አገራት በጋራ ሰርቶ ለመጠቀምና በጋራ ለማደግ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ትብብር ከሚፈጥሩባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ሲሆን ይህ ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ደግሞ የንግድና ኢንቨስ ትመንት ትብብሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ለጋራ ጥቅም ሲሉ የሚጀምሩት ትብብር በተለይ በንግድ ሚዛን አለመመጣጠን ካስከተለ በመካከላቸው መጠራጠርን ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአሜሪካና የቻይና ጉዳይ አብይ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የንግድ ሚዛን መዛባት ምንም እንኳን ቻይናን ከአሜሪካ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ቢያስገባትም፤ ለአፍሪካ አገራትም ስትራቴጂያዊ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነቷ ግን የማይካድ ሀቅ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም ካላት አንጻራዊ ሰላም፣ የኢኮኖሚ እድገትና ምቹ ሁኔታዎች አኳያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አገር እንደመሆኗም የቻይናን ቀዳሚ ትኩረት መያዝ ችላለች።
ለአብነትም 400 ያክል የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ተሰማርተው በ100 ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችና መሰረተ ልማቶች ቻይና በድጋፍም ሆነ በብድር ቀዳሚ የፋይናንስ አጋር ናት፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ሚዛን እጅጉን የሰፋና ለቻይና ያደላ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይሄን ሚዛን ማስተካከል ደግሞ በአገራቱ መካከል ለሚኖረው ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አጋርነት ጉዞ ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበትም ክፍተቱን ለመሙላት ያግዛሉ የተባሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል፡፡ ለዚህም በተለያዩ አገራት (በተለይም በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ያሉ) የተሰማሩ የቻይና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ካሉት ጋር ልምድ የሚለዋወጡበት የቻይና ንግድ ሳምንት አውደ ርዕይ አንዱ ነው፡፡
አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ ኩባንያዎቹን በኢትዮጵያ ማሳተፍ የሚቻልበትን እድል ለመፍጠርና በኢትዮጵያ ያሉትም ከሌሎቹ ልምድ በመቅሰም የገቢ ምርቶችን የሚተካ ምርት የሚያመርቱበትን እድል ለመፍጠር የሚያግዝ ስለመሆኑ ይነገ ራል፡፡ ሰሞኑንም ሶስተኛው የቻይና የንግድ ሳምንት በሚሊኒዬም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ ተሳታፊ ድርጅቶች መካከል አይዞን ማኑፋክቸሪንግ አንዱ ሲሆን፤ ከውጭ ሲገቡ የነበሩ ነገር ግን አገር ውስጥ ባለ ቴክኖሎጂና ጥሬ እቃ በመተካት ያመረታቸውን ፈርኒቸሮችን ለዕይታ ይዞ ቀርቧል፡፡ የአይዞን ማኑፋክ ቸሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ቴክኖ ሎጂስት አቶ ፋሲል ክፍለየሱስ እንደሚናገሩት ደግሞ፤ ምርቶቹ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ናቸው። አሁን እዚህ በመመረታቸው ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል፡፡
አውደ ርዕዩ የሰሯቸውን ስራዎች የሚያስተ ዋውቁበት መስኮት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፋሲል፤ ምርቱን የሚፈልጉ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አካላትን በጋራ ያገናኘ ከመሆኑም በላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም የጎበኟቸው እንደመሆኑ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የምርቶችን ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል የሰጣቸው መሆኑን በመጠቆም፤ ዓለማቀፍ ጎብኚዎችም ኢትዮጵያ የተሻለ ምርት ማምረት እንደምትችል የሚረዱበትና ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችላትን አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል፡፡ ሌላው የኤግዚቢሽኑ ተካፋይ ከዱከም ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን፣ ዡሃንዢን ዋንግ ፕላስቲክ ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን፤ የተለያየ የስፋት መጠን ያላቸውን ኤች.ዲ.ፒ.ኢ የውሃ ፓይፖችን እና ኤች.ዲ.ፒ.ኢ ደብል ዎል ኮሮትድ የድሬኔጅ ፓይፖችን ለዕይታ ይዘው ተገኝተዋል፡፡
ዡሃንዢን ዊነግ ፕላስቲክ ማኑፋክቸሪንግ የገበያና ሽያጭ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሱራፌል ካሳሁን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በተለይ ደብል ዎል ኮሮትድ ፓይፖች ከውጭ ሲገቡ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ተወስዶ በአገር ውስጥ መመረት ጀምሯል፡፡ በዚህ መልኩ አገር ውስጥ መመረቱ ደግሞ አሁን ላይ ለዴሬይኔጅ ስራ የሚውሉ የኮንክሪት ፓይፖችን በቀላል ቴክኖሎጂ ለመተካት የሚያስችል ነው፡፡ አቶ ሱራፌል እንደሚሉት፤ በአገር ውስጥ መመረት የጀመረው የደብል ዎል ኮሮትድ ፓይፕ የገቢ ምርትን በአገር ውስጥ የመተካት አንድ እርምጃ ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት አውደ ርዕይ ላይ ይዞ መቅረብ ደግሞ ምርቱን ከፈላጊዎቹ ጋር ለማገናኘት ትልቅ እድል የሚፈጥር ሲሆን፤ በርካቶችም ምርቱን እንደሚፈልጉት ገልጸውላቸው አድራሻ ተለዋውጠዋል፡፡
ከዚህ በዘለለ በሌሎች የቻይና ኩባንያዎች በሌሎች አገራት የሚመረቱ ቴክኖሎጂዎችን ለመመልከትና ምርቶቹን አገር ውስጥ ለማምረት የሚቻልበትን እድል የሚፈጥርም መድረክ ነው፡፡ በሌሎች አገራት የሚሰሩ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት ማሳደራቸውን ተመልክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከቻይና ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችል ልምድ የሚገኝበት እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ገቢ ምርቶቿን በአገር ውስጥ የመተካቱ ሂደት እንዲፋጠንም መንግስትም ሆነ ባለሃብቱ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ የተሳተፉና ለጋዜጣው አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ አምራች ኩባንያ ተወካዮች እንዳሉት፤ ቻይና በአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባትና ለንግድና ኢንቨስትመንት ያላት መልካም እድል ከቻይና ጋር ላላትና ለሚኖራት ትብብር እጅጉን አጋዥ ነው፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትም ከእለት እለት እየጨመረ እንደመሆኑም፤ አውደ ርዕዩ ለሁለቱ አገራት ቀጣይ የተሻለና የተመጣጠነ የንግድ ትብብር የሚፈጠርበትን እድል ለማመቻቸት በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድም የጋራ ስራ እንዲያከናወኑ እድል የሚፈጥር ነው፡፡ አውደ ርዕዩን ከጎበኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መካከል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር ደዋኖ ከድር እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ቡናና ሌሎች ምርቶችን ወደ ቻይና የምትልክ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው ምርት በመጠኑ የበዛ እንደመሆኑ የንግድ ሚዛኑ ለቻይና ያደላ ነው፡፡ ይሄን ለማስተካከል ደግሞ ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ባለው ሁኔታ ደግሞ ከስጋ ምርት ጀምሮ ለበርካታ የኢትዮጵያ ምርቶች ሰፊ የገበያ ዕድል በቻይና አለ፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ የሚሆን በቂና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በኢትዮጵያ የለም፡፡ የምርት ስነምግባርን ተከትሎ ያለመስራትም ተደማሪ ችግር ነው፡፡
እነዚህን ችግሮች ማስተካከል ከተቻለ ግን ቻይና ለኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ አላት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በርካታ የግብርና ውጤቶችን ማምረት ትችላለች፤ ቻይና ደግሞ እነዚህን ምርቶች ትፈልጋለች፡፡ ዘመኑ የውድድር እንደመሆኑም ጥሩ ምርት ያመረተ ጥሩ ገበያ ያገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ ከአርሶአደሮች ጀምሮ የሚያመርቱትን ምርት ጥራቱን በጠበቀና ገበያውን ባማከለ መልኩ መስራት ይገባል፡፡ አሁን ያሉ ችግሮችም የአቅም፣ የታማኝነት፣ የጥራትና ተያያዥ ጉዳዮች እንጂ የገበያ ባለመሆኑ ከእነዚህ ችግሮች ተላቅቆ ለውድድር የሚሆን ምርት በብዛትና በጥራት አምርቶ መገኘት የግድ ይሆናል፡ ፡ ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤንባሲዎች በአገር ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች ተገቢውን ገበያ የማፈላለግ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በሚቀጥለው ሰኔ የሚጀምረውን የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካውያን ትልቅ እድል እንደመሆኑ፤ የኢትዮጵያ አምራቾች አውሮፓና አሜሪካን ወይም ሌላ አህጉርን ሳይሆን አፍሪካን ትልቁ መዳረሻቸው አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያም የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች እንደመምጣቷ አሁን ላይ ወደ አፍሪካ አገሮች ምርቶችን መላክ ጥሩና አዋጪ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ማንኛውም የአገር ውስጥ አምራች በቂ ምርት አለኝ ካለም ውጭ ጉዳይ ገበያን ያመቻቻል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ባለው ሰፊ የንግድ ግንኙነትና ልውውጥ ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ቅባት እህሎችና በከፊል ያለቀላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ቻይና ትልካለች፤ ከቻይናም ብዙ ምርት ታስገባለች፡፡ ይሁን እንጂ የንግድ ልውውጡ ለቻይና ያደላ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እአአ ከ2012 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በየአመቱ በአማካይ 388 ሚሊዮን ዶላር ምርት ወደ ቻይና ትልካለች፡፡
በአንጻሩ ከ4ነጥብ4 ቢሊዬን ዶላር በላይ ከቻይና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ታስገ ባለች፡፡ በመሆኑም ይሄንን የንግድ ልውውጥ ሚዛን ለማስጠበቅና የቻይና ገበያን ለመጠቀም እንዲቻል በኢትዮጵያ በኩል ብዙ መስራት፤ ምርቶችንም በብዛትና በጥራት ብቻ ሳይሆን እሴት ጨምሮም ወደ ቻይና መላክን የግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከቻይና የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ የሚሰራ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የቻይና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ዞኖች ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግስት ሰፊ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በርካታ የቻይና አምራች ኩባንያዎችም ምርቶቻቸውን ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብና ሲተርፋቸውም ወደተለያዩ የአፍሪካ ገበያዎች እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ምክንያቱም ቻይና በገበያም ሆነ በኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ቀዳሚውን ቁጥር ትይዛለች፡፡ ሆኖም ይህ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲጓዝ የሚሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም የትብብር ሚዛኑን በማስጠበቅ ቻይና ስትራቴጂክ የኢንቨስትመንትና ንግድ አጋርነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል፡፡ አውደ ርዕዩም ይሄን ማድረግ የሚችሉና የገቢ ምርት ጫናን ለመቀነስ የሚያግዙ ባለሃብትና ኩባንያዎችን መመልመል የሚያስችል መድረክ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
ወንድወሰን ሽመልስ