በኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የሚካሄዱ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዱ ይገኛሉ። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ኢንዱስትሪ አልባ እስከ ማድረግ አቅም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይነገራል። ይሁን እንጂ ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር የተያዘው ሕገወጥ ንግድ ዛሬም በኢትዮጵያ አሳሳቢነቱ እንደጎላ ነው።
በገቢ ምርቶች ረገድ አብዛኞቹ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህም ሳቢያ የሀገር ውስጥ አምራቾች እየተጎዱ እንደሚገኙ ሳይጠቀስ ታልፎ አያውቅም። ሕገወጥ ንግድ የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ በሚደረጉ ንግዶችና በገንዘብ ዝውውር ያጣችው የሀብት መጠን ከዓመት ዓመት እያደገ እንጂ እየቀነሰ እንዳልሆነ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 70 ቢሊዮን ዶላር በደረሰኝ ማጭበርበር እንደምታጣ የሚያመላክቱ ጥናቶች ለችግሩ ግዝፈት ማስረጃ ናቸው። ይህም ከገቢና ወጪ ንግድ ሒደት ጋር ተያይዞ ዋጋን አሳንሶና ከፍ አድርጎ በማቅረብ በሚፈጸም ማጭበርበርና ገንዘብን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር በማሸሽ (በካፒታል ፍላይት) የሚታጣ ነው። እዚህ ላይ የበይነመረብ ግብይትን በመጠቀም መንግሥት የማያውቃቸው ንግዶች እንደሚኖሩ መጠርጠሩም አይከፋም። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ተደማምረው በአሁኑ ወቅት የሕገወጥ ንግዱ በህጋዊ መንገድ የሚካሄደውን እየተፈታተነ መሆኑ ችግሩን አንገብጋቢ አድርጎታል።
በኮንትሮባንድ የሚገባውና የሚወጣው ብዛት ያለው ሲሆን በአንፃሩ ተያዘ የሚባለው ግን አነስተኛ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ አሰራር አለመኖር፣ የችግር ፈጣሪዎቹ ተለዋዋጭ ባህሪ ችግሩ እልባት እንዳያገኝና ሁሌም አሳሳቢ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። የኮንትሮባንድ ቁጥጥሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ካልተሳተፈበት ውጤታማ እንደማይሆን ሁሉም የሚገነዘበው ሃቅ ነው። ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ አልባ ሊያደርጋት የሚችለው ትልቁ ሥጋት ኮንትሮባንድ ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር መወዳደር አቅቷቸው እንዲዘጉ እስከማድረስ የሚዘልቅ ትልቅ አደጋ አለው።
ኮንትሮባንድ ከኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና ከመሳሰሉት አልፎ ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶች ሳይቀር በሕገወጥ መንገድ እየገቡ መሆኑ ችግሩን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ቀውስ የሚፈጥር ያደርገዋል።
ይህ አሳሳቢ ችግር በጊዜ መላ ካልተበጀለት በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የሚያመርተው የሀገር ውስጥ አምራች በኮንትሮባንድ በሚገባውና በተሻለ ጥራትና በዝቅተኛ ዋጋ መሃል ከተማ ላይ እየተሸጠ በሚገኘው ምርት እየተንኮታኮተ መሄዱ አይቀሬ ነው። የሀገር ውስጥ አምራች ጉዳት ውስጥ እየወደቀ ከሄደ ደግሞ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚያርፈው በትር ቀላል አይሆንም። በዚህ ሂደትም መንግሥት ከፍተኛ የሚባል የታክስ ገቢ እያጣ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
የሕገወጥ ንግዱ መነሻ ሞራል የጎደላቸው ነጋዴዎች በምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የሚፈጥሩት ሰው ሠራሽ የሆነ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው። እነዚህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ነጋዴዎችም ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ አካባቢ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን እንዲፈጠር አድርገው በሌላ በኩል አቅርቦቶችን ለማሟላት በኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ በመሳተፍ የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም መገንዘብ አዳጋች አይደለም።
በዚህ ውስጥም የሙሰኛ ተዋናዮች ተሳትፎ፣ ድጋፍና ሽፋን መስጠት ችግሩን እያባባሰው ነው። በፈቃድ አሰጣጥ ላይ፣ በድንበር ጥበቃ ላይ፣ በግብር አከፋፈልና የመሳሰሉት ላይ የሚታየውን ችግር የሚፈጥሩትም እነዚሁ አካላት ናቸው።
ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት በዋነኛነት የሚጠቀሰው በድንበሮች አካባቢ ያለው የሳሳ የቁጥጥር ስርአት ነው። በዋናነት ግን ችግሩን በቋሚነት ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት መፍጠርና ከዘመቻ ይልቅ መልክ ቋሚና ዘላቂ አሰራር መዘርጋት ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረጉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲታይ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ አንዱ የመፍትሔ ቁልፍ የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው፡፡ ሙስና ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ የተቆራኙ በመሆናቸው ይህን መዋጋት ቅድሚያ ሊሰጠው ግድ ነው።
ኢንሳና ቴሌኮሙዩኒኬሽንን የመሳሰሉ ተቋማትን በመጠቀም የቁጥጥር ሥራን በዘመናዊና በተቀናጀ መልኩ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕገወጥ የገንዘብና እያንዳንዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ አጋር ስላለው ይህንን ያመቻቸው ማነው ብሎ መመርመርና በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ተገቢውን ርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
አንድ የኮንትሮባንድ ዕቃ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ እንዲሁም አልፎ ሲመጣ ያሳለፈን ኬላ ተጠያቂ የሚያደርግ ጠበቅ ያለ ሥርዓት መዘርጋትም ችግሩን ሊያቃልል ይችላልና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን የሀጋ ጣለት የሆነ ተግባር ለማስቆም ሊረባረብ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015