በኢትዮጵያ ባህልና ወግ መሠረት ነውር ናቸው ተብለው ትውልዱ እንዳይፈጸማቸው ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡት በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ሌብነት የሚለው ቃል ነውርና አስጸያፊ ድርጊት እንደሆነ ሲነገረን የኖረ ነው። በማህበረሰቡ ባህል ነውር(አጸያፊ) የሆነው ይህ ድርጊት በሃይማኖታዊ አስተምሮትም እንዲሁ የማይደገፍና የማይበረታታ ነው።
በባህልና በእምነት በአንድ ላይ የሚወገዝ በመሆኑ ደግሞ ህብረተሰቡም ወደዚህ መጥፎ ድርጊት እንዳይገባ ያደርገዋል። ይህንን ተላልፎም ተግባሩን ሲፈጸም የተገኘ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። በዚህ መንገድ እየተጓዘ ትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የሚገኘው በጎ ልምድ ሆኖ ረ ዘም ላሉ ጊዜያት ቆይቷል ።
አሁን ላይ የማህበረሰቡ ባህልና ወግ እየተሸረሸረ ነውር( አጸያፊ) ተብለው ሲወገዙ የኖሩት ተግባራት በተቃራኒ መንገድ በጎ ተግባራት እንደሆኑ እየተቆጠሩ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ነውር በሚለው የሚታወቁት አጸያፊ ተግባራት አሁን ላይ ጸያፊነታቸው ቀርቶ እንደ መልካም ሥራ በበርካቶቻችን ዘንድ እየተፈጸሙና እየተለመዱ መጥተዋል።
አሁን ላይ በተለይ በገሃድ እየተሰሙና እየታዩ እንዲሁም እየተለመዱ ያሉት የሌብነት ድርጊቶች ትንሽ ብለን ከምንላቸው ቦታዎች ጀምሮ እስከ ትልቅ ብለን እስካስቀመጥናቸው ድረስ በሁሉም ቦታዎች ላይ በሚታወቅ እና በሚታይ መልኩ እየተፈጸሙ እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ መጥፎና ሊለመድ የማይገባው አካሄድ አንድ ነገር አስታወሰኝ፤ ‹‹እማዬ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ …›› አለ ሌባው የሚለውን የሌባው ሲቀጣ ያሰማውን ተማጽኖ።
እንደ ማህበረሰብ አሁን ምን ላይ ነን? ወዴትስ እየሄድን ነው? ብለን መጠየቅ የሚያስፈልግ ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል። ሌብነት አሁን ባለው አያያዙ ቀጥሎ ስር ከሰደደ በቀላሉ የምንፈታው ጉዳይ አይሆንም። ሌብነት ለመከላከል እየተሰራ ባለው ሥራ የመጀመሪያ ሊሆን የሚገባው ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ ማፍራት ላይ ማተኮር እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲመክሩ ይሰማል።
ሌብነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ደግሞ ከሁሉም በላይ ትውልድ የሚያፈሩ ተቋማት ጥልቁን ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። ለዛሬም ላነሳ የፈለኩት በዚሁ ጉዳይ ላይ ነው፤ በተለይም ሀሰተኛ የትምህርት መረጃን በሚሸጡ ተቋማት ዙሪያ አሁን አሁን መማር ሳይስፈልጋቸው፣ እውቀት የሚለው ነገር ሳያሳሰባቸው፤ ብዙም ሳይለፉና ሳይደክሙ እቤታቸው ቁጭ ብለው የፈለጉት አይነት የትምህርት ማስረጃ በቀላሉ መግዛት የሚችሉ ዜጎች ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚህ ሕገወጦች በየሥራ መስኮቹ ተሰግሰገው ስራዎች በአግባቡ በሚመጥናቸው ባለሙያዎች እንዳይሰሩ ተግዳሮት እየሆነ ነው።
ሰው እውቀትና ችሎታን ሳይኖረው እውቀት በብሩ መግዛት ከቻለ፤ በአቋራጭ መንገድ የሚፈልገው ኃላፊነት ሆነ ሙያ ላይ መቀመጥ ከቻለ ሁሉም ነገር እዚያ ጋር ነው የሚያበቃው። ሳይለፋና ሳይደክም እውቀት ሳይፈልግ ያለምንም ችሎታ በቦታው ላይ መቀመጥ ከቻለና ኃላፊነት ከተሰጠው በሚፈልገውና በሚመስለው ጎዳና እንደ ውሃ የሚፈስ ከሆነ አካሄዱ ሀገርና ሕዝብን ችግር ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው።
በሀገራችን የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በርካቶች በሀሰተኛ ትምህርት መረጃ የማይመጥናቸው ቦታና ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በየክልሉ በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች ሳይቀረ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት በሚያደርጉበት ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንደተገኘባቸው ስለመሆኑም በስፋት እየተነገረ ነው።
በኛ ሀገር ሀሰተኛ የትምህርት መረጃን በሚሰጡና በሚያቀርቡ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ እምብዛም ነው። አስተማሪ እርምጃ ተወስዶ ለሕዝቡ ሲነገርም አይሰማም። የሚመለከታቸው አካላት በችግሩ ዙሪያ የማያዳግም እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ ዛሬ ላይ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዲህ አቅላቸውን እስከምንስት ድረስ ውስጡ ገብተን ባልተቦራጨቅን ነበር።
ባለፈው ወር የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን እንዳስታወቀው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ከተደረገባቸው ከአምስት እስከ ስድስት በመቶ ትክክለኛ አለመሆናቸው አረጋግጧል። በእነዚህ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የመረጃ ማደራጀት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ከአምስት እስከ ስድስት መቶ የሚሆኑት የሚለው ቁጥር በራሱ ምን ያህል ችግሩ ውስጥ እንዳለን ማሳያ ነው።
ችግሩ ምን ያህል የገነገነ እንደሆነ ያመላክታል። በቅርቡ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ የሚፈልጉ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ በመሆን የማረጋገጫ ወረቀት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ማስታወቁን ይታወሳል። ይህ እሰየው ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።
ቴክኖሎጂን መጠቀም ሙሉ ለሙሉ ሀሰተኛ የትምህርት መረጃ አሰጣጥን እስከ ወዲያኛው ለማጥፋት ባያስችል እንኳን ሥርዓት ለማስያዝ የሚያግዝ ነውና ለተግባራዊነት መፍጠንን ይጠይቃል። ያለንን የቴክኖሎጂ አቅም አሟጦ በመጠቀም የሌብነትን ሰንሰለት በመበጣጠስ ሌብነት የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት ግን ከዛሬ ጀምሮ ባለን አቅም ልንቀሳቀስ ይገባል ።
በተለይ በዚህ የተበላሸ አሠራር ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ አካላት ዞር ብለው እራሳቸው መፈተሽ አለባቸው። አስነዋሪ ተግባራቸው በሀገርና በትውልድ ላይ የሚፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነውና ከድርጊታቸው ተቆጠበው የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው ባይ ነኝ። የሌብነት ትንሽ ሆነ ትልቅ የለውም፤ ሌባ ያው ሌባ ነው። ሥርዓት ሊበጅለት የግድ ይለዋል፤ በተለይ በሀሰተኛ የትምህርት መረጃ ጉዳይ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል።
ቸር እንሰንብት።
ትንሳኤ አበራ
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም