ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታትና የሰላም አየር የሞላበት ማህበረሰብ ለመፍጠር አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ዋንኛ መፍትሄ እንደሆነ ይታመናል። የትናንት ጠባሳዎችን በይቅርታ በማከም ነገዎች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ መኖር እንዲችሉ እድል መስጠት የዚሁ እውነት አንድ አካል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
በተለይም እንደኛ ባሉ ያደሩ ችግሮች ሁሌም ዛሬዎችን በሚናጠቋቸው ማህበረሰቦች ውስጥ፤ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት ለውይይትና ለድርድር የተገዛ አእምሮ፤ ለይቅርታ የተከፈተ ልብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት ሊያመጣ አይችልም።
ያለፉት ትውልዶች በየዘመኑ ባጋጠሟቸው ችግሮች ዙሪያ ተወያይቶ ሁሌም ሀገርና ህዝብን አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ባህል ማዳበር ባለመቻላቸው እስከ ዛሬዋ ድረስ፤ ችግሮችን በኃይል እና በሴራ የመፍታት አስተሳሰብ ሀገራዊውን የፖለቲካ መድረክ ተሸክሞታል። በዚህም ሀገር እና ህዝብ ሁሌም ተጎጂ የሚሆኑበት አዙሪት ውስጥ ለመኖር ተገደናል።
ከግለኝነትና ከዚህ ከሚቀዳው የገዘፈ የማንነት ግንባታ የሚመነጨው ይህ የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ ለኃይል እና ለኃይል ብቻ ቅድሚያ መስጠቱ ፣ ዜጎች ጎራ እየለዩ በየዘመኑ ጠመንጃ አንግበው የራሳቸውን ብሩህ ነገዎች እንዲያጨልሙ አድርጓቸዋል ። የቀን ጨለማ በሚፈጥረው ግራ መጋባት እና ቁዘማ ውስጥ ፤ ተ ስፋ መቁረጥና ምሬት ውስጥ እንዲኖሩ አ ድርጓቸዋል።
በየዘመኑ ድህነትን እና ኋላቀርነትን አሸንፎ ወደቀደመው የስልጣኔ ማማ የመመለስ መሻታቸውን ትርጉም አልባ ህልም ከማድረግ አልፎ ፤ የሀገርን ብሄራዊ ክብር የሚያጎድፉ ፣ የግጭት እና የተመፅዋችነት አለም አቀፍ ትርክት ማጣፈጫ ዜማ ለመሆን ተገደዋል። ይህም በህዝባችን ዛሬዎች ላይ እየፈጠረ ያለው የስነ ልቦና ስብራት ቀላል አይደለም።
ራስ ወዳድነት ከፍያለ ደረጃ ላይ በደረሰበት ፤ እያንዳንዷ ሀገራዊ ሆነ አለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገበት ባለንበት ዘመን ፤ ይዘነው የመጣነው ለኃይል እና ለሴራ የተገዛው የፖለቲካ አስተሳሰብ በየትኛውም መልኩ እንደ ግለሰብ /ፖቲከኞቻችንን/ ፤ እንደ ሀገር / ህዝባችንን/ ተጠቃሚ ሊያደርግ አይችልም ።ለዚህ ደግሞ የቅርብ ሀገራዊ ተሞክሮዎችን መመልከት ተገቢ ነው።
እንደሚታወቀው ባለፉት ስድስት አስርት አመታት ውስጥ የነበሩ ትውልዶች ለሀገሪቱና ለህዝቦቿ ብዙ በጎነቶችን ተመኝተዋል፡፡ ብሩህ የሆኑ ነገዎችን አልመዋል ። ለምኞትና ለህልሞቻቸውም ህይወታቸውን እስከ መስጠት የደረሰ መታመን ታይቶባቸዋል። ከፍ ያለ መስዋእትነት በመክፈልም ከቋንቋ ያለፈውን ቁርጠኝነታቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል።
ብዙ በጎነቶችን መመኘታቸው ፤ ብሩህ የሆኑ ነገዎችን ማለማቸው ፤ ለዚህም የህይወት መስዋእትነት መክፈላቸው ብቻውን እራሳቸውንም ሆነ ሀገርና ህዝብን አላተረፈም፡፡ ለተጨማሪ የግጭትና የእልቂት ጥቁር ታሪክ ገጽ ግብአት ፣ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰለባ ከመሆንም አልታደጋቸውም። ከተስፋ መቁረጥ እና ከዚሁ ከሚመነጭ የህይወት መሰላቸት አላተረፋቸውም።
የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ማዕከል ደግሞ ልዩነቶችን በውይይት እና ለተሻለ ሃሳብ ተገዢ ሆኖ ችግሮችን የመፍታት የፖለቲካ ባህል ካለማዳበራችን የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም በየዘመኑ ትውልዶች እየከፈሉት ያለውን ያልተገባ ዋጋ ዛሬ ላይ ተነጋግሮ ማስቆም ያስፈልጋል። የዚህ ትውልድ ጀግንነት፤ በታሪክ ውስጥ ደምቆ የሚነበብበት ትልቁ ገድልም ይሄው ተነጋግሮ መግባባት፤ ተግባብቶም መስማማት፤ ተስማምቶም ሀገርን ከየትኛውም አይነት ተግዳሮት መታደግ መቻል ነው።
እንደ ሀገር ከግለኝነት እና ከዚህ ከሚመነጨው የገዘፈ የማንነት ግንባታ ወጥተን ሁሌም በውይይት /በመነጋገር / ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚና አሸናፊ ወደሚያደርግ ለሃሳብ የበላይነት የተገዛ የፖለቲካ ባህል ልንሻገር ይገባል፡፡ ዜጎችንም ጎራ እየለዩ ጠመንጃ አንግበው የራሳቸውን ብሩህ ነገዎች ከሚያጨልሙባቸው የቀደሙት የጥፋት መንገዶች ልንታደጋቸው ይገባል።
ለዚህ ደግሞ መላው ህዝብ ችግሮቻችንን ቁጭ ብለን በመነጋገር ለመፍታት የተጀመሩ ሀገራዊ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ የማይተካ ሚናውን ሊጫወት ይገባል። ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ ጊዜ ካለፈበትና ትውልዶችን ብዙ ዋጋ ካስከፈለ የኃይልና የሴራ ፖለቲካ ወጥተው ፤ ቁጭ ብሎ ለመወያየት እና ከውይይት ለሚገኝ የሀገርና የህዝብ አሸናፊነት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2015