‹‹ኢትዮጵያዊው ሼክስፒር›› ይለዋል ጉምቱው ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚያሔር ወዳጁ ስለነበረው ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ወይንም አያ ሙሌ ሲናገር፡፡
የአያ ሙሌ የሕይወት መንገድ እጅግ በጣም ረዥም ነው። እንደ ምድር ባቡር ከንፈው እንደ ሰማይ አሞራ ቢበሩም የእርሱን የኑሮ ግዛት ተናግረው አያገባድዱትም። ለመድረስም ሆነ ደርሶ ለመያዝ ያዳግታል፣ ምክንያቱም ስራዎቹ ብቻ ሳይሆኑ እርሱ እራሱ ቅኔ የነበረ ሰው ነውና፡፡
ከአባቱ ከአለቃ ተስፋዬ ገብረኪዳን እና ከእናቱ ከወይዘሮ ታጋይ ንጋቱ ሚያዚያ 18 1946 ዓ.ም በወሎ ጠቅላይ ግዛት በወልዲያ ከተማ ነበር የተወለደው። የ1ኛ ደረጃ ትምህርቱን በእቴጌ ጣይቱ ትምህርት ቤት ተማረ። በወልዲያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ደግሞ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጠለ። አያ ሙሌ ስለ አስተዳደጉ ብዙ ተናግሯል። “የድሃ ልጅ ነኝ። እናቴ እጄን ይዛ ትምህርት ቤት ያስገባችኝን ቀን እንጂ የገዛችልኝ ደብተርና እስክሪፕቶ ትዝ አይለኝም። ያደኩትም በውጣውረድ ነው” ይላል ልጅነቱን በአንድ ወቅት ሲያስታውስ፡፡
የልጅነት ሕይወቱን የገፋው እንደ አብዛኛው ልጅ ከቤተሰቦቹ ጥላ ስር ሆኖ አልነበረም። ያደገው ከአያቱ ጋር ቢሆንም ምንም የማድረግ አቅም ስላልነበራቸው የኑሮን ፈተና በራሱ ሊጋፈጣት ግድ አለው። ሊስትሮ ሆኖ ጫማ በመጥረግ እንዲሁም ቱሪስቶችን የማስጎብኘት ስራም ይሰራ ነበር። ከወዛደርነት ጀምሮ ያልሞከራቸው የሥራ አይነቶች የሉም። ሊስትሮ እየሰራ በነበረበት ወቅት የደንበኛውን ሱሪ በቀለም አበላሽቶ የቀመሳት ኩርኩም ጊዜው አልፎም ‹‹ታመኛለች›› ይል ነበር።
የግጥም ስብስቦቹም ሆኑ የሙዚቃ ሥራዎቹ እያደር እንደ ወይን እየጣፈጡ የሚሄዱ ናቸው። ቅኔዎቹን ከየትም አያመጣቸውም። ስለምን ልጻፍ እያለም አይጨነቅም። ሁሉንም ከሕይወቱ እየጨለፈ ይቀዳቸዋል። ከ30 ዓመታት በፊት የሰራቸው የሙዚቃ ግጥሞች ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ ይደመጣሉ። ብጽዓት ስዩም በእንባ ታጅባ ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› እያለች ስታዜም ብዙዎች በእንባ ተራጭተዋል።
ሃና ሸንቁጤና ኩኩ ሰብስቤን ጨምሮ ለበርካታ እውቅ ድምጻውያን የሰራቸው የሙዚቃ ግጥሞች ከጆሮ በላይ ልብን የሚያረሰርሱ ናቸው። በርካቶችን ከዝና ማማ ላይ ሰቅሎ እርሱ ግን የጉስቁልና ኑሮ እጣፋንታው ሆነ። ከስሥራዎቹ ሁሉ አንደኛው ግን እንዲሁ እንደዋዛ ተናግሮ ለማለፍ የማይቻል ነው። አያ ሙሌ እራሱ ይህንን ስራ ‹‹ልክ እንደልጄ ነው›› ይለዋል። ወፍዬ..ወፊቱ ድምፃዊ አበበ ተካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይወጣ ከሕዝብ ልብ ውስጥ ገብቶ የቀረበት ስራ ነው። ለዘመናት ደግመን ደጋግመን ብንሰማውም የሙዚቃው ውበት ሊደበዝዝ፣ ቅኔውም ሊረግፍ አልቻለም። የሙዚቃውን ሙሉ ግጥም ለማስፈር ባይቻልም እስቲ ገሚሱን እንኳን እንመልከት።
….ጭራ ጭራ የምታድረው
ጭራ ለቅማ የምታድረው
እንዴት አስናቀችኝ
ቀድማኝ ጎጆ ወጥታ ጎጆ አስተማረችኝ
……..
ገመና ከታቹን የሳር ቤት ያማረሽ
ሚስጥረ መለኮት ማነው ያስተማረሽ
ካፈር ክዳን ጎጆ መሬቱን ፈልፍሎ
ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ
…..
ፈጣሪዋን አምና ያፏን ጥሬ ሰጥታ
ለጭሮ አዳር ውሎ በዝማሬ ወጥታ
አዳኝ እንዴት ያጥቃት ፍርድና ዳኛ አጥታ
አጣው ነጣው ብላ እንደሰው ባይከፋት
ምፅዋት ባትለምን ተርፎን ባንደግፋት
ጎጆዋ ለቻላት ምን ነበር ባንገፋት
………
ታማ ትንፋሽ አጥሯት ደክማ ስታጣጥር
ማን ያቃናት ይሆን ውለታ ሳይቆጥር
ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት
ያፉን ማን ይሰጣል የጁ ሲርቅበት
እህህ ወፊቱ እሁሁ ወፊቱ እህህ ወፍዬ እህህ ወፊቱ እህህ ወፊቱ…
በዚህ የሙዚቃ ግጥም ያፉን ማን ይሰጣል የእጁ ሲርቅበት እያለ ወፊቱ ለልጇ የምትከፍለውን መስዋዕትነት ይገልጸዋል። ሙዚቃውን ልብ ብለን ካደመጥነው ግን በሙዚቃው ውስጥ ያስቀመጠው ቅኔያዊ ሃሳብ ምን ያህል ጥልቅና በቀላሉ የማንረዳው እንደሆነ እናያለን። ከወፊቱ ውስጥ የሚገኘው ምስል ቃላትም ሆነ ብሩሽና ሸራ ሊገልጡት የሚችሉት አይደለም። ይህ ስራ የምናቡ ርቀት ምን ያህል እንደሆነ ያሳየናል።
በ1977 ዓ/ም በሃገራችን ድርቅ በተከሰተበት ወቅት አያ ሙሌ ለፈጣሪው ‘ከመንበርህ የለህማ’ እያለ ክርር ባለ ስሜት የጻፈው የግጥም ስራው ዛሬም ድረስ ከብዙዎች አዕምሮና ልብ ውስጥ አለ፡፡ እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ የእርሱ ሥራዎች ለቁጥር የሚታክቱ ወሰን አልባ የጥበብ ድንበር ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ አያ ሙሌ ከአማርኛ ውጭ ትግርኛ፣ ግዕዝ፤ አፋርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ ቅኔ የሚዘርፈው በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛውም የሚጽፋቸው ግጥሞች የእወነትም የሼክስፒር እንጂ የአንድ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ አይመስሉም።
ጠቢቡ ባለቅኔና ሕይወቱ ግን የአንዲት ምድር ሁለት ዳርቻ ናቸው። ከባለሥልጣናት እስከ ቱጃሩ የጥበብ ሰዎችን ጨምሮ ከሊቅ እስከ ደቂቁ በቅርበት የሚያውቃቸውና የሚያውቁት በርካታ ሰዎች እያሉ እርሱ ግን በብቸኝነት ዓለም ከርታታ ባህታዊ ሆኖ ምንም እንደሌለው ሰው ከጎዳና እስከ ገዳማት ሲናውዝ ነበር የሚኖረው። ስላጣ ነው ብለን እንዳንል በሙዚቃ ሥራዎች ያገኘውን ገንዘብ እንኳን ለራሱ ሳይሆን ለድሆች ነው የሚያድለው።
