ባለፉት ሶስት አመታት እንደ አገር በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋርና ከሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች ጋር ተያይዞ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሞት፣ ስደትና መፈናቀል ተዳርገዋል። ቤት ንብረታቸውንም አጥተዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ ቀውስ መሃል እነዚህን ወገኖች ለመርዳት ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት የሚያደርጉና የግል ምቾታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በርካቶች ናቸው፡፡
ከነዚህ ውስጥ አንዷ ራሷን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ በመስጠት ሳሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘውን ወገን ለወገን በጎ አድራጎት ልማት ድርጅት የተቀላቀለችው የሃያ አንድ ዓመቷ ወጣት አፀደ ሰማን ናት፡፡ ወጣቷ በሙያዋ ፋርማሲስት ስትሆን ወደ ሥራ ዓለም ከተሰማራች ሁለተኛ ዓመቷን ይዛለች፡፡ ተወልዳ ካደገችበት ሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ መጥታ ነው ድርጅቱን በአባልነት ተቀላቅላ እያገዘች ያለችው፡፡
አፀደ በጎ አድራጎት ድርጅቱን የተቀላቀለችው በአንድ አጋጣሚ ነበር። ባህር ዳር ከተማ የምትኖረው አክስቷን ልትጠይቅ በሄደችበት አጋጣሚ ወደ ድርጅቱ ይዛት ሄደች:: አክስት ወጣቷ በተቻላት አቅምም ድርጅቱን እንድትደግፈው መከረቻት፡፡ ወጣቷ ከዚህ በፊት ከጦርነትና ግጭት ጋር ተያይዞ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ገጥመዋታል፡፡ በተለይ እሷ ትኖር በነበረችበት ቅማንት በሚባለው አካባቢ ረብሻ፤ ሁከትና ግርግር እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በዚህ ምክንያት ብዙዎች ቤታቸውና ንብረታቸው በእሳት እንደጋየም ታውቃለች። ብዙዎች ለሞት፤ ለስደት፤ ለረሀብና መፈናቀል ሲዳረጉም ተመልክታለች፡፡ ይህ ቅማንት ብቻ ሳይሆን በማይካድራና ጦርነቱ በነበረባቸው አከባቢዎች ሁሉ የሚስተዋል ችግር እንደነበረም ትገልፃለች፡፡
ከዚህ አንፃር እነዚህን ወገኖች በመርዳት የተቀደሰ ዓላማ ውስጥ መሳተፍ ለወጣት አፀደ እጅግ አስፈላጊ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ያለው ጽህፈት ቤት በመጣችበት አጋጣሚ ስለተቀደሰው ዓላማ የበለጠ ተረዳች፡፡ ወደ ጭልጋ ተመልሳ በሄደች በሦስት ወሯ ተመልሳ መጣችና ማህበሩን ተቀላቀለች፡፡
አሁን ላይ ድርጅቱ ምንም ዓይነት የራሱ ገቢ ስለሌለው ለድርጅቱ ገቢ ለማሰባሰብ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችል ድንኳን ለመትከል አንዲት ካሬ በ አንድ ሺ ብር እንዲገዛ ከማድረግ ባለፈ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በመሸፈን የጉልበት እገዛ እያደረገችም ነው፡፡ ድንኳን ሲፈቀድ ደግሞ የእርዳታ ገንዘቡን ለማሰባሰብ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡
ድርጅቱን የማገዝ ሀሳብ ሰንቃ እዚህ አዲስ አበባ ከመጣች ወዲህ 3ሺ 500 ብር ቤት ተከራይታ የምትኖር መሆኗን የምትጠቁመው ወጣት አፀደ፤ ማህበሩን ለማጠናከርና ቤት ኪራይ መሸፈኛ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ትጠቅሳለች፡፡
ወላጆቿ አርሶ አደሮች መሆናቸውንና እነርሱ ባይማሩም እሷን ግን ማስተማራቸውንም ነው የምትገልፀው፡፡ ለራሳቸውና ከእርሷ በታች ላሉ እህትና ወንድሞቿ እንደማያንሱና ከእርሷ ምንም እንደማይጠብቁም ትናገራለች፡፡ ሙሉ የወጣትነት ጊዜዋንና ገንዘቧን ለድርጅቱ ለማዋል መወሰኗንም ታስረዳለች፡፡ ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚለውን መርህ ተከትለው ለወገን እየደረሱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሆኑ ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ትናገራለች፡፡
እነዚህ ከየትኛውም ሀይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነፃ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የተቀደሰ ዓላማ ያነገቡ ድርጅቶች በተለይ በሰሜኑ ጦርነትና ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመደገፍና ለመቋቋም ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱንም ወጣት አፀደ ትናገራለች፡፡
የወገን ለወገን በጎ አድራጎት የልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት እንዳለ በበኩላቸው፣ መቀመጫውን በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር አድርጎ እንደ አገር በስፋት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ አሶሳ፤ በአዲስ አበባ፤ በአፋር ሰመራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከፈተም ከፍቷል፡፡ በሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈትም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረግና አደረጃጀቱን ማጠናከር የሚያስችለውን ገቢ ያሰባስባል፡፡
ድርጅቱ በእሳቸውና በአንዲት እህት አማካኝነት በጦርነትና ከጦርነት ጋር በተያያዙ በሌሎች ምክንያቶች የተጎዱ፤ የተፈናቀሉና ከቀያቸው የተሰደዱ፣ ለርሃብ የተጋለጡና በመጠለያ እጦት የሚንገላቱ ወገኖችን ለመደገፍና ለማቋቋም ዓላማ አድርጎ ነሀሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተመስርቷል። ማህበሩ አምስት የቦርድ አመራር ያሉት ሲሆን ሦስቱ ወንዶች ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ በነዚህ አመራሮችና እና አንድ፤ አንድ እያሉ ድርጅቱን በተቀላቀሉት አባላት አማካኝነት በጉልበት፤ በዕውቀትና በገንዘብ እየተደገፈ አቅሙን በማጎልበት ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ወደ ሥራ ለመግባትና ወገንን ለመደገፍ ያስችለው ዘንድ ድርጅቱ አደረጃጀቱን እያጠናከረ ይገኛል፡፡ ከቀበሌ፤ ወረዳ፤ ዞንና ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ፍላጎት አለው፡፡ ድርጅቱ የሚደግፈውም የተቸገሩ ወገኖችን ነው፡፡ ለዚህም ድርጅቱ ከወረዳ፤ ቀበሌና ዞን ጋር በመቀናጀት ትክክለኛ ተረጂ የሆኑትን ወገኖች የመለየት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም ለዘላቂ ድጋፍ ያመቻል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015