የግብርና ምርቶችን በጥሬያቸው ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ የተሻለ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚያስችል ይታመናል፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚገነባውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ እሴት ሳይጨመርባቸው ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩ እንደ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማርና ሌሎችም የግብርና ምርቶች አሁን ላይ እሴት ተጨምሮባቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ መቅረብ ጀምረዋል፡፡ በዚህም ሀገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች፤ ተጨማሪ የስራ እድልም ይፈጠራል፡፡
ኢትዮጵያ የተገነቡ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማድረግ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ሲሆን፤ በተለይም ከተለያዩ የዓለም አገራት የተወጣጡ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መሥራት የሚችሉበትን ሰፊ ዕድልም እየፈጠሩ ይገኛሉ፤ ከውጭ ኢንቨስተሮች በተጨማሪም የአገር ውስጥ አምራቾች በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ በር ከፍቷል፡፡
በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ምርቶች በማምረት ሥራ ላይ ከተሰማሩ የአገር ውስጥ አምራቾች መካከልም በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው “ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር” አንዱ ነው፡፡
‹‹ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር ምርቱን ለባለንብረቱ የሰጠና ማር ያናቢው ነው›› በማለት ስለ መጠሪያ ስሙ ያብራራልን የኩባንያው መስራችና ባለቤት አቶ ቢንያም ቡልቻ ነው፡፡ አቶ ቢንያም፤ በሺዎች ከሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ምርቱን ሰብስቦ የተጣራና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ ያናቢ ባህላዊ የንብ ማነብ አሰራርን አዋጭ ወደሆነው ዘመናዊ የንብ እርባታ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ ያለ የንግድ ድርጅት መሆኑን ጠቅሶም፤ ድርጅቱ በአገር ውስጥ በዘመናዊ የማር ማዘጋጀት አሰራር የሚመረተውን ተጨማሪ የማርና የሰም አቅርቦት ዓለም አቀፍ የገበያ ፍላጎትን በሚያሟላ መልኩ እንደሚያቀርብ ይገልፃል፡፡
ኩባንያው የማርና የሰም ምርቶችን በማቀነባበር፣ በማሸግና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ቀዳሚ እንደሆነ ያነሳው አቶ ቢንያም፤ ወደ ዘርፉ ከመግባቱ አስቀድሞ በስደት መቆየቱንና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ተሰማርቶ እንደነበር አጫውቶናል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ተወልዶ ያደገው አቶ ቢንያም፤ በስደት ከሀገር የወጣው ገና በጠዋቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባጠናቀቀ ማግስት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ የስደት ቤቱም ኖርዌይ ነበረች፡፡ በዚያም ከመማር በተጨማሪ ዝቅተኛ ከተባለ ሥራ ጀምሮ የግል ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡
ለአስራ አምስት ዓመታት በስደት ከቆየባት አገረ ኖርዌ በመመለስ ብትን ጨርቆች፣ መኪኖችና ሌሎች ቁሳቁስን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። በተሰማራበት የንግድ ስራ ዘርፍ የሚፈጠር የሥራ ዕድል እና በአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አነስተኛ መሆኑን በማመን ወደ ማር ሥራ መግባቱን አቶ ቢኒያም ይገልፃል። ይሁን እንጂ ወደ አገር ውስጥ ያስመጣቸው ከነበሩ ምርቶች መካከል ጨርቃ ጨርቆችን አሁንም ድረስ እያስገባ ይገኛል፡፡
የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት ባለፈ የኢትዮጵያ የሆኑ ምርቶችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ ያሰበው አቶ ቢንያም፤ ንግዱን ሰፋ አድርጎ ለመሥራት በኢትዮጵያ የተገነቡ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ምርጫው አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ማር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀርብ ለማስቻልም በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የማርና የሰም ምርትን በማቀነባበር ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡
“ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር” ወደ ሥራ በገባበት ወቅት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወሰው አቶ ቢንያም፤ ኩባንያው ብዙ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም ይገልጻል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግና አገርን በማስተዋወቅ ረገድ አበርክቶው የጎላ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዘርፉ በርካታ አርሶ አደሮችን ማሳተፍ የሚችል መሆኑን ገልጾ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራም በርካታ ዜጎችን ማሳተፍ እንደሚያስችል አመላክቷል፡፡
