አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት አቅሙ ብቻ ሳይሆን፤ ለዚህ የሚሆን ሰፊ ማህበራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች ያሏቸው ሕዝቦች ናቸው። ይሁን እንጂ ይህንን አቅማቸውን ተጠቅመው ከግጭት ነፃ የሆነች አህጉር መመስረት ያልቻሉት በአብዛኛው የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ፈተና ስለሆኑባቸው እንደሆነም ይታመናል።
ለዚህ ደግሞ በነጻነት ዋዜማቸው አፍሪካውያን ስለነገዎቻቸው ተስፋ አድርገው ያለሟቸውንና ከነጻነት ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ለመኖር የተገደዱባቸውን አመታት መመልከት ተገቢ ነው። እነዚህ አመታት ለአህጉሪቱ ሕዝቦች የቱን ያህል የምጥ አመታት እንደሆኑ ነጋሪ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም።
ከስድስት አስርት ዓመታት በሚበልጡ በነዚህ ጊዜያት የአህጉሪቱ ሕዝቦች በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል። በዚህም ሰላምና መረጋጋት አጥተው፤ ለአስከፊ እልቂቶች፣ ስደትና ስነልቦናዊ ቀውሶች ተዳርገዋል።
የቀደሙት አህጉሪቱ የነጻነት አባቶች ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ተስፋ ያደረጓቸው ነገዎች፤ እንዲሁም ነገዎቹ የተሸከሟቸው ህልሞቻቸው፣ የቅዥት ያህል ተለውጠው ህልመኞቹን ሳይቀር በልተው አህጉሪቱ የግጭትና የሁከት፤ የተስፋ መቁረጥና የቁዘማ ም ድር እንድትሆን ተደርጋለች።
እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ከነሱም በኋላ የተነሱ ስለ አህጉሪቱ ሕዝቦች ነገዎች ብሩህ ህልም የነበራቸው አፍሪካውያን ተስፈኞች በአንድም ይሁን በሌላ ከተስፋቸው ተፋተው ባልተገባ መልኩ ለሞት እና ለስደት ተዳርገዋል። ፍጻሜያቸውም ለሌሎች እንደ ማስፈራሪያ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ ተገምዶም ታይቷል።
በዚህ የአፍሪካውያን የስድስት አስርት አመታት የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ፤ ከዚህ በመነጩ የግጭት፣ የእልቂት፣ የስደት፣ የረሀብና የእርዛት ትርክቶች በስተጀርባ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ሰፊ ወስን ስፍራ እንደሚይዙ፤ የአፍሪካ ችግሮችም አልፋና ኦሜጋ እንደሆኑ ተጨባጭ እውነታዎች የሚያረጋግጡት ጉዳይ ነው።
ይሄም የነፃነት ትግሉና ትግሉ የወለደው አህጉራዊ መነቃቃት በቅኝ ገዥዎች መንደር የፈጠረው መደናገጥ፤ አፍሪካውያን የነጻነት አባቶች የትናንት ህልሞች እውን እንዳይሆኑ ፈተና የመሆኑን ያህል፤ ያው ስጋት እስከዛሬ ድረስ አፍሪካውያን ብሩህ ነገዎቻቸውን ሰርተው እንዳይኖሯቸው ተግዳሮት እንደሆነ ነው።
ኢትዮጵያም እንደ አገር የቅኝ ግዛት ሰለባ ባትሆንም፤ እንደ የትኛውም አፍሪካዊ አገር የዚሁ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሰለባ ስለመሆኗ ባለፉት ስድስት አስር ዓመታት የመጣችባቸው ውጣ ውረዶች፤ ሞት እና ስደት፤ ረሀብና እርዛት የበዙባቸው ጉዞዎቿ ተጨባጭ መገለጫዎች ናቸው።
በቅርቡ እንኳን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት እና ጦርነቱ በሁለንተናዊ መልኩ በአገሪቱ ላይ እያስከተለ ያለው ተጽእኖ ስንመለከት፤ አፍሪካውያን ብሩህ ነገዎቻቸውን ለመስራት ቁርጠኛ ሆነው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ የቱን ያህል የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ዋነኛ ፈተና እንደሚሆኑባቸው ያመላከተ ነው።
ከዚህ ዘመናት ካስቆጠረ ተጨባጭ ችግር በመነሳት ኢትዮጵያ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሄደችበት መንገድ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ ችግሩን በውይይትና በሰላም ስምምነት ለመፍታት አስችሏታል፡፡
ይህ ተጨባጭ ተሞክሮም አፍሪካውያን ፖለቲከኞች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶችን መከላከል ከቻሉ ችግሮቻቸውን መፍታት የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላቸው ያሳየ፤ ከዚህም በላይ የትኛውንም አይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት የሕዝቦቻቸውን ብሩህ ነገዎች ከማጨለም ባለፈ ምን አይነት ፋይዳ እንደሌላቸው ያመላከተ ነው።
በግጭት ውስጥ ያሉ የሱዳን ኃይሎችም ይህንን ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ አፍሪካውያንን ዋጋ እያስከፈለ ያለ ችግር በአግባቡ በመረዳት፤ በውጭ ጣልቃ ገብነቶች የሱዳንን ሕዝብ ከቀደመው ዘመን የከፋ ዋጋ እንዳይከፍል በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
በተለይም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ ኢጋድ የአካባቢው አገራትን በማስተባበር በሱዳን ላለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ በአዲስ አበባ ሊያካሄድ ቀነ ቀጠሮ ለያዘለት የሰላም ውይይት፤ ተደራዳሪ ኃይሎች እራሳቸውን በተገቢው መንገድ በማዘጋጀት በእርግጥም ሱዳናውያን እንደ አንድ የአህጉሪቱ ሕዝቦች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015