ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕገ ወጥ የማዕድን ፍለጋ፣ ልማትና ግብይት ሳቢያ ከወርቅ ምርቷ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት አልቻለችም፤ ሕገወጥ ተግባሩ የሀገርንና ማዕድኑ የሚለማባቸውን ክልሎችን ገቢ በእጅጉ እየጎዳ ይገኛል። ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት ያለበት የወርቅ መጠን እየቀነሰ ስለመምጣቱ በዚህ ዓመት የሰጠው መረጃ ያመለክታል። ወርቅ በስፋት የሚመርትባቸው ክልሎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጸጸም ሪፖርት ላይ በተወያየበት ወቅት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ የስድስት ወር የወጪ ንግድ ገቢ ትንሽ ቅናሽ ለማሳየቱ የተሰጠው አንድ ምክንያት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ነው።
የችግሩን አሳሳቢነት የተረዳው መንግስት ወርቅና ሌሎች የሀገሪቱ ሀብቶች በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እንዳይወጡ ለመቆጣጠር እንደሚሰራም በወቅቱ አረጋግጧል። በቀጣይም የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ቀዳሚ ተግባር ኮንትሮባንድን መዋጋት፣ በኮንትሮባንድ የሚመዘበረውን የኢትዮጵያን ሀብት መከላከል እንደሚሆን አስገንዝቦም ነበር።
የማዕድን ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የነበረው ድርሻ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ወደ ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት እንዳይሸጋገሩ ችግሮችን የሚለይና መፍትሄ የሚያስቀምጥ ሀገር አቀፍ ካውንስል ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በተግባራዊ እንቅስቃሴውም ሕገወጦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛሉ። ባለፈው መጋቢት ወር ከወጣ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው፤ የጸና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎችንና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢት ተይዘዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በተጨማሪም ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራትና ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችም ከእነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ይህ በሕገወጥ የማዕድን በተለይም የወርቅ ማዕድን ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይት ውስጥ በተገኙ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያን ላይ የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተያዘው ሰኔ ወር መጀመሪያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ አመልክቷል። በዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት ውስጥ በባህላዊ መንገድ ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ የተሰጣቸው ማኅበራት አመራሮች፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የጥቅም ተጋሪዎቻቸውም ተሰማርተው ተገኝተዋል።
በወርቅ ማዕድን ላይ የሚታየውን ሕገወጥነት ለመግታት ርምጃ መውሰድ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንደጨመረም በቅርቡ የወጣው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል። መንግስት ሕገወጦቹን በቁጥጥር ስር እያዋለ ያለበት እንዲሁም ይህን ተከትሎም ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ ያለበት ሁኔታ ሕገወጦቹን የመቆጣጠሩ ሥራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ያመለክታል።
ይሁንና በቁጥጥር ስር ከዋሉት በሕገወጥ ድርጊቱ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች፣ የባህላዊ ወርቅ አምራች ማኅበራት አመራሮችና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ካሉ ተባባሪዎቻቸው አኳያ ሲታይ የመከላከልና መቆጣጠር ሥራው በእጅጉ ፈታኝ መሆኑን ያመለክታል። ይህም የበለጠ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል።
ሕገወጦችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ብሔራዊ ባንክ በሚገባው የወርቅ መጠን ላይ ለውጥ ማምጣት የተቻለው የተከናወነውን ጠንካራ ስራ ተከትሎ ነው። ሕገወጥ ድርጊቱን ለመከላከል ብዙ ዝግጅት ተደርጎ፣ ጥናት ተሰርቶ ነው ወደ ስራው የተገባው። በቀጣይም ከዚህ በላይ መስራትን እንደሚፈልግ በሕገወጥ ድርጊቱ ከተሳተፉበት አካላት ማንነት መረዳት ይቻላል።
ሕገወጥ ተግባሩን በመከላከልና መቆጣጠር ስራ የተሰማሩ አካላት ርብርብ ምስጋና ሊቸረው ይገባል፤ ይህን ምስጋና ማቅረብ የበለጠ ኃላፊነትም መስጠት ይሆናልና። ሕገ-ወጥ ተግባሩ ገቢን የሚያሳጣ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ደኅንነት ስጋትም ጭምር ነው እንጂ። ይህም የመከላከልና መቆጣጠር ሥራውም ሰፊና የተጠናከረ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል። ችግሩን የመፍታቱ ሥራ ከእስከ አሁኑም በላይ የሁሉንም አካላትና የመላውን ሕዝብ ርብርብ በእጅጉ ይጠይቃል።
የእስከ አሁኑ ሥራን የአጠቃላይ ሕገ-ወጥ ንግድ መከላከል ሥራው መጀመሪያ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሕገ-ወጦቹ ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው። ይህ ስራ በሌሎች ወርቅ አምራች አካባቢዎች እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ይህን የሚመጥን ስራ ለመሥራትም ዝግጁ መሆን ይገባል፡፡ በሕገወጦቹ ላይ የሚወሰደው ርምጃ ፈጣን፣ አስተማሪና የማያዳግም ሊሆን ይገባል። በሌላ አነጋገር ሌሎች ትምህርት የሚወስዱበት ጠንካራ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፤ ያንን ማድረግ ከተቻለ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም