ለበርካታ ወራት ተሰውሮ የነበረው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬ በሰፈራችን ተከስቷል፡፡ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል፡፡ ጊዜው የሰፈራችን ሰዎች ወደ «በተስኪያን» የሚሄዱበት ሰዓት ነበር፡፡ በእኛ ሰፈር ያሉ ሰዎች በሙሉ በተስኪያን ሳይሄዱ በፊት ምንም አይነት ሥራ አይጀምሩም፡፡ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከብዙ ቀናት መሰወር በኋላ ዛሬ ስለተከሰተ ዋርካው ስር መጮህ ሲጀምር በሰፈራችን የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በተስኪያን መሄዳቸውን ትተው የይልቃ አዲሴን ንግግር ለማዳመጥ እየተቻኮሉ ወደ ዋርካው ስር ተሰባሰቡ፡፡
የሰፈራችን እና የእድራችን መሪዎች እንዲሁም ተፎካካሪዎቻቸው ወፈፌው ይልቃል አዲሴ በሚመራው ስበስባ ላይ መገኘታቸው የዛሬውን ስብሰባ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይልቃል አዲሴ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው ዛሬም ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ስር እስኪሰበሰቡ ድረስ “ጥሩ የሰሩ ሰዎች ቢሞቱም ቢኖሩም አይጨነቁም ! አለ ሶቅራጥስ” እያለ የተለመደ ዲስኩሩን በጩኸት ይናገር ነበር ፡፡
የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታ ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ፣ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ እህ.. እህ… ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ ‹‹በዛሬው ስብሰባ የሰፈራችን እና እድራችን መሪዎች እንዲሁም ተፎካካሪዎቻቸው መገኘታቸውን ተከትሎ በሰፈራችን የሚገኝ አንድም ጥሩንባ ነፊ አልቀረም ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ የሚገርመው የጡርንባ ነፊዎች መገኘት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ይልቃል አዲሴ በመራቸው ስብሰባዎች አንድም ቀን ተገኝተው የማያውቁት አታሞ ደላቂዎች መገኘታቸው ነው ፡፡
እኔን የሚገርመኝ የጡርንባ ነፊዎች ነገር ነው፡፡ ጥሩንባ ንፉ ከተባሉ ዝም ብለው ይነፋሉ። የሰፈራችን እና የእድራችን መሪዎች እንዲሁም ተፎካከሪዎቻቸው አንድ ነገር ትንፍሽ ካሉ፤ የቱንም ያህል ንግግራቸው ስህተት ቢኖረው እንኳን ንግግራቸውን ምንም ሳያርሙ የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ይመስል እንዲሁ እንደወረደ ያነበንቡታል። የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ እንኳን የተወሰነ ደለል እና ቆሻሻ ያስቀራል፡፡ የእኛ ሰፈር ጡርባ ነፊዎች ግን እንኳንስ ከተነገራቸው ሊቀንሱ ይቅርና የእድራችን ሰብሳቢ ያሉትን ለማሽሞንምን በማሰብ የእድራችን ሰብሳቢው ያላሉትን ብቻ ሳይሆን ያላሰቧቸውን ቃላት በመፍብረክ የሰፈራችንን አየር በጩኸት ይሞሉታል ፡፡
አንድ ቀን አንዱ ጡርባ ነፊ የእድራችን ሰብሳቢ ወግ ለማሽሞንምን አስቦ የእድራችን ሰብሳቢ ከተናገሩት የሚጣረስ ቃላቶችን ተናገረ፡፡ ምንም ስህተት የማያልፉት የእድራችን ሰብሳቢም ጡሩምባ ነፊውን ወዲያውኑ ከስራው ከማባረር አልፈው ወደአልታወቀ ስፍራ ወስደው እንዳስቀጠቀጡት ሰማን፡፡ ስለእውንት ይህንን የእድራችን ሰብሳቢ ውሳኔ እጅጉን ወድጀዋለሁ፡፡
ከላይ እንደነገርኳችሁ የዛሬው ስበሰባ ከጡሩምባ ነፊዎች ባሻገር በአታሞ ደላቂዎች የታጀበ ነው። አታሞ የሚመታው የብሄር ብሄረሰቦችን ሙዚቃ መሰረት ተደርጎ መሆኑን ስመለከት አግራሞቴን የባሰ ከፍ አደረገው ፡፡ በሰኔ ስለእርሻ ማውራት ሲገባን እንዴት የብሔር ብሔረሰቦች መብት እያልን ለማላዘን እንኳትናለን ? ጎበዝ !
