ ሲሆን፣ መድረኩ በተለያዩ ኩነቶች ተከብሯል።

ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደው ይህ መድረክ፣ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ነው። ዋና ዓላማውም የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ እንደ ማበረታቻ የሚዳሰሱትን በአፍሪካ የበለጸገ የጥበብ ፣ የባህል ፣ የቅርስ ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማስተዋወቅ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውህደት በማበረታታት የአፍሪካን በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማክበር ነው።

የአፍሪካ ታከብራለች መድረክ የ2024 ዋና ዓላማ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ጋር የሚራመድ አፍሪካውያን ማስተማር ፣ ለአፍሪካውያን ብልጽግና እና ውህደት በጥበብ ፣ ባህል ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ታሪክ እና ንግድ ላይ ጠንካራ ግንዛቤን መፍጠር የሚሉ ናቸው።

ኒቆዲሞስ የሺጥላ ‹‹ በእንደራሴ የወጣቶች ማህበር›› ውስጥ ዋና ጸሀፊ ነው። የወጣት ማህበሩ በአንድ ወጣት ሀሳብ አመንጪነት ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ላይ የማሳተፍ እድል በመስጠት ወጣቶች ራሳቸውን በተለያየ መስክ እንዲያበቁ የሚያደርግ ማህበር ነው›› ሲል ይገልጻል።

ማህበሩ በሲቪል ማህበረሰብ ምዝገባ እውቅና አግኝቶ ስራ ከጀመረ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ‹‹እንደራሴ ወጣቶችን ለማንቃት እድል ይሰጣል፤ ባለው ነባራዊ ሁኔታም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እድሎችን እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል ›› በማለት ወጣት ኒቆዲሞስ ያብራራል።

እሱ እንዳብራራው፤ እንደራሴ በዙሪያው ያሉ ወጣቶችን ለማብቃት በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ ከተለያዩ ሀገር ውስጥ ከሚገኙ የወጣት ማህበራት እና ቡድኖች ጋር እንዲሁም ከአህጉረ አፍሪካ ትልልቅ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚጠቀሙበትን እድል ይፈጥራል።

ይህ የ‹‹አፍሪካ ታከብራለች›› መድረክ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ ነው የተካሄደው። የፋሽን ኤግዚቢሽን፣ የባህል ምሽት እንዲሁም የአፍሪካ ወጣቶች ፎረም በመድረኩ ተካሂደዋል።

በፋሽን ኤግዚቢሽኑ ከመላው አፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ በርካታ ዲዛይነሮች ተሳታፊ ሆነዋል። ‹‹ ከካሜሮን፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል›› በማለት ያብራራው ወጣት ኒቆዲሞስ፣ አፍሪካ ለፋሽን ኢንዱስትሪው ሊውሉ የሚችሉ ከሌሎች አህጎሮች በተለየ በርካታ ባህሎች እና የደመቀ የባህል አልባሳት እንዳሏትም ተናግሯል።

የፋሽን ኤግዚቢሽኑ እነዚህን የአፍሪካ ሀገራት ማሳተፍንና አንድ ማድረግን ያለመ ሲሆን፣ ከአፍሪካውያን ውጪ ለሚገኙ ለሌሎች ዜጎችም ጭምር ማሳየትን መሆኑን አንስቷል። በፋሽን ኤግዚቢሽኑ ላይ ዲዛይነሮች የኢትዮጵያ የባህል አልባሳትን ይዘው ቀርበዋል። ከተፈጥሯዊ ግብዓቶች የተዘጋጁ እና ሙሉ ለሙሉ የእደ-ጥበብ ውጤት የሆኑ፣ ከቆዳ የተሰሩ ቦርሳዎችን እንዲሁም ሌሎች የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ከመላው አፍሪካ ይዘው የቀረቡ ተሳታፊዎችን በኤግዚቢሽኑ ላይ ተመልክተናል።

በአፍሪካ እና በአፍሪካውያን የተሰሩ አልባሳትን፣ የምግብ አይነቶችን፣ የኪነጥበብ ስራዎችን ማበረታትን ዓላማው ያደረገው ይህ የአፍሪካ ታከብራለች ክንውን፣ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥ እና ቱሪዝምን መደገፍ፣ ሴቶች እና ወጣቶችን ማብቃትንም ዓላማው ያደረገ ነው።

ባለፉት ጊዜያት ‹‹የአፍሪካ ታከብራለች›› የፋሽን ኤግዚቢሽኖች 38 የሚጠጉ የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉባቸው ስለመሆናቸው የአፍሪካ ሰለብሬት ይፋዊ ድህረ ገጽ የጠቆመ ሲሆን፣ 11 የሚሆኑ ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ሀገራትም በፋሽን ኤግዚቢሽኑ ላይ መሳተፋቸውን አስታውቋል።

በሰሞኑ የፋሽን ኤግዚቢሽን ላይ ስራቸውን ይዘው ከቀረቡት ውስጥ እታገኝ እንግዳወርቅ አንዷ ናት። እታገኝ ‹‹ ፒፖስ ፋሽን ›› የተሰኘ የራሷ የፋሽን ብራንድ አላት። በዲዛይን ስራ አምስት ዓመት ያህል የቆየች ሲሆን፣ የአፍሪካውያን ጨርቅን ከኢትዮጵያውያን የባህል ልብስ ጋር በማጣመር የዲዛይን ስራዎቿን ለደንበኞቿ ታቀርባለች።

‹‹በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ ነው። አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሆኖ ከመስራት እንዲዚህ አይነት ዝግጅቶች ላይ መገኘት ራስን ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል። ›› የምትለው እታገኝ፣ የምትሰራቸው ልብሶች በአብዛኛው በአፍሪካውያን ዘንድ የተለመዱ እና አይን ያዝ የሚያደርጉ የሚማርኩ ቀለማት ያላቸው መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡

ሁነቱን ከምትሰራው ስራ ጋር የተጣጣመ ሆኖ አግኝታዋለች። ኢትዮጵያዊ ሆና በብዛት የአፍሪካውያን የባህል አልባሳት ይዛ መቅረቧ ከጎብኚዎች የተለያዩ አስተያየቶች እንዲሰጣት ማድረጉንም ገልጻለች። ‹‹ አፍሪካውያን የራሳቸውን አልባሳት ይዘን ሲያዩን በጣም ደስ ይላቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ አልባሳቱን እኛ የምናዘጋጃቸው አይመስላቸውም፤ ከአፍሪካ ሀገሮች አምጥተን የምንሸጥ ይመስላቸዋል ›› ስትልም አብራርታለች።

ወደ አፍሪካ ፊቴን አዙሬ የአፍሪካ ጨርቆችን ዲዛይን ማድረግ ከጀመርኩ አምስት ዓመት ሆኖኛል ስትል ጠቅሳ፣ አቀባበላቸው ጥሩ መሆኑንም ትገልጻለች። ‹‹ስራውን ስጀምረው አንዳንድ የአምባሳደር ባለቤቶች ደንበኞቼ ወደውት ጨርቁን ከሀገራቸው እያመጡልኝ እሰራ ነበር፤ አሁን አሁን ብዙ ሰው ይፈልገዋል ትላለች።

በዚህ የፋሽን ኤግዚቢሽን መድረክ ላይ መገኘቷ ከሰዎች ጋር አድራሻ ለመለዋወጥ፣ ምርቶቿን ለመሸጥ እና ሌላ ጊዜ ልታገኛቸው የማትችላቸውን ደንበኞች ማግኘት እንዳስቻላትና በጣም ጥሩ መድረክ ሆኖ እንዳገኘችው ገልጻለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You