የተጣራ የኢትዮጵያ ማር ለምን በውጭ አገራት መደርደሪያ ላይ አይታይም በሚል መነሻ ወደ ሥራው የገባ መሆኑን ያነሳው አቶ ቢንያም፤ የኢትዮጵያ ማር ሳይጣራና ሳይዘጋጅ ከነሰፈፉ ለውጭ ገበያ ይቀርብ እንደነበርም ነው የሚገልጸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ማሩ ለብቻ ተጣርቶ እንዲሁም ሰፈፉ ለብቻው ተዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዚህም አገር የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በእጥፍ እየጨመረ እንደሚመጣ ነው ያመለከተው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ማር ተጣርቶ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በጥሩ ዋጋ መሸጥ እንዲችልና በውጭ አገራት መደርደሪያ ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የቻልንበት የመጀመሪያው ምክንያት ከልብ የመነጨ ፍላጎት ነው›› የሚለው አቶ ቢንያም፤ ያለው አቅም ምን ያህል እንደሆነ፣ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ያለው ፍላጎት ምን እንደሚመስል የምርቱ ባለቤት ከሆነው አርሶ አደር ጋር በማጥናት በመለየት ወደ ስራ መግባቱን ይናገራል። ከዚህ መነሻ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ በቁርጠኝነት ወደ ስራው መግባቱን ይገልፃል። ምንም ነገር ቢሆን ከልብ በመነጨ ፍላጎት ለመሥራት ከታቀደ መሥራት እንደሚቻልም ነው ያስገነዘበው።
በሥራ አጋጣሚ ወደ ውጭ አገር በሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ማር በትንሽ ገንዘብ በበርሜል ተደርጎ ሳይጣራ ለውጭ ገበያ ሲሸጥ የሚያውቀው አቶ ቢንያም፤ በተመሳሳይ ደግሞ ይህንኑ ማር ነጮቹ አጣርተው በውድ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ ሲሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህም ዛሬ ላይ ማርን በማቀነባበር ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ያነሳሳው ሌላ ምክንያት መሆኑን አጫውቶናል፡፡ ወደ ሥራው ከመግባቱ አስቀድሞ ምዕራባውያኑ ማርን እንዴት እንደሚያጣሩትና ምን የተለየ ነገር እንደሚጨምሩበት አጥንቷል፡፡ በጥናቱም ማሩን በሚገባ የሚያጣራ ማሽን የግድ መሆኑን በመረዳት ዘመናዊ ማሽን በመትከል እንደ ሌሎቹ ሁሉ የተጣራ ማር አዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአነስተኛ ዋጋ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የማር ምርት በማስቀረት የተጣራ ማር በተሻለ ዋጋ ለተለያዩ የዓለም አገራት እያቀረበ ያለው አቶ ቢንያም፣ የገበያ መዳረሻዎቹም ጃፓንን ጨምሮ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ እንደሚዘልቅ ይጠቁማል፡፡ ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር በአጭር ጊዜ ውስጥ ገበያ ውስጥ ገብቶ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ማሩን ሰብስቦ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ማርና ሰም በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚያዘጋጅ የጠቀሰው አቶ ቢንያም፤ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል የማር ምርቱን ያገኛል፡፡ ለአብነትም ጉጂ፣ ኖኖ፣ ኢሊባቦር፣ ማሻ፣ ሸካ፣ ቦንጋ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልም እንዲሁም ሰቆጣ፣ አዊና በሌሎች ማር ካለባቸው አካባቢዎች ሁሉ በማሰባሰብ ተፈጥሯዊነቱን ጠብቆ ማጥራት እንዲሁም ውስጡ ያለውን ሰምና ባክቴሪያዎች ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም በመለየት ንጹህና በውጭው ዓለም የሚፈለገውን ማር እያመረተ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
ምዕራባውያኑ የሚከተሉትን ደረጃ በማሟላት አስፈላጊ ማሽኖችን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማር ምርት ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን የገለጸው አቶ ቢንያም፤ ከማሩ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለምዶ ሰፈፍ ተብሎ የሚወጣውን ተረፈ ምርት አዘጋጅተውና አቀነባብረው ለውጭ ገበያ እየላኩ እንደሆነ ይገልጸል፡፡
ሰሙም በስፋት እንደሚፈለግ ይናገራል፡፡ “ሰም በራሱ አንድ ዘርፍ ነው” የሚለው አቶ ቢንያም፤ ሰሙ ተጣርቶ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርበ የተለያዩ የዓለም አገራትም ለበርካታ ግልጋሎት እያዋሉት እንደሆነ አጫውቶናል። ለአብነትም ለመድሃኒትነት፣ ለፊት ማስክ፣ ለቅባትና ለሌሎች ጉዳዮች ጭምር ነጮቹ እንደሚገለገሉበት አስታውቋል፡፡
ለአውሮፓ ሀገሮች፣ አሜሪካና ጃፓን ማርና ሰሙን በስፋት ተደራሽ እያደረገ እንደሆነ የጠቀሰው አቶ ቢንያም፤ ሌሎች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እያገኘ መሆኑንም ነው ያመላከተው፡፡ ከእነዚህም መካከል በአውሮፓ አዳዲስ አገራትና በመካከለኛው ምስራቅም ተፈላጊ እየሆነ ስለመምጣቱም ተናግሯል። ለዚህም የገበያ ማፈላለግ ሥራ በስፋት ሠርተዋል፡፡ እየሰፋ ለመጣው ገበያ በቂ ምርት ማቅረብ እንዲቻልም ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የገለጸው አቶ ቢንያም፤ በተለይም አርሶ አደሩ ዘመናዊ ቀፎ እንዲያገኝና በብዛት እንዲያመርት ከውጭ ድርጅቶች ጋር እየሠራ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በሺዎች ከሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ጋር እንደሚሰራ የገለጸው አቶ ቢንያም፤ ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር የሚያገኘው በህብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ በየአካባቢው በሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየኖች አማካኝነት እያንዳንዱን አርሶ አደር በመደገፍና በመከታተል እንዲሁም ስልጠና በመስጠት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻል።
አቶ ቢኒያም እንዳብራራው፤ ከእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሩን መልቀም የማይቻል በመሆኑ በዩኒየኖች አማካኝነት ማሩ ይሰበሰባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር ዘጠኝ ከሚደርሱ ዩኒየኖች ጋር ስምምነት ፈጽሞ ማር እየገዛ ይገኛል፡፡ ከስምምነት ውጭም ከተለያዩ ዩኒየኖች ማር ይረከባል፡፡ በእያንዳንዱ ዩኒየን ውስጥም ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ አባላት በመኖራቸው በአጠቃላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሺዎች ከሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ጋር እየሰራ ነው፡፡
ማር አምርተው የሚያቀርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ጨምሮ በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 60 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው አቶ ቢንያም፤ በድምሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም ነው ያጫወተን፡፡
ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ማር የሚያመርተው አርሶ አደር ውጤታማ መሆን እንዲችል ዘመናዊ ቀፎና ስልጠና በመስጠት ከሚያደርገው ድጋፍና ክትትል በተጨማሪ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶች ዘመናዊ ቀፎዎችን ለመስጠት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ሁለት ባህላዊ የንብ ቀፎ ላለው አንድ ወጣት ሁለት ዘመናዊ የንብ ቀፎ ጨምሮ በመስጠት የበለጠ ማምረት እንዲችል ያደረጋል፤ በዚህም ከ500 እስከ 1000 የሚደርሱ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አጫውቶናል፡፡
በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር አበቦችና ንቦቹን ጨምሮ ምቹ የሆነ አየር በመኖሩ ማር ላይ ብዙ ብንሠራ ውጤታማ መሆን እንችላለን የሚለው አቶ ቢንያም፤ በተፈጥሮ ከታደልነው ጸጋ በተጨማሪ ማርን ከመብላት ባለፈ እንዴት ማልማት እንደሚገባ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ስለመኖሩም ተናግሯል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማር መብላቱንም ማምረቱንም ለሚያውቀው ማህበረሰብ ዘመናዊ ቀፎዎችን በማቅረብ በብዛት ማምረት የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አገሪቷ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ መቶ ሺ ቶን ማር የማምረት አቅም እንዳላት የጠቀሰው አቶ ቢንያም፤ ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር በሰዓት 1ሺ250 ኪሎ ግራም የማምረት አቅም እንዳለው ነው የጠቀሰው፡፡ በቀጣይም ሥራውን በማስፋት በምስራቅ አፍሪካ የማርና ፍራፍሬ ምርቶችን በማቀነባበር፣ በማሸግና ከአገር ውስጥ ባለፈ ኤክስፖርት በማድረግ የቀዳሚነት ስፍራን ለመያዝ ማቀዱን ጠቁሟል፡፡
በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለበት አካባቢ ተጨማሪ ምርት ለማምረት የሚያስችል ምቹ ስፍራ መሆኑንም አቶ ቢንያም ይናገራል፡፡ ሌሎች ምርቶችን ይዞ ወደ ገበያው እየመጣ እንደሆነም ነው አቶ ቢንያም የገለጸው፡፡ በዋናነት ማርና ሰም እያመረተ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ያናቢ ሸካ ኖርዲክ ማር፤ በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ፍራፍሬ በማቀነባበር ተጨማሪ ዘርፍ ላይም መግባቱን አቶ ቢንያም ይጠቁማል፡፡
እሱ እንዳለው፤ በአካባቢው በስፋት የሚገኙትን ፓፓያ፣ ስትሮበሪና ሌሎች ፍራፍሬዎች ከአርሶ አደሩ በመሰብሰብ እሴት በመጨመር አዘጋጅቶና አሽጎ ለገበያ የማቅረብ ሥራው ተጀምሯል፡፡ አሁን ላይ ያለው ዕቅድም ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ሲሆን፣ በቀጣይ ሁለትና ሶስት ዓመታት ከአገር ውስጥ ባለፈ ለጎረቤት አገራት የማቅረብ አላማን አንግቦ እየሰራ መሆኑን አቶ ቢኒያም ይናገራል። ምርቱ በስፋት ልጆች የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ በቀላሉ ዳቦ ላይ ተቀብቶ የሚበላ የተዘጋጀ ፍራፍሬ እንደሆነ በማስረዳት፤ በአገር ውስጥ ገበያ የሚገኙት ተመሳሳይ ምርቶች 90 በመቶ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውን አቶ ቢንያም አመላክቷል፡፡
ከፍራፍሬው በተጨማሪም ዳቦ ላይ የሚቀባ ቸኮሌት እያዘጋጀ ለገበያ እያቀረበ እንደሆነም ይገልጻል፡፡ እነዚህን ምርቶች ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን መተካት እንደሚችሉ ጠቅሶ፣ የሚሰጡት ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ በተለይም የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015