“የሆነው ሆኖ ዛሬ ወደ ተሰበሰብንበት የስበሰባ አጀንዳ ልመልሳችሁና” አለና ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጠለ… ‹‹ አሁን ወቅቱ ሰኔ ነው ። በሰኔ በሬ እና ገበሬ ዝምድናቸው የሚጨምርበት፤ አብረው ውለው አብረው የሚያድሩበት ነው።
ገበሬዎችም በእንጉርጉሮ እና በተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች ለበሬዎቻቸው ብሶታቸውን የሚነግሩበት ፤ ችግራቸውን የሚያወያዩበት ፤ ሚስጥራቸውን የሚያካፍሉበት ነው፡፡ በአጠቃላይ በሰኔ የበሬ እና የገበሬ ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ሳንባችንን አጋጥመን በአንድ አፍንጫ እንተንፍስ የሚሉበት ወቅት ነው።
በተለይ እንደኛ ሰፈር ተጨባጭ ሁኔታ እና የእኛ ሰፈር ኢኮኖሚ በእርሻ ላይ እንደመመስረቱ ወርሐ ሰኔ ለእኛ ሰፈር ገበሬዎች እና ነዋሪዎች የተለየ ትርጉም አለው፡፡ የእድር እና የሰፈራችን መሪዎችም የሚቀጥለው ዓመት ገበያ የተትረፈረፈ እንዲሆን በማሰብ ከወዲሁ የምርጥ ዘሩን እና የማዳበሪያውን ግበዓት ለአርሶ አደሩ ለማሟላት ከላይ ታች የሚሉበት ነው፡፡
ተፎካካሪዎች እና አንዳንድ ማህበራትም የምርጥ ዘሩን እና የማዳበሪያውን አቅርቦት እየተመለከቱ የየራሳቸውን አስተያየት በማዥጎደጉድ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ እንዲቀርብ ለማድረግ በእድር እና በሰፈራችን መሪዎች ላይ ግፊት የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩት ሰኔዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚገኙ እድራችን እና ሰፈራችን ነዋሪዎች እንዲሁም መሪዎች እና ተፎካካሪዎቻቸው ለእድራችን እና ለሰፈራችን የቀጣይ ዓመት የምግብ ፍጆታ ምርቶችን ለማምረት የሚኳትኑበት ጊዜ ነበር፡፡ በዘንድሮው ሰኔ ግን አልፎ አልፎ በፖለቲከኞች የሚፈጸሙ ያለተገቡ ነገሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ እውነት እኛን ለመሰለ የዓመት ዝናብን ጠብቆ ለሚዘራ እና ራሱን የሚመግብ ህዝብ በሚገኝብት ሰፈር እና እድር በሰኔ ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው ? ሰኔ ላይ በእኛ ሰፈር የሚፈለገው አውርቶ የሚኖር ሳይሆን በተግባር ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ለገበሬው የሚያቀርብ ሰው ነው፡፡
“ዋዘኛ ገበሬ ይሞታል በሰኔ መባል ያለባቸው እንደእነዚህ አይነት ፖለቲከኛ ነን ባዮችን ነው። ሰው ምርጥ ዘር እና ማደበሪያ በሚፈልግበት ወቅት በፖለቲካ መጎሻሸም ምን የሚሉት ነው?” ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው::
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ… “ዘላዕስ ነፍሱ ይኤብስ ለመኑ ኄረ ይከውን (ለራሱ የሚነፍግ ለማን ቸር ይኆናል ?) እንዲሉ በእኛ ሰፈር ሚገኙ አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደዚህ አይነት ሰዎች ናቸው ፡፡
መላው የሰፈራችን እና የእድራችን ነዋሪዎችን እንዲሁም መሪዎችን እና ተፎካከሪዎችን እየመገበ ያለን አርሶ አደር በወርሃ በሰኔ ተልካሻ የፖለቲካ ምክንያት እየፈጠሩ ምርት እንዳይመረት ጋሬጣ መሆን ምን የሚሉት ፖለቲከኝነት ነው ?
የሚገርው ደግሞ ውሸታችሁ ነው ፡፡ አንዳችሁ ከአንዳችሁ አትሻሉም ፡፡ ሁላችሁም አንድ ናችሁ።“ ይኄይስ ህዳጥ በዘጽድቅ እምብዙኅ ብዕለ ኃጥአን (ውሸት ከመናገር ዲዳነት ይሻላል፡፡) እንዲሉ ምን አለበት ፈጣሪ ክፉ አሳቢ ፖለቲከኞችን ወርሃ ሰኔ እስኪያልቅ ልሳናችሁ በዘጋው ብዬ ተመኘሁ ፡፡
ምክንያቱም “ጻማ ከናፍር (ጉንጭ አልፋ)” እንዲሉ ሁሌም ትከራከራላችሁ፤ ሁሌም ትነታረ ካላችሁ፤ ፖለቲካን አብሳላችሁ ታነኩራላችሁ ነገር ግን ክርክራችሁ አንድም ቀን መፍትሄ አምጥቶ አያውቅም፡፡ እንዲሁ ክርክር!፡፡ የእናንተ ንትርክ መሬት ቆፍሮ አገር የሚቀልበውን ገበሬ ጭምር ያናጠበ መሆኑን ስመለከት አርሶ አደሩ ማሳውን አለስልሶ ዘሩን እንዳይዘራ መድሃኒት አልባ ደንቀራ ሁናችሁ ትታዩኛላችሁ፡፡
ሁሌም ምታደርጉት ክርክር የራሳችሁን ጥቅም ለማሳደድ እንጂ የሰፈራችሁን አርሶ አደሮች ጥቅም ለማስጠበቅ እና ለማሻሻል እደንዳልሆነ ስመለከት በፅኑ ያበግነኛል፡፡
በነገራችን ላይ አሁን አሁን በሰፈራችን እየተስተዋለ ያለው ፖለቲካን እየጋገሩ የማንኮር ተግባር በአርሶ አደሮቻችንም ተጋብቶ ተመለከትኩ። በእርሻ ላይ እያለ ገበሬ ድሮ ድሮ በሬዎቹን ሲያበረታታ
“አያ በሬ በሬ፤
ልቀበር ባገሬ፤
በገዛ ድንበሬ ፡፡‘ ይል ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ሁሉን እርግፍ አድርጎ ትቶ ለበሬው የሚዘፍነው እና የሚያንጎራጉረው የፖለቲካ ግጥሞችን የያዙ ስንኞችን ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ታች መንደር የሚገኝ አንድ አርሶ አደር …
”በርዬ በርዬ በአንተ ጉልብት አርሰን ካልሆነ ነገሩ፤
ከዙፋን ተጠግተን እንዝረፍ ከብሩ፡፡
ማዳበሪያም ያለ ከዙፋኑ ስር፤
ድሎቱም ያለው ከዙፋኑ ስር፤
ምነው እኔ እና አንተ በብርድ እንረር?‘ ሲል ሰማሁት ፡፡ እርሻውን ትቶ የፖለቲካ ወንበር መፈለጉን ከግጥሙ ተገነዘብኩ ፡፡ ስለእዕውነት ይህንን አባባል መሬት ቆፍሮ ሀገር ከሚቀልበው አርሶ አደር መስማት ያማል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው? ስል ራሴን ጠየኩ። ምክንያቱም የተማረውም ያልታማረውም ፤ ፖለቲከኛውም ሌላ ስራ የሚሰራውም በፖለቲካው ግብቶ መፈትፈት ከጀመረ በሰፈራችን አንድ የከሸፈ ነገር እንዳለ ይሰማኛል ፡፡ ምነው አርሶ አደሩም፣ አውርቶ አደሩም ፣ አርብቶ አደሩም ፣ በልቶ አደሩም፣ ዋሽቶ አደሩም ፣ ወጥቶ አደሩም ፖለቲከኛ እንሁን አለ?
እየሄድንበት ያለንበት መንገድ ትክክል አይ ደለም። ሁሉም የሚመለከተውን እና የሚችለውን ቢሰራ አትራፊ እንሆናለን፡፡ ነገር ግን ፖለቲካን ተገን አድርጎ አንዱ እየሰራ ሌላው ለመስረቅ መሞከር ተገቢ አይደለም ፡፡ አሁን ላይ በሰፈራችን ባለው ተጨባጭ ፖለቲካን ለስርቆት እና ለወንጀል መደበቂያ ምሽግ የማድረግ አዝማሚያ በአንዳንድ ሰዎች ይስተዋላል። ይህ ትክክል አይደለም ፡፡
“ሌላ በሰራው ስራ ለመክበር የሚሞከርን ሰው ስመለከት በ1952 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታተመውን “ምን ይባላል ?” የተሰኘውን የማሞ ውድነህ አንድ ግጥም ያስታውሰኛል፡፡ ማሞ ወድነህ በግጥሙም
መዶሻ ሲሰራ ሲቆፍር በአካፋ ፡፡
ሲጥር ሲግደረድር ለማለፍ ፈተና፤
ምኑንም ያንንም ሲጀምረው ገና ፡፡
ነጋ አልጋ ብሎ ለሥራ ሲነሣ ፤
በስራ ሲደክም ሲቀበል አበሳ ፡፡
አንደኛው ዝም ብሎ ቆሞ መመልከቱ
ኩራት ነው ስንፍና ምንድን ነው ብልሃቱ።
ወሬ ማውራት ብቻ ለምዶ ድሮውን
ስራ መስራት ተወ እዩት ይህንን፡፡ ሲል ተቀኝቶ ነበር” ብሎ አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡
አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ወደ መቀመጫው መመለሱን የመለከተው የሰፈራችን እና የእድራችን ሰብሳቢ ጉሮሮውን ለንግግር እየጠራረገ ንግግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤ በባለፉት ወራት የሃምሳ ሺህ ዩሮ መጽሀፍ ስለገዛች አንዲት አርሶ አደር በስፋት ሲዘገብ ሰምቻለሁ፡፡ ምነው ይች ሰው ተሞክሮዋን ለእኛ ሰፈር አርሶ አደሮች ብታካፍል? ስል ተመኘሁ፡፡
አሁን ላይ የሰፈራችንን ምርት ለመጨመር ከታሰበ የሃምሳ ሺህ ዩሮ መጽሐፍ የገዛቸውን አርሶ አደር ተሞክሮ በተለያዩ ክፍሎች በማደራጀት እና የሥልጠና ማንዋሎችን በማዘጋጀት በመላው ሰፈራችን ለሚገኙ አርሶ አደሮች እሁድ እና ቅዳሜ ሥልጠና ሊሰጥ ይገባል፡፡
አንድ አርሶ አደር በማሳ ያመረተው ምርት ከእርሱ አልፎ ሃምሳ ሺህ ዩሮ አውጥቶ መጽሐፍ መግዛት ካስቻለው፤ የዚህን አርሶ አደር ተሞክሮ ለሰፈራችን እና ለእድራችን አርሶ አደሮች በተሞክሮነት ማሠልጠን ያስፈልጋል ባይ ነኝ ፡፡ ምክንያቱም የእዚህችን አርሶ አደር ተሞክሮ የወሰደ የሰፈራችን ሠልጣኝ አርሶ አደር የሃምሳ ሺህ ዩሮ መጽሐፍ መግዛት ባይችል እንኳን፤ ሃምሳ ለሚሆኑ የሰፈራችን ሰዎች በአነስተኛ ዋጋ የምግብ ፍጆታ ማቅረብ የሚያስችለው ይመስለኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ በሰፈራችን እና በእድራችን የተጀመረውን ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ጅማሮ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ይሆናል።
“ስለሆነም በሃምሳ ሺህ ይሮው መጽሐፍ የገዛቸው ገበሬ የአመራረት ተሞክሮ በሰፈራችን ለሚገኙ መላው አርሶ አደሮች ስልጠና ሊሰጥ ይገባል፡፡” ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡
ይህን ተከትሎ ይልቃል አዲሰም ከሥልጠና ጋር ተያይዞ “እኔም የምናገረው ነገር አለ፡፡” ብሎ ንግግሩን ቀጠለ… ‹‹በዓለማችን የውሃ እጥረት ከሚያሰቃያቸው አገራት አንዷ የሆነችው እስራኤል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑትን የዜጎቻን ቀለብ የምትሸፍነው ራሷ ባመረተችው ምርት መሆኑን ሳስብ አብዝቼ እደነቃለሁ፡፡ እናም! እስራኤል ዜጎቿን በዚህ ልክ ልትቀልብ የቻለችበትን ተሞክሮ ለእኛ ሰፈር ሰዎች ማስተማሩ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም ፡፡ ዝም ብሎ ኩታ ገጠም ፤ ስም ገጠም ፤ ምን ገጠም ቢሉት ዋጋ የለውም ፡፡
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጥሎ…“በዓለማችን ተክኖሎጂን ተጠቅሞ ሰው ሰራሽ ዝናብ መጀመሩን በተመለከተ፤ በ1952 ዓ.ም ቻይና በደቡብ ቻይና የሚገኝን አስር ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ደረቅ ቦታ ላይ ማዝነቧን በወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቦት ነበር፡፡
በቅቡም ይህ አካሄድ በእኛ ሰፈር መጀመሩንም ሰምተናል፡፡ ያው ወደ ቴክኖሎጂው መግባታችን በጎ ቢሆንም ነገር ግን ብዙ ወጭ ሊያስጣ ይችላል። ስለሆነም አገራችን ለእንደዚህ አይነቱ ቴክኖሎጂ ወጭ ከምታወጣ ለምርጥ ዘር እና ማለዳበሪያ መግዣብታደርግ፤ እንዲሁም ያለሙያቸው ፖለቲካ ውስጥ ገብተው የሚፈተፍቱ እና ዜጎች በተሰማሩበት ስራ ምቾት ተሰምቷቸው እንዳይሰሩ የሚያደርጉ አካላትን አደብ ለማስገዛት በሚደረግ ስራ ላይ ወጪ ቢደረግ መልካም ነው ፡፡” ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎችም ለይልቃል ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ስብሰባው ተበተነ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015