ምናልባት ወፈፍ ቢያደርገው ነው ብለን እንዳንፈርድ ደግሞ እራሱን ከመጉዳቱ ውጭ ፍጹም ከዚህ የተለየ ሰው ነው። አያ ሙሌ እያበሳጨ የሚያስቀን፣ እያናደደ የሚያስለቅሰን በሁለት የተለያዩ ስሜቶች ግራ የሚያጋባን እርሱ እራሱ ቅኔ የሆነ ሰው ነው። ስለ ሃይማኖት ሲያወራ አንዴ ዳዊት የደገመ ቄስ፣ ሌላ ጊዜ ሃዲስና ቁርአን የቀራ ሼህ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ነብይም ይቃጣዋል፡፡ ይሆናሉ የሚላቸው ብዙ ነገሮች ሆነው እንደሚገኙ የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክራሉ።
አደላድሎ የሚያኖረውን የሥራ እድል ቢያገኝም እሱ ግን አልሆንልህ እያለው ሥራውን እየለቀቀ የነብሱን ጥሪ ፍለጋ ይሄዳል። በአንድ ወቅት በተራድኦ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ደሞዝ ተቀጥሮ በመሥራት ላይ ሳለ ለሥራ ወጣ ወዳለ አካባቢ ሄዶ የህጻናቱን ራብ በመመልከት በዚያው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ ሥራውን ጥሎ ለረዥም ጊዜ ወዴት እደተሰወረ አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ። እርሱ ግን ምንም ነገር ላለማየትና ላለመስማት ወደ ገዳም ገብቶ ነበር፡፡ በታዋቂ ጋዜጣና መጽሄቶች ላይ በጋዜጠኝነት እየሰራም በመሃል መልሶ ይተወዋል። ባህታዊ ይሆንና ድንገት ከነበረበት የሕይወት ዘይቤ አፈንግጦ ይወጣል።
የአያ ሙሌ ገጠመኞችና የኑሮ ሰበዞች አያሌ ናቸው። ጊዜው አበበ ተካ በሙዚቃው የነገሰበት ወቅት ነበር። አያ ሙሌ ደግሞ ሥራ አስኪያጁ። አንድ ጊዜ ወደ ጎንደር ለስራ ሄደው ለብቻው ከአስፋልት ዳር እየተጓዘ ሳለ ብዙ የተቸገሩ ሰዎች ተሰብስበው ይመለከታል። እናም አያሙሌ ሁሉንም ጠርቶ በዙሪያው ሰበሰባቸውና ከኪሱ የነበረውን እረብጣ ብር እያወጣ ማደል ጀመረ።
ይህን የተመለከተው ፖሊስም በነገሩ ተጠራጥሮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞት ሄደ። ደግነቱና ለሰው አዛኝነቱ በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ ተቸግሮ በባዶ እግሩ የሚሄድ ሰው የተመለከተ እንደሆን የእግሩን ጫማ አውልቆ ይሰጥ ነበር፡፡ ለራሱ ቁሳዊ የሆኑ ጉዳዮች አያስጨንቁትም። አለባበሱም እንደነገሩ ነው። አንድ ጊዜ እንዲያውም ወደ አንድ ሆቴል ሊገባ ሲል የሆቴሉ ዘበኛ አመናጭቆ ይመልሰዋል፡፡ አያ ሙሌም ጠጋ ብሎ “ትናንትና በረባሶ አድርገህ ገብተህ ዛሬ በረባሶ ያደረገ ሰው ትንቃለህ” ሲል ተናገረው ይባላል።
ቀደም ሲል አያ ሙሌ ለኢህዴግ መንግሥት ትልቅ ባለውለታ ነበር። ወያኔ የደርግን መንግሥት ጥሎ ሲገባ እንዳገዛቸው ይነገራል። ከዚያ በኋላም ከባለሥልጣናቱ ጋር የቅርብ ወዳጅ ነበር። የእርሱን ግጥሞች መስማትም ያስደስታቸዋል። በተለያዩ ጊዜያትም ዝግጅቶች ሲኖሩ ከቤተመንግሥት ገብቶ ግጥሞቹን ያቀርብ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን አያ ሙሌ ወደ ቢሯቸው ሄዶ የሰጡትን ሽጉጥ አስረክቦ ደመወዙንም ሳይቀበል ጥሎ ወደ ጎዳና ሕይወት ወጣ። በወቅቱም ታምራት ላይኔ መልዕክተኛ ልኮ እንዲመለስ ቢጠይቀው አያ ሙሌ ግን እንዲህ ነበር ያለው “አመሰግናለሁ መንገዴንም ለይቻለሁ” በሌላ ጊዜ ደግሞ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበረው በረከት ስምኦን ካለበት ጎዳና ድረስ መጥቶ ቢያንስ የ11 ዓመት ህጻን ልጅህ አታሳዝንህም ብሎ እንደለመነው ይነገራል፡፡
ከዚህ በኋላ የአያ ሙሌ ሕይወት እንደማንኛውም የጎዳና ልጅ ሆነ። እየዞረ ለምኖ ያመጣውን ምግብ መልሶ ለሌሎች የጎዳና ልጆች ይሰጣል። ከልክ ያለፈ ደግነቱ እዚህም ተከትሎት መጣ። በጎዳና ላይ እያለ ለስጋው የምትሆን ትንሽዬ ምግብ ካገኘ በቂው ነበር። ፈጽሞ ግን በኪሱ የሚያስቀምጣት ገንዘብ አይፈልግም። ገንዘብ እንዲሰጡትም አይለምንም። አያ ሙሌ ልክ የወፊቱን አይነት ኑሮ መኖር ጀመረ። ወፊቱ ሲል የራሱ ሕይወት ታይቶት ነበር። አደራ ልጄን አደራ ብሎ ሲጽፍም ልጁን ጥሏት እንደሚሄድ ተገልጦለት ነበር።
እነዚህን ነገሮች ስንመለከት ባለቅኔው ነብይም ጭምር ነበር እንድንል ያደርገናል። አያ ሙሌ እንደዋዛ ጎዳና ላይ ወጥቶ ከባዘነ በኋላ ልጁን በአደራ ተቀብላ ስታሳድግ የነበረችው ስንዱ አበበ ነበረች። እርሱ ከጎዳና እንዲመለስ ጥረት ብታደርግም ሊሳካላት አልቻለም። አያ ሙሌ የሚጽፋቸው ግጥሞች የትም የማይገኙ ትልቅ ሀብት ቢሆኑም እርሱ ግን እየጻፈ ይተዋቸው ነበር። የእርሱን ግጥሞች ካሉበት ሁሉ እየሰበሰበች በመጽሃፍ መልክ ያሳተመችውም ስንዱ አበበ ናት።
የአያ ሙሌ የሕይወት ጀንበር እያዘቀዘቀች ስትመጣ ሌላ አስፈሪ ጭለማ ወደ እርሱ እየቀረበ እንደሆን ተረድቶ ነበር። በቀናት የሚቆጠር በጣም አጭር የምድር ቆይታ እንደቀረው ሲረዳ አሁንስ ማረፍ እፈልጋለሁ በማለት ልጁን ካገኛት በኋላ ከቤተክርስቲያን ደጅ ቆሞ ረዥም ጸሎት አደረገ። ከዚያም አዲስ አበባን ለቆ በመኪና ተሳፍሮ ወደ ዓለም ገና አመራ። እዚያም ከአንድ ሆቴል መኝታ ይዞ አደረ። ሲነጋ ግማሽ በድን ሆኖ ተገኘ። ነብሱ ግን አልወጣችም ነበር፡፡ ይዘውት በሚወጡበት ሰዓት ዘበኛው ይህንን አለ “ኧረ ይሄስ ነብይ ሳይሆን አይቀርም። ሌሊቱን ሙሉ ለጆሮ የሚከብዱ ነገሮችን ሲናገር ነው ያደረው” በማግስቱ ነሀሴ 28 ቀን 1996 ዓ/ም አረፈ፡፡ አያ ሙሌ ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ የእርሱ ሕይወት ቅኔ እንደሆነ ለእኛ ግን ዘመን የማይንዳቸው የቅኔ ሥራዎቹን ትቶልን ወደማይመለስበት ሄደ